አንዳንዱ ብድግ ይልና ስላለፈው ትናንት ማውራት የለብንም፤ ያለቀለትና የሞተ ጉዳይ ነው፤ የማይመልስ ነገር ነው ይላል። አሁን ስላለውና ወደፊት ስለሚኖረው ነገር ነው ማሰብ የሚጠበቅብን በማለት ይመክራል። በዛሬ ትናንትን ዋጋ ያሳጣል። አንዳንዱ ደግሞ መልካምነትና ፍቅር፤ እውነትና እምነት ድሮ ቀረ በማለት በምናብ ወደ ኋላ ይወስደናል። በትናንት ዛሬን ያናንቃል። እውነት ነገራችን ሁሉ እንዲህ ነው ወይ? በእርግጥ ሰው ይበልጥ ስለሚያውቀው ነገር ማሰቡና መናገሩ ክፋት የለውም። ችግሩ ከወዲሁ ነው። እውነት ትናንትንም ሆነ ዛሬን መወደሱም ሆነ መውቀሱ በምክንያትና በዕውቀት ላይ ተመስርቶ ነው? ከትናንት የተሻለ ነገር ሳንሰራ ትናንትን መውቀሱም ሆነ፤ ያለ በቂ ማስረጃ የትናንትን መልካምነት ማወደስ መጃጃል እንዳይሆን መጠንቀቅ ያስፈልጋል። ትናንት ላይ ሆነን ከዛሬ የሚሻል ታሪክ ሳይኖረን ዛሬን ማንኳሰስ የሚጠቅም ትርጉም የለውም። በዚህ ዝግጅት ውስጥ በዋናነት የአስተሳሰብ መዛባት በተያያዥነት ጥንቃቄ የጎደለው የቃላት አጠቃቀም የማይፈለግ ዋጋ እንደሚያስከፍሉ እንዳስሳለን።
መልካምም ሆነ መጥፎ ነገሮች በቃላት፤ በሐረግ፤ በአረፍተ-ነገርና በሐሳብ ይገለጻሉ። ስለምናስብ ሐሳብ አለን። ያለንንና የሚኖረንን ሐሳብ በተለያዩ መንገዶች እንገልጻለን። እውነትን የሚገልጹ ወይም የሚሸፍኑ ሃሳቦች አሉ። ማደናገሪያ ሆነው በመሣሪያነት የሚያገለግሉም እንዲሁ። እኛ ኢትዮጵያውያን የብዙ ጉዳት ሰለባ የሆንነው ባብዛኛው ከቃላት ወይም ከቋንቋ አጠቃቀም ጉድለትና ከሃሳብ መዛባት ነው። ሰዎች የቃላትን፤ የሐረጎችንና የሐሳቦች ትርጉምና መልዕክት በውል አውቀውና አሳውቀው የማይጠቀሙ ወይም ሆን ብለው በማውገርገር የሚጠቀሙ መሆናቸው አንድ ችግር ነው። የአንዳንድ ቃላት ትርጉም ከሚገባው በላይ የሚለጠጥ ሲሆን የሌሎቹ ደግሞ ከሚገባው በታች የሚጨመቅ ነው። ትርጉም ወይም መልዕክት ያላቸው የሚመስሉ ነገር ግን ተበትነው ሲፈተሹ የተባለውን መልዕክት የማይዙ ሃሳቦችን መጠቀም ሌላው ችግር ነው።
በተለይ በሀገራችን ፖለቲካዊና ማህበራዊ ሕይወት ውስጥ የሚፈጠሩ ችግሮች መሠረታዊ ምንጭ የተሳሳተ የቋንቋ አጠቃቀምና የሃሳብ መዛባት ነው። ለምሳሌ ያህል ፖለቲከኞች ቋንቋንና ሃሳብን እንዴት እንደሚጠቀሙ እንይ። እንደ ፍላጎታቸውና ዓላማቸው አንዳንድ ቃላትንና ሐረጎችን በመምረጥ ተቀናቃኞቻቸውን የሚያሸማቅቁበትና የሚያደናግሩበት፤ የሚከፋፍሉበትና ከሕዝብ በመነጠል አቅም የሚያሳጡበት መሣሪያ ያደርጓቸዋል። ደጋፊዎችን ለመሰብሰብና ተቀናቃኞችን ለማዳከም ካገለገሉ ቃላት መካከል ጥቂቶችን ለአብነት እንጥቀስ። ገንጣይ፣ አስገንጣይ፣ ቀይ ሽብር፣ ነጭ ሽብር፣ ወንበዴ፣ ሽፍታ፣ ነውጠኛ፣ ጠባብ፣ ትምክሕተኛ የሚሉ ቃላት አሉታዊ ትርጉም አላቸው። እነዚህ ቃላትና ሐረጎች ባብዛኛው ለሀገር፤ ለመብትና ለነፃነት የሚሟገቱ ዜጎችን ለማዳከም አገልግለዋል።
በኢትዮጵያ ውስጥ ተዘውትረው ከተሰሙ አንገት ማስደፊያ፤ የፍርሃትና የሥጋት ድባብ መፍጠሪያ ቃላት መካከል ጠባብነትና ትምክህት በማስረጃነት ሊጠቀሱ ይችላሉ። የትምክህት መንፈስ የነበራቸው ሰዎች ተቃዋሚዎቻቸውን ጠባቦች ይሏቸዋል። የጠባብ ስሜት የሚሰማቸው በበኩላቸው ተቀናቃኞቻቸውን ትምክህተኞች ብለው ይፈርጇቸዋል። ፍረጃው በበቂ ምክንያትና ማስረጃ የተደገፈ አይደለም። ሁለቱም ቃላት ባላቸው አሉታዊ መልዕክት የሕዝቦችን ማህበራዊ ጉዳይና ሰላማዊ ሕይወት አጠልሽተዋል። ምንም ነገር የማይወክሉ ባዶ ቃላት አንዳንድ ጊዜ ከጥይትና ከቦምብ የበለጠ አደገኞች ሲሆኑ አይተናል። የአስተሳሰብ ምክንያታዊ አቅም ደካማ በሆነበት ኅብረተሰብ ውስጥ ምንም ትርጉም ሳይኖራቸው ሰዎችን ማፋጀት የቻሉና የሚችሉ ቃላትና አስተሳሰቦች ብዙ ናቸው።
የኢትዮጵያውያን ችግሮች በዋናነት የሚመነጩት ከአስተሳሰብ ነው። እጅግ ግዙፍ የሆነ የአስተሳሰብ ድህነት አለብን። ቋንቋን ራሱ በአግባቡ መጠቀም እንዳንችል የሚያደርገን እርሱ ነው። መለያችንና መገለጫችን የሆኑ እንደ ኢትዮጵያዊነት፤ አንድነት፤ ብዝሃነት (ልዩነት) ያሉ ቃላት ራሳቸው በተዛባ መንገድ ጥቅም ላይ ውለው የችግሮች መንስኤ ሆነው ቆይተዋል። አስተሳሰብ ችግር መሆን የማይገባውን ነገር ችግር ሊያደርገው ይችላል፤ ችግር መሆን የሚችለውን ደግሞ ማምከን ይችላል። በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ችግር መሆን የማይገባቸው ነገሮች ሁሉ በአስተሳሰብ ድህነት ምክንያት ሀገርንና ሕዝብን ለትርምስ ዳርገዋል። በተለይ የተማሩና ያልተማሩ ልሂቃን ዘመናዊ በሚመስል ነገር ግን ፊውዳላዊ በሆነ አስተሳሰብና እምነት ዛሬም የኢትዮጵያን ሕዝብ ግንኙነት በመመረዝ መተማመንና መፈቃቀድ፤ መከባበርና መፈላለግ በሚፈለገው መጠን እንዳይዳብር እያደረጉ ነው።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የጥንት መልካምነታችንንና ትልቅነታችንን የሚያወድሱና ወደዚያው መልካምነት መመለስ እንዳለብን የሚያወሱ ንግግሮችን እንሰማለን። ወደ ድሮ ፍቅራችን እንመለስ የሚሉ አባባሎችና ንግግሮች ይደመጣሉ። ይህ ችግሮች ከመቼውም ጊዜ በላይ ዛሬ የተወሳሰቡት የትናንት ዓይነት አስተሳሰብ፤ አመራር፤ አሠራርና አኗኗር በመታጣቱ ነው የሚል አንደምታ አለው። መልካምነትንና ፍቅርን መፈለጋችንና መናፈቃችን መልካም ነገር ሆኖ እነዚህን ከትናንት ማንነታችን መቅዳት እንደምንችል መታሰቡ ግን የሚያዘናጋ ይመስላል። ለመሆኑ ለዛሬ ሞዴል መሆን የሚችል መልካምነትና ፍቅር ነበረን ወይ? በየትኛው ጊዜ፣ በማን ዘመነ-መንግሥት፣ ያን ገናና መልካምነትን ማን አጠፋው፣ ያን ደማቅ የሕዝቦች ፍቅር ማን አመከነው?ለምን? መልካምነትም ሆነ መጥፎነት የሰው ልጅ እንቅስቃሴ ውጤት ነው። ሁለቱም የማይለያዩ ቢሆንም አንዱ ገንኖ የሚወጣው ሌላኛው ሲዳከም ነው። የአንዱን መኖር መረዳት የሚቻለው በሌላው መኖር ነው። መልካምነት የሚጎለብተው መጥፎነት ሲዳከም ወይም ሲወገድ ወይም ለሁሉም ተስማሚ የሆኑ እሴቶች ተኮትኩተው ሲለሙ ነው።
መልካምነት በትናንትናችን ውስጥ በሚፈለገው መልክ አልነበረም ቢባል መሳሳት ይሆን? ትናንት ከነበረንና ዛሬ አለመኖሩ ከተረጋገጠ አንድም ጭራሽ አልነበረም፤ አሊያም ጠፍቷል ማለት ነው። የጠፋውን የትናንት መልካምነት ለመፈለግ የምናባክነው ጊዜና ጉልበት መኖር የለበትም። ይልቁንም ለዛሬያችን የሚመጥን መልካምነት ለማምጣት መስራት ነው። የተባለው ራሱ እውነት ቢሆን በጊዜው የነበረ ነገር ግን ዛሬ የሌለ ነው። ራሱንና ጊዜውን ሆኖ ያለፈ ታሪክ ነው። ስለዚህ ዛሬ እጅግ ሊያሳስበንና ሊያነጋግረን የሚገባው የዛሬና የነገ ጉዳያችን ነው። ከትናንት የሚወሰዱ መልካም ነገሮችና የማይወሰዱ መጥፎ ነገሮች አሉ። ዛሬ ከትናንት የተሻለ የሚሆነው ይህ ሲሆን ብቻ ነው። ዛሬ የሚፈጠሩ መልካም ነገሮች የበለጠ ጉልበት አላቸው – ጊዜውን የሚዋጁ ናቸውና። ይህ ትናንትን በመናፈቅ የሚሆን ሳይሆን በቁርጠኝነት ዛሬ ውስጥ በመስራትና በመሆን የሚገኝ ነው።
ትናንት ሰላም፤ ፍቅር፤ እፎይታ፤ ደስታ፤ መተማመንና መፈቃቀድ ነበር? ምን ያህል ሰው ወይም ሕዝብ ነው ያለ ሥጋት፤ ፍርሃትና ጭንቀት ይኖር የነበረው? ምቾት፤ ቅልጥፍና፤ ውጤታማነት፤ ፍትሃዊነትና ሕጋዊነትን ያሰፈነ ሥርዓት ነበር? እንዲህ ዓይነት ሥርዓት በሌለበት ትናንት የኖረ ሰው እንዴት ብሎ ትናንትን የኋሊት ይመኛል? ትናንትን የማያውቁ ዜጎች ይኖራሉ። ትናንት ከዛሬ የተሻለ ይሁን አይሁን መመስከር ሊቸግራቸው ይችላል። ትናንትን የሚያውቁ ዜጎችም አሉ። ስለሚያውቁት ትናንት መመስከር ይችላሉ። የሚመሰክሩት ግን ለራሳቸው በኖሩት ልክ ወይም ሀገርና ሕዝብ በነበራቸው ሕይወትና ዕድገት አንጻር ሊሆን ይችላል።
ከግል ሕይወትና ልምድ አኳያ ከሆነ ደልቶት የኖረውና ያልኖረው እኩል ይመሰክራሉ ተብሎ አይታሰብም። ከሀገርና ከአጠቃላይ ሕዝብ ልማትና ሕይወት ዓይን ከታየ ግን ትናንት በምንም መለኪያ ከዛሬው የተሻለ አይደለም። ለዚህ ብዙዎቻችን የዓይን ምስክሮች ነን። ከዚያም በላይ ዛሬ ሀገራችንና ሕዝባችን ያሉበት ሁኔታ ራሱ ትናንት የተሻለ መሆኑን አያሳይም። አሉብን የምንላቸው ፖለቲካዊ፤ ኢኮኖሚያዊ፤ ማሕበራዊና ባሕላዊ ችግሮች ባብዛኛው ዛሬ የተፈጠሩ አይደሉም። ይልቁንም ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲተላለፉ የቆዩ ናቸው። ስለዚህ ትናንት ይሻላል በሚል እያላዘንን መቼም ቢሆን ተመልሰው የማይመጡትን ሥርዓቶች መናፈቅ አይጠቅምም። በባዶ ትርክት መንፈሳችንን ባናዳክምም መልካም ነው።
ሌሎች ወገኖች ደግሞ ትናንትን በዜሮ ያባዛሉ። በእነዚህ ወገኖች እምነት እጅግ ብዙ ግፍና በደሎች በኢትዮጵያና በኢትዮጵያውያን ላይ ተፈጽሟል። ስለዚህ ትናንት የሚኮነን እንጂ የሚናፈቅ አይደለም በማለት ይከራከራሉ። እንዲያውም ትናንት እንደተኖረበት ሳይሆን እንዳልተኖረበት መቆጠር አለበት ይላሉ። የዚህ ክርክር ዓላማ ዛሬ ከትናንት የተሻለ ነው ለማለት ነው። በእርግጥ ዛሬ ከትናንት የተሻለ መሆኑ የግድ ነው። ይሁን እንጂ ገዢዎች አባቶቻችንንና ወገኖቻችንን አጣልተው ሳያስታርቁ አለፉ። የተፈጠረውን ቂምና ጥላቻ እንደመልካም ነገር ለእኛ አስተላለፈው ሄዱ። እኛም የቂምና ጥላቻ መንፈስን እንደ በጎ ነገር ተረክበን ደምረንና ደማምረን ሀገራችንን የችግሮች ሁሉ ማማ አደረግናት። አሁን ያለነው በዚህ መልክ ነው። ስለዚህ የት ጋ ነው ዛሬ ከትናንት የሚሻለው ብሎ መጠየቅ ያስፈልጋል።
ሁለቱም አስተሳሰቦች ችግሮች አሏቸው። የነገሮችን ተያያዢነት አልተገነዘቡም። በዛሬ ውስጥ ትናንት፤ በትናንት ውስጥ ዛሬ መኖሩን ማየት አልቻሉም ወይም አልፈቀዱም። ዛሬ ብዙዎቻችን መያዝ ያለብንን ስብእና አልያዝንም፤ መሆን የሚገባንን ያህል አልሆንም። ኢትዮጵያ ራሷ መሆን የሚገባትን ኢትዮጵያ አልሆነችም። ኢትዮጵያውያን በዜግነታቸው መሸማቀቅ እንጂ መኩራት አልቻሉም። መሆን የሚገባው ሁሉ ያልሆነውና መሆን የማይገባው ሁሉ የሆነው እኛ የሚገባውን ትተን የማይገባውን በመፈጸማችን ነው። ስለዚህ በትናንት ዛሬን መኮነን፤ በዛሬ ትናንትን ማጣጣል ስሕተት ነው።
ትናንትና እና ዛሬ አይነጣጠሉም። አንዱ ሌላውን ባይሆንም አንዱ ያለ ሌላው አይኖርም። አንዱ ሌላውን ባይተካም አንዱ ከሌላው ውጪ አይደለም። ትናንት በዛሬ ውስጥ አለ- በሁለት መልኮች። አንዱ መልክ በጎ ሲሆን ሌላው መጥፎ ነው። መልካሙ የሚወሰድ ሲሆን መጥፎው የሚወገድ ነው። ዛሬም በትናንት ውስጥ አለ – የተፀነሰውና የበቀለው ከእርሱ ነው። መልካምም ሆነ መጥፎ አለበት – ከትናንት የተወረሰ ወይም ከዛሬ የተገኘ። ወደኋላ እያየን ወደፊት ለመራመድ ማሰብ፤ ወደፊት እያየን ወደኋላ መጓዝ አያዋጣም።
ከትናንት የወሰድናቸው መጥፎ ነገሮች ዛሬ ከፈጠርናቸው ጋር ተደምረው ትርጉም ያለው ዕድገት እንዳናመጣ አድርገውናል። በእኛ ሀገር እንደ ልብ የሚያድገው ችግር ነው፤ የሚቀጭጨው ልማት ነው። ልክ እንደ ትናንት ዛሬም እየቀጨጭን ነው፤ ልክ እንደ ዛሬ ትናንትም ቀጫጫ ነበርን። አዳዲስ ችግሮችን ከመፍጠር አልታቀብንም። እንደ አዲስ ከተፈጠሩት ችግሮች መካከል ሙስናን እንደ አንድ ማስረጃ መውሰድ ይቻላል። ሙስና በዘመናችን ከተፈጠሩ ግዙፍ ችግሮች አንዱ ነው። እጅግ ውስን ቢሆንም በሀገራችን ድሮም ነበር። ያኔ ጉቦ በመባል ይታወቃል። ሁለት ሲበዛ ደግሞ ከሦስት አኃዝ በላይ ያልሆነ ብር የሚከፈልበት ነበር።
ዛሬ ግን ሀገርንና ሕዝብን ለከፍተኛ አደጋ ማጋለጥ የሚያስችል ጉልበት አግኝቷል። በጥቂት ዓመታት ውስጥ ሰማይ ጠቀስ ፎቆችን መስራት የሚያስችል አቅም ያፈሩ የመንግሥት ባለሥልጣናት ተፈጥረዋል። ሕግና መንግሥት የሚያውቁት የገቢ ምንጭ ሳይኖራቸው የበርካታ ተሽከርካሪዎች ባለቤት መሆን የቻሉ ወገኖች ዛሬ አፍርተናል። በሕግና በኅብረተሰብ የሚታወቅ ሥራ ሳይኖራቸው ሚሊየነሮች የሆኑ ዜጎች አሉ። ምንጩ ያልታወቀ ብዙ ገቢ ያላቸው ሰዎች እንዳሉ ይታሰባል። በሕዝብ መካከል ከፍተኛ የገቢ ልዩነት በአጭር ጊዜ ውስጥ ተፈጥሯል። ሕሊናቸውን የማይፈሩ ሙሰኞች፤ ለጥቅማቸው ሀገርንና ሕዝብን ለድርድር የሚያቀርቡ ሹማምንቶች በዘመናችን ተፈጥረዋል። ሰፋፊ ፕሮጀክቶች የተከፈቱት የመንግሥት ወኪሎች እንደሚነግሩን የሀገርና የሕዝብ ድህነት በፈጠረው ቁጭት በመነሳሳት ሳይሆን ሰፋፊ የሙስና በሮችን በጊዜው ለነበሩ ባለሥልጣኖች ለመፍጠር ሲባል እንደሆነ ማስረጃዎች ያመለክታሉ።
አሁንም ያለነው በተመሳሳይ ሁኔታ ውስጥ ነን። ዛሬም እንደ ትናንቱ በዚያው የጭቆናና የአፈና ዓለም ውስጥ እየተደፋፈቅን ነው። ተመሳሳይ የታሪክ ምዕራፍ እየጻፍንና እያነበብን ነው። ከድሮዎች የምንሻለው ዘመናዊ ቃላትና መሣሪያ በመጠቀማችን ነው። በአስተሳሰብ ከቀደምቶቻችን እናንስ እንደሆን እንጂ አንበልጥም። እነርሱ የሳይንስና የቴክኖሎጂ አቅም ባልነበረበት የታሪክ ዕድገት ላይ ሆነው ለሰሩት ስህተት በእጅጉ እንኮንናቸዋለን። የተሻለ ሥራ ሳንሰራ ትናንትን መኮነን መደበኛ ሥራችን አድርገናል። ይህ ብልጠት ቢመስልም ጅልነት መሆኑን አለመረዳት ደግሞ ድርብ ጅልነት ነው። ዛሬ ላይ ሆነን የቀደምቶችን ስሕተት ለማረም የምንሞክረው አዋጭ በሆኑ አዳዲስ አስተሳሰቦች ሳይሆን ባረጁ አስተሳሰቦች አዳዲስ ስሕተቶች በመፍጠር ነው።
በኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ ተናጋሪ አለ። ብዙ አድማጭም አለ። ቁምነገሩ ከተነገረውና ከተደመጠው ምን ያህሉ ወደ መሬት ወርዷል የሚለው ነው። መሬት ወርደው ጥያቄን የመለሱና ችግርን የፈቱ ንግግሮች ብዙ አይደሉም። አሁን የሚያነታርኩን ነገሮችና ክፋቶች ዛሬ ብቻ የተፈጠሩ አይደሉም። ክፋቶችና ስሕተቶች በጊዜያቸው ስላልታረሙ እየተደመሩና እየተባዙ ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተንከባለሉ ተረኛ ለሆነው ለዛሬው ትውልድ ደርሰውታል። አሁን ኳሷ በእኛ እጅና አእምሮ ውስጥ ነች። ታሪካዊ ሕፀፆቻችን በሐሳብ ወደኋላና ወደፊት በመወርወር ትውልድን ማዘናጋት አይጠበቅብንም። ሕፀፆች ትናንትም ይፈጠሩ ዛሬ መታረም አለባቸው። ዋናው ጉዳይ በዛሬ ውስጥ ሆኖ ትናንትን ብቸኛ ተወቃሽ ማድረግም ሆነ ትናንትን በማወደስ ዛሬን ተወጋዥ ማድረግ ሳይሆን በሁለቱም ውስጥ መልካምነትም ሆነ መጥፎነት የነበሩና ያሉ መሆናቸውን በትክክል መረዳት ነው። በትናንትም ሆነ በዛሬ ውስጥ መጥፎነት የነበረውና ያለው ጉልበት መልካምነት ከነበረውና ካለው የበለጠ መሆኑን መገንዘብ ነው።
በአስተሳሰብ ድህነት ምክንያት ከሴራ ፖለቲካና ሽኩቻ ነፃ አይደለንም። ፖለቲካችን ልክ እንደ ትናንቱ ዛሬም በአዳዲስ ቋንቋ የቆሸሸ አስተሳሰብ ይገፋል። አሮጌ አስተሳሰቦች የፈጠሯቸው ችግሮች እንዳሉ ሆነው አዳዲስ ችግሮች እየተፈጠሩ ነው። አንድ ግልጽ መሆን ያለበት ሀቅ ግን አለ። ካሁን በኋላ በኢትዮጵያ ምድር በቂምና በጥላቻ ማንም አያሸንፍም። ጥላቻን በማግዘፍ ማንም ምንንም አያተርፍም። ሁለት ምርጫዎች ብቻ ቀርተውናል – በክፋት መጠፋፋት ወይም በፍቅርና በእውነት መተቃቀፍ። የኢትዮጵያ ልጆች ቂምና ጥላቻን መረዳት በቻለው አእምሯቸው ለምንድነው ስለ እርቅና ይቅርታ የማያስቡት፤ የማይሰብኩት፤ የማይሟገቱት? ለምንድነው ብዙ ነገራችን በማይጠቅምና በሚጎዳ ጉዳይ ላይ የሚባክነው?
ማገናዘብ ከሚችልና ምክንያታዊ ከሆነ አእምሮ ቂምና ጥላቻ መውጣት አልነበረባቸውም። ጥላቻን የሚያስብና የሚሰብክ አእምሮ ጤነኛ አይደለም። ከጤናማ አእምሮ የሚመነጨው ጤናማ፤ ሚዛናዊና ምክንያታዊ አስተሳሰብ ነው። ለበጎ ከሆነ ከአሁን ወዲያ የሚያዋጣው አንድ ነገር ብቻ ነው። ሁሉም ባንድ ገዢ ሐሳብ ስር ተሰባስቦ፤ በቁመቱ ልክ ተሰልፎ፤ በአስተዋጽኦ መጠን እውቅና ተሰጥቶት መኖርና ማደግ የሚያስችል ሥርዓት መፍጠር ብቻ ነው። ስሕተቶች በሆነ የታሪክ አጋጣሚ ሊከሰቱ ይችላሉ። ማብቂያ የሌላቸው ሸክምና ዕዳ መሆን ግን የለባቸውም። ሀገርም ሆነ ሕዝብ የሚበለፅጉት መሪ የሆነው አስተሳሰብን ሲያበለጽጉ ብቻ ነው። ይህ ይሆን ዘንድ ያለመታከት መስራት ነው።
ሰላም!
አዲስ ዘመን አርብ የካቲት 20/2012
ጠና ደዎ (ፒኤችዲ)፣አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ