
የጥቁር ሕዝብ ታላቅ ድል የሆነው ዓድዋ የተራሮቿን ያህል ገዝፎ የኢትዮጵያውያንን ገድል ለዓለም ማድረሱን ቀጥሏል። ጥንት ለዚቺ አገር ክብር አጥንታቸውን የከሰከሱ፤ ለአገር ሉዓላዊነት እራሳቸውን መስዕዋት ያደረጉ ጀግኖች በብዙ መልክ መታወሳቸውን ቀጥሏል። እነዚያ ጀግኖች በልጆቻቸው ተግባር በብዙ ይወሳሉ። የአገርን መወረር፤ የድንበርን መጣስ የሰሙት አባቶች ለመጋደል ወደ ሰሜን በእግራቸው ተጉዘዋል።
ያ ዘመን የየብስ መጓጓዣ መኪና ተጠቅመው የሚሄዱበት፤ አውሮፕላንን ተጠቅመው የሚበሩበት አልነበረም። ከአንድ ሺህ በላይ ኪሎ ሜትሮችን አቋርጠው በአገር ፍቅር ስሜት በኋላ ቀር መሣሪያ ጠላትን የተፋለሙበት አባቶች ዛሬም በሌላ ገፅ ይታያሉ። እነዚያ ጀግኖች በልጆቻቸው ብርቱ እግሮች ይዘከራሉ።
ዛሬ በእግር ጉዞ ልዩ ክስተት ይታሰባል። በዓድዋ ተጓዦች፤ ከመላው ኢትዮጵያ ከተለያዩ አካባቢዎች፤ ከልዩ ልዩ እምነትና ብሔር የተውጣጡ ለአንድ አላማ የተሰለፉ 102 ብርቱ እግሮቻቸውን ተጠቅመው ቁጥራቸው 51 የሆኑ ኢትዮጵያውያን ወደ ዓድዋ ተጉዘው፤ መንገድ ላይ ኢትዮጵያዊ ፍቅር ከወገኖቻቸው ጋር ተካፍለው፣ የማህበረሰቡን እሴትና ባህል ተጋርተው፣ የአኗኗርና የአብሮነት ልምዱን ቀስመው የዛሬ 124 ዓመታት አባቶቻቸው የሠሩትን ገድል ወደ ኋላ ተመልሰው በተግባር ዘክረዋል።
የዓድዋ ጉዞ መሥራችና አስተባባሪ አርቲስት ያሬድ ሹመቴ የጉዟቸውን አላማ ሲያስረዳ ኢትዮጵያዊ አንድነትን ለማጠናከር የርዕስ በርዕስ ግንኙነቱን መልካምነት ለማጉላትና የአባቶችን ታላቁን የዓድዋ ድል መታሰቢያ አድርጎ ፍቅርና አንድነትን ለመስበክ እንደሆነ ያስረዳል። ጉዟቸው የተለየዩ ማህበረሰቦችን አብሮ የመኖር እሴት በማጉላት ኢትዮጵያዊ አንድነትን ለማጠናከር እንደሚረዳም ይናገራል።
ዛሬ ታላቁን ክብረ በዓል የሚከናወንበት ታሪካዊው ዓድዋ ላይ መዳረሳቸውን የገለፀው አርቲስት ያሬድ ሹመቴ የዓድዋ ጉዞ የኢትዮጵያ ህዝብ ዛሬ ድረስ አንድነቱና ሕብረቱን ጠብቆ የቆየና በአንድነት የሚያምን ሥነ ልቦና የተላበሰ መሆኑን ማሳየቱን ይገልፃል።
ዘንድሮው ለ7ኛ ጊዜ በመደረግ ላይ ያለው ጉዞ ዓድዋ የተጓዦቹን ስሜት በሐሴት እንዲሞላ ያደረጉ ብዙ ገጠመኞች መኖራቸውን የሚያስረዳው አርቲስት ያሬድ በየ መዳረሻቸው በልዩ አቀባበልና ኢትዮጵያዊ ጨዋነት እየተስተናገዱ መሆኑን ይገልፃል። “ኢትዮጵያውያን አንድነትና ሕብረታችን የተጠናከረ በብዙ መልኩ የተጋመዱ ልዩ ታሪክ ያለን ህዝቦች ነን።” በማለት የኢትጵያውያንን አብሮነት በልዩ መልክ ይገልፀዋል።
በዘንድሮው ጉዞ ዓድዋ ተሳታፊ የሆኑ ስልሳ ሦስት ኢትዮጵያውያን ሲሆኑ ዘጠኝ ሴት ተጓዦች ተሳትፎ አድርገዋል። የአራት ልጆች እናትን ጨምሮ ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ተሳታፊ የሆኑት ተጓዦቹ በየደረሱበት የማህበረሰቡ ባህልና እሴት እየተመለከቱና በልዩ ልዩ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ፍቅር በተሞላበት መልኩ ጉዞ እያደረጉ መሆኑን ይናገራል።
አብሮነትን ለማጎልበትና ታሪክን ለመዘከር የሚደረገው ጉዞ የተያዘለትን ዓላማ ለማሳካት ትልቅ አቅም መፍጠሩን የሚገልፀው አርቲስት ያሬድ፤ ትውልዱ አባቶቹ በሕብረትና በአንድነት ጠብቀው በመስዕዋትነት ያቆዩለትን አገሩን መጠበቅና የጋራ ፍቅሩን ለማፅናት መትጋት ይገባዋል በማለት ምክረ ሐሳቡን ይለግሳል።
የዘንደሮው የ“ጉዞ ዓድዋ” ተጓዦች በ43 ቀናት ጉዟቸው የተለያዩ የኢትዮጵያ ከተሞችን ያቆራረጡት የዓድዋ ተጓዦች፤ ኢትዮጵያውያን አንድነትና ህዝባዊ ግንኙነትን የሚያጠናክሩ የሰላም መልዕክቶችን በማስተላለፍና ዛሬ ዓድዋ የከተሙት ተጓዦች አገራዊ ሕብረትና መልካም ግንኙነት በማጠናከር ያለው ሚና የጎላ መሆኑ ተገልጿል።
በሌላ በኩል፤ ባለፈው ሳምንት አገር አቀፍ የሰላም ጉዞ ለማድረግ መነሻቸውን አዲስ አበባ ያደረጉት አቶ አዳሙ አምባቸው፤ በተለያዩ ከተሞች ላይ በመዘዋወር የሰላም መልዕክት ማድረሳቸውና ከህብረተሰቡ መልካም የሆነ ድጋፍ ማግኘታቸውን ገልፀዋል። የሰላም ተጓዡ አቶ አዳሙ የህብረተሰቡ የሰላም ወዳድነት አድንቀው ይዘው የተነሱትን የሰላም መልዕክት ለህብረተሰቡ በሚያስተላልፉበት ወቅት የተሰጣቸው ምላሽ ደጋፊና አበረታች መሆኑን ለዝግጅት ክፍላችን ገልፀዋል።
በጉዟቸውም በአማራ ክልል ደብረ ብርሃን፤ ሻዋ ሮቢት፤ ኮምቦልቻ፤ ከሚሴ፤ ወልዲያ፣ ቆቦን ማቋረጣቸውንና የተነሱበትን ዓላማ የሚያስተላልፉት መልዕክቶችን ለህብረተሰቡ ማድረሳቸውን ተናግረዋል። በተመሳሳይ በትግራይ ክልል አላማጣ፣ መቀሌ፣ አዲግራት ከተሞች ላይ በመዘዋወር ስለ ሰላም መልዕክት ማስተላለፋቸውን ጠቁመው ከጉዞ ዓድዋ ተጓዦች ጋር ዛሬ ዓድዋ ከተማ ገብተው ታሪካዊ ክብረ በዓሉን እንደሚሳተፉ ገልፀዋል።
አዲስ ዘመን የካቲት 23/2012
ተገኝ ብሩ