የወጣትነት ዕድሜ በፈተናዎች የተሞላ መሆኑ እሙን ነው። በተለይም የተሻለ ሥራ መሥራትም ሆነ ጥሪት ማፍራት የሚቻለው በዚያ ዕድሜ እንደመሆኑ የሚያጋጥሙትን መሰናክሎች አልፎ መገኘት ትልቅ ብልሐትን ይጠይቃል። ይህ የዕድሜ ዘመን ስህተትም የሚበዛበት፤ ለአጓጉል ሱሶችም የምንጋለጥበት መሆኑ ደግሞ ብዙዎቻችን ወጣትነትን ከዕሳት ጋር እንድንመስለው ያስገድደናል። ዕሳት እንደ አጠቃቀማችን ነው። ለጥፋት እንጠቀመዋለን፤ ነገሮችን ለመሥራት እንጠቀመዋለን። ዕሳት ምግብ ያበስላል፤ በጥንቃቄ ካልተያዘ ቤት ያቃጥላል። ወጣትነት በዚህ ይመሰላል።
በወጣትነት ዕድሜ ውስጥ ከሚከሰቱ ነገሮች አንዱ ሁሉ አማረሽ መሆን ነው። የድሀ ልጅ ሲሆኑ ደግሞ ችግሩ የከፋ ይሆናል። ጓደኞቹ ያደረጉትን ነገር ለማድረግ ይጓጓል። ያ ካልሆነ በቀላሉ ተስፋ ይቆርጣል። ወደ አልባሌ ቦታዎችና ሱስ ይገባል። በዚያ ሱስ ሰበብ የወደፊት ህይወቱን ሁሉ ያበላሻል። ለአደገኛ በሽታዎች ይጋለጣል። ይሄ ደግሞ አንድም የተጎሳቆለ ሕይወት እንዲኖር ያደርገዋል፤ አልፎ ተርፎም ህይወት እስከማጣት ያደርሳል። በበርካታ ወጣቶች ዘንድ የሚስተዋለው ይሄ ነው።
የዛሬ ‹‹እንዲህም ይኖራል›› እንግዳችን ለብዙ ወጣቶች ምሳሌ መሆን የሚችል ነው። የወጣትነት ፈተናዎችን ሁሉ ማሸነፍ የቻለ ነው። እነዚህን ፈተናዎች ያሸነፋቸው በከፍተኛ ችግር ውስጥ ሆኖ ነው። አሁንም በዚያው ችግር ውስጥ ነው። ይህም ቢሆን እነዚህ ችግሮች ያልፋሉ በሚል ከፍተኛ ተስፋ መሰነቁ አልቀረም። እነዚህ ችግሮች ያልፉ ዘንድ ደግሞ የወጣትነት ስሜቶችን መግራት እንደሚገባ አምኗል። ፋሽን ልብስ መልበስ፣ ፋሽን ስልኮችን መያዝ፣ በመዝናኛ ቦታዎች መዝናናት የወጣትነት ስሜቶች ናቸው። እነዚህን ማድረግ ያልቻለ ወጣት ነው በብስጭት ወደ አጓጉል ነገሮች የሚገባው። ይሄ ወጣት ግን ብልህ ሆኗል። ከጊዜያዊ ደስታ ይልቅ ዘላቂ ደስታን ለማግኘት መርጧል። ድህነቱን ማሸነፍ ፈልጓል። ለዚህ ደግሞ ዋነኛ መሣሪያ ያደረገው ትምህርትን ነው።
ወጣቱ መለሰ ገብረሚካኤል ይባላል። ተወልዶ ያደገው በከፋ ዞን ጊንቦ ወረዳ ውስጥ ነው። ከአንደኛ እስከ ስምንተኛ ክፍል በዚያው በትውልድ አካባቢው ተማረ። 9ኛና 10ኛ ክፍል ደግሞ ቦንጋ ከተማ ተማረ። 10ኛ ክፍል የወሰደው አገር አቀፍ ፈተና ግን ወደ መሰናዶ ትምህርት ቤት የሚያስገባ አልሆነም።
መለሰ ከአንደኛ እስከ 10ኛ ክፍል የተማረው በድሀ ቤተሰብ ውስጥ ነው። ለትምህርት አስፈላጊ የሆኑ ነገሮች እንኳን ከቤተሰብ አይሟሉለትም። የትምህርት መሣሪያዎችንና ልብስ ለማሟላት ትንንሽ ሥራዎችን ይሠራል። በተለይም 9ኛና 10ኛ ክፍል ሲማር ደግሞ ከቤተሰብ ርቆና ቤት ተከራይቶ ስለነበር ጫናው እየጨመረ መጣ። እነዚህን ነገሮች ለማሟላትም ከቀን ሥራ ጀምሮ ያገኘውን ይሠራል። በዚህ ሁኔታ ለሚወስደው አገር አቀፍ ፈተና በቂ ዝግጅት ማድረግ አልቻለምና ወደ መሰናዶ የሚያስገባ ውጤት አልመጣም።
እንደሚታወቀው በአገሪቱ ነባራዊ ሁኔታ ከ10ኛ ክፍል ወደ መሰናዶ የሚያስገባ ውጤት ያልመጣላቸው ተማሪዎች ወደ ኮሌጅ ነው የሚገቡት። ወደ ኮሌጅ ለመግባት ደግሞ የቤተሰብ ድጋፍ ያስፈልጋል። እዚህ ላይ የቤተሰብን የኢኮኖሚ አቅም ብቻ ሳይሆን የግንዛቤ አቅምም ይጠይቃል። የመለሰ ቤተሰቦች ይህን ሊያደርጉለት አልቻሉም፤ የኢኮኖሚ አቅማቸውም አይፈቅድም።
መለሰ በቤተሰብ ድጋፍ እንደማያገኝ አውቆ እጁን አጣጥፎ አልተቀመጠም። በመጀመሪያ ከቀን ሥራ ጀምሮ ያገኛውን መሥራት ጀመረ። እንደ ወጣትነቱም በተስፋ መቁረጥ የሱስ ተገዢ አልሆነም ። ይልቁንም በቀን ሥራም ይሁን በተላላኪነት ያገኛትን ሳንቲም ያስቀምጣል። እንዲህ እንዲህ እያለ ትምህርቱን ጀመረ።
መለሰ አሁን ሁለተኛ ዓመት የማኔጅመንት የኮሌጅ ተማሪ ነው። ሳይደግስ አይጣላም እንዲሉ በምን ሁኔታ ላይ እንዳለ የሚያውቁ ጓደኞቹ በአንዳንድ ነገሮች ድጋፍ ያደርጉለታል። የቤት ኪራይም ያግዙታል። ይህን የሚያደርጉለት የሚማርበት ኮሌጅ ተማሪዎችና ሠራተኞች ብቻ ሳይሆኑ የሌላ ኮሌጅ ተማሪዎችና ሠራተኞች ጭምር ናቸው።
መለሰ እንዲህ በሰዎች ለመረዳት የበቃው ትምህርቱን ሲል ነው። ትምህርቱን እርግፍ አድርጎ ቢተወው የተሻለ ገቢ እንደሚያገኝ ያምናል። መማር የወደፊት ሕይወቱን እንደሚያስተካክልለት ስላመነ እንጂ ለዛሬው ብቻ ብሎ ቢያስብ እንኳን ለቤት ኪራይ ለሌላም የሚተርፍ ሥራ መሥራት ይችላል። የሻይ ቅጠል ማምረት ሥራ ጀምሮ ነበር፤ ይሁንና ከትምህርቱ ጋር አብሮ ለመሄድ ስላልቻለለት ሥራውን ለማቋረጥ ተገደደ። በአንድ በኩል የሻይ ቅጠል ማሣ በሚሠራበት ጊዜ ጥሩ ገንዘብ ማግኘት ጀምሮ ስለነበርና በዚያው ቢቀጥል ወደ ሌላ ንግድ የሚያስኬድ ገንዘብ እንደሚያገኝ ያምናል። መንጃ ፈቃድ አውጥቶ በአሽከርካሪነት ሥራ ለመሰማራትም ጀምሮ ነበር። ዳሩ ግን በእንዲህ አይነቱን ሥራ ቶሎ ማደግ እንደሚቻል አላጣውም፤ ይሁንና በወጣትነቴ መማር አለብኝ በሚል ቁርጠኝነት ትምህርቱ ዘመዱ አደረገ።
መለሰ እንዲህ እንዲህ እያለ የቦንጋ ዩኒቨርሲቲ የጉልበት ሠራተኛ የቅጥር ማስታወቂያ አውጥቶ ተመለከተ። ወደ ዩኒቨርሲቲውም ገብቶ አመለከተ። ፈተናውንም አንደኛ ሆኖ አለፈ። አሁን በቦንጋ ዩኒቨርሲቲ በጉልበት ሠራተኝነት እያገለገለ ይገኛል። በዩኒቨርሲቲው ውስጥ ጠረጴዛም ሆነ ሌሎች ዕቃዎችን የማስተካከልና የጉልበት ሥራዎችን ይሠራል። እነዚህ ሥራዎች ከትምህርት ሰዓቱ ውጭ የሚሠሩ ናቸው።
በዚህ የጉልበት ሥራ የቤት ኪራይና የትምህርት ወጭውን እንደምንም ይሸፍናል። በየወሩ ለትምህርት 300 ብር ይከፍላል። የቤት ኪራይና የዕለት አስቤዛ አለበት። ከጉልበት ሠራተኝነቱ በተጨማሪ ሌሎች ሥራዎችን ለመሥራት ደግሞ የከተማዋ ዕድገትም ብዙም ምቹ አይደለም። በዚያ ላይ ለትምህርቱ ከሚሰጠው ጊዜ ጋር አልተመቻቸለትም።
መለሰ የዛሬ ጥንካሬው ለነገ ሕይወቱ ወሳኝ መሆኑን ያምናል። ዛሬ ላይ ቢቸገርም ነገ የተሻለ ሕይወት ይኖረኛል ብሎ ከፍተኛ ተስፋ ሰንቋል። ለዚህ ደግሞ ህይወቱን በብልሃት መምራት እንደሚገባው ተገንዝቧል። እንዲህ አይነት የቤተሰብ ድጋፍ የማያገኙ ወጣቶች በራሳቸው ብልህነትና ብልጠት ካልሆነ የከፋ ጉዳት ላይ ይወድቃሉ። በተለይም የወጣትነት ጊዜያቸው ሲያልፍ የጉልበት ሥራ እንኳን መሥራት የማይችሉበት አቅም ማጣት ይፈጠራል። በወጣትነት ቋሚ ሥራ ከፈጠሩ ግን የሰው እጅ ከማየት ያድናል።
መለሰ ወጣት ነው። የጉልበት ሥራ የሚሠራው ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ነው። የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን ሕይወት ጠዋት ማታ ያያል። የፋሽን አይነት የሚቀያይሩ ናቸው። መለሰ ግን እነዚህ ነገሮች ብዙም አያጓጉትም። ይልቁኑ እኩዮቹ ተማሪዎች የሚገለገሉበትን ዕቃ እሱ ይሸከማል። ለመዝናናት በቡድን ሆነው ወደ ከተማ ሲወጡ እሱ አቧራ ያዘለ ልብስ ለብሶ ዕቃ ሲሸከመር የዛሬውን ሳይሆን የወደፊቱን ብሩህ ቀን ያልማል።
የመለሰ ጥንካሬ እንግዲህ እዚህ ላይ ነው። በዚያ የወጣትነትና የአፍላነት ዕድሜ ይህን አርቆ አሰበ። ነገ ከእነዚህ ልጆች የተሻለ እንደሚሆን ባለሙሉ ተስፈኛ ሆነ። ብዙ ወጣቶች የሳቱትን ግን እዚህ ላይ ነው። ጥቂት የማይባሉት የእድሜ እኩዮቹ በወጣትነት ጊዜያቸው ሲንሸራሸሩ ኖረው የወጣትነት ዕድሜው ሲያልፍና አንዳች ጥሪት ሳያፈሩ መቅረታቸውን ሲገነዘቡ እንደሚቆጩ እሙን ነው። ምክንያቱም የፈሰሰ ውሃ አይታፈስም፤ ለላፈ ክረምት ቤት አይሰራም እንደሚባለው ነውና።
መለሰ ይህን ያደረገው በሁለት መንገድ ነው። አንድ፤ የነገ ሕይወቱን ለማሳመር፣ ሁለት፤ የሥራ ትንሽ የለውም ብሎ ስለሚያምን። እነዚያ ተማሪዎች እየተማሩ ነው፤ በቃ እሱም እየሠራ ነው። ፒ ኤች ዲ ያለው መምህር እያስተማረ ነው፤ መለሰም ዕቃ እየተሸከመ ነው። ሁለቱም የሚሠሩት ለእንጀራ ነው። ዶክተሩ የሚያስተምር ለሰማይ ቤት ብሎ ሳይሆን ለዕለት እንጀራው ነው፤ መለሰም ዕቃ የሚሸከም ለዕለት እንጀራው ነው።
መለሰ አሁን የማኔጅመንት ተማሪ ነው፤ ማን ያውቃል ነገ ከፍተኛ ባለሥልጣን ወይም በንግድ ዘርፍ ተሰማርቶ ከፍተኛ ኢንቨስተር ቢሆንስ? ማን ያውቃል? እኛ ግን ከወዲሁ እንዲሳካለት እየተመኘን እንሰነባበት።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ የካቲት 21/2012
ዋለልኝ አየለ