የኢትዮጵያዊያን ዋና ጠላት ድህነት ነው:: ድህነትን ማሸነፍ የሚቻለው ደግሞ በልማት ነው:: ለዚህ ደግሞ መንግስትና ህዝብ ከድህነት ለመውጣት የሚያስችላቸውን የልማት ስራ በራስ አቅም እና በአጋር ሃገራትና ተቋማት ድጋፍ መስራት ከጀመሩ አመታትን አስቆጥረዋል:: የሃገሪቱን የተፈጥሮ ሃብት ጥቅም ላይ በማዋል ከፍተኛ የመሰረተ ልማት ግንባታም እየተካሄደ ነው:: በተለይ የሀገራችን የሃይል አቅርቦት ፍላጎትን ለማሟላትና ለውጭ ገበያ በማቅረብ የውጭ ምንዛሬ ለማግኘት ግድቦች ተገንብተዋል፤ እየተገነቡም ነው:: ከእነዚህ ውስጥ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ አንዱ ነው::
ታላቁ የህዳሴ ግድብ የኢትዮጵያዊያን ሃብት ነው፤ በራሳችን አቅም፤ በራሳችን ሉኣላዊ ግዛት የሚገነባ ሃብት:: በፍትሃዊ የውሃ ተጠቃሚነት መርህ የታችኞቹ ተፋሰስ ሃገራት ላይ ጉልህ ተጽእኖ በማያሳርፍ መልኩም እየተገነባ ይገኛል:: ኢትዮጵያ የሕዳሴውን ግድብ የምትገነባው ግድቡን የመገንባት ሙሉ መብት ስላላት ነው:: ግድቡ በስጦታ ወይም በሌላ ወገን ይሁንታ የሚገነባ አይደለም:: በሃገር ውስጥ አቅም መላው የሃገሪቱ ህዝቦች ቦንድ በመግዛት የሚገነቡት የራሳቸው ግድብ ነው::
ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊያን የራሳቸውን የተፈጥሮ ሀብት ተጠቅመው የልማት ስራ መስራት መብታቸው ነው:: ምክንያቱም ዜጎቻችን ከድህነት የመላቀቅ ሙሉ መብት አላቸው። አባይን የመሰለ የተፈጥሮ ሀብታችን ስናለማ በዚህ ወንዝ ላይ ህይወታቸውን የመሰረቱ የታችኞቹ የተፋሰሱ ሀገራት ላይ ጉልህ ተፅእኖ እንዳያሳድር በማድረግም ነው። ኢትዮጵያ ከግድቡ ዲዛይን ጀምሮ ይህንን ታሳቢ በማድረግ ግንባታውን እያከናወነች ትገኛለች። ስለሆነም በዚህ ግድብ ዙሪያ የአሜሪካ ግምጃ ቤት ያወጣው መግለጫ ተቀባይነት የሌለው መሆኑ መታወቅ አለበት:: ኢትዮጵያ በሉአላዊ ግዛቷ ለምትገነባው ግድብ መቼ ውሃ ይሞላል፤ መቼ ሃይል ያመነጫል በሚለው ጉዳይ ማንም ሃገር ትእዛዝ የማስተላለፍ ስልጣን የለውም:: ምክንያቱም ግድቡ የእኛ ነው::
ኢትዮጵያ በዚህ መልኩ ግድቧን ብትገነባም የታችኞቹ የተፋሰሱ ሀገራት ማረጋገጫ የሚፈልጉ በመሆናቸው ወደ ድርድር ተገብቷል። በዚህ የድርድር ሂደትም ኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብፅ በበርካታ ጉዳዮች ላይ ተደራድረው ልዩነቶቻቸውን ማጥበብ ችለዋል። በአሜሪካ ሲደረጉ በነበሩ ድርድሮችም በበርካታ ጉዳዮች ላይ ከስምምነት ቢደረስም፤ ከቴክኒካዊም ሆነ ከሕግ ጉዳዮች አንፃር ስምምነት ያልተደረሰባቸው ነጥቦች አሉ። ኢትዮጵያ ስምምነት ባልተደረሰባቸው ጉዳዮች ላይ በመነጋገር በድርድር እንደሚፈቱ እምነት አላት:: ከዚህ ውጭ በትእዛዝ ያውም በድርድሩ ሂደት ታዛቢ ሆኖ የቀረበ ሃገር ወሣኝ ሆኖ መቅረቡ በማንኛውም መለኪያ ትክክል አይደለም:: ተቀባይነትም የለውም:: ምክንያቱም የኢፌዴሪ የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ “ግድቡ የእኔ ነው” እንዳሉት ግድቡ የእኛ የኢትዮጵያዊያን ነውና::
በህዳሴ ግድብ ዙሪያ ግብጽ የምታነሳው ሃሳብ መፍትሄው መደራደርና ስምምነት ላይ መድረስ ብቻ መሆኑን መገንዘብ አለባት:: ዛቻ ግንኙነትን ከማሻከር ያለፈ ፋይዳ የለውም:: አሜሪካም ቢሆን ይህንን ታሳቢ በማድረግ ሀገራቱ በራሳቸው ወደ ስምምነት እንዲደርሱ ግፊት በማድረግ በጎ ሚናዋን ብቻ መወጣት አለባት:: ከዚህ ያለፈ ሚና ተቀባይነት የለውም።
በአሁን ወቅት ግንባታው 72 በመቶ ደርሷል:: በሚቀጥለው ሐምሌ ወር ግድቡ ውሃ መያዝ ይጀምራል:: በዚህ ጊዜም አራት ነጥብ ዘጠኝ ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ውሃ ይይዛል:: በቀጣይም አመት የካቲትና መጋቢት ወራት ሙከራና ሀይል የማመንጨት ሥራ ይጀምራል:: ስለዚህ ይህንን ግድብ በዛቻና በጫና ማስቆም አይቻልም:: ግንባታው በሃገራችን ሉኣላዊ ግዛት ላይ የሚካሄድ፤ በውሃ ሃብታችን የፍትሃዊ ተጠቃሚነት መብታችን እውን የምናደርግበት ነው:: ይህን ስናደርግ ግን በታችኞቹ ተፋሰስ ሃገራት ጉልህ ተጽእኖ በማያደርስ መልኩ ነው:: ስለሆነም የግንባታውን ሂደት፣ ውሃ ከመሙላትና ሃይል ከማመንጨት ማቆም አይቻልም:: ምክንያቱም “ግድቡ የእኛ ነው”::
አዲስ ዘመን የካቲት 26/2012