ጣልያን ቅኝ ለመግዛት ወደ አፍሪካ አህጉር ስትመጣ ረፍዶባታል። ያዘገያት ደግሞ ሀገሪቷ ውህደት ላይ መሆኗ ነበር። ውህደቷ እንደተጠናቀቀ ታዲያ ወደ አፍሪካ ስትመጣ አብዛኛዎቹ የአፍሪካ ሀገራት በተለይ በእንግሊዝና በፈረንሳይ ቅኝ ግዛት ስር ወድቀዋል። የራበው ጅብ ያገኘውን ከመብላት ወደኋላ አይልምና ጣልያን በቅድሚያ ሊቢያን በቅኝ ግዛት ቀንበር ውስጥ ለማስገባት ብዙ ጊዜ አልፈጀባትም። ከሊቢያ በመቀጠል በምስራቅ አፍሪካ የቅኝ ግዛቷን ለማስፋፋት ውጥን የነበራት ጣሊያ ስትገሰግስ ወደ ኢትዮጵያ መጣች።
ጣሊያን ወደዚች ምድሯ የለመለመና አየሯ የሰጠ ኢትዮጵያ ስትመጣ ግን ልክ እንደ ሊቢያ ነገሮች ሁሉ አልጋ በአልጋ አልሆኑላትም። ገና ከመነሻው የኢትዮጵያን ምድር በቅኝ ግዛት ለማዋል ስትመጣ በቅድሚያ በኤርትራ ግዛት ዶጋሊ፤ ኳቲትና ሰአቲት ላይ በኢትዮጵያውያን ጀግና አርበኞች ሽንፈት ተከናንባለች። በኋላ ላይ አቅሟን አጠናክራ ወደ መሃል ኢትዮጵያ ለመግባት ክፉኛ ተፍጨረጨረች። ወደትግራይ ግዛት ዘልቃ ገባች። ብዙም ሳትቆይ ግን በመቀሌ ጦርነት የሽንፈት ፅዋዋን ድል በለመዱት ኢትዮጵያውያን አርበኞች ተጎነጨች።
እንግዲህ ኢትዮጵያውያን አርበኞች በዶጋሊ፤ በኳቲት፤ በሰአቲትና በመቀሌ በመሳሰሉ ትላልቅ አውደ ውጊያዎች ወራሪውን የጣሊያን ጦር በዱር በገደሉ አርበድብደው ያሸነፉ ቢሆንም ብዙ ጊዜ የሚጠቀሰው ትልቁና ዋነኛው ጦርነት ግን በአድዋ የተካሄደው ነው። ጦርነቱ በኢትዮጵያ ንጉሰ ነገስት አፄ ሚኒሊክ የክተት ዘመቻ አዋጅ መላ ኢትዮጵያውያን ህዝቦችን ከዳር እስከዳር በማነቃቀነቅ በየካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም ወራሪው ጣልያን ድል ሆኗል። ድሉ መላው ኢትዮጵያውያን ከጫፍ እስከ ጫፍ ተነቃንቀው ዳር ድንበራቸውን ያስከበሩበት በመሆኑ ትልቅና አኩሪ ገድል ተደርጎ ይቆጠራል።
አድዋ ጥቁር አፍሪካውያን በተለይም ኢትዮጵያውያን በነጭ ወራሪ ላይ የተጎናፀፉት ድል በመሆኑ ድሉ የመላው ጥቁር አፍሪካውያን የነፃነት ተምሳሌትም ሆኖ ይቆጠራል። በወቅቱ ከስልጣኔ ማማ ላይ ደርሰናል ላሉ ነጮች ትልቅ ትምህርት የሰጠም ነው። በአፍሪካና በጥቁር ህዝቦች ብቻም ሳይመሰን ወደኤሽያ ተዛምቶ ጃፓናውያንም የያኔ ወራሪዎቻቸውን ሩሲያውያንን ተዋግተው ድል አድርገዋል። ይህ ሁሉ መነሳሳት በኢትዮጵያ የታየው አይደፈሬ ይባሉ የነበሩትን አውሮፓውያንን ወይንም ነጮችን ሌሎች ህዝቦች ሊያንበረክኳቸው እንደሚችሉ ያረጋገጠ ገድል ነው። የጥቁር አፍሪካውያን አሻራ የሆነው የአድዋ ድል ሲነሳ ታዲያ ንጉሰ ነገስት አፄ ሚኒሊክም አብረው ይነሳሉ።
አፄ ሚኒሊክ ዘመናዊነትን ለኢትዮጵያ ከማስተዋወቅ በዘለለ በአድዋ ጦርነትም ከጫፍ ጫፍ ህዝባቸውን በጋራ አሰባስበው፤ ራሳቸውም ዘምተው የሃገሪቷን ዳር ድንበር አስከብረዋል። ባለቤታቸው እቴጌ ጣይቱም በዚያን ጊዜ ሴትነታቸው ሳይበግራቸው ከጎናቸው በጦር ሜዳ ላይ በመሰለፍ በርካታ ጀብዱ ፈፅመዋል።
እኚህ ንጉሥ በጊዜው ሀገራቸውን ለመውረር የመጣውን የጣልያን ጦር ለመመከት ብቻቸውን ወደጦር ሜዳ አልሄዱም። የእርሳቸውን ዘር ብቻ ለይተውም ክተት አላስነገሩም። ከዚህ ይልቅ ከሰሜን እስከ ደቡብ ከምስራቅ አስከ ምእራብ ድረስ ያሉ መላ ኢትዮጵያውያንን በጋራ በማሰባሰብ በውጪ ወራሪ ላይ በጋራ እንዲዘምቱ አድርገዋል። በዚህም ያውም በነጮች ላይ አንፀባራቂ ድል ከህዝባቸው ጋር ተጎናፅፈዋል።
አሁን ባለው ወቅታዊ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሁኔታ ግን በተሳሳቱ የታሪክ ትርክቶች አንዳንድ የፌስቡክ አርበኞች ነን ባዮች አፄ ሚኒሊክን እንደጨቋኝ፣ ፈላጭ ቆራጭና አንድ ብሄር ላይ በማተኮር ሲያጠቁና ሲያሰቃዩ እንደነበሩ አድርጎ የመቁጠር አዝማሚያዎች ይታያሉ። በዚህም የአድዋ ድልን የአንድ ወገን እንጂ የብዙሃን ኢትዮጵያን ተሳትፎ ያልታየበት አድርጎ የመሳልና በአሉን የማደብዘዝ ሁኔታዎች ይስተዋላሉ።
ዞሮ ዞሮ የሚያግባበው ጉዳይ ግን በአድዋ ጦርነት የተሳተፈው መላው የኢትዮጵያ ህዝብ እስከሆነ ድረስ ድሉ የመላው ኢትዮጵያውያን ነው። ለዚህ አንፀባራቂ ድል መገኘት ደግሞ ንጉሰ ነገስት አፄ ሚኒሊክ ህዝቡን ከፊት ሆነው በመምራት ከፍተኛ አስተዋፅኦ በማበርከታቸው ሊከበሩ እንጂ ሊንቋሸሹ አይገባም። በእርሳቸው መሪነት መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ወራሪውን የጣልያን ጦር በአድዋ ጦርነት ድል በማድረጉም ከቅኝ ተገዥነት አምልጠናል። ነፃነታቸውንና ክብራቸውንም ማስጠበቅ ችለዋል።
ንጉሱ የሚተቹበት ምንም አይነት ምክንያት የለም ብሎ መደምደም ባይቻልም የፈፀሙትን አኩሪ ገድል ግን መካድ አይገባም። የዚያኑ ያህል ደግሞ በታሪክ አዋቂነትና በአመክንዮ ንጉሱ በአጥፊነት የሚያስፍርጃቸው ምክንያት እስካለ ድረስ መተቸቱ አይከፋም። በርግጥ አንድ መሪ መጥፎም ሆነ ደግ ሊሰራ ይችላል። ይሁን እንጂ፤ በዚህ ዘመን ለመስማት የሚዘገንኑ አስቃቂ ድርጊቶች ከሚኒሊክ በኋላ ባሉ የሀገሪቷ መሪዎች ተፈፅመዋልና ሚኒሊክ ከጥፋታቸው ይልቅ ያደረጓቸው አኩሪ ተግባራት ስለሚበልጡ በጥቃቅን ነገሮች ልንኮንናቸው አንችልም። አይገባምም።
ነፃነታችንንና ዳር ድንበራችንን ያስከበሩልንንና ጥሩ የሰሩልንን ሁሉ ልናመሰግን እንጂ ልናቋሽሽ አይገባም። የሀገር መሪ አብዛኛው ምግባሩ ጥሩ ከሆነና ለዜጎች ቀና አሳቢ እስከሆነ ድረስ ሊወደድ እንጂ ሊጠላ አይገባም። በተለይ በጋራ ለሚያግባቡ ሃገራዊ ጉዳዮች ላይ አበርክቶ ከፍተኛ ከሆነ ከዚህ በላይ ምን መሪ አለና!
አዲስ ዘመን የካቲት 23/2012
አስናቀ ፀጋዬ