ግለሰቦችና ቡድኖች ብቻ ሳይሆኑ ቃላትም በፖለቲካ ንክር ተፈርጀው ታርጋ እንደሚለጠፍባቸው የታወቀ ነው። ለምሳሌ፤ ከሰሞንኞቹ ዝነኛ ቃላት መካከል “ብልፅግና” የሚለውን ቃል ያህል ኒሻንና ሜዳሊያ የተጎናጸፈ ቃል ስለመኖሩ እርግጠኛ አይደለሁም። አየሩ፣ ሣር ቅጠሉ፣ ምግብ መጠጣችን፣ እንዲያው በጥቅሉ የሰማይ ምድሩ ዲ.ኤን.ኤ ቢመረመር የ“የብልፅግናን” ዘረ መል ያጣል ማለት ዘበት ነው። “ብልፅግና” የሚለው ቃል በፖለቲካ ቅባት ወዝቶ ሥርዎ ቃሉ መልኩን ቀይሯል።
ይኸው “ብልፅግና” የሚለው ቃል የሥልጣንና የኃይል መገማመቻና መራኮቻ መድረክ በመሆንም ብዙዎችን እያፋለመ ያለ አጀንዳ ሆኗል። “ብልፅግና” ለሕዝብና ለሀገር ትንሣኤ የሚያስገኝ መሲህ እንደሆነም እየታመነበት የእምነት ያህል ወደ ኃይማኖት ዳርቻ እየተንፏቀቀ በመጓዝ ላይ ነው። በግሌ እንደምጠረጥረውና ከአሁን በፊት በሀገራዊ ተሞክሮ ተፈትሾ እንደተረጋገጠው በቅርብ ጊዜያት ውስጥ “ብልፅግና ካፌ፣ ብልፅግና ት/ ቤት፣ ብልፅግና ኤሌክትሮኒክስ፣ ብልፅግና የውበት ፋሽን ወዘተ.” የሚሉ የንግድ ቤት ማስታወቂያዎች ሀገሪቱን ሳያጥለቀልቁ እንደማይቀሩ ገማቾች በሹክሹክታ ሲያሙ ሰምቻለሁ። በአንጻሩም “አብዮታዊ ዴሞክራሲ” የሚለው ቀን የመሸበት ሀረግም የሾህ አክሊል ደፍቶ “ኤሎሄ! ኤሎሄ! ላማ ሰበቅታኒ!” እያለ መቃተቱን ልብ ይሏል።
ታሪክ እንጂ ትዝታ አያረጅም
“ብልፅግና የእኛ!” እየተባባሉ አደባባይ የሚዋልባቸውን ሰሞንኛ ሰላማዊ ሰልፎች፣ ቅስቀሳዎችና ዲስኩሮች ልብ ብዬ ሳስተውል የዛሬ 35 ዓመታት ግድም የተፈጸሙ መሰል እንቅሰቅስቃሴዎችን ያስታውሱኛል። ከ1970 ዓ.ም አጋማሽ ጀምሮ የነበሩት ወራት ለአሥረኛው ዓመት የአብዮት ክብረ በዓል፣ ለኢሠፓ (የኢትዮጵያ ሠራተኞች ፓርቲ) እና ለኢሕዲሪ (የኢትዮጵያ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ሪፑብለክ) ምሥረታ ይደረጉ የነበሩ ሽር ጉዶች እድሜውን ያደላቸው ዜጎች የሚያስታውሱት ታሪክ ነው። የደርግ “አዲሱ ፓርቲ (?)” እና “የዴሞክራሲያዊ መንግሥቱ (?)” ምሥረታ ተፍ ተፍ ሀገሪቱን በአንድ እግሯ አቁሟት ነበር። መንግሥታዊ ፕሮፓጋንዳው፣ የቀበሌ፣ የወረዳና የከፍተኛ ጽ/ቤቶች ከበሮ ድለቃ ዛሬም ድረስ በብዙዎቻችን ጆሮ የሚያቃጭል ይመስለኛል። የወቅቱ የፖለቲካ “ብፁዓን” እና ደመወዛቸው ከ500 ብር በላይ የሆኑ “ምርጥ ዜጎች” ይለብሷቸው የነበሩት ሦስት ቀለማት ያላቸውን ካኪዎች ለማሰፋት የነበረው ተጋድሎ የሀገሪቱን ልብስ ሰፊዎች “ቱጃር አድርጓቸው” ነበር።
ከሰሜን ኮርያ በመጡ ባለሙያዎች ይሰጡ የነበሩ የትርዒት ሥልጠናዎችና ከተሞችን በባለቀለም አምፖሎች ለማንቆጥቆጥ የተከናወኑ ተግባራት በፍፁም የሚረሱ አልነበሩም። በተለየ ሁኔታ “መንግሥትን ለሚመራው ፓርቲ” መመሥረት የነበረው ሸብ እረብና መጠን የለሽ መገባበዝ በምጥን ቃላት ሊገለጽ የሚችል አይደለም።
በአንጻሩ በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል “ገንጣይና አስገንጣይ” ይባሉ ከነበሩት በረኸኞች ጋር ይደረግ የነበረው የጦርነት መተጋተግና አሰቃቂ የርሃብ ክስተት በጥቂት አናቅጽ ብቻ ተዘርዝሮ የሚጠናቀቅ አይደለም። ያረጀና ያፈጀ ታሪክ እና ለትካዜ የሚዳርገውን ትዝታ እዚህ ላይ አቁሜ ወደ “ብልፅግና” ነገረ ጉዳዬ ልመለስ። የወቅቱ “የብልፅግና” ገናናነት ለምን የትናንቱን ያረጀ የሀገራችንን ታሪክ እንዳስታወሰኝ ጥቂት ተስፋዎችንና ስጋቶችን ልጠቃቅስ።
የዘመነ ብልፅግና ተስፋ፤
“ብልፅግና” የሚለው ቃል ከጠቅላይ ሚኒስትሩ የመደመር ፍልስፍና ስያሜ ጋር ተጣምሮ መገለጹ በራሱ ተስፋን የማለምለም ብርታቱ ከፍ ያለ ነው። አንደ ጉም ከሚተንኑትና ከማይጨበጡት የፖለቲካ ቃላትና ሬቶሪኮች በተሻለና በበለጠ መልኩ ከብልፅግና ጋር እየታከኩ የሚነገሩት ቃላትና ሃሳቦች በዜጎች የሕይወት ለውጥና በሀገሪቱ ልማት ላይ ትኩረት ማድረጋቸውን እኔ በግሌ ወድጃቸዋለሁ፤ አክብሬያቸዋለሁም። የቃላቱና የፍልስፍናውን ቀያሽና አስፈጻሚ ጠቅላይ ሚኒስትሩንም እንደ ብዙው ዜጋ ሁሉ ልቤ ከልብ ወዷቸዋል። የብልፅግናው ትሩፋት እስኪገመጥና እስኪዳሰስ ድረስ ትዕግሥት ስለሚጠይቅ “ሱሬ ባንገት ካልወጣ” በሚል ትንቅንቅ መፋተጉ የሚበጅ አይመስለኝም። “ልጅ ከሆነ ይገፋል፤ እህል ከሆነ ይጠፋል!” እንዲሉ። እንደዚያም ቢሆን ግን የፖለቲካ ቅባት ብቻ ሳይሆን “የፖለቲካ መርዝ” ጭምር እየለወሱ ከበከሉት ከ“አብዮታዊ ዴሞክራሲ” ጠረን ፖለቲካው መቶ እጥፍ ነፃ ስለወጣ ለዜጎች ትልቅ እፎይታ ነው።
“አብዮታዊ ዴሞክራሲ፣ አብዮታዊ መስመር፣ አብዮታዊ ትግል፣ አብዮታዊ ርዕዮት ወዘተ.” እየተባለ ሲቀለድበት የኖረው “ዴሞክራሲ” ለግሪኮቹ አማልክት ስለት ሳያገባ የቀረ አይመስለኝም። እርሱም ነፃ በመውጣቱ እኛ ዜጎችም ከማደናገሪያ ፍልስፍና በመላቀቃችን “እንኳን ደስ አላችሁ!” ብንባባል የሙጥኝ ብለው የተቆራኙትን የሚያስከፋ አይመስለኝም።
እዚያ ማዶ በድንክ አልጋ ላይ ኩርምት ብለው በተኙ አሮጌ ፖለቲከኞች የጦርነት ጭስ እየጨሰ በስመ አብዮታዊ ዴሞክራሲ አጋፋሪው ድግስ ይደግሳል።” ቡሄ ጨፋሪ ሕጻናት “ያንን ድግስ ውጬ፣ ውጬ” እንዲሉ፤ አንዳንዶች የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ሌጋሲ ሕያው ሆኖ እንዲቀጥል ስለሚፈልጉ ዋርድያ ሆነው አናስነካም ብለው ይሟገታሉ። ደጉና የዋሁ፣ ርሁሩህና መልካሙ ሕዝብ ግን ዛሬም ድረስ ግራ ተጋብቶ የአምላኩን ጣልቃ ገብነት እየተማፀነ ይገኛል።
የዘመነ ብልፅግናን ተስፋና ሀሌታዊ እርምጃ ጸሐፊው የሚያደንቀው በንፁህ ህሊናና ከወገንተኝነት ፍረጃ ራሱን አፅድቶ ነው። ታላላቅ የልማት ፅንሶችን ያረገዘው የብልፅግና ፍልስፍና እየተዋወቀ ያለው በሰላማዊ ሰልፎችና በስብሰባ ብዛት ብቻ እንዳይደለ ለመመስከር በቅርቡ ያስተዋልኩትን አንድ አብነት ብቻ ልጥቀስ።
ከአራት ቀናት በፊት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ (ዶ/ር) ቁጥሩ በርከት ያለን አንድ ስብስብ ለጉብኝት ጋብዘው ነበር። የጉብኝቱ መርሃ ግብር የተጀመረው ከታላቁ የኢዮቤልዩ ቤተመንግሥት ሲሆን፣ በሸራተን አካባቢ እየተገነባ ባለው ተዓምራዊ የሸገር ፕሮጀክት ቆይታ ተደርጎ ሥራው እየተፋጠነ ባለው የእንጦጦ መናፈሻ ቅኝት ከተደረገ በኋላ መርሃ ግብሩ የተጠናቀቀው የአንድነት ፓርክን በመጎብኘት ነበር።
ብዙዎቻችን የተገረምንበት አንዱ ክስተት የኢዮቤልዩን ቤተመንግሥትና የሸራተን አካባቢን ልማት ያስጎበኙት እንደ አንድ የቱር ጋይድ ባለሙያ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ራሳቸው ነበሩ። ከጎብኝዎቹ ጋራ አቧራና ፀሐይ እየተፈራረቀባቸውና ተገቢውን ማብራሪያ እየሰጡ ጭምር።
ወደ ዝርዝር ጉብኝቱ ስንመለስ የኢትዮጵያ ሕዝብ እንኳን በዓይኑ ሊያያቸው ቀርቶ ታሪካቸውን ለመስማት እንኳ ዕድል የተነፈገባቸው የንጉሡ ልዩ ልዩ ተዓምረኛ ኦቶሞቢል መኪናዎችን ማየትና መዳሰስ እንደ ትልቅ ዕድል የሚቆጠር ነው። ልክ እንደ ዛሬዎቹ የሆሊውድ ፊልሞች ከግማሽ ክፍለ ዘመናት በፊት የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት በውሃ ላይ እንደ ጀልባ፣ በምድር ላይ እንደ ኦቶሞቢል አገልግሎት የሚሰጥ ተሽከርካሪ ነበራቸው ቢባል ማን ያምናል? አሽሙሩንና አቃቂሩን ለጊዜው ንቀን ለንጉሡ ስምና ለዙፋናቸው ክብር ተብሎ በተለየ ስሪት የተፈበረኩ በርካታ ተሽከርካሪዎችና ልዩ የባቡር ፉርጎዎችም ነበሩ ቢባልስ? እንደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ርዕይ ተሽከርካሪዎቹ በሙሉ በልዩና በደማቅ የትርዒት ዝግጅት በቅርቡ ለሕዝብ ይፋ ስለሚሆኑ የተደነቅሁባቸውን ሁኔታዎች ሁሉ በዝርዝር ከመተረክ በይደር ማስተላለፉን መርጫለሁ።
በዚያው በኢዮቤልዩ ቤተመንግሥት ውስጥ ለዘመናት ታሽገው ከእይታ የራቁት የወግና የክብር ዕቃዎችም ልዩ ትርጉም የሚሰጣቸው ናቸው። በወርቅና በብር የተንቆጠቆጡትን ቁሳቁሶችና ታሪካዊ ቅርሶች “ዓይኔ ነው ባሌ ነው?” ብላ እንደጠየቀችው ሴት በርግጥም ግርምት ማጫር ብቻ ሳይሆን ዓይንንም ያጥበረብራሉ። እነዚህ ሁሉ ቅርሶች በዓመታት ውስጥ አንደምን ከቀበኞችና ከመንታፊዎች ተሰውረው እንደኖሩ ምሥጢሩን የሚያውቀው አንድዬ ብቻ ነው። እነዚህን ሁሉ ሀገራዊ ሀብቶች የምሥጢር በሮቹን ከፋፍተው ላስጎበኙን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ክብርና ሞገስ ይሁን። የቤተመንግሥቱ ሙሉ ግቢ ወደ ሙዚዬምነት ተለውጦ በቅርቡ ለሕዝብ ይፋ ይሆናል የሚለው የምሥራች በራሱ ለዘመነ ብልፅግና በፈቃዳችን ክብር እንድንሰጥ እንገደዳለን።
የሸራተን አካባቢ ከፊል የመናፈሻና የመዝናኛ ፕሮጀክትና በእንጦጦ ተራራ ላይ ሥራው እየተፋጠነ ያለውን የመዝናኛ ማዕከል በዝርዝርና በስፋት ለመተረክ ከመሞከር ግሩም! ብቻ ብሎ ማለፉ ይቀላል። ከእንጦጦ አራት ኪሎ ድረስ የሚዘረጋው ከተሽከርካሪ ነፃ የሆነው መንገድና ለእግረኞች ብቻ የሚፈቀደው ጎዳና ሲጠናቀቅ ከአዲስ አበባ ጋር “ዓለምሽ ዛሬ ነው ዛሬ” እየተባለ መጨፈሩ አይቀርም።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ራሳቸው እንደ አንድ አስጎብኚ ግለሰብ ዝቅ ብለው የርዕዮቻቸውን ውጥንና የግንባታዎቹን አካሄድ እየተነተኑ ሲያስረዱ ማስተዋል በርግጥም የብልፅግና ዘመን ከደጃፍ መድረሱንና ሽታውም እያወደ እንዳለ ጥሩ ማሳያ ነው። እስከ ዛሬ እንደ እሳቸው ከከፍታው ዝቅ ብሎ ያገለገለ መሪ ኢትዮጵያ ስለማፍራቷም ታሪካችን የመሰከረልን ምንም ነገር የለም። የሀገሬ የብልፅግና ተስፋ በርግጥም እውን ለመሆን የተቃረበ ይመስላል። ሕዝቧ ለዘመናት የቃተተበት ጸሎትም በፈጣሪ ዘንድ ተደምጦ ምላሹ እየተቃረበ ይመስላል። የአንድነት ፓርክን አስደናቂ ይዘት በተመለከተ ብዙዎች ብዙ ስላሉ ደግሜ ከመከለስ ለሌላ ቀጠሮ ማሸጋገሩን መርጫለሁ። ጠቅላይ ሚኒስትር ሆይ ለእስከ ዛሬ ትጋትዎና ጥረትዎ መቼም ዴሞክራሲን ስለሚሰብኩ “ሺህ ዓመት ይንገሡ!” ብለን አንሸነግልዎትም። ዕድሜዎን ያርዝምልን፤ ጤና ይስጥልን ማለቱ ግን አግባብ ይሆናል።
ሽው የሚሉብኝ የዘመነ ብልፅግና ስጋቶች፤
የጠቅላይ ሚኒስትሩ ርዕዮችና የብልፅግና ፓርቲያቸው ፍልስፍና በማንና እንዴት በሙላት ሊተገበር ይችል ይሆን? በማለት ብዙ ዜጎች መጠየቃቸው አልቀረም። “በአሮጌ አቁማዳ፤ አዲስ የወይን ጠጅ” ማከማቸት ይሆንን? እያሉ በተደጋጋሚና ግራ በመጋባት የሚጠይቁም አልጠፉም። ምክንያታቸውን ሲገልጹም የብልፅግና ካባ ደርበው “ዛሬም አለን!” የሚሉ አንዳንድ ነባር ኢህአዴጋውያን እንደምን አብረው ሊጠመዱ ይችላሉ የሚል ስጋት ስለሚያንዣብብባቸው ቢጠይቁ አይፈረድባቸውም።
ከአሁን ቀደም ሕዝብን በቅንነትና በመሰጠት ከማገልገል ይልቅ “ካቦነታቸውን” ማስመስከር የሚቀናቸው ሹማምንት እንደምን በሥራና በውጤት ከሚፈትነው ፍልስፍና ጋር አብረው እንደሚጓዙ ሲያስቡት በእጅጉ ሊያሳስብ ይገባል።
ሁለተኛው ስጋት “የዘሬን ብተው ያንዘርዝረኝ!” እንዳለችው ሴት የኢህአዴግ አልጋ ወራሽ የሆነው “ብልፅግና” ፓርቲም የቢሮክራሲውን የቢሮ ደጃፎች በሙሉ ቸንክሮ በተራዘመ ስብሰባ ከፍተኛ አመራሮች፣ መካከለኛ አመራሮች፣ ዝቅተኛ አመራሮች፣ ተራ አባሎች፣ ደጋፊዎች ወዘተ. እያለ መንግሥታዊ ስራ መበደሉና ባለጉዳይ መጉላላቱን በግሌ ያለመውደድ ብቻ ሳይሆን እንደ አንድ ዜጋ እያሳዘነኝም ነው። ምናለ የስብሰባ ቀናት አጥረው ሕዝብ በቅንነት ቢገለገልና ምሬት ቢቀንስ? አስሬ የሚጠየቅ ጥያቄ ቢሆንም የተሻሻለ ነገር ባለመታየቱ ለቅሬታ መዳረጉ አልቀረም። “እንኳም ዘንቦብሽ እንደውም ጤዛ ነሽ” አንዲሉ የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ዱሮውንም ቢሆን አፍቃሬ ስብሰባ ናቸው፤ እንኳንም ሰበብ አግኝተው – እያልንም በጓዳችን ማማታችን አልቀረም።
ሌላውና የብልፅግና ፓርቲ መሪውን የምንማጸነው ሹማምቱን ትህትና ያስተምሩልን። ባለጉዳይን በአክብሮት እንዲያስተናግዱ ይምከሩልን በማለት ነው። ምናልባትም ከሚያገለግሏቸው ዜጎች መካከል ከእነርሱ በዕድሜም ሆነ በዕውቀት የሚልቁ እንዳሉም ያስገንዝቡልን። በአጭሩ የሕዝብ ምሬት ወደ ብልፅግና ፓርቲም በውርስ እንዳይተላለፍ ይደረግልን።
ሕዝቡ በየክልሉና በየአካባቢው በነቂስ እየወጣ “የእኔ ነህ” እያለ ያከበረው ፓርቲና አመራሮቹ ቀደምት ታሪካችንን ደግመው ራስን ወደማበልፀግ ዝቅ ብለው የሚረክሱ ከሆነ አወዳደቃቸው እንደማያምር በውል እንዲረዱት ይደረግ። በአንድ ሀገራዊ ምሳሌ ነገሬን ልቋጭ። ሚጥጥዬ ትንኝ ነች አሉ፤ ወደ እናቷ ቀረብ ብላ “እማማ ሰዎች ሁሉ በአጠገባቸው ሳልፍ እያጨበጨቡ ያደንቁኛል። ምክንያቱ ምንድን ነው?” ብላ ብትጠይቃት አናትም፤ “አዬ ልጄ ያጨበጨቡልሽ መሰለሽ እንጂ ጨፍልቀው ሊገሉሽ ነው” አለቻት ይባላል። ልብ ያለው ልብ ያድርግ፤ ጭብጨባ ወደ ጥፋት እንዳይመራ ይታሰብበት። ሰላም ይሁን!!
አዲስ ዘመን ቅዳሜ የካቲት 21/2012
(ጌታቸው በለጠ – ዳግላስ ጴጥሮስ)
gechoseni@gmail.com