ኢትዮጵያ ሉዓላዊነቷን ጠብቃ ከመኖሯም ባሻገር ለሌሎች ጭቁን ህዝቦች በምታሳያቸው ተቆርቋሪነት ከፍተኛ የሆነ ዝናና ተቀባይነት አግኝታለች፡፡ ሀገሪቱ ለተገፉ እና በጭቆና ቀንበር ውስጥ ለወደቁ ህዝቦች በምታሳየው ወገናዊነት ጭቁን ህዝቦች ሀገሪቱን የነጻነትና የተስፋ ምድር አድርገው እንዲቆጥሯት አድርጓታል፡፡ በዚህም የተነሳ ከደቡብ አፍሪካ እስከ ካሪቢያን ከዛም እስከ ሰሜን አሜሪካ ድረስ የ ‹‹ኢትዮጵያኒዝም›› ዕሳቤ እንዲዳብርና ሁሉም በያለበት ኢፍትሃዊነትን እንዲፋለም በር ከፍቷል፡፡
ኢትዮጵያ ኢፍትሃዊነትን ከታገለችባቸውና ታግላም በአሸናፊነት ከወጣችባቸው መድረኮች መካከል የአድዋ ድል አንዱና ዋነኛው ነው፡፡ የአድዋ ድል በጥቁር ህዝቦች ታሪክ ውስጥ ኢፍትሃዊነትን ታግሎ ማሸነፍ እንደሚቻልም ምሳሌ የሆነ የተጋድሎ ታሪክ ነው፡፡ የዛሬ 124 ዓመት ኢትዮጵያውያን በአልበገር ባይነት ያሳዩት የነጻነት ተጋድሎ ጥቁር ህዝቦች ጭቆናንና ኢፍትሃዊነትን ታግለው ማሸነፍ እንደሚችሉ ህያው ምስክር ሆኖ የቆመ ሀውልት ከመሆኑም ባሻገር በአራቱም የዓለም አቅጣጫ የሚገኙ ህዝቦችም ለጭቆና እንዳይንበረከኩ የቃል ኪዳን ሰነድ ሆኖ ያገለገለና አሁንም ድረስ በተምሳሌትነት የሚነሳ ነው፡፡
ኢትዮጵያ የራሷን ነጻነት አስጠብቃ ከመኖሯና ለሌሎችም የነጻነትና ተስፋ ምድር ከመሆኗም በሻገር በቅኝ ግዛት ስር የነበሩ በርካታ የአፍሪካ ሀገራት ከቅኝ አገዛዝ ቀንበር እንዲላቀቁ የበኩሉዋን ጥረት ያደረገች ሀገር ነች፡፡ አፍሪካውያን የራሳቸውን ውሳኔ ካለማንም ጣልቃ ገብነት በራሳቸው እንዲወስኑና በአንድ ላይ ሆነው ድምጻቸው እንዲሰማ ያደረገች የአፍሪካ ብርሃንም ነች፡፡ መላው አፍሪካ በድቅድቅ ጨለማ ውስጥ በነበረበት ዘመን የአፍሪካ አንድነት ድርጅት እንዲቋቋም ግንባር ቀደም ሚና የተጫወተችና እስከ አፍሪካ ህብረት ምስረታም ድረስ በጽናት የዘለቀች ሀገር መሆኗም የአደባባይ ሀቅ ነው፡፡
አፍሪካውያን ከቅኝ ግዛትና የዘር መድልኦ (አፓርታይድ) ጭቆና እንዲላቀቁ የሃሳብም የሞራልም ድጋፍ ከማድረግ ባሻገር የቀድሞ የደቡብ አፍሪካ መሪን ኔልሰን ማንዴላን ወደ ሀገሯ ጠርታ ወታደራዊ ስልጠና እስከመስጠት የደረሰ ‹‹ ከእኔ›› ይልቅ ‹‹እኛ›› የሚለውን መርህ በመከተል ተምሳሌት የሆነች ሀገርም ነች፡፡ ለነጻነት ተምሳሌት የመሆን ይሄው የማይናወጥ አቋሟም በህዳሴው ግድብ ላይ ተስተውሏል፡፡
ኢትዮጵያ ታላቁ የህዳሴ ግድብን በህዝቦቿ ጥረት በራሷ አቅም ለመገንባት ስትነሳ በአንድ በኩል በአገሪቱ ልማትና ዕድገት ለማፋጠን በሌላ በኩል ደግሞ ለዘመናት ተጭኖባት የቆውን ኢፍትሃዊ ውሃ አጠቃቀም በራሷና በሌሎች ተፋሰሱ ሀገራት የጋራ ጥረት በመቀየር ፍትሃዊ የሆነ የውሃ ክፍፍል ስሌት ላይ እንዲደረስ ለማስቻል ነው፡፡ ግድቡ ፍትሃዊነትን በማንገስ ማንኛውም ሀገር የሌላውን መብት ጠብቆ የመልማት መብት እንዳለው የሚያሳይ የፍትሃዊነት አርማም ጭምር ነው፡፡
ይህ የፍትሃዊነት ጥያቄ አልዋጥላቸው ያሉ ሀገራት የተለያዩ ስልቶችን በመቀየስ ኢትዮጵያ ለዘመናት ሰፍኖ የቆየውን ኢፍትሃዊ ውሃ አጠቃቀም መርህ እንድትከተል የተለያዩ ጫናዎችን በማድረግ ላይ ይገኛሉ፡፡ ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ ጥንትም ሆነ ዛሬ ኢፍትሃዊነትን የመሸከም ባህልም ሆነ ልማድ የሌላት በመሆኑ ዛሬም እንደትናንቱ በጸናው አቋሟ በመቆም ለኢፍትሃዊ አካሄድ ቦታ እንደሌላት ደገማ አሳይታለች፡፡ ይህ ደግሞ ኢትዮጵያ በአድዋ ሉዓላዊነትን ለማስከበር በተደረገ ትግል የተገኘውን ፋና ወጊ ድል በጋራ ተጠቃሚነት መርህ ቃኝታ በመጓዝ ላይ መሆኗን ያመላክታል!
አዲስ ዘመን ቅዳሜ የካቲት 21/2012