የዛሬ 45 ዓመት በዛሬው ዕለት ወታደራዊው ደርግ አስገራሚ አዋጅ አወጀ:: ይህ አዋጅ መላ አገሪቱን ከዳር እስከ ዳር አነቃነቀ:: አዋጁ ‹‹ መሬት ለአራሹ ›› የሚል ነበር:: በዚህ ዓምዳችን ይኸው ታሪካዊ አዋጅ እንዴት እንደታወጀና ያስከተለውን ውጤት በወቅቱ የደርግ አባል ከነበሩትና በጠቅላይ ሚኒስትርነት ካገለገሉት ከሻምበል ፍቅረስላሴ ወግደረስ “እኛና አብዮቱ” መጽሀፍ ላይ የተቀነጨበውን ታሪክ እንደሚከተለው አቅርበንላችኋል::
የደርግ አባላት በአንድ ጉዳይ ላይ ተከራክረው ውሳኔ ካሳለፉ ነኋላ ለአፈጻጸሙ ወደ ታች ወርደው ይሳተፋሉ:: የገጠር መሬት አዋጅንም ለማስፈጸም አብዛኞቹ አባላት በየክፍለ አገሩ እንዲሰማሩ ተወሰነ:: በዚህ ውሳኔ መሰረት በመላ አገሪቱ በመዘዋወር የአዋጁን መንፈስ ለገበሬው ለማስረዳት የደርግ አባላት በአስራ አራት ቡድኖች ተደለደሉ::
አዋጁ ከመታወጁ ጥቂት ቀናት በፊት ቡድኖቹ በየአካባቢው መሰማራታቸው በጉጉት ሲጠበቅ የነበረው የመሬት አዋጅ ዕውን ሊሆን መቃረቡን ለመላው ህዝብ በአጠቃላይ ደግሞ አዋጁን ለማስፈፀም ሃላፊነት ለተጣለበት ክፍል ሰራተኞችና ለዘማች ተማሪዎች ታላቅ የምስራች ነበር:: አዋጁ በእርግጠኝነት እንደሚታወጅ ሁሉም አወቀ:: ግልጽ ሆኖ ሊታወቅ ያልተቻለው አዋጁ የሚታወጅበት ቀን ብቻ ነበር:: ደርግ አብዛኞቹን ታላላቅ ውሳኔዎች ወይም አዋጆች በተለምዶ የሚገልጸው ቅዳሜ ጠዋት ወይም ማታ ወይም እሁድ ጠዋት ስለነበር የገጠር መሬት አዋጅ እንደሚታወጅ ጭምጭምታ ከተሰማበት ጊዜ ጀምሮ በእነዚህ ቀናት ሁሉ ህዝቡ ሬዲዮኑን ከፍቶ ይጠባበቃል::
በ1966 በየካቲት ወር የፈነዳው ህዝባዊ አመጽ መሆኑን ለማስገንዘብ ሲባል የገጠር መሬት አዋጅ በየካቲት ወር ውስጥ መታወጅ እንዳለበት ሁላችንም የተስማማንበት ጉዳይ ስለነበር በዚሁ ስምምነት መሰረት የካቲት 25 ቀን 1967 ማክሰኞ ጠዋት እንዲታወጅ ተወሰነ:: አዋጁ ከሚወጣበት አንድ ቀን ቀደም ብሎ ለሚኒስትሮች፣ ለከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣናት ለክፍለ ሀገር አስተዳዳሪዎች፣ ለጦር አዛዦች፣ ለውጭ ዲፕሎማቶች በአፈጻጸሙ ላይ ለሚሳተፉ መሥሪያ ቤቶችና ለዕድገት በህብረት ዘመቻ መምሪያ ተነገረ::
በማግስቱ ጠዋት ታላላቅ አዋጆች ከመነበባቸው በፊት በመክፈቻ የሚተላለፈው ሙዚቃ ተሰማ:: ከዚያም አሰፋ ይርጉ የተ ባለው ባለ ጥሩ ድምጹ ጋዜጠኛ ‹‹የገጠርን መሬት ለህዝብ ያደረገ አዋጅ ቁጥር 31›› ብሎ ማንበብ ጀመረ:: መላው ህዝብ በያለበት ወደ ሬዲዮ ጠጋ ብሎ ማዳመጡን ቀጠለ:: አዋጁ አንቀጽ በአንቀጽ ተነቦ እስኪያልቅ ድረስ ምንም እንቅስቃሴ ሳይደረግ በጸጥታ ሲያዳምጥ የነበረው ህዝብ ‹‹ይህ አዋጅ ከዛሬ የካቲት 25 ቀን 1967 ጀምሮ የጸና ይሆናል::
የጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ!›› ብሎ አንባቢው ሲጨርስ አንዳች ነገር የቀሰቀሰው ይመስል ከፊሉ ከመቀመጫው በመነሳት እየጨፈረ፣ እየሳቀ፣ እየተንከተከተ አጠገቡ ያገኘውን ሁሉ እያቀፈ ሳመ:: የተወሰነው ደግሞ ከደስታው ብዛት እምባ እየተናነቀው‹‹ አይ ደርግ! ወንድ!›› እያለ ደርግን እያመሰገነና እያደነቀ በአዋጁ የተሰማውን ደስታ ይገልጽ ነበር :: በየቦታውና በየቤቱ የታየው ትዕይንት በጣም አስደናቂ ነበር:: በደስታ የተዋጠው ህዝብ ደስታውን ለመግለፅ ግብታዊ በሆነ መንገድ ወደ አደባባይ ወጣ:: በተለይ በአዲስ አበባ ከተማ ከየአቅጣጫው ከቤቱ የወጣው ህዝብ መንገዶችን አጥለቅልቆ ቀኑን ሙሉ ደስታውን ሲገልጽ ዋለ::
በማግስቱ የካቲት 26 ቀን 1967 ዓ.ም. ከዚያን በፊት በኢትዮጵያ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ 800‚000 (ስምንት መቶ ሺህ) የአዲስ አበባ ህዝብ የገጠር መሬት አዋጅን በመደገፍ ወደ አደባባይ ወጣ:: ማን እንዳዘጋጃቸው የማይታወቁ የተለያዩ መፈክሮች ተይዘዋል:: ጭፈራው፣ ዘፈኑ፣ ፉከራው፣ እስክስታው፣ በየመልኩ በየብሔረሰቡ በየሥፍራው ይካሄዳል:: ህጻንና ሽማግሌ እንኳን እቤቱ የቀረ አይመስልም:: ሁሉም በደስታ ብዛት ተውጦ የሚያደርገውን አያውቅም ::
ያለምንም ቅስቀሳና ግፊት የወጣው ህዝብ ‹‹ዋይ ዋይ መሳፍንት እንግዲህ ቀረ ሳይሰሩ መብላት ›› እያለ ሙሾ እያወረደና መፈክር እያሰማ በደርግ ጽ/ቤት በኩል ተመመ:: ደርግ በከፍተኛ ደረጃ በህዝብ የተመሰገነበትና የተወደሰበት፣ ለወደፊት ምሥረታውም ህዝባዊ ድጋፍ ያገኘበት ቀን ነበር:: አዋጁ ለብዙሃኑ ብሩህ ተስፋ የሚያበስር የመሆኑን ያህል ለጥቂቶች ዋይታና ለቅሶን የሚያስከትል መርዶ የመሆኑ ጉዳይ የሚጠበቅ ነበር::
ለብዙ ዓመታት በመሬት ክርክር በመንገላታት ለዳኞች ጉቦ በመስጠት፣ ለጠበቆች የአገልግሎት ክፍያ በመፈጸም ቤት ንብረታቸውን ያጡ፣ መሬታቸውን በጉልበተኞች ተነጥቀው ከገጠር በመባረር ለከተማ ችግር ሰለባ የሆኑ፣ ቤተሰቦቻቸው በጭሰኝነት የሚማቅቁባቸው የከተማ ነዋሪዎች በገጠሩ ኑሮ ተማርረው ወደ ከተማ በመሰደድ ለአስከፊ ችግር የተጋለጡ፣ በቀጥታ ወይም በተዘዋዋሪ መንገድ አዋጁ ችግራቸውን ያቃለለላቸው ሁሉ በደስታ ተውጠው ከቁጥጥር ውጭ በመሆን ሲዘሉ፣ ሲጨፍሩ፣ ሲዘፍኑ፣ ሲያለቅሱ ታይተዋል:: ሰልፉ ከጠዋት የጀመረ እስከ ዘጠኝ ሰዓት ዘለቀ:: በተመሳሳይ ሁኔታ በሁሉም የአገሪቱ ከተሞች ህዝባዊ ሰልፍ ተካሄደ:: በየክፍለ ሀገራቱ ተሰማርተው የነበሩ ዘማቾች የተሰማቸው ደስታ ወደር አልነበረውም:: አዋጁን በእነሱ ግፊት ደርግ እንዳወጀው በመቁጠር እየተኩራሩ ለአካባቢያቸው ህዝብ ገለጻ አደረጉ::
አዋጁን የሚደግፈው ሀይል በዚህ ዓይነት በየቦታው ደስታውን ሲገልጽ፤ በተቃራኒው ደግሞ የመሬት ከበርቴዎችና ቤተሰቦቻቸው ማቅ ለበሱ:: ፈጣሪያቸውን አማረሩ፣ ሰማይ የተደፋባቸው መሰላቸው:: ነጭ ጤፉን፣ በጉን፣ ማሩን፣ ቅቤውን ባላገሩ እየተሸከመ ማምጣቱ መቋረጡ፣ ሲኩራሩበት የነበረው የመሬት ባለቤትነታቸው ዘመን ማክተሙ፤ በጣም አስቆጣቸው:: መሬት መወረሱን በሬዲዮ ከሰሙበት ቀን ጀምሮ በርካታ ባለመሬቶች በሽተኛ ሆኑ:: አንዳንዶቹ ወዲያውኑ ልባቸው ቆሞ ህይወታቸው ቀጥ ስትል፤ የተወሰኑት ባለመሬቶች ደግሞ በብስጭት ታመው መሞታቸው ታውቋል::
ባለመሬቶች መሬታቸው መወረሱ የማይበቃ ይመስል ‹‹አካላዊ ጉዳት ይደርስብናል›› ብለው ሰጉ:: ከቤታቸው መውጣትና በአደባባይ መታየትን ፈሩ፤ የተወሰኑ ባለመሬቶች ‹‹ከእግዚአብሄር የመጣ ቁጣ ነው›› በማለት ለመጽናናት ሲሞክሩ የተወሰኑት ግን ደርግን አምርረው ጠሉ:: ጥርሳቸውንም ነከሱበት:: ማንኛውምን ዘዴ ተጠቅመው ለመበቀል ለራሳቸው ቃል ገቡ::
ይህም ሆኖ ግን የመሬት አዋጁ ለባለ መሬቶች አንድ በቀላሉ የማይታይ ጥቅም አስገኝቶላቸዋል:: ‹‹መሬቴ ተገፋ፣ ውርስ ለእኔ ይገባ ነበር፣ የመሬት ክፍፍል ሲደረግ አድልዎ ተደርጎብኛል›› ወዘተ… በማለት ጥቃቅን መሬት ነክ ጉዳዮችን እንደዋና የመለያያ ምክንያቶች በማድረግ ወንድም ከወንድሙ፣ እህት ከእህቷ እየተጠላሉና እየተቀያየሙ ተኳርፈው በፍርድ ቤት በመካሰስ ለብዙ ዓመታት ሲነታረኩ የነበሩ ከአዋጁ በኋላ ‹‹ለመቀያየማችን ምክንያት የነበረውን መሬት ደርግ ስለወረሰን ከዚህ በኋላ መኮራረፍ ተገቢ አይደለም::›› እያሉና ‹‹ይቅር ለእግዚአብሄር ››እየተባባሉ በመታረቅ ዝምድናቸውን ለማጠናከር በቅተዋል::
አዲስ ዘመን ረቡዕ የካቲት 25/2012