አንዳንዴ ግራ ሲገባ ግራ የሚያጋቡ ጥያቄዎች ይጠየቃሉ:: አንዳንዴም ብዙ የተባለበት ጉዳይ ደግሞ እንዲባልለት በሁኔታዎች አስገዳጅነት ጥያቄ ይቀርባል:: በዛሬው ነጻ የግል ሃሳብ መድረኬ ላይ ብዙ ቢባልለትም ጥቂት እንኳን ሊገባን ባልቻለ አንድ መሠረታዊ ሀገራዊ ጉዳይ ላይ የንባብ ቁዘማ እናደርጋለን::
ሀገራችንም ሆነች እኛ ምስኪን ዜጎች ከፖለቲከኞቻችን ጋር ተያይዞ ከምንነጋገርባቸው ወቅታዊ ጉዳዮች መካከል በቀዳሚ ረድፍ ላይ ተሰልፎ ግራ የሚያጋባንንና የሚያስተክዘንን አንድ ጉዳይ ደግመን እንከልሳለን:: ወቅቱ የሀገራዊ ምርጫ ነፋስ ሊነፍስ ዳር ዳር እያለ መሆኑን በማስታወስ::
ሣር ቅጠሉ፣ ሰማይ ምድሩ ፖለቲካ የሆነበት ሀገር ከእኛ ሀገር ውጭ ማግኘት ያዳግት ይመስለኛል:: ምግብ ፖለቲካ ሆኗል:: መጠጥም እንዲሁ:: ልማትም በዘመን ወለድ ፖለቲካ ተፈርጇል:: አልባሳትም የፖለቲካ ታርጋ ተለጥፎባቸዋል:: የፀጉር አቆራረጥና አበጣጠር ፋሽን እንኳ ሳይቀር በፖለቲካ “አምበሬ ጭቃ” ከተቀባ ሰነባብቷል (አምበሬ ጭቃ ከአንድ አራት ዐሠርት ዓመታት በፊት ዝነኛ የነበረ የቅባት ዘር ነው):: ፖለቲከኞች ሁሉም ነገር ከፖለቲካ ውጭ ሊሆን አይችልም እያሉ ፎክረው የሚያስፎክሩት ለዚህ ሳይሆን አይቀርም::
የዐድዋን ድል በማስታወስ እንንደርደር፤
የሀገራችን በርካታ ነባር ታሪካዊ እሴቶችም በፖለቲከኞች ነን ባዮች ከረከሱ ቆይተዋል:: ኢትዮጵያ ውስጥ ዜጎች ብቻ ሳይሆኑ የተፈረደባቸው ቋንቋዎችና ዘመን ያሸበቱ ባህሎችና ወጎችም ሳይቀሩ በፖለቲካ ወዝና ጠረን ከታጠኑ ሰነባብተዋል:: ብዙዎችም ከመከበር ይልቅ ተዋርደዋል::
ከትናንት ወዲያ የካቲት 23 ቀን ለ124 ጊዜ የተከበረው የዐድዋ ደል በዓልን አስመልክተው በአንዳንዶች ዘንድ (ለነገሩማ ቁጥራቸው ከአንዳንዶችም ዘለግ ይላል) ይወረወሩ የነበሩ ትችቶ በርግጥም እንደሚባለው የደረስንበትን ማኅበራዊ ንቅዘት ፍንትው አድርገው የሚያሳዩ ናቸው:: በአንዳንድ የሕዝብ ሚዲያ እንኳ ሳይቀር::
በጸሐፊው የግል መረዳት የዐድዋ ድል በዓል ከየትኞቹም ዓመታት ይልቅ በወጣቶች መንፈስ ላይ ትልቅ መነቃቃት የፈጠረ ይመስለኛል:: ከበዓሉ ቀደም ብሎና የዕለቱ ዕለት ወጣቱ የለበሳቸው አብዛኞቹ አልባሳት የዳግማዊ ምኒልክ፣ የእቴጌ ጣይቱና የወቅቱ የዐድዋ ጀግኖች አርበኞች ምስል የታተሙባቸውን ቲ-ሸርቶች ነበር:: አልፎ አልፎም ጎፈርና መሰል ጥንታዊ የወግ አልባሳትን የተጎናጸፉ ወጣቶችም በብዛት ተስተውለዋል:: ግሩም ነው!
በመሠረቱ ጉዳዩ የአልባሳቱ ብቻ ሳይሆን በዋነኛነት ሊታይ የሚገባው የወጣቱ ትውልድ መንፈስና ህሊና ምን ያህል ለበዓሉ ክብር ነቅቷል የሚለው ስለሆነ የትኩረቱ ዋነኛ ማጠንጠኛ መሆን ያለበት እሱ እንደሚሆን አልጠፋኝም:: ለዚህም ነው በግርድፍ ምልከታዬ ብዙው ዜጋ የታሪኩን ክቡርነትና ፋይዳ ከመቼውም ጊዜ በተሻለ ሁኔታ ገብቶታል ለማለት የደፈርኩት::
በአንጻሩ ጥንታዊ አልባሳቱን አጥብቀው የሚተቹ፣ የጀግኖቹን ምስሎች የሚጠየፉ፣ ቀረርቶውና ፉከራው ያጥወለወላቸው፣ የጀግኖቹ ስም ሲጠራ እየመረረ የጎፈነናቸው፣ በአጭሩ መንፈሳቸውን ያቃራቸው ብዙ ዜጎችም ተስተውለዋል:: ይህ ለምን ሆነ ወይንም ሊሆን ቻለ ብሎ መቆጨትና መንተክተኩ አግባብ አይመስለኝም:: ማንም ሰው የፈለገውን መደገፍና መቃወም ተፈጥሯዊ መብቱ ነው:: ግራ ተጋብተው ግራ ለሚያጋቡን “ፖለቲከኞች” ዕድሜ ባልለምንም ዛሬ አዝመራው ዘርዝሮ ለማየት የበቃነው እነርሱ የዘሩት ክፉ ዘር ውጤት በማሳየቱ እንደሆነ ለመገንዘብ አያዳግትም:: የሚያሳዝነው ግን ዛሬ በኩራት እንድንኖር ምክንያት የሆነንን የገዘፈ ታሪክ ለማዋረድ አቅም መገኘቱ ነው:: ዓለም ከዳር ዳር የሰገደለት ታሪክ በራስ ልጆች መዋረዱ በእንቆቅልሽነቱ መታየት ብቻ ሳይሆን አንገት ማስደፋቱም አይቀርም:: ይህም አንዱ “የፖለቲከኞቻችን” የትዝብት ውርስ አካልና የመንፈስ ንቅዘት መገለጫ ጭምር ነው::
ለማንኛውም ሁሉንም ባይሆን ጥቂቶቹን የዐድዋ ጀግኖች በመንፈስና በቃላት አክብሮ ማለፉ አግባብ ይሆናል:: ምኒልክና ጣይቱ በቀዳሚነት፣ የአካባቢ ንጉሦች፣ ራስ ቢተወደዶችና ራሶችን በተከታይነት፣ ዳጃዝማቾችን፣ ሊጋባዎችን፣ ፊታውራሪዎችን፣ አጋፋሪዎችን፣ ቀኝ አዝማቾችንና ግራዝማቾችን፣ ባላምባራሶችንና ሻቃዎችን፣ ባልደራሶችና ባሻዎችን፣ የበቅሎና የፈረስ ባለሙያዎችን፣ ካህናትን፣ ዘበኞችን፣ ውሃና ስንቅ አዳዮችን፣ ጋጋሪዎችና ወጥ ቤቶችን፣ ፈረሰኞችና ለፎ ተዋጊዎችን፣ አዝማሪዎችንና ሰላዮችን፣ የውስጥ አርበኞችንና ከተማ ጠባቂዎችን በሙሉ ሕይወታቸውን ገብረው አኩሪ ታሪክ ስላስረከቡን ክብርና ሞገስ ይሁንላቸው:: የአሞራ ራት ሆነው አፅማቸው በወጉ ያልተነሳውና ዕድል ገጥሟቸው በክብር ላረፉት አያት ቅድመ አያቶቻችን በሙሉ ሐውልት ባይቆምላቸውም እንኳ ውለታቸውና ታሪካቸው በልባችን ውስጥ ከዘላለም እስከ ዘላለም ከትውልድ ትውልድ እንደተተከለ ይኖራል:: ዘላለማዊ ክብር ለዐድዋ ጀግኖች!
“የፖለቲከኞቻችን” ያልሰከነ ፖለቲካና ውጤቱ፤
ፖለቲካችን ብቻ ሳይሆን አብዛኞቹ ፖለቲከኛ ተብዬዎች ጭምር ከርሞ ጥጃ፣ አድሮ ጮርቃ እንደሆኑ ዘመን ጠብቶ መሽቷል:: የሀገራችን ፖለቲካ የአሜባ ዲ.ኤን.ኤ ያለው ይመስል ባህርይው በአጥፍቶ መጥፋት ተቃኝቶ መኖሩን ሀገር ያወቀው ፀሐይ የሞቀው እውነታ ነው:: ጠንከር እንበል ካልንም ፖለቲካችን አርስጣጥሊስን (384-322 ቅ.ል.ክ) ከመሳሰሉት የፍልስፍናው ቀያሽ ግሪካዊያን አስተሳሰብ ገና ሙሉ ለሙሉ የተላቀቀ አይመስልም::
“Politics” የሚለው ቃል ከግሪኩ “Polis” የተወለደ ሲሆን ኦርጂናል ትርጉሙም “City-State” ወይንም “የከተማ ሥርዓተ መንግሥትን (?)” የሚያመላክት ጽንሰ ሃሳብ ነበር:: የፖለቲካ ጽንሰ ሃሳብ ፈጣሪ ተደርጎ የሚታሰበው አርስጣጥሊስ ይህንን የፖለቲካ ፍልስፍናውን ያስፋፋው በሁሉም የግሪክ ከተሞች ሳይሆን በዋነኛነት የከተሞች ቁንጮ ተደርጋ ትታሰብ በነበረችው የመንግሥታዊና የሃይማኖታዊ ማዕከሏ ጥንታዊቷ አቴንስ ላይ ነበር::
የእኛ ፖለቲከኞችም ከጥንታዊያን ግሪኮች ጋር ለመወዳደር ወግ የደረሳቸው የፖለቲካቸውን ንድፍ ሲያበጁ የኖሩት በመላው ሀገሪቱ ሳይሆን በዋነኛነት በአዲስ አበባ ብቻ ስለሆነ እንደሆነ ጸሐፊው ያምናል:: እርግጥ ነው የየሀገራቱ ዋና ከተሞች ብዙውን ጊዜ የፖለቲካው፣ የኢኮኖሚውና የማሕበራዊ ሽክርክሪት መሆናቸው ይታወቃል:: ችግሩ ግን ሲመችም ሆነ ሳይመች የእኛ ሀገር ፖለቲከኞች ሁሌም የሚቁለጨለጩት የአዲስ አበቤን ዓይን ዓይን ብቻ እያዩ መሆኑ ነው::
ስለሚያራምዱት ፖለቲካና የዲሞክራሲ ምንነት አተገባበር የሚሰጡትን ትንታኔም በተመለከተ እንኳን ለሕዝቡ ይቅርና ለራሳቸውም የገባቸው አይመስልም::
ጎበዙ የሀገራችን ገጣሚ እንዲህ ብሎ ነበር፤
አያቶች በባዶ መስክ ተመራምረው፣
ጠበባቸውን፣ ዕድሜያቸውን ገብረው፣
የጎጆ ንድፍ ሲያበጁ፤ አረጁ::
ዘመናቸውን ፈጁ::
አባቶች! መላ ዘመናቸውን፣
ጎጆ በመቀለስ አሳለፌ፤ ሳይኖሩበት አለፉ::
ልጆች! ጎጆውን ለመውረስ ሳይከጅሉ፣
እንዲህ አሉ፤ “ያባቶቻችን ጎጆ፣
ይሁን ባዶ ይሁን ኦና፣
በኛ ቁመት፣ በኛ መጠን አልተቀለሰምና::
ግሩም ግጥም ነው:: በግሌ የሀገሬን ፖለቲከኞች የምመድባቸው በሚከተለው ቅደም ተከተል መሠረት ነው::
የመጀመሪያ ምድብተኞች፤
በዘመነ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የፊውዳሉን ሥርዓት በመኮነን የፖለቲካ ጥርሳቸውን የነቀሉ ጎምቱ ተብዬዎች ናቸው:: እነዚህ ፖለቲከኞች የትግል ስልት አድርገው ያምኑ የነበረው ከውይይት ይልቅ አውቶቡሶችንና ሕንጻዎችን በመሰባበር ስለነበር ፍልስፍናቸው መንግሥትን ማንበርከክ የሚቻለው በጡንቻ ብቻ ነው የሚል ነበር:: መገለጫቸውም ተጠራጣሪነት ነው:: በነጻነት ዓላማቸውን ከማስረዳት ይልቅ ሁሌም በህቡዕ መንቀሳቀስ ይመርጣሉ:: የሌላው ጠንካራ ተሞክሮ በፍጹም አይታያቸውም:: እነርሱ ካሉት ውጭ ተከታዮቻቸው አዳዲስ ሀሳብ እንዲያፈልቁም ዕድል አይሰጧቸውም:: ቋንቋቸው ምፀት የተሞላበት፣ ተቃውሟቸው ሽርደዳ የታከለበት ዓይነት ነው:: “በእኛ ዘመን” የሚለው ሀረግ የተዘወተረ የንግግራቸው መክፈቻ ነው:: እንደነዚህ ዓይነቶቹ “ውሎ ገቦች” (አንዴ ውጭ አንዴ ውስጥ ገባ ወጣ የሚሉ) ፖለቲከኞች በሃሳብ ልዕልና ከመመራት ይልቅ ተቀናቃኞቻቸው የሚሰሯቸውን ስህተቶች አድፍጦ እጅ ከፍንጅ ለመያዝ ሁሌም እንዳደቡ ነው:: ያንንም ችግር እያጮኹ መከራከሪያ ለማድረግ ማንም አይቀድማቸውም::
አዲስ ሃሳብ ስለሌላቸው ህልውናቸውን አስጠብቀው ለመኖር የሚሞክሩት ከአንዱ ድርጅት ወደሌላው ድርጅት እየተገለባበጡና ራሳቸውን እየለዋወጡ ነው:: መንገዱን ልቀቁልን ለሚሏቸው ተከታዮቻቸው ምላሻቸውን የሚሰጡት በንግግርና በውይይት ሳይሆን ስማቸውን በማጉደፍና በማጠልሸት ነው:: እነዚህ የዘመነ አፄው ፖለቲከኞች ዛሬም በፖለቲካው ምህዳር ውስጥ ካልተጫወትን እያሉ ሲፋተጉ እያስተዋልናቸው ነው:: ፖለቲካው ለእነርሱ ዝና፣ እንጀራ፣ ክብር ስለሆነ ፈቅ በሉ የሚላቸው ጠላታቸው ነው::
ሁለተኞቹ ምድብተኞች፤
በአምባገነኑ የደርግ ግንድ ላይ የበቀሉ ቅርንጫፎች ናቸው:: ብዙ ዕውቀት ባይኖራቸውም እንዳላቸው አድርገው ስለሚከራከሩ ለራሳቸውም ተቸግረው ሰሚያቸውንና ተከታዮቻቸውን የሚያስቸግሩት በይሉኝታ ቢስነት ነው:: ዛሬም ግባ መሬቱ የተፈጸመው የሶሻሊዝም ሥርዓት በትንሣኤ አርጎ “በወዝ አደሩ አምባገነንነት” እየተሳበበ ቢነገድ ደስታቸው ነው:: የተለየ መታወቂያቸው በየቢሯቸው አቧራው ሳይራገፍ በመጻሕፍት መደርደሪያቸው ላይ የሚስተዋሉት የማሌ (ማርክሲስት ሌኒኒስት) መጻሕፍት ናቸው:: በነገራችን ላይ በአንድ የተለየ አጋጣሚ አንድ ከፍተኛ የፓርቲ ባለሥልጣን ቢሮ በተገኘሁበት አጋጣሚ እነዚህን መሰል መጻሕፍት ተደርድረው አስተውያለሁ:: ችግሩ የመጻሕፍቱ መደርደር ሳይሆን ዛሬም ድረስ ሰዎቹ ከቅዠት ዓለም መላቀቅ ያለመቻላቸውን ነው::
ሦስተኞቹ ምድብተኞች፤
“የአብዮታዊ ዲሞክራሲ” የጡት ልጆች ስብስብ ነው:: ብዙዎቹ በረኸኞችና በረኸኞቹ አዲስ አበባን ሲቆጣጠሩ ቄጤማ ጎዝጉዘው የተቀበሏቸው የዚህ ምድብ አባላት የፖለቲካቸው አልፋ ኦሜጋ ጫካ ሳሉ የማሉለት መርህ ነው:: እነርሱ ከቀየሱት የፖለቲካ ፍልስፍና ውጭ ሌላ አመለካከት ለማስተናገድ ቀርቶ ሲያስቡት ራሱ ይተናነቃቸዋል:: ንግግራቸውን የሚጀምሩት ደርግን በማውገዝ፣ የእነርሱን የ27 ዓመታት “ትሩፋት” በመተረክ እንጂ አዲስ ርዕይና ዓለም እንዳለ እንኳ አይታያቸውም:: “በፋሲካ የደነቆረች ሁሌም ፋሲካ ይመስላታል” እንዲሉ ነጋ ጠባ ደርግን አንበርክከን እያሉ መፎከር ባህላቸው አድርገውታል:: እነዚህ ፖለቲከኞች ቀዳሚው መርሃቸው በትግላችን ትሩፋት ቅድሚያ እፍታው ለእኛና በእኛ ዙሪያ ላሉት መሆን ይገባዋል ባዮች ናቸው:: ተደርጎም አስተውለናልና አይገርመንም:: ዛሬም ምኞቱ አልጠፋም:: ጠብመንጃ በእጃቸው ላይ እንኳ ባይኖር የቃላት ቀለህ እየተኮሱ ለማሸማቀቅ መሞከር ዋናው መገለጫቸው ነው::
አራተኞቹ ምድብተኞች፤
የህልመኞች ስብስብ ነው:: በእውንም ሆነ በሌሊት የሚታያቸው ሹመትና የተሻሉ ጥቅማ ጥቅሞች ብቻ ናቸው:: በራስ ተማምኖ በሥራ ከሚገኝ ውጤት ይልቅ በኔትወርክ ፍብረካ ላይ በአብዛኛው ሲተጉ ይስተዋላል:: ተቀናቃኞቻቸውን በኔትወርካቸው ጠልፈው ለመጣልና ከጨዋታ ውጭ ለማድረግ የሚተጉት በሞት በሽረት ወኔ ነው:: ግምገማ ዋና የማጥቂያቸው ስልት ነው::
አምስተኞቹ ምድብተኞች፤
ቁጥራቸው ጥቂትና አስተውለው የሚራመዱ ናቸው:: የሚጨክኑት የሕዝባቸውን ሰቆቃ ለማስወገድ ነው:: ከራሳቸው ይልቅ የሀገራቸውን ክብር ያስቀድማሉ:: ከሥጋ ድንዳኔ ይልቅ የሚሰሩት ከህሊናቸው ጋር እየተማከሩ ነው:: የነገዋ ብሩህ ፀሐይ ዛሬ ወለል ብላ ትታያቸዋለች:: ከፖለቲከኝነት ይልቅ ለሰብዓዊነት ክብር ቅድሚያ ይሰጣሉ:: ቁጥራቸው ቢያንስም ዓላማቸው ግን ግዙፍ ነው:: ለዓላማቸውም የጨከኑ ናቸው::
በሀገራችን ውስጥ እየተተረማመሱ ያሉት እንዲህ ዓይነት መልክና ቀለም ያላቸው “ፖለቲከኞች” ናቸው:: ይህን መሰሉ ያልጠራ የፖለቲካ ትርምስምስ ስላሳሰበኝ ነው “የፖለቲከኞቻችንን የፖለቲካ መርህ” ወደ ጎን ገፍተን በነፃነት ብንኖርስ? ብዬ በርዕሴ ድምፀት የጠየቅሁት:: አከራካሪ ሃሳብ እንደሆነ ይገባኛል:: አንዳንዶችም በሃሳቤ እንደማይስማሙ ይገባኛል:: ቢሆንም ግን ባገኘሁት “የግል ሃሳብ ነፃነቴ” እኔ ይህንን ብያለሁ:: ሰላም ይሁን!!
አዲስ ዘመን ረቡዕ የካቲት 25/2012
በጌታቸው በለጠ/ዳግላስ ጴጥሮስ