የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የውድድር ዓመቱ አንደኛ ዙር መርሐ ግብር ከሦስት ወራት ቆይታ በኋላ ባሳለፍነው ሰኞ የካቲት 16 ቀን 2012 ዓ.ም ተጠናቋል። የመጀመሪያው ምዕራፍ በተለያዩ ክስተቶች የታጀበ ሆኖም አልፏል።የመጀመሪያው ዙር ቆይታ የኢትዮጵያ እግር ባለፉት ሁለትና ሦስት ዓመታት ከገባበት የስፖርታዊ ጨዋነት ስጋት አንፃራዊ በሆነ መልኩ መሻሻል የታየበት ነው።ፕሪሚየር ሊጉ ሲወቀስበት ከነበረው የስፖርታዊ ጨዋነት ስጋት ወጥቶ አዲስ መልክ እንዲይዝ በማድረግም የሊግ ኮሚቴው ውጤት ማሳየት የጀመረበት ነበር።
በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ በተለይ ከሦስት ዓመት ወዲህ የስፖርታዊነት ጨዋነት ችግር የእግር ኳሱ ትልቅ ፈተና ሲሆን ታዝበናል። በየጨዋታዎች በደጋፊዎች መካከል የሚነሱ ፀቦች እንደ ፋሽን መታየት የጀመሩበት ጊዜም ነበር። በፌዴሬሽኑ፣ በክለቦች ፣በመንግሥት በኩል ለችግሩ መፍትሔ ማምጣት የሚያስችሉ ሥራዎች እንደተሠሩ ቢነገርም ስታዲየሞችን የፀብ መነኸሪያ ከመሆን መታደግ አልተቻለም ነበር።ስታዲየሞች የእግር ኳስ ስሜትን ሳይሆን የፖለቲካ ስሜትን ማንፀባረቂያ መድረክ ወደ መሆን እስከመሻገር ደርሰዋል።የትግራይና የአማራ ክልል ክለቦች ፤በደቡብ ክልል የሚገኙ ክለቦች እርስ በዕርስ ተገናኝተው ለመጫወት አዳጋች እስከመሆን ያደረሰንም ስርዓት አልበኝነት ሰፍኖ ነበር።
በ2009 ዓ.ም በርካታ ቁጥር ያለው የስቴዲየም ሁከት በተለይም በፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች ቢከሰቱም ከብጥብጦቹ ጀርባ እግር ኳስን የሚሻገሩ ገፊ ምክንያቶች እምብዛም እንዳልነበሩ ይጠቀሳል። ከ2009 ወዲህ ግን በልዩ ልዩ ምክንያቶች የሚለኮሱ የስቴድየም ግጭቶችና ረብሻዎች ቁጥር ከዘንድሮው የውድድር ዓመት በፊት አይለው ነበር።በ2010 የውድድር ዓመት ሐዋሳ፣ ድሬዳዋ፣ አዲግራት፣ ጅማና ወልዲያ ከተሞች ውስጥ የስቴድየም ሁከትና ግጭቶች ተበራክተው እንደነበር ይታወሳል።በተለይም በውድድር ዓመቱ በወልዲያ ስፖርት ክለብና በመቀሌ ከተማ መካከል ሊደረግ የነበረው የእግር ኳስ ጨዋታ ከመጀመሩ ከሰዓታት በፊት በሁለቱ ቡድኖች ደጋፊዎች መካከል በተቀሰቀሰው ግጭት ህይወት የጠፋ ሲሆን ንብረት ላይ ዘረፋና ወድመት ተከስቷል። በዕለቱም ማገባደጃ ላይ በመቀሌ ከተማ መንገዶች ላይ ክስተቱን ለመቃወም በርካታ ሰዎች ወጥተው እንደነበር አይዘነጋም። ጨዋታው ካለመካሄዱ በተጨማሪም የግጭቱ አሻራ እስከ ቀጣይ ቀናት ሲሻገርና ከእግር ኳሳዊ ምክኒያት ይልቅ ፖለቲካዊ አንደምታው ሚዛን ሲደፋ ታይቷል።በወቅቱ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት የነበሩት አቶ ጁነዲን ባሻ ክስተቱ ከእግር ኳስ የሚሻገር ገፅታ እንዳለው ተናግረው ነበር፡፡
የ2010 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ መርሐ ግብር ከረብሻዎች ጋር በተያያዘ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በተለያዩ ክለቦች ላይ የጣለው ቅጣት ግማሽ ሚሊዮን ብር ገደማ መሰብሰብ መቻሉ ግጭቶች በምን ያህል ደረጃ እንደተበራከቱ ማሳያ ነው።በእንቁላሉ ጊዜ ያልተቀጣው እግር ኳስ ከፖለቲካም በላይ ጦዞ ለፀጥታ አስከባሪዎች ፈተና ከመሆን አልፎ እንደ አገር ስጋት የሆነበት ደረጃ ላይ ደርሶም ነበር።ሰላም በራቃቸው የስፖርት ማዘውተሪያዎች መደበኛ የውድድር መርሐ ግብሮች መተማመኛ ማግኘት አልቻሉም ነበር።በክልል የሚካሄዱ ጨዋታዎች በፖለቲካ ትኩሳት ሳቢያ ተጨማሪ ራስ ምታት እየሆኑ መምጣታቸውም አሳሳቢ ነበር።
በስፖርቱ ዓለም የተመልካቾች ነውጠኝነት ምክንያቶች ብዙ መሆናቸውን በስፖርቱ ጥልቅ እውቀት ያላቸው ባለሙያዎች ሲናገሩ ይደመጣል።ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊ ወይንም ምጣኔ ሀብታዊ ብሶቶች ስቴዲየም ላይ ሊያጠሉ እንደሚችሉም ይታመናል።በኢትዮጵያ እግር ኳስን የታከከ ግጭትና ሁከት ሲከሰት የመጀመሪያው ባይሆንም በተለይም ባለፈው የውድድር ዓመት ቀይ መስመር አልፎ ነበር።የቅርብ ጊዜ ክስተቶችን ስናጤን ደግሞ ከእግር ኳስ ባሻገር ከእነዚህ ምክኒያቶች ሁሉ ለስፖርት ጠንቅ የሆነ የፖለቲካ አጀንዳ መኖሩን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ራሳቸው አስተውለውታል።እግር ኳስ ማኅበረሰባዊ መሰረት ከሌለው በስተቀር የጠነከረ የእኔነት ስሜት ሊፈጥር አይቻለውም የሚሉ ተንታኞች፤ ክለቦች ከማኅበረሰባዊ መሰረታቸው በዘለለ ብሔር ተኮር መልክን እየተላበሱ የመምጣታቸው አዝማሚያ አደገኛ መሆኑ የበርካታ ስፖርት ቤተሰቦች እምነት ነው፡፡
ክለቦች ሲቋቋሙ ወይንም ሲዋቀሩ አካባቢያዊ መገለጫ ወይንም ከተማዊ ስያሜ ሊኖራቸው ቢችልም ከብሔር፣ ከዘር ወይንም ከኃይማኖት ጋር በተቆራኘ መልኩ መደራጀት ክልክል መሆኑን የስፖርት ኮሚሽን የስፖርት ማኅበራት ማደራጃ መመሪያ አንቀፅ 50 ቁጥር 2 ይገልፃል። ነገር ግን ባለፉት ዓመታት ብቻ ፌዴሬሽኑ በሚያስተዳድራቸው ሊጎች የብሔር ስም የተቀጠላላቸው በርካታ ክለቦች ውድድር እያደረጉ መጥተው ነበር።እግር ኳሱ ከአንዳንድ ሁከቶች አልፎ እጅግ ወደተደራጀ ነውጠኛነት እያመራ ስለመሆኑም ሲነገር ቆይቷል።ቀስ በቀስም ወደ መቧደን እየተጓዘ ነበር።
ይህ አዝማሚያ የ2012 ዓ.ም የውድድር ዓመት ከመጀመሩ አስቀድሞ በእግር ኳሱ ላይ ምን ሊፈጠር እንደሚችል በበርካቶች ዘንድ ስጋት ፈጥሮ ነበር።በዚህ ስጋት ውስጥ እያለ ኅዳር 21 ቀን 2012 ዓ.ም የተጀመረው ፕሪሚየር ሊግ ከፌዴሬሽኑ መሪነት ወጥቶ በሊግ ኮሚቴ መመራቱን ተከትሎ ቢያንስ ቢያንስ በመጀመሪያው ዙር የታሰበው ስጋት ሊረግብ ችሏል።
በውድድር ዓመቱ በመጀመሪያ ዙር ከተደረጉ 30 ጨዋታዎች ቢያንስ 25 ጨዋታዎች ስፖርታዊ ጨዋነት የነገሠባቸው ነበሩ። ስፖርቱን ከፖለቲካ በመቀላቀል ስታዲየሞችን የፀብ መናገሻ የማድረጉ ዝንባሌ እንዳይኖሩ የተደረጉ ጥረቶችም ከሞላ ጎደል ፍሬያማ ነበሩ ማለት ይቻላል።ለዚህ ደግሞ የአማራ ክልልና ትግራይ ክልል ክለቦችን እንደ ማሳያ ማንሳት ይገባል። አምና በሁለቱ ክልል ክለቦች ደጋፊዎች መካከል የነበረውን መፋጠጥ በውድድር ዓመቱ እንዳይደገም ማድረግ ተችሏል። የባህር ዳር ወጣቶች የመቐለ 70 እንደርታ ተጫዋቾችና ደጋፊዎች በወንድማዊ ስሜት ‹‹እንኳን ወደ ውቢቷ ከተማችሁ በደህና መጣችሁ›› ሲሉ በፍቅር በመቀበል ፀብን ለማራቅ የሄዱበት ርቀት ትልቅ ርምጃ ነበር።የመቐለ 70 እንደርታ ደጋፊዎች ከባህር ዳር ከነማ ደጋፊዎች በጋራ በመሆን ከተማዋን በማፅዳት አንድነታቸውን ያሳዩበት ድርጊት የከረረውን ስጋት መበጠስ ችሏል።
የሁለቱ ክለቦች ደጋፊ ማህበራት በአብሮነት መሥራት መቻላቸው ስፖርት ለሰላም፣ ለአንድነትና ለወንድማማችነት መርህን በተግባር እንዲታይ አድርጓል። የፋሲል ከነማ እግር ኳስ ክለብ ወደ መቐለ ከተማ ባቀናበት ወቅት የነበረው ሁኔታ ፤በሁለቱ ክለብ ደጋፊዎች መካከል ተጨማሪ የአንድነት ስሜት እንዲጎለብት ያደረገ ነበር። የመቐለ ከተማ ወጣቶች የፋሲል ከነማ እግር ኳስ ክለብ ተጫዋቾችና ደጋፊዎችን ፍጹም ፍቅር በተሞላበት መልኩ ተቀብለው በመሸኘት የልዩነቱን ግንብ ማፍረስ የቻሉበትን አጋጣሚ ፈጥረዋል። በሁለቱ ክልሎች የሚገኙ የክለቦች ደጋፊ ማህበራት በኩል የታየው ቆራጥነት ለዚህ ውጤት መገኘት ትልቅ ድርሻ የያዘም ነበር። የሁለቱ ክልሎች የመንግሥት አመራሮች በኩል የታየው ቀናኢነትና ከደጋፊ ማህበራቱ መቀናጀት ጋር ተደምሮ የእግር ኳሱ ስጋት ሊረግብ ችሏል።
በደቡብ ክልል የሚገኙ ክለቦች ደጋፊዎች ስፖርታዊ ጨዋነት እንዲሰፍን ያሳዩት ቁርጠኝነትም የመጀመሪያው ዙር አንፃራዊ ሰላም እንዲሰፍንበት ትልቅ ሚና ነበረው።በወላይታ ድቻና ሲዳማ ቡና ክለብ ደጋፊዎች መካከል የነበረውን መፋጠጠ በውድድር ዓመቱ አዲስ የሰላም መልክ መያዝ መቻሉ ለዚህ ስኬት ምሳሌ ነው፡፡
ለኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ውበት ከሆኑ ክለቦች መካከል የሸገር ደርቢዎቹ ኢትዮጵያ ቡናንና ቅዱስ ጊዮርጊስን እዚህ ላይ ሳይጠቅሱ ማለፍ አይቻልም።የከተማዋ ተፎካካሪ ክለቦች ቅዱስ ጊዮርጊስና ኢትዮጵያ ቡና ተመልካቾች መካከል የተስተዋለው መከባበርና ሥነ ሥርዓት ለክልል ክለብ ደጋፊዎች እንደማሳያ መወሰድ እንዳለበት የብዙኃን አስተያየት ጭምር ነበር።ቀደም ሲል ሁለቱ ክለቦች ጨዋታ ሲኖራቸው በከተማዋ የሚኖረው ውጥረትና የፀጥታ ስጋት በዚህ ዓመት ከከተማዋ ዋንጫ ጀምሮ ሰላማዊና የሚያስመሰግናቸው ጭምር ነበር።የሁሉም ክለቦች ደጋፊ ማኅበር ፕሬዚዳንቶች በጥምረት የመሠረቱትን ማኅበር ተከትሎ፣ እንደዚህ ዓይነት ችግሮች ዳግም እንዳይከሰቱ የሸገር ደርቢዎች የነበራቸውን ሚናም በጉልህ የሚጠቀስ ነው።የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ ሚና ከዚህ ስኬት ጋር አብሮ መነሳት ይገባዋል። ከንቲባው በተለያዩ ጊዜያት ከኢትዮጵያ ቡና እና የቅዱስ ጊዮርጊስ የስፖርት ክለብ አመራሮች ጋር በወቅታዊ እና መሠረታዊ ጉዳዮች ዙሪያ በመወያየት በደጋፊዎች መካከል ይፈጠር የነበረውን ግጭት እንዲከስም ያላሳለሰ ጥረት ሲያደርጉ ነበር። በሸገር ደርቢ ጨዋታ ወቅት በአዲስ አበባ ስታዲየም ይሰማ የነበረው የፀብ ዜና በሰላም እንዲተካ በማድረግ ረገድ ምክትል ከንቲባውና የሁለቱ ክለቦች ደጋፊ ማህበራት ቆራጥነት ሳይደነቅ የሚታለፍ አይደለም።
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ2012 ዓ.ም የውድድር ዓመት አንደኛ ዙር ቆይታ ከስፖርታዊ ጨዋነት አኳያ አበረታች ውጤት የታየበት ቢሆንም በመጨረሻዎቹ ሁለትና ሦስት ጨዋታዎች እንከኖች መታየታቸው አልቀረም።ኢትዮጵያ ቡና ከወላይታ ድቻ በነበራቸው ጨዋታ፣ ወልቂጤ ከተማና ሲዳማ ቡና በነበራቸው ጨዋታ በደጋፊዎች መካከል የተፈጠረ ግጭት ቢኖርም እንዳለፉት ዓመታት የተጋነነ ነው ለማለት አይቻልም።ያም ሆኖ የሊግ ኮሚቴው እንዲህ ዓይነት ግጭቶች ወደ ሁለተኛው ዙር እንዳይዛመቱ ሰሞኑን ፋሲል ከነማንና ቅዱስ ጊዮርጊስን ከዚሁ ከስፖርታዊ ጨዋነት ጋር በተያያዘ ቅጣት እንዳስተላለፈባቸው ሌሎቹንም ተመልክቶ ፍትሐዊ ቅጣት ማስተላለፍ ይጠበቅበታል።ይህም ሳይቃጠል በቅጠል እንዲሉ የመጀመሪያው ዙር በተሻለ ስፖርታዊ ጨዋነት እንደተጠናቀቀው ሁሉ ለሁለተኛውም ዙር ከወዲሁ የቤት ሥራዎችን ጨርሶ መሻገር ለነገ የሚባል አይደለም።
አዲስ ዘመን አርብ የካቲት 20/2012
ዳንኤል ዘነበ