ኢትዮጵያ ከውሃ ኃይል ብቻ እስከ 45ሺ ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት የሚያስችል አቅም ቢኖራትም እስከአሁን እያመነጨች ያለው ግን ከአራት ሺ ሜጋዋት የሚበልጥ አይደለም።
አቅም አጥተን ለዘመናት ሳንጠቀምበት ለዘመናት ሲፈስ የኖረው የአባይ ወንዝ የገጠሩን ህዝብ የመብራት አገልግሎት ተጠቃሚ ሊያደርግ፤ ለኢንዱስትሪው ደግሞ የኤሌክትሪክ ኃይል ደጀን ሊሆን በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል በመተከል ዞን በጉባ ወረዳ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ እየተካሄደ ይገኛል።
የግድቡ የመሰረት ድንጋይ ከተጣለበት ዕለት ጀምሮ እስከአሁን ድረስ ህዝቡ በግድቡ ግንባታ ላይ እያሳየ ያለው የገንዘብም ሆነ የሞራል ድጋፍም ለባለቤትነቱ መተማመኛ ነው። ኢትዮጵያዊያን ድህነትን ለመቀነስ ብሎም ለማስወገድ ቁርጠኛ መሆናችንን ያሳየ ነው። ግድቡ በአሁኑ ወቅት አፈጻጸሙ ከ72 በመቶ በላይ ደርሷል።
ቀደም ሲል ኢትዮጵያ የአባይን ወንዝ ለመጠቀም ብታሰብም የእርስ በእርስ ጦርነትና ድህነቷ «የበይ ተመልካች» አድርጓት ቆይቷል። በተለይ ኢትዮጵያ ከዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት የገንዘብ ድጋፍ አግኝታ ግድብ ገንብታ የኤሌክትሪክ አገልግሎት የማያገኙትን ህዝቦቿን ተጠቃሚ እንዳታደርግ የግብፅ ባለስልጣናት ስውር እንቅስቃሴ ሲያደረጉ ነበር። የአባይን ውሃ በፍትሐዊነት የመጠቀም መርህን በጣሰ መልኩም የዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማትን በሮች ሲያዘጉባትም ቆይተዋል። እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ደግሞ በራሷ አቅም እንዳትገነባ ድህነቷ አላላውስ ብሏታል።
አሁን ግን ይህ ታሪክ ተቀይሮ የህዳሴ ግድብ መገንባት ችላለች። የዚህ ግድብ ባለቤቶች አሁንም ኢትዮጵያዊያን መሆናቸውን ዓለም ማወቅ አለበት። የውጭ ታዛቢም ሆነ አደራዳሪ በህዳሴ ግድብ ዙርያ የሚያቀርበው ሃሳብ የኢትዮጵያዊያንን ጥቅም የሚጎዳ መሆን የለበትም።
በኢትዮጵያ ከተሞችና ኢንዱስትሪዎች እየተስፋፉ መምጣታቸውን ተከትሎም የኤሌክትሪክ ኃይል ፍላጎት በእጅጉ እየጨመረ ይገኛል። በተለያዩ አካባቢዎች ግድቦች የተገነቡ ቢሆንም አሁንም እያደገ የመጣውን የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ፍላጎቷን ማርካት አልቻለችም። ችግሩን ለመፍታት እየተሠሩ ከሚገኙ ሥራዎች መካከል አንዱ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ነው።
ግድቡ የኢትዮጵያን የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት አስተማማኝ ከማድረጉ ጎን ለጎን በተለይ የታችኞቹን ተፋሰስ አገሮች የማይጎዳ ነው። ይህ ግድብ የኢትዮጵያን የኤሌክትሪክ ኃይል ፍላጎት ከማሟላት በአሻገር የተፋሰሱ አገሮችን በኃይል አቅርቦት ለማስተሳሰርም የሚያስችል ነው። ስለሆነም በግድቡ ዙርያ መያዝ ያለበት አቋም ይህን ታሳቢ ያደረገ መሆን አለበት። በዚህ ረገድ መንግሥት የያዘው አቋም ትክክል ነው።
ኢትዮጵያ በአባይ ውሃ አጠቃቀም እውነትና ፍትሐዊነት ላይ የተመሰረተ ትብብር መኖር አለበት የሚል መርህ እየተከተለች ነው። ይህን መርህ ይዛ እስከአሁን ድረስ በነበሩ ድርድሮች ስትሳትፍ ቆይታለች። በአሜሪካ መንግሥትና የዓለም ባንክ ታዛቢነት ሲደረጉ የነበሩት የሦስትዮሽ ውይይቶች ያለውጤት እንዲበተኑ የሆነው የግብጽ መከራከሪያ ነጥቦች መለዋወጥ ምክንያት ነው።
የኢትዮጵያ ተደራዳሪ ቡድን በአገር ውስጥ ከባለድርሻ አካላት ጋር የሚያደርገውን ውይይት ባለማጠናቀቁና የመወያያ ነጥብ እስኪለይ ድረስም ኢትዮጵያ በዚህ ሳምንት የሚደረገውን ውይይት እንደማትሳተፍ መግለጿም የሚታወስ ነው።
የዓለም አቀፍ የውሃ ኤክስፐርቶች የግምገማ ውጤት እንደሚያመለክተው ታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ የኃይል ማመንጫ ግድብ በግብጽም ሆነ በሱዳን ላይ የጎላ የሚባል ተፅእኖ እንደማያስከትል ቢያረጋግጡም የግብፅ ባለስልጣናት በግድቡ ዙሪያ በሚደረገው ድርድር በየጊዜው የሚቀያየር ሃሳብ እያቀረቡ ድርድሩ እስከ ዛሬ ድረስ ሊቋጭ አልቻለም። ይሁን እንጂ አሁንም ኢትዮጵያ በአባይ ጉዳይ ላይ ያላት አቋም የፍትሐዊ ተጠቃሚነት መርህን የተከተለ ነው። ይህን መርህ ይዛም ነው ግድቡን እየገነባች የምትገኘው።
ስለዚህ የህዳሴው ግድብ የኢትዮጵያዊያን ነው ስንል የሦስትዮሽ ድርድሩ የኢትዮጵያን ጥቅም የሚጎዳ መሆን የለበትም። የኢትዮጵያ ጥቅምም ለድርድር መቅረብ አይችልም ማለታችን ነው። ስለሆነም የህዳሴው ግድብ ሁለንተናዊ ጥቅማችንን የምናረጋግጥበት በመሆኑ ግንባታው አጠናቀን ፍሬውን ለመብላት ተግትን መሥራት ይኖርብናል። ድርድር አስፈላጊ ቢሆንም ለአገሪቱ የተሻለው መንገድ የሚሆነው ከንግግሩ በተጨማሪ ግንባታውን ማፋጠን ይገባል።
አዲስ ዘመን የካቲት 20/2012