ኢትዮጵያውያን ጋዜጠኞች አንድ የተለመደች አባባል አለቻቸው፡፡ “የዘንድሮውን በዓል ለየት የሚያደርገው…” የምትል፡፡ አዎ!.. የዘንድሮውን 124ኛ የአድዋ በዓል ለየት የሚያደርገው የዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር ለአድዋ ባለድሎቹ ኢትዮጵያውያን ማስጠናቀቂያ አዘል መግለጫ ባስነገረ ማግስት የሚከበር መሆኑ ነው፡፡
በግብጽ ጠያቂነት ኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብጽ ከህዳሴ ግድብ ውሃ ሙሌት ጋር ተያይዞ በዋሽንግተን የጀመሩት ድርድር አስመልክቶ የዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካ መንግሥት ዓርብ የካቲት 20 ቀን 2012 ዓ.ም ማምሻውን ያወጣው ማስጠንቀቂያ አዘል መግለጫ ኢትዮጵያውያንን ክፉኛ አስቆጥቷል፡፡
ማስጠንቀቂያውን ብዙ ኢትዮጵያውያን ለአድዋ ጦርነት መንስኤ የነበረውና የኢጣሊያን ጥቅም ለማስጠበቅ ከተፈረመው የውጫሌ ውል ጋር መሳ ለመሳ አስቀምጠውታል፡፡
ዩናይትድ ስቴት አሜሪካ መግለጫውን ያወጣችው ኢትዮጵያ በሰሞኑ ስብሰባ ለመካፈል እንደማትችል ከገለጸች በኋላ ነው፡፡ የታላቁ የህዳሴ ግድብን የተመለከተ ውይይት በኢትዮጵያ፣ ግብጽ እና ሱዳን መካከል በአሜሪካ ግምጃ ቤት ኃላፊ እና የዓለም ባንክ ፕሬዚዳንት በታዛቢነት የተገኙበት የሶስትዮሽ ድርድር በአሜሪካ ሲካሄድ መቆየቱ ይታወሳል።
የኢትዮጵያ ተደራዳሪ ቡድን በአገር ውስጥ ከባለድርሻ አካላት ጋር የሚያደርገውን ውይይት ባለማጠናቀቁ የካቲት 19 እና 20 ቀን 2012 ዓ.ም በዋሽንግተን ዲሲ ከተማ ሊካሄድ በታሰበው የሶስትዮሽ ድርድር ላይ እንደማይሳተፍ የውሃ ፣ መስኖ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር ቀደም ሲል አስታውቆ ነበር።
ሚኒስቴሩ በተጠቀሰው ጊዜ አሜሪካ በመገኘት ድርድሩን ማድረግ እንዳልቻለ ጥሪውን ላደረገው የአሜሪካ ግምጃ ቤት ቢሮ ገልጿል።
የአሜሪካ የገንዘብ ሚኒስቴር ስቴቨን ምኑቺን ሰሞኑን ባወጡት መግለጫ ቀደም ሲል የነበረውና ግንባታው በታችኛው የተፋሰሱ አገራት ላይ ጉልህ ጉዳት እንዳይደርስ በሚለው የመርህ ስምምነት መሠረት “ግድቡን በውሃ የመሙላትና ሥራውን የመሞከር ሒደት ስምምነት ሳይደረግ መከናወን የለበትም” ብሏል።
መግለጫው አያይዞም ከዚህ በፊት በነበሩ ስምምነቶች መሠረት ግድቡን በውሃ የመሙላቱ ሥራ ከመጀመሩ በፊት በአገራቱ መካከል ስምምነት መፈረም አለበት። ለዚህም በተፋሰሱ አገራት መካከል የተጀመረው ድርድር በቶሎ መጠናቀቅ እንዳለበት የሚኒስትሩ መግለጫ አመልክቶ፣ ግብጽ ስምምነቱን ለመፈረም ያሳየችውን ዝግጁነት አድንቋል።
መግለጫው አያይዞም በኢትዮጵያ በኩል በጉዳዩ ላይ እየተካሄደ ያለውን ብሔራዊ ምክክር እንደሚረዳ በማመልከት ምክክሩ በቶሎ ተጠናቅቆ የድርድር ሂደቱን በማጠናቀቅ በተቻለ ፍጥነት ስምምነቱ እንዲፈረም ፍላጎታቸው መሆኑን ጠቅሷል።
ግድቡን በውሃ የመሙላት ሥራ ከመጀመሩ በፊት በዓለም አቀፍ ደረጃዎች መሠረት ሁሉም አስፈላጊ የደህንነት እርምጃዎች ተግባራዊ ከመደረጋቸው አንጻር በታችኞቹ ተፋሰስ አገራት ግብጽና ሱዳን ሕዝብ ዘንድ ያለውን ስጋት እንደሚገነዘቡ አመልክቷል።
“አንቀበለውም ” ኢትዮጵያ፤ የካቲት 2012
በህዳሴ ግድብ ድርድር ዙሪያ ከኢትዮጵያ መንግስት ሰሞኑን የተሰጠው መግለጫ እንዲህ ይላል፡፡ የኢትዮጵያ ፌዴራለዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና የውሃ፣ መስኖ እና ኢነርጂ ሚኒሰቴር የአሜሪካ የግምጃ ቤት ዲፓርትመንት ሴክሬታሪ በየካቲት 21 ቀን 2012 ዓ.ም. (እ.ኤ.አ. በ28 ፌብሩዋሪ 2020) የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን በተመለከተ ኢትዮጵያ ያልተሳተፈችበትን ስብሰባ ተከትሎ የወጣውን የፕሬስ መግለጫ በከፍተኛ ቅሬታ ተመልክተውታል። ስብሰባው የተካሄደው ኢትዮጵያ አስቀድማ ለግብጽ፣ ለሱዳን እና ለአሜሪካ ስብሰባው ለሌላ ጊዜ እንዲተላለፍ አሳውቃ እያለ ነው፡፡ የግድቡ ባለቤት የሆነችው ኢትዮጵያ በመርሆዎች መግለጫ ስምምነቱ መሠረት የግድቡን ሙሌት ከግንባታው ትይዩ በፍትሐዊ እና ምክንያታዊ አጠቃቀም እና ጉልህ ጉዳት ያለማድረስ መርሆዎች መሠረት የምታከናውን ይሆናል።
ኢትዮጵያ የግድቡን የመጀመሪያ ሙሌት እና የውሃ አለቃቅ መመሪያ እና ደንብ ለማዘጋጀት የሚደረገው ድርድር ተጠናቋል በሚል የተሰጠውን መግለጫ አትቀበልም። በዋሽንግተን ዲሲ የግብጽ ዐረባዊት ሪፐብሊክ ፈርሞበታል የተባለው “ረቂቅ” የሶስቱ ሀገራት የድርድርም ሆነ የሕግ እና ቴክኒክ ቡድኖች ውይይት ውጤት አይደለም።
የቴክኒክ ጉዳዮች ድርድሩም ሆነ የሕግ ማዕቀፍ ዝግጅቱ ላይ የሚደረገው ድርድር አልተጠናቀቀም፡፡ ኢትዮጵያ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የመጀመሪያ ሙሌት እና የውሃ አለቃቀቅ መመሪያ እና ደንብ የሚዘጋጀው በሶስቱ ሀገራት ብቻ እንደሆነ አቋሟን ቀድማ አሳውቃለች።
ኢትዮጵያ ግብጽ እና ሱዳን በሚያውቁት እና በተስማሙበት እንዲሁም በመርሆዎች መግለጫ ስምምነት መርህ አንቀጽ ስምንት አድናቆታቸውን በሰጡት ሂደት መሠረት ሁሉንም የግድብ ደህንነት የሚመለከቱ ጉዳዮች በዓለም አቀፍ የባለሙያዎች ቡድን ምክረ ሃሳብ መሰረት የተሰጡትን ምክረ-ሃሳቦች መፈጸሟን ትቀጥላለች።
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የመጀመሪያ ሙሌት እና የውሃ አለቃቀቅ መመሪያ እና ደንብን ለማዘጋጀት ቀሪ መሰረታዊ ልዩነቶችን ለመፍታት ኢትዮጵያ ከግብጽ ዐረባዊት ሪፐብሊክ እና ከሱዳን ሪፐብሊክ ጋር የጀመረችውን ሂደት ለመቀጠል ቁርጠኛ ናት።
“አንቀበልም” ኢትዮጵያ 1881
ለአድዋ ጦርነት መንስኤ የነበረው የውጫሌ ውል የተፈረመው ከአዲስ አበባ በስተሰሜን 468 ኪሎ ሜትር ከውጫሌ ከተማ ግርጌ ከአምባሰል ተራራ ስር ወሎ ውስጥ ንጉስ ይስማ እየተባለ በሚጠራ ሥፍራ ነው:: ከውጫሌ ውል እጅግ አወዛጋቢ የነበረው 17ኛው አንቀጽ እንዲህ ይላል፡፡ “ኢትዮጵያ ከማንኛውም አገር ጋር የውጭ እና የዲፕሎማሲ ግንኙነት የምታደርገው በኢጣሊያ በኩል ነው፡፡” ሰሞኑንም ኢትዮጵያውያኖችን ያስቆጣው የዩናይትድ ስቴትስ መግለጫ በአጭሩ ሶስቱ አገራት (ኢትዮጵያ፣ ግብጽና ሱዳን) ሳይስማሙ ኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌትና ኃይል ማመንጨት ለመጀመር እንዳታስብ የሚያስጠነቅቅ ነው፡፡
ከውጫሌ ውል አንቀጽ 17 ሌላ የኢትዮጵያን ሉዐላዊነት የሚፃረሩ በርካታ አንቀፆች ሆን ተብሎ በጣሊያኖች በኩል የተካተቱበት በሴራ የተሞላ ውል ነበር። ለመሆኑ ከ17ኛው አንቀፅ ሌላ የሀገራችንን ነፃነት በቅኝ ገዢነት ለመንጠቅ ጣልያኖቹ የቀመሟቸው የተንኮል አንቀፃች የትኞቹና ምን የሚሉ ነበሩ?
ጣልያን፤ አፍሪካን በተቀራመቱበት የበርሊኑ የአውሮፓ የግዛት ቅርጫ ክፍፍል ደህና ግዛት አልደረሰውም፡፡ኢትዮጵያውያን ደግሞ ለነፃነታቸው የማያመነቱ እምቢ ባዮች መሆናቸውን ያውቃል። እና ምን ይሻላል ? ክሪስፒ እና አፈ ጮሌው አንቶኖሊ በውጫሌው ውል አስረው ኢትዮጵያን ለመጣል ወሰኑ። በዚያ ዘመን የአፍሪካ ሀገራትን እንደ ሉዐላዊ መንግስት ቆጥሮ ውል የሚዋዋል የአውሮፓ ሀገር አልነበረም ።
እኛን ግን ያውቁናልና ቀስ በቀስ እርስ በእርስ በስልጣን ተቀናቃኞች መሀል የነበረውን ክፍተት ተጠቀሙ። ቀይ ባህርንና ከመረብ ምላሽ ያለውን ግዛት አቋርጠው መላዋን ሀገራችንን ለመጠቅለልም የውጫሌን ውል አረቀቁ ።
ዐፄ ምኒልክ ዙፋናቸው በውስጥ ተቀናቃኝ መሳፍንት የተነሳ በደምብ አለመፅናቱን የሚያውቀው አንቶኖሊ “በሰሜን በኩል ተቀናቃኞችዎ መሳሪያ እንዳያገኙ አግዳለሁ። መሳሪያ የሚገባው ለእርስዎ ጦር ብቻ ይሆናል፤ ስለዚህ የንግድ እና የትብብር ውል ሀገርዎና ሀገሬ ይፈርሙ” ብሎ አግባባቸው። ይህም የውጫሌ ውልን ወለደ። ውሉ ሃያ አንቀፆች ነበሩት።
አንቀፆቹ ግን እንደተባሉት የወዳጅነት ሳይሆኑ ጣልያኖቹ ሉዓላዊነታችንን ለመንጠቅ በጎነጎኗቸው ሴራዎች የተሞሉ ነበሩ ።
1 .ጣልያን በወረራ የያዛቸውን የሰሜን ግዛቶች ሀገራችን አምና እንደተቀበለች ለማስመሰል የጣልያን ግዛት እና የኢትዮጵያ በሚል አካሏል።
2. ሀገራችንን እንደ ሉዐላዊ ሀገር ባለመቁጠር በግዛታችን ያሉ ጣልያኖች ከባድ ወንጀል ከፈፀሙ በጣሊያን ሕግ እንዲዳኙ፤ በሀገራችን የሚኖሩ ጣልያኖች ከተካሰሱ በጣሊያን የምፅዋ ሹም እንዲዳኙ፤ ኢትዮጵያዊና ጣልያን ሲጣሉ ግን የኢትዮጵያና የጣልያን የምፅዋ ሹም ወኪል ባለበት እንዲዳኙ የሚል አንቀፅ ተካቶበታል።
3. በምፅዋ ወደብ መሳሪያ ለማስገባት በጣልያን ፈቃድና ጥበቃ ስር እንዲሆን አድርጓል። በወደቡ ለሚገቡና ለሚወጡ የንግድ እቃዎች ጣልያን ክፍያ እንድትቀበል የሚለው አንቀፅ፣
4. ደብረ ቢዛን ገዳም በጣልያን ግዛት ስር እንደሆነ አድርጎ ባለቤትነቱን የኢትዮጵያ በማድረግ የጦር ሰፈር እንዳይሆን መከልከሉ፣
5. የዘመኑን የአውሮፓ አፍሪካን የማሰልጠን የቅኝ አገዛዝ ማስመሰያ ፋሽን በመከተል የባሪያ ንግድ እንዲቀር በጣልያን በኩል ሀገራችን የተስማማች የሚያስመስል አንቀፅ አካቷል።
6. ውሉ በኮንቶኖሊ እና በምኒሊክ ከተፈረመ ከሚያዝያ 25 ቀን 1881 ዓ.ም ጀምሮ በኢትዮጵያ ላይ አስገዳጅ ሲሆን ለጣልያን ግን በሮማ ቀርቦ በፍጥነት እንዲፀድቅ በሚል የጣልያንን ፍላጎት በሚያስጠብቅ መልኩ ክፍተት መተው እና የድንበር ወሰንን በተመለከተ እንዳይሻሻል መከልከሉ ፤
7. የውሉ የአማርኛ እና የጣልያንኛ ትርጉም እኩል ተቀባይነት እንዳለው የሚገልፅ አንቀፅ መካተቱ ጣልያኖቹ የቀመሟቸውን ሌሎች የተንኮል አንቀፆች የሚያሳዩ ናቸው።
እነዚህን ሁሉ ነፃ ሀገራችንን የመተብተቢያ አንቀፆችን ያካተተውን የውጫሌ ውል ግን የ17ኛው አንቀፅ የጣልያንኛው ትርጉም አላማቸውን አጋለጠው። ይህ አንቀፅ ጣልያንኛው “ኢትዮጵያ ለሚኖራት የውጭ ግንኙነት ሁሉ በጣልያን በኩል ብቻ እንዲሆን ተስማምታለች” የሚል ነበር አማርኛው ግን “ትችላለች” ይል ነበር።
ኮንቶኖሊ ይህን የጣልያንኛውን ትርጉም ከአማርኛው ጋር እንዲመሳሰል አስተካክል ቢባል የተርጓሚው የግራዝማች ዮሴፍ ስህተት ነው፤ የጣልያንኛው ትርጉም ትክክል ነው አለ። ውሉን ያዩ የአውሮፓ መንግስታትም በጣልያን በኩል ካልሆነ የኛን መልዕክተኞች አልቀበል አሉ። ውሉ ከተፈረመ በኋላ ለሰባት ዓመታት በድርድር ጥረት ቢደረግም ሊስተካከል አልቻለም።
በመጨረሻም የኛ ብቻ ሳይሆን የጥቁር ህዝብ ኩራት የሆነው የአድዋ ጦርነት ተወለደ። ዘመናዊ ስንቅና ትጥቅ ያለው የኢጣሊያ ጦርም፤ እምብዛም የረባ የጦር መሳሪያ በሌለው፣ የአገር ፍቅር ወኔ ብቻ በታጠቀው የኢትዮጽያ ጦር ድባቅ ተመትቶ የሽንፈት ጽዋውን ሊቀበል ግድ ሆነ፡፡
በመጨረሻም
የመሠረት ድንጋዩ ከተቀመጠ 9 ዓመታትን የቆጠረው የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ 71 በመቶ፤ የህዝቡ ተሳትፎም በገንዘብ 14 ቢሊየን ብር ደርሷል፡፡እንደሚታወቀው የናይል ወንዝ (አባይ) ግድብ ከ86 በመቶ በላይ አስተዋጽኦ የምታደርገው አገራችን ናት፡፡ በአንጻሩ የኤሌክትሪክ ኃይል ጨርሶ ያላገኙ ወገኖች ቁጥር ከ60 በመቶ በላይ ነው፡፡ የግድቡ ግንባታ የአገር ውስጥ የኤሌክትሪክ ፍጆታን ከማሳደግ ባለፈ ለጎረቤት አገራት ኃይል በመሸጥ የውጭ ምንዛሪ ገቢ ለማስገኘት ያለመ ነው፡፡
አንጋፋው የአሜሪካ የጥቁሮች ሰብዓዊ መብት ተሟጋች ጄሲ ጃክስን በታላቁ ህዳሴ ግድብ ሰሞኑን አሜሪካ ያራመደችውን አቋም በመታዘብ የተናገረውን ልጥቀስ፡፡ “የአሜሪካ መንግሥት በኮሎራዶ ወንዝ ላይ የገነባውን የሁቬር ግድብ ቁጥጥር እና የወንዙ ባለቤትነት ሉአላዊ መብቱን ለሚፈስበት ለሜክሲኮ አሳልፎ ይሰጣልን? በፍጹም አያደርግም፡፡ ስለዚህ ኢትዮጵያ አሁን የቀረበላትን ስምምነት እንድትፈርም አሜሪካ የምታስገድድ ከሆነ ግብጽ በወንዙ ላይ ባለሙሉ ሥልጣን ማድረግ በመንፈስም ሆነ በተጨባጭ የኒዮ ኮሎኒያል ስምምነት ዓይነት ነው፡፡ ይህ አገሪቱ በገዛ ውሃዋ ላይ እንዳትጠቀም የሚያደርግ የአሜሪካ እና የዓለም ባንክ ተግባር ታሪክም ሆነ የዓለም አቀፍ ሕግ የማይዘነጋው ወንጀል ይሆናል፡፡ ይህም ግሬት ብሪታኒያ የ1929ን የቅኝ ግዛት ውል ትክክለኛና ተቀባይነት ያለው የ21ኛው ክፍለ ዘመን ሕጋዊ ሰነድ አድርጎ እንደማቅረብ ይቆጠራል፡፡”
የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትርና የኢትዮጵያ ዋና ተደራዳሪ ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ ለታዲያስ አዲስ የራዲዮ ፕሮግራም ሰሞኑን በሰጡት አጭር መግለጫ እንዲህ ብለው ነበር፡፡ “የህዳሴ ግድብ ዕጣ ፈንታ ምንም የሚለወጥ ነገር የለም፡፡ ግንባታውም እየተካሄደ ነው፤ የኮንስትራክሽን ሒደቱ የውሃ ሙሌት ደረጃ ሲደርስ መሙላት ይጀመራል፡፡ ድርድሩም ይቀጥላል፤ ድርድሩን የሚያቆም ምንም ምክንያት የለም፡፡”
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ የአድዋ ድል 124ኛ ዓመት በዓል አስመልክቶ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ባስተላለፉት መልዕክት “የውሃ ሙሌት መቼ መጀመር እንዳለብን የምንወስነው እኛ ኢትዮጵያውያን ነን ብለዋል፡፡ “አያቶቻችን በጋራ አድዋ ላይ የሞቱት ሌሎች አገራት በእኛ ጉዳይ እንዳይወስኑም ጭምር ነው፡፡ ግድቡ ተገንብቶ ይጠናቀቃል፤ ከወዳጆቻችንም ጋር እንመርቀዋለን” በማለት የማያወላውል ቁርጠኛ አቋማቸውን አንጸባርቀዋል፡፡ (ማጣቀሻዎች፡- የታላቁ ህዳሴ ግድብ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት፣ ቢቢሲ፣ ዊኪፒዲያ፣ኢትዮ ኤፍ ኤም፣ የኪዳኔ መካሻ መጣጥፍ፣…)
አዲስ ዘመን ረቡዕ የካቲት 25/2012
ፍሬው አበበ