ምስረታውን በ1985ዓም ያደረገው ኢትዮ ዩናይትድ ኢንተርናሽናል ቴኳንዶ በዓለም አቀፍ ደረጃ ባለው መከፋፈል መሰረት በኢትዮጵያም በሶስት አሶሴሽኖች ሲንቀሳቀስ ቆይቷል። በኢትዮጵያ በተለይ በወጣቱ ዘንድ እጅግ ከተስፋፉ ስፖርቶች መካከል አንዱ የሆነው ይህ የማርሻል አርት ስፖርት በፌዴሬሽን ደረጃ ለመደራጀትም ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል። በኢፌዴሪ ስፖርት ኮሚሽን 2003ዓ.ም በወጣው የስፖርት ማህበራት ማቋቋሚያ መመሪያ መሰረትም የድሬዳዋ ኢትዮ ዩናይትድ ኢንተር ናሽናል ቴኳንዶ ፌዴሬሽን ሊመሰረት ችሏል።
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ስፖርት ኮሚሽን ስር የነበሩት ሶስት አሶሴሽኖችም በመጣመር ፌዴሬሽን ያቋቋመ ሁለተኛው ከተማ አስተዳደር ሆኗል። በፌዴሬሽኑ ማቋቋሚያ ጉባኤ ላይም የስፖርት ኮሚሽኑ ተወካይ አቶ መኮንን ገብረህይወት የፌዴሬሽኑን ምስረታ አብስረዋል። ተወካዩ በመድረኩ ላይ ባደረጉት ንግግር፤ የአሰራር ሂደቱንና ደንቡን በተከተለ መልኩ የፌዴሬሽን ምስረታ መካሄዱን አረጋግጠዋል። ፌዴሬሽኑ በስድስት ክፍለ ከተሞች ውስጥ ብቃታቸው የተረጋገጠ 16 ክለቦችን ያቀፈ፣ በ ‹‹ኤ ላይሰንስ›› ሁለት፣ በ ‹‹ቢ ላይሰንስ›› ስድስት፣ በ ‹‹ሲ ላይሰንስ›› አስር ዳኞች እንዲሁም ከ2-7ኛ ዳን ያላቸው 16 አሰልጣኞች ያሉት በመሆኑ የማቋቋሚያ ጉባኤ ማድረግ የሚያስችላቸው መሆኑን ጠቁመዋል። በዚሁም መሰረት ስራ አስፈጻሚዎችን በመምረጥ ወደ ስራ እንዲገቡ፤ በሂደትም ጽህፈት ቤትና የስፖርት ማዘውተሪያ ገንብተው ከመንግስት ድጎማ እስኪላቀቁ በኮሚሽኑ ቢሮ እንዲሁም በትምህርትና ስልጠና ማዕከላት እንዲገለገሉ ፈቃድ ተሰጥቷል።
በመጀመሪያው ጉባኤ ላይም አዲስ ፌዴሬሽን እንደመሆኑ ሪፖርት ማቅረብ ባይቻልም ቀጣይ እቅዶች ግን ለጉባየተኛው ቀርበዋል። በዚህም የክለቦችን ቁጥር አሁን ካለበት ቁጥር ወደ 33 ማሳደግ፣ ጠንካራ ፌዴሬሽን እንዲሆን መስራት፣ ገቢውን በማሳደግ ከኮሚሽኑ ድጋፍ የሚላቀቅበትን መሰረት መጣል፣ የስፖርት ማሰልጠኛ ማዕከላትን ማሳደግ፣ ስፖርተኞችን በሀገር አቀፍና ዓለም አቀፍ ውድድሮች ማሳተፍ፣ የተለያዩ ቻምፒዮናዎችን በማዘጋጀት ከተማ አስተዳደሩን እንዲሁም ሀገርን ለመወከል የሚችሉ ስፖርተኞችን ማፍራት፣ በትምህርትና ስልጠና የዳኞችንና አሰልጣኞችን ቁጥር ወደ 100 ማሳደግ እንዲሁም በክትትልና ድጋፍ ላይ ለመስራት መታቀዱ ተገልጿል። ገለጻውን ያዳመጠው ጉባኤም በሙሉ ድምጽ አጽድቋል። በመተዳደሪያ ደንቡ ላይም ማሻሻያ ከተደረገ በኋላ በጉባኤው አባላት ይሁንታ ሊያገኝ ችሏል።
ከተሳታፊዎች በተሰጠው አስተያየትም ስፖርቱ እስከ ወረዳ በመውረድ በይበልጥ እንዲስፋፋ ፌዴሬሽኑ ከክፍለ ከተሞች ጋር በቅንጅት መስራት እንዳለበት እና ከመንግስት ድጎማ ለመላቀቅ የሚያስችለውን መንገድ ማፈላለግ እንዲሁም የሀብት አሰባሰብ ላይ ማተኮር እንደሚገባው ተጠቁሟል።
በተካሄደው የስራ አስፈጻሚዎች ምርጫም አቶ በቀለ በዳዳ በ14 ድምጽ በማሸነፋቸው ከቀድሞው የአሶሴሽኑ ፕሬዚዳንት ኢንተርናሽናል ኢንስትራክተር ሲኒየር ሳቦም ተሾመ አበበ የስራ ደንብና መመሪያ ተረክበዋል። አቶ መንሱር ጀማል ምክትል ፕሬዚደንት ሲሆኑ፤ ወይዘሮ ሰብለወንጌል ቁምላቸው አቃቤ ነዋይ እንዲሁም ሌሎች አራት ግለሰቦች የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት በመሆን ተመርጠዋል። ተመራጮችም በጋራ በመሆን ስፖርቱን ለማሳደግ የሚሰሩ መሆኑን ቃል ገብተዋል።
ከማርሻል አርት ስፖርቶች መካከል አንዱ የሆነው ኢንተርናሽናል ቴኳንዶ እአአ 1966 በጄኔራል ቾይ ሆንግ ሃይ ነው የተመሰረተው። የሁለቱን ኮሪያዎች መነጣጠል ተከትሎም ኢንተርናሽናልና ወርልድ ቴኳንዶ በሚል ሲከፈል፤ ኢንተርናሽናል ቴኳንዶ በሰሜን ኮሪያ በስፋት ይከወናል። በሲኒየር ማስተር አብዲ ከድር መስራችነትም በኢትዮጵያ አሶሴሽኑ እስካሁን ሲንቀሳቀስ ቆይቷል። በዚህ ወቅት የዓለም አቀፉ ኢንተርናሽናል ቴኳንዶ ፌዴሬሽን መቀመጫ በኦስትሪያ ቬና ሲሆን፤ ኢትዮጵያም አባል አገር ናት።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ የካቲት 21/2012
ብርሃን ፈይሳ