እርሱ የጥበብ አድባር ነው። ታላላቆቹም
ሆኑ የሙያ ተማሪዎቹ በአንድ ቃል ይመሰክሩለታል። ባለ ተሰጦ፣ ባለ እውቀት፣ ሃያሲ፣ ፍቅር ወዳድ፣ ፀብ የሚርቅ ሲሉ። ጥበብን ከዚያ
ከፍ ሲልም ኢትዮጵያን የማወደስ ስሜቱን፣ እስትንፋሱን ወደ መጪው ትውልድ ማጋባት እንደሆነ በሙሉ ልባቸው ይናገራሉ። ባለ ተሰጦውን
ለማክበር በተዘጋጀ መድረክ ላይ አጋፋሪው፣ በጥበብ ተሰጦውና መምህርነቱ በስፋት የሚታወቀው ዶክተር ሱራፌል ወንድሙ ‹‹ንጉሡን ሳይሆን
ይሄን የህዝብ ሎሌ እናክብረው›› በማለት የደራሲና ገጣሚ ጌትነት እንየውን ምሽት ትህትና በተሞላ መልኩ ነበር ያስጀመረው።
ባህላችን እየተጫነን ነው መሰል ኢትዮጵያን ያገለገሉና ከክብር ማማ ጫፍ ዝቅ እንዳትል የሚታትሩ ጀግኖችን በህይወት እያሉ ማመስገን አለመደብንም። ፊት ለፊታቸው ሆነን በቅጡ አክብሮታችንን መግለፅ የቋጥኝ ያህል ይከብደናል። ሆኖም ጥቂት ዕድለኞች ይህ ንፉግነታችን አልደረሰባቸውም። ለዛሬ በኪነ ጥበብ ገፅ ላይ የምንዳስሰው የጥበብ ሰው ጌትነት እንየውም ይህ ዕጣ የደረሰው ይመስላል። ነብስ ድረስ ዘልቀው የሚገቡ አስተማሪና ስሜት ኮርኳሪ ሥራዎቹን አቀብሎን በምላሹ ደግሞ ‹‹አንተ የህዝብ ሎሌ እናመሰግናለን›› የሚል ካባን ከሙያው አክባሪና አድናቂ ወዳጅ ቤተሰቦቹ ያለስስት ተቸሮታል። ኢትዮጵያዊ የጥበብ ቤተሰቦች ይህን ሰው ለምን ሲባል አመሰገኑት?
የጌትነት መንገድ
ለ35 ዓመታት በብሄራዊ ቴያትር በድርሰት፣ አዘጋጅነት፣ ገጣሚና የመድረክ ተዋናይነት የገዘፈ አሻራውን ማኖር ችሏል። ይህ ታላቅ የጥበብ ሰው ከሦስት አስርት ዓመታት በላይ ሙያው ላይ ሲቆይ ከአንጋፋዎቹ ተምሮ፣ እኩዮቹ ጋር መክሮ፣ ታናናሾቹን ደግሞ በጥበብ ፍቅር አንፆ ህያው ታሪክ በጉልህ ስፍራ መከተብ ችሏል። አሁንም በንስር እይታዎቹ በበሳል ብእሩ እየነቀሰ አደባባይ የሚያወጣቸው ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ታሪካዊ የስነ ጥበብ ሥራዎቹ ተወዳጅና ሁሌም ተፈላጊ ናቸው። እስቲ ለዓመታት የረገጠውን ዳና እየተከተልን አሻራውን እንፈልግ!
ሃያሲው ደራሲው ዳይሬክተሩና የብዙ የጥበብ ሙያ ባለክነቱ ጌትነት እንየው በአንክሮ ለቃኘው በዝምታ ውስጥ ጉልህ ሆነው የሚታዩ የጥበብ ሥራዎችን ለልቦናችን ቸሮናል። ለዚህ ደግሞ ህያው ምስክር በመሆን አንጋፋው አርቲስት ደበበ እሸቱ ስለ ሥራዎች እንዲህ ይናገራሉ።
እርሳቸው ስለ ጌትነት ሲያነሱ ጊዜውን በውል ባያስታውሱትም ዘለግ ካለ ዓመት በፊት በተፈጠረ አንድ አጋጣሚ መተዋወቃቸውን አይረሱትም። በጊዜው አርቲስት አበበ ባልቻ፣ አለምፀሐይ ወዳጆ፣ ፍቃዱ ተክለማሪያም በአንድ ላይ ሆነው የአፍሪካ ሙያተኞች ማህበር የመጀመሪያውን የኤች አይ ቪ ቀን ሲያከብር በኢትዮጵያ፣ ኬኒያ፣ ዩጋንዳና ታንዛኒያ በተካሄደ የተውኔት ፅሑፍ ውድድር ላይ እንደተሳተፉ ይናገራሉ። በዚህ ውድድር ላይ በቀዳሚነት ጌትነት እንየው አሸናፊ እንደነበር ይገልጻሉ። ይህ ሥራ ተተርጉሞ በአፍሪካና አውሮፓ በመዞር ለእይታ እንዳበቁትም አይዘነጉትም። የሁለቱ ጥበበኞች ትውውቅ እዚያ መድረክ ላይ እንደተጀመረም ያስታውሳሉ።
‹‹የድርሰት፣ የግጥም፣ የልቦለድ፣ የተውኔትና የሚፃፉ ጥበብ ነክ ጉዳዮች ሁሉ አባት ነው። በኪሱ ይዟቸው ይዞራል›› በሚል ድንቅ አገላለፅ በማስቀመጥ ሙሉ ሰው መሆኑን ይመሰክራሉ። በተለይ የግጥምና ተውኔት ሥራዎቹን በመድረክ ላይ የሚያቀርብበት መንገድ የታዳሚውን ዓይንና ጆሮ የመማረክ አቅሙ በእጅጉ ከፍተኛ እንደሆነ ይገልፃሉ።
በብሄራዊ ቴያትር ለዓመታት በሙያ አጋርነት የምታውቀው አርቲስት አልጋነሽ ታሪኩ ጌትነትን ለመጀመሪያ ጊዜ የተዋወቀችው በበላይ ዘለቀ ቴያትሩና የተውኔት ብቃቱ እንደነበር ትናገራለች። ሁሌም እርሱን ስትጠራው በመድረክ ስሙ ‹‹በላይዬ›› እያለች በቁልምጫ ነው። ይህ ደግሞ በቀላሉ ለእርሱ ያላትን አክብሮት የምትገልጽበት ነው። እርሱ የደረሰውን ይህን ታሪክ ቀመስ ቴያትር አርበኛ በመሆን ተሳትፋለች። የሙያ ብቃቱንና የሥራ ትጋቱን ያለስት ነው የምታደንቀው። በቀላሉ እርሱ የአገርም የቲያትር ቤቱም ፈርጥ እንደሆነ የምትናገረው በልበ ሙሉነት ነው።
አሁን ላይ እውቅ አርቲስት የወጣቸው ሴትም ሆነ ወንድ አንጋፋ የመድረክ ፈርጦች ይህን ታላቅ የጥበብ ሰው በተለየ ሁኔታ ‹‹መምህራችን ነው›› ሲሉ ይደመጣሉ። እርሱን ለማመስገን በተዘጋጀው ልዩ መድረክ ላይ በቀጥታ በመገኘት ጭምር አክብሮታቸውን ሲቸሩት ለተመለከተ የሰሉ ብእሮቹና የቴያትር ዝግጅት ብቃቱ ፊቱ ድቅን ሳይልበትም አይቀርም። በህንደኬ፣ በሀምሌት፣ በውበትን ፍለጋ፣ በየሌሊት እርግቦች፣ በበላይ ዘለቀ ፣ ቴዎድሮስ እና መሰል የቴያትር ሥራዎቹ እየሠራ ያልተማረ እየተመለከተ ያላደነቀ ተዋናይም እንዳልነበረም ይገነዘባል።
ከላይ ያነሳነውን ሃሳብ በሰላ አመክንዮ የሚያቀርበው ደግሞ ሌላኛው የሙያ አጋሩ ሽመልስ አበራ ጆሮ ነው። እርሱም ጌትነትን እንዲህ ያስቀምጠዋል ‹‹በቀላሉ ፈላስፋና ባለቅኔ ነው›› ይላል። የህይወት መረዳቱና መስመሩ የተለየ መሆኑን ሲገልፅ። በትምህርት ብቻ የተገኘ ሙያ ሳይሆን በተፈጥሮ የታደለ ጥበበኛ መሆኑን ሲመሰክር። በተለይ በቴያትር ዝግጅቱና ድርሰቱ ላይ ገፀ ባህሪያቱን የሚቀርፅበትንና የሚገልፅበት መንገድ ድንቅ እንደሆነ ይናገራል። ለእርሱ በተለይ የአፄ ቴዎድሮስ ራእይን በመድረክ አዘጋጅቶ ሲያቀርበው ጀግንነቱን ብቻ ሳይሆን ሌላኛው ሰዋዊ ጎኑን ያሳየበት መንገድ አሁንም ድረስ እንደሚያስደንቀው ይናገራል። በዚህ ሥራው ላይ ቆፍጣናውንና ጀግናውን ቴዎድሮስ ሲያፈቅርም ሆነ ጓደኛ ሲሆን ምን እንደሚመስል ጉልበት ባለው ጥበባዊ ስነ ፅሑፍና የማዘጋጀት አቅም በምስል ከሳች አሁናዊ ትእይንት ቁልጭ አድርጎ ማስቀመጥ መቻሉም እንዳስገረመው ሳይናገር አላለፈም።
ውበትን ፍለጋ
ይህ ታላቅ ፀሐፊ ተውኔት በስካይ ላይት ሆቴል በታላቅ ዝግጅት በሙያ አጋሮቹና በወዳጆቹ ሲከበር ሌላ አንድ ተጨማሪ ብስራት ነበር። በቀኑ የእርሱን ክብር ከፍ አድርጎ የሚያሳይና በተውኔት ህትመት ፈር ቀዳጅ መሆን የሚችል አጋጣሚም ተፈጥሮ ነበር። እርሱም ከ20 ዓመታት በብሄራዊ ቴያትር በፊት ለእይታ ቀርቦ እጅግ ከፍተኛ ተቀባይነት ያገኘው የ‹‹ውበትን ፍለጋ›› ቴያትር ተውኔት ለመጀመሪያ ጊዜ በመድረኩ ላይ በመፅሐፍ መልክ ተፅፎ ለአንባቢያን እንዲደርስ ተመርቆ ነበር።
ይህ እውነት ታላቁ የጥበብ ሰው በሠራቸው ሥራዎች ከመከበሩ ሌላ ያልተለመደውን የተውኔት ህትመት እንደሚያነቃቃ ተተንብዮለታል። በጌትነት ተደርሶ የተዘጋጀው ይህ ቴያትር መፅሐፍ ሆኖ ከመሰራጨቱ በፊት ወደ ፊልም የመቀየር አጋጣሚውም ነበረው። ገና እያደገ ያለው የፊልም ዘርፉ ላይም እሴት የጨመረና ተወዳጅነትን ያተረፈ እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው።
መፅሐፉ ይፋ በሆነበት መድረክ ላይ ለጋዜጠኞች ሃሳቡን የሰጠው ደራሲና አዘጋጁ ጌትነት እንየው ‹‹በኢትዮጵያ የቴአትር ታሪክ ውስጥ በተለይ በብሔራዊ ቴአትር ቤት አንድ የራሱን አሻራ አሳርፏል የሚል ዕምነት አለን›› በማለት የነበረውን ተወዳጅነት ለማንሳት ሞክሯል። ባልተለመደ መልኩ ተውኔቱ ለህትመት እንዲበቃ በማድረግ አዲስ መንገድ መክፈት መፈለጋቸውንም አልሸሸገም። ውበትን ፍለጋ ከ20 ዓመት በፊት በ1992 ዓ.ም ብሔራዊ ቴአትር ለመድረክ የበቃ ቴአትር ነበር፤ በወቅቱ እጅግ በርካታ ተመልካቾችን የሳበ በጣም በብዙ ወረፋ ይታይ ነበር፡፡ ለአራት ዓመታት በመድረክ ሲታይ ብዙ አድናቆትን ማትረፉን ተመልካቹ፣ የቴያትር ባለሙያዎችና የሙያ አጋሮቹ በትውስታ መለስ ብለው ይናገራሉ፡፡
‹‹ውበትን ፍለጋ ለምን በመፅሐፍ መልክ ሊታተም ቻለ›› የሚለውን ጥያቄ ዘርዘር ባለ መልኩ የሚያነሳው ጌትነት በዋነኝነት በሰዓቱ የነበሩ ጓደኞቹ እስከአሁን ድረስ ለምን ታትሞ አይቀመጥም፤ ለምንስ ለአንባቢ አይቀርብም የሚሉ ግፊቶች በተደጋጋሚ ይቀርቡ ስለነበር ሊታተም መቻሉንም ያነሳል። ዋናውና ቀዳሚው የመታተሙ ምክንያት ግን የነበረው ተወዳጅ መታሰቢያ እንዲሆን ታስቦ፤ በሌላ መልኩ ደግሞ ተውኔቶች ከነ ጋሽ ፀጋዬ ጀምሮ በነአቶ መንግስቱ፣ አቤ ጎበኛና ሌሎችም አንጋፋ ጸሐፍት ይታዩ የነበሩ ቴአትሮች እየታተሙ መምጣታቸውን በማስመልከት ተጨማሪ ተምሳሌት መሆን መቻል እንደሆነ ይናገራል፡፡
‹‹ተውኔትን ደግሞ ከመድረክ ውጪ እንዲቀጥል የሚያደርገው መታተሙ ነው›› የሚለው ደራሲው ጌትነት እንየው፤ ይህ ካልተደረገ ግን ከመድረክ ሲወርድ ጠፍቶ የሚቀር እንደሆነ ይገልፃል፡፡ ከታተመ ግን ምንጊዜም በታሪክ የሚወሳ፤ አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘም በድጋሚ ፕሮዲውስ ማድረግ እንደሚቻል ይናገራል።
ጌትነት እና የሙያ አጋሮቹ ይህን መፅሐፍ አትሞ ማሰራጨት በርካታ ጥቅሞች እንዳሉት ነው የሚገልጹት። ከእነዚህ ውስጥ ደግሞ በቀጣይ እራሱ ደራሲው የሚያነሳው ሃሳብ እንደ ጠንካራ አመክንዮ መውሰድ ይቻላል።
‹‹በአገራችን በርካታ ዩኒቨርሲቲዎች እየተከፈቱ ነው፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ከስምንት በላይ የሚሆኑት የቴአትር ጥበባት ትምህርት ክፍል ከፍተዋል›› የሚለው ጌትነት እንየው፤ አስተማሪዎች ተማሪዎቻቸውን ሲያስተምሩ ስለትወና፣ ቴአትር ዝግጅትና ተውኔት አፃፃፍ እንደሚያካትቱ ይናገራል። የተውኔት አፃፃፍ አንዱ ፈታኙ ነገር ቴክኒኩን ማወቅ እንደሆነም ይገልፃል፡፡ ለዚህ እንደ አንድ ተጨማሪ ማጣቀሻ ግብአት እምነት እንዳለው በመጠቆምም ውበትን ፍለጋ በመፅሐፍ መልክ መታተሙ አንድ ዕድል እንደሚፈጥር ይገልፃል፡፡ እንደ እርሱ ምልከታ ከዛሬ ሃያ ዓመት በፊት የነበሩ ተዋናዮች ውብ አድርገው ስለሠሩት እጅግ ብዙ ተመልካች ይጎርፍ ነበር። ከሃያ ዓመት በኋላ ደግሞ የመጡ ተዋናዮች በትውልዳቸው በድጋሚ ይህንኑ ተውኔት ቢጫወቱት ከሰውም ከታሪክ ዶሴም አይጠፋም ይላል፡፡ ተውኔቱን በደረሰው ጌትነት ዕድሜ የነበሩ ትልልቅ ተውኔቶች ደግሞ ለመሥራት ሲፈለጉ እንደማይገኙ ያስታውሳል። ይህን ዓይነት ስህተት ላለመድገም ውበትን ፍለጋ በዚህ መልኩ ለአንባቢም ሆነ ለባለሙያው መታተሙ ችግሩን ይቀንሳል የሚል እምነት አሳድሮበታል፡፡
ውበትን ፍለጋ ተውኔት ጌትነትና መሰሎቹ የነበሩበትን ትውልድ አስተሳሰብ፣ የማህበረሰብ ግንኙነትና የወቅቱን ባህል ይጠቁማል፡፡ ዛሬ ላይ ይህን መሰል ተውኔት ለቴያትርና ጥበብ አፍቃሪው በሚመች መልኩ መቅረቡ ያለ ጥርጥር ትውልድ ከማቀራረብ ባለፈ ፈተና ውስጥ እየወደቀ የሚገኘውን ዘርፍ ለመታደግ ትልቅ የምስጢር ቁልፍ መክፈቻ እንደሆነ የዝግጅት ክፍላችን ያምናል። ይህን መሰል ዕድል ማግኘት እንዲቻል ደግሞ ጀግኖቻችንን ማክበርና ማድመጥ ያስፈልጋል።
ውበትን፣ ጥበብን፣ እውቀትን ፈላጊው ፀሐፊ ተውኔቱ፣ ደራሲው፣ አዘጋጁ የህዝብ ሎሌ ጌትነት እንየው ምንም እንኳን በየዘመናቱ በሚቀያየረው የመንግሥት ፍላጎት ጫና ውስጥ እየወደቀ ፈተናዎቹን በትዕግስት ቢያልፍም፤ ሳይረፍድ ግን የሚገባውን ክብር አግኝቷል። መሰል ብልህ ውሳኔዎችን በሌሎቹም ታላላቅ ጀግኖቻችን ላይ መቀጠል ይኖርበታል። ይህን ማድረግ ከቻልን ያነሱንን ጀግኖች አብዝተን በድምሩ ታላቅ አገር ለመሥራት ያን ያክል ከባድ የቤት ሥራ አይጠብቀንም። ሰላም!
አዲስ ዘመን የካቲት 22/2012
ዳግም ከበደ