ሰሞኑን የቢራ ዋጋ መጨመርን ተከትሎ የማህበራዊ ገፆች ቀልድ በቀልድ ሆነዋል። እዚህ ላይ ግን አንድ ነገር ተረዳሁ። ለካ
እውነትም ህዝባችን ጨዋ ነው። እንዲያውም እኮ ሲባል የነበረው የቢራ ዋጋ ቢጨምር ይሄ ሰካራም ወጣት የተቃውሞ ስልፍ ይወጣል የሚል
ነበር። የቢራ ዋጋ መጨመር ግን ከማህበራዊ ገፆች ቀልድ አላለፈም። በሌሎች ነገሮች ላይ እኮ እዚህ ግባ በማይባሉ ጉዳዮች ጭምር
ቅሬታዎች ሲፈጠሩ አይተናል። በቴሌቪዥን ጣቢያዎች አስተያየት ሲሰጡ አይተናል። የቢራ ዋጋ ተወደደ ብሎ በቁም ነገር የተቃወመ ግን
አላየሁም። የትንሽ ትልቁ መቃወሚያ የሆነው ፌስቡክ እንኳን ከቀልድ ያለፈ ምንም አልተባለበትም፡፡
ምንም እንኳን ዝርዝር ጉዳዩ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ድርሻ ቢሆንም ለሁላችንም ግልጽ የሆነ ነገር አለ። ኢትዮጵያ ታዳጊ አገር ናት። መንግሥትም ሆነ ህዝብ በቂ አቅም የላቸውም። መንግሥት አቅሙን ለማጎልበት ከውጭ የሚገቡ ዕቃዎች ላይ ቀረጥ ይጨምራል። ህዝቡ ደግሞ ከውጭ የሚያስገባቸው ዕቃዎች ከቀረጥ ነፃ ቢገቡለት ይፈልጋል፤ ነፃ መሆኑ ቢቀር እንኳን እንዲቀንስለት ይፈልጋል። ሁለቱም ይህን የሚያደርጉት ትልቅ አቅም ስለሌላቸው ነው። መንግሥት ትልቅ አቅም ቢኖረው ኖሮ ዕቃዎችን ከቀረጥ ነፃ ማስገባት ይችል ነበር። ህዝቡም አቅም ቢኖረው ኖሮ ቀረጥ ቢከፍል አይጎዳም ነበር።
ልብ ብላችሁ ከሆነ በየስብሰባውና በየውይይቱ ከቀረጥ ነፃ ይግባልን የማይባል ነገር የለም። የሚባለው ሁሉ ከቀረጥ ነፃ ይግባ ቢባል መንግሥት ባዶ እጁን አጨብጭቦ ሊቀር ነው ማለት ነው፤ መንግሥት አጣ ማለት ደግሞ ህዝቡም ተጎዳ ማለት ነው።መሰረተ ልማትና ማህበራዊ ፍላጎቶች በሌለበት ሀብታምም ቢሆን ወዴትም መወላፈት አይቻልም፡፡
እንግዲህ ለዚህ መፍትሔው ማቻቻል ነው። ይሄ ማለት መሰረታዊ የሆኑ ነገሮች ላይ መቀነስ፤ የቅንጦት ነገሮች ላይ ደግሞ መጨመር ማለት ነው።ለምሳሌ መንግሥት የግብርና መሣሪያዎች ከቀረጥ ነፃ እንዲገቡ እየሠራ ነው ተብሏል። ግብርና ለኢትዮጵያ ምን እንደሆነ ይታወቃል። የግብርና ምርቶች ሁሉ መሠረታዊ ፍላጎቶች ናቸው። የግብርና መሣሪያዎች ከፍተኛ ቀረጥ ቢጣልባቸው ግብርናው ሳይዘምን ሊቀር ነው ማለት ነው።
በዚህ በቀረጥ ጉዳይ ላይ ዋና ክርክር የሆነው፤ የቱ ነው መሠረታዊ ፍላጎት? የቱ ነው የቅንጦት? የሚለው ነው። በነገራችን ላይ በዚህ ዘመን ሁሉም ነገር መሠረታዊ ፍላጎት ሆኗል።ለምሳሌ የእጅ ስልክ የቅንጦት ነበር፤ አሁን ግን የግድ ነው፤ መኪና የቅንጦት ነበር፤ አዲስ አበባ ውስጥ ግን መኪና የግድ ሆኗል፤ ስለዚህ መሠረታዊ ፍላጎት ነው ማለት ነው።
ወደ ቢራችን እንመለስ፡፡
የሆነውስ ሆነና ግን ቢራ የቅንጦት ነው ወይስ መሰረታዊ ፍላጎት? ምናልባት እንደየሰው ይለያይ ይሆናል። አንድ ነገር ግን ማስተዋል እንችላለን። እውነት ‹‹ቢራ ሳልቀምስ መዋል አልችልም!›› የሚል ሰው ይኖራል? አይመስለኝም። እርግጥ ነው ብዙ የመጠጥ ሱሰኛ አለ፤ ዳሩ ግን መተው ከሚቻሉ የሱስ አይነቶች ሁሉ ቢራ በጣም ቀላሉ ነው፡፡የዘርፉ ምሁራን እንደሚሉት ቢራ ብቻ ሳይሆን የትኛውም የአልኮል መጠጥ መተው የሚቻል ነው። ይሄ እንግዲህ ከሌሎች የሱስ አይነቶች ጋር ስናነፃፅረው ነው።ለምሳሌ ሲጋራ ለመተው ከባድ ነው፤ ቆራጥ ውሳኔና ወኔ ይጠይቃል። ጫትም እንደ ሲጋራ ባይሆንም ሱሱ ከባድ ነው።ቢራ ግን ይሄን ያህል አይሆንም።
ቢራ የሚጠጡ ሰዎችን ልብ ብለን እንይ። ሱስ አንደርድሮ አይደለም የሚያስገባው። ወይኔ! ቢራ አጣሁ ብሎ እያፋሸከ ወይም ዓይኑ ጨልሞ ወይም እንቅልፍ እንቅልፍ እያለው አይታይም። ቢራ የሚጠጣው ከጓደኛ ጋር ሲገናኙ ለመጫወትና ለመዝናናት ነው። በዓላት ወይም ሌላ ዝግጅት ነገር ሲኖር በዓሉን ወይም ዝግጅቱን ለማድመቅ ነው። በእረፍት ቀናት አረፍ ለማለት ነው።ከዚህ ውጭ የቢራ ሱስ ከቤት ወይም ከመሥሪያ ቤት አስፎርፎ የሚያስኬድ አይደለም። ታዲያ ይሄን መሠረታዊ ፍላጎት ነው ማለት እንችላለን?
የሰሞኑን የቢራ ዋጋ መጨመር ምክንያት በማድረግ ይመስላል መጠጥ ቤቶች ፀጥ ብለዋል። በነገራችን ላይ ገና አዋጁ ሳይፀድቅ አንድ ክርክር ነበር። ወጣቱ የቱንም ያህል ቢራ ቢወደድ መጠጣት አያቆምም ተብሎ ነበር። ዳሩ ግን እንደተባለው አልሆነም። መቀነስ ጀምሯል። አይቀንስም ይሉ የነበሩ ሰዎች ምክንያታቸው፤ አምስት ብር የነበረው እስከ አሥራ ምናምን ሲደርስ የጠጪ ቁጥር አልቀነሰም የሚል ነው። ልብ ያላሉት ነገር ግን ያ እና ይሄ ይለያያል። ያኛው ጭማሪ በሂደት ነው። አንድ ጊዜ አንድ ብር ጨምሮ ከሆነ ከብዙ ጊዜ በኋላ አንድ ብር እያለ ነው። በዚያ ላይ ከቤት ቤት ይለያያል። ይሄን ማንም ልብ አይለውም። በአዋጅ ሲሆን ግን አንድ ጊዜ ነው ልብ የሚባለው።ሁሉም ትኩረት ይሰጠዋል።‹‹እንዲህ እየጠጣሁ ልዘልቅ ነው እንዴ!›› የሚል ቁጭት ማሳደሩ አይቀርም።
እኛም ከአዋጁ መፅደቅ በኋላ የተለያዩ መጠጥቤቶችንና ግሮሰሪዎችን ተዘዋውረን ለመታዘብ ሞክረናል። አዋጁን ተከትሎ ግሮሰሪዎች ፀጥ ብለዋል። አሁን ለስካር ሳይሆን ለማንበቢያነት ነው የሚያስመኙ። በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ይሁንባችሁ ሲላቸው አዋጁ ከመፅደቁ ደግሞ የአብይ ፆም ገባ። ሥጋ ነገር ካልተበላ ቢራ ብዙም አይጠጣም፤ ቢራ የሚጠጡት ደግሞ በአብዛኛው የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ስለሆኑ የአብይ ፆምም አብይ ሚና አለው።
የሆነውስ ሆነና ግን የቢራ ዋጋ መቀነስ የሰካራም ቁጥር ይቀንስ ይሆን? የሚቀንስ ከሆነ መንግሥትም ህዝብም ተጠቀመ ማለት ነው። መንግሥት በሚያገኘው ቀረጥ፤ ህዝብ በሚያገኘው ሰላም። የቢራ ማስታወቂያዎች በልክ ይጠጣ ቢሉም በልክ የሚጠጣ አልነበረም። ስካር ነውር ነው ቢባልም ነውር ነው ተብሎ አልተተወም። አልኮልነቱ እንደ ግለሰብ ጤናን ይጎዳል፤ ስካሩ ደግሞ ማህበረሰብን ይጎዳል። ስለዚህ በዚህ አጋጣሚ እንኳን የጠጪ ቁጥር የሚቀንስ ከሆነ ውሳኔው ጥሩ ነው፡፡
ከአንድ የሥራ ባልደረባዬ ጋር በዚሁ ጉዳይ ዙሪያ ስንጨዋወት ያነሳልኝን ነጥብ ግን ሳልጠቅሰው ማለፍ አልፈልግም። የሥራ ባልደረባዬ እንዳለው አብዛኞቻችን አንድ ነገር ሲመጣ በወረት የመደገፍና የመንቀፍ ወይም የመተውና መጀመር አባዜ ይታይብናል። የመርህ ሰዎች አይደለንም። አንድን ነገር ከውስጣችን አምነንበት መደገፍ ወይም መንቀፍ ባህል የለነም። ሁሉንም ነገር በደቦ የመፈፀም ባህል አዳብረናል። ስለዚህም ብዞዎቻችን ለጊዜው በዋጋ ውድነቱ ተደናግጠን ለጊዜው ከመጠጣችን ብንታቀብም መርህ አልባ በመሆናችን ቀስ በቀስ ወደነበርንበት መመለሳችን አይቀርም የሚል ውሃ የሚቋጥር ሐሳብ አንስቶልኛል። እኔም የዚሁ ጓደኛዬን ሐሳብ ለመደገፍም ሆነ ለመንቀፍ ስለተቸገርኩ ሁሉንም ጊዜ ይፈተዋል በሚል ተሰነባብተናል።
እኔም በቢራ ላይ የተጣለው የኤክሳይስ ታክስ በፈጠረው ጭማሪ ለጊዜው የጠጪውን ቁጥር የቀነሰው ይመስላል፡፡ ነገር ግን ይህ ሁኔታ እስከመቼ እንደሚቆይ በእርግጠኝነት ለመናገር ነገን መጠበቁ የግድ የሚል ይመስለኛል፡፡
አዲስ ዘመን ቅዳሜ የካቲት 21/2012
ዋለልኝ አየለ