በተለያዩ የዓለም አገራት የህብረተሰብ መሠረት የሆነው ቤተሰብ የሚመሰረተው በተለያየ መልኩ ቢሆንም ዋናው ግን የህብረተሰቡ አካል የሆኑት ሰዎች (ወንድ እና ሴት) በሚፈፅሙት ጋብቻ ነው። ቤተሰብ የህበረተሰቡ ዋና መሰሶ በመሆኑ ትልቅ ቦታና ከበሬታ የሚሰጠውም ነው። ይህ ትልቅ ቦታና ከበሬታ የሚሰጠው የህብረተሰቡ መሠረት የሆነ ተቋም በሕግና ሥርዓት መመራት ይኖርበታል። ለዚህም ሲባል በኢትዮጵያ ቀድሞ የነበረው የቤተሰብ ሕግ እንዲሻሻል ተደርጓል።
ቤተሰብ የህብረተሰብ መነሻ በመሆኑ በህብረተሰቡና በመንግሥት ጥበቃ ሊደረግለት ይገባል። የመንግሥት ጥበቃ የሚገለፀውም የቤተሰብ ግንኙነትን በሕግ በመደንገግ ነው። ይህ ሕግም የህብረተሰብ የዕድገት ደረጃንና ነባራዊ ሁኔታን ከግምት ውስጥ ያስገባ መሆኑ ተቀምጧል። ይህም ሆኖ ዛሬም ድረስ እንደ ግለሰብ ሁለት ጥንዶች ጋብቻ ከመፈፀማቸው በፊት አልያም በጋብቻ ውስጥ እያሉም፤ በአጠቃላይ በህብረተሰቡ ዘንድም መሰረታዊ ስለሆኑት የቤተሰብ ሕጎች በቂ ግንዛቤ አልተያዘም። በመሆኑም በተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ የተሻሩትና የተካተቱት ዋና ዋና ነገሮች ምን እንደሆኑና ምን ፋይዳ እንዳላቸው በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኛና የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ኮርት ማናጀር የሆኑት አቶ ጎሽዬ ዳምጣው እንደሚከተለው አብራርተውልናል።
የቤተሰብ መመስርቻ የሆነው ጋብቻ በህብረተሰቡ ዘንድ ተቀባይነት ኖሮት እንዲዘልቅ ህብረተሰቡ በአወጣው ሕግ መሠረት መመስረትና መመራት ይኖርበታል። በቆይታው ጊዜ የሚፈጠሩት ግንኝነቶችና ውጤቶችም በተመሳሳይ በሕግ መሠረት ከለላ ሊኖራቸው ይገባል። ለምሳሌ ያህል የልጅ አስተዳደግና አስተዳደር፣ በትዳር ውስጥ ስለሚፈጠሩ ንብረቶች፣ ከትዳር በፊት የነበሩ ንብረቶች፣ በባልና ሚስት መሐል ስለሚኖረው ግለሰባዊ ግንኙነቶች፣ ትዳር ውስጥ ሆኖ ማድረግ ስለተከለከሉ ነገሮች እና ወዘተ የመሳሰሉት በሕግ መደንገግ ይኖርባቸዋል።
በተጨማሪም ሰዎች በዚች ምድር ላይ ሲኖሩ መጋጨታቸው ወይም በተለያየ ምክንያት የመሰረቱትን ጋብቻ ሊያፈርሱ እንደሚችሉ ግልጽ ነው። ተጋቢዎች ሕጉን ጠብቀው እንደተጋቡ ሁሉ ፍቺ የግድ ሲሆን ደግሞ ሕጋዊ በሆነ ሁኔታ መፋታት ይኖርባቸዋል። በመሆኑም ሕጉ ጋብቻ የሚፈርስባቸውን ምክንያቶችና ውጤታቸውንም ያስቀመጠ ሲሆን፤ በዚህም መሰረት ተጋቢዎች ፍቺውን በአንዱ ወይም በሁለቱም ተጋቢዎች ጥያቄ በስምምነት ማድረግ ይችላሉ። በዚህ መሰረት የሚከናወን ፍቺም ሕጋዊ ውጤቱ የእኩልነትን መርህ መሠረት አድርጎ መፈፀም ይኖርበታል።
የተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሕገ መንግሥትና ኢትዮጵያ ባፀደቀቻቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶች የተደነገጉትን መሠረታዊ መርሆዎች ታሳቢ ያደረገ ነው። በሐገ መንግሥቱ መሰረት በጋብቻ አፈፃፀም ወቅት፣ በትዳር ጊዜ፤ በቤተሰብ አመራር፣ በንብረት አስተደዳር፣ እንዲሁም በፍች፣ ወንድና ሴት በእኩልነት መታየት እንዳለባቸው ያስቀምጣል። ለህፃናት መብት የተለየ የሕግ ጥበቃና ከለላ መደረግ ያለበት በመሆኑ፣ ለጋብቻ በደረሱ ወንድና ሴት ነፃ ፈቃድ መመስረት እንዳለበት፣ እንዲሁም የቤተሰብ ጉዳዮች በሕግ መሠረት በተቋቋመና ብቃት ባለው ነፃና ገለልተኛ የፍትህ አካል መዳኘት እንዳለባቸው ይደነግጋል።
በመሆኑም የተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ እነዚህን መሰረታዊ ሐሳቦች ከግምት በማስገባት የጋብቻ አፈፃፀም ሥርዓቶችን፤ ጋብቻ ሳይፈፀም እንደባልና ሚስት አብሮ የመኖር ሁኔታዎችንና ህጋዊ ውጤቶችን፤ የቤተሰብ ክርክርና የዳኝነት ሥልጣንን፤ ጋብቻ ስለሚፈርስባቸው ምክንያቶች፤ የጋብቻ፣ የምዝገባና የማስረጃ ሁኔታዎችን ከላይ በዝርዝር የተቀመጡትን ሕገ መንግሥታዊና ዓለም አቀፍ መሠረታዊ መርሆዎችን መሠረት አድርጎ የተዘጋጀ ነው። በዚህም መሰረት ቀድሞ የነበር የቤተሰብ ሕግ የነበሩበትን ክፍተቶች ለማስተካከል፣ የልጆችንና የሴቶችን ሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብት ለማስከበር፤ የተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ በ1952 ዓ.ም ከወጣው የፍትሐብሔር ሕግ ጋር ሲነፃፀር የሚከተሉት መሠረታዊ ነጥቦች አካቶ ይገኛል።
የትዳር አመሠራረትን በተመለከተ፡- መተጫጨት እንደ አስፈላጊነቱ ከጋብቻ በፊት ሊፈፀም የሚችል ስምምነት ሲሆን በቀደመው ሕግ ለትዳር የመተጫጨት ግንኙነት በአብዛኛው ባህልን መሠረት ያደረገ ስለሆነና አፈፃፀሙም ሆነ ውጤቱ ተመሳሳይ ባለመሆኑ በተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ እንዳይካተት ተደርጓል። በኢትዮጵያ በስፋት የሚስተዋለውንና የተለያዩ የሠነ ልቦና፣ የጤናና የማህበራዊ ችግሮች የሚያደርሰውን ያለዕድሜ የሚፈፀም ጋብቻ ለማስቀረት ይቻል ዘንድም ቀድሞ ለሴት አስራ አምስት ዓመት የነበረውን በመሻር ዝቅተኛው የጋብቻ እድሜ ለወንድም ሆነ ለሴት 18 ዓመት እንዲሆን ተደርጓል። ይህ እንደ ተጠበቀ ሆኖ ለጋብቻ ከተወሰነው እድሜ መቀነስን በተመለከተ የፍትህ ሚኒስቴር (ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ) በተቀመጡት መስፈርቶች መሰረት ከሁለት ዓመት ላልበለጠ ጊዜ ለመቀነስ መፍቀድ የሚችልበት እድል እንዳለውም ተደንግጓል።
ከዚሁ ጋር ተያይዞም ወንድም ሆነ ሴት በጋብቻ አፈፃፀም በጋብቻ ዘመንም ሆነ በፍች ጊዜ እኩል መብት ያላቸው ስለመሆኑ በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 35 ላይ ተደንግጓል። በመሆኑም ከዚህ በፊት በነበረው በፍትሐ ብሔር ሕጉ የወንድን የበላይነት የሚያንፀባርቁ አድሏዊ ድንጋጌዎች ተሻሽለው የተጋቢዎች ግላዊ፤ ማህበራዊና የንብረት ግንኙነት የእኩልነትን መርህ በሚያስጠብቅ አኳኋን እንዲፈፀሙ ተደንግጓል። ከእነዚህም መካከል ለፍች ከባድ ወይንም ቀላል የሚለው ምክንያት የቀረ ሲሆን ጥንዶቹ አብረው ለመቀጠል ፈቃደኛ እስካልሆኑ ድረስ ፍቺ መፈፀም የሚችሉ ይሆናል። ከዚሁ ጋር በተያያዘ ፍች በመፈፀም ይጣል የነበረውም ቅጣት እንዲሰረዝ የተደረገ ሲሆን ፍች በቤተዘመድና ሽምግልና ጉባኤ መወሰኑ እንዲቀርም ሆኗል። ረጅም ጊዜ በመውሰድ አሰልቺና ለብዙ ወጪ ይዳርግ የነበረው የፍች ውሳኔ አካሄድም ለባለጉዳዮች በተለይም ለሴቶች ከአቅም በላይ በመሆኑ የጀመሩትን የፍርድ ሂደት ሳይቋጩ እንዲቀሩ ያደርጋቸው ነበር። በተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ ግን ይህንን በመገንዘብ ጉዳዩ በአራት ወራት የሚያልቅበት ሁኔታ ተመቻችቷል።
ተጋቢዎች በመካከላቸው አለመስማማት ተፈጥሮ ያላቸውን ግንኙነት ለማቋረጥ ቢፈልጉ ፍቺውን ተከትሎ በፍርድ ቤት ለሚወሰኑ ውሳኔዎች በቂ ማስረጃ ሊኖር ይገባል። ለዚህም በጋብቻ ግንኙነት ላይ ሊነሱ የሚችሉ አወዛጋቢ የማስረጃ ክርክሮችን ለማስወገድ ብሎም ለማህበራዊና ለኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች የሚኖረውን ጠቀሜታ ለመገንዘብ የምዝገባ ሥርዓት ተቋቁሞ በየትኛውም የጋብቻ አፈፃፀም ሥርዓት የተፈፀመ ጋብቻ በክብር መዝገብ ሹም መመዝገብ እንደሚኖርበት ተደንግጓል። ጋብቻ በተጋቢዎች ነፃ ፍቃድና ፍላጎት የሚመሠረት ግላዊ ግንኙነት ከመሆኑ አንፃር አብረው መኖር የማይችሉ ባልና ሚስት የፍች ጥያቄ ለፍርድቤት በማቅረብ በስምምነት መለያየት የሚችሉ መሆናቸውን የሚያረጋግጡ ድንጋጌዎችን አካቷል። ባልና ሚስቱ በአለመግባባት የተነሣ አብረው በአንድ ቤት ውስጥ መኖር ካልቻሉ ፍርድ ቤቱ ማን ከቤት ቢወጣ ይሻላል የሚለውን መረጃ በመሰብሰብ አጣርቶ አንደኛውን ወገን ከቤት ሊያስወጣ የሚችልበት ፈቃድ ተሰጥቶታል።
በፍቺ ወቅት የሚወሰን የንብረት ክፍፍልንም በተመለከተ በነባሩ የቤተሰብ ሕግ የጋራ ንብረትን በተመለከተ አንደኛው ወገን የአጋሩን ስምምነት ሳይጠብቅ ለሌላ ወገን ቢሸጥ ወይንም አስተላልፎ ቢገኝ ሽያጩ ወይም ስምምነቱ በፍርድ ቤት ሊፈርስ እንደሚችል አልተደነገገም ነበር። በተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ ላይ የጋራ ንብረትን በተመለከተ በአንደኛው ወገን ፍላጎት ለሦስተኛ ወገን ሊተላለፍ እንደማይችል እና ተላልፎም ከተገኘ ስምምነቱ በፍርድ ቤት ሊፈርስ የሚችል መሆኑን ተደንግጓል።
ከጋብቻ ወጭ በሚፈፀም የግብረ ሥጋ ግንኙነትና እንደ ባልና ሚስት አብሮ በመኖር በግልም ሆነ በጋራ ጥረት የጋራ ሀብት የሚፈጥሩ በመሆኑ ግንኙነቱ ሲቋረጥም ላፈሩት ንብረት የጋራ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ይደነግጋል። ከጋብቻ ጋር በተያያዙ የሚነሱ የቤተሰብ ክርክሮች በመደበኛ የዳኝነት ሥርዓት ሊታዩና ሚዛናዊ የሆነ ውሳኔ ሊሰጥባቸው የሚገባ የመብት ጥያቄዎች በመሆናቸው በመደበኛ ፍርድ ቤት ይታያሉ። የቤተዘመድ ሽምግልና ጉባኤ ሚና በእርቅ ላይ ብቻ እንዲያተኩር ተደርጓል። የመኖሪያ ቦታን በተመለከተ ባልና ሚስት በጋራ የመምረጥ (የመወሰን) መብት ተጠብቋል።
ህፃናትን የሚመለከቱ ጉዳዩችን በተመለከተ በቅድሚያ ለደህንነታቸው ትኩርት መደረግ እንደለበት የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 36 (2) ላይ ተደንግጓል። በሌላ በኩል የልጅ አስተዳደግን በተመለከተ በነባሩ ሕግ ልጁ (ልጅቷ) አምስት ዓመት ካልሞላው (ካልሞላት) ከእናቱ (ከእናቷ) ብቻ እንድትሆን ያደርግ ነበር:: ነገር ግን ከእናት ጋር መሆኗ በትክክል የልጁን አልያም የልጅቷን ደህንነት ያረጋግጣል ለማለት አያስችልም። በመሆኑም በሚደረገው ማጣራት መሰረት የልጆቹን አጠቃላይ ተጠቃሚነት ከግምት በማስገባት ከማን ጋር እንደሚኖሩ በፍርድ ቤቱ የሚወሰን ይሆናል። በተጨማሪ ከቤተሰብ ውጭ ያሉ ልጆችንም ደህንነት ማስጠበቅ ስለሚገባ በሀገርም ውስጥ ሆነ ከአገር ውጭ የሚደረግ ጉድፈቻ የልጆችን የዘለቄታ ደህንነትና ጥቅም በተሟላ ደረጃ ለማስጠበቅና ለማረጋገጥ የሚያስችል ስለመሆኑ ሕገ-መንግሥቱንና ተቀባይነት ያላቸውን ዓለም አቀፍ ድንጋጌዎችን መሰረት ያደረጉ ድንጋጌዎች ተካተዋል።
ዛሬ ዛሬ በርካታ ኢትዮጵያውያን በተለያዩ ጉዳዮች ከአገር ውጭ እንደሚኖሩ ይታወቃል። በዚህ ረገድ በነባሩ ሕግ በውጭ አገር ስለሚፈፀም ጋብቻ ያስቀመጠው ነገር አልነበረም። በተሻሻለው የቤታሰብ ሕግ ከኢትዮጵያ ውጭ የተፈፀመ ጋብቻ በተፈፀመበት የጋብቻ አፈፃፀም ሕግ መሠረት በኢትዮጵያ የህዝብን ሞራል እስከልተቃረነ ድረስ በተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ እንዲገዛ ሆኗል። ይህም ኢትዮጵያውያን ተጋቢዎች ባሉበት አገር ሆነው የሚመሰርቱት ትዳር በሀገሪቷ ሕግም ተቀባይነት እንዲኖረው የሚያደርግ ነው። በጋብቻ አብሮ ስለመቆየት የተለያዩ መረጃዎች መቅረብ የሚችሉ ቢሆንም በነባሩ የቤተሰብ ሕግ ስለጋብቻ ምስክር ወረቀት ስለማቅረብ የሚለው ነገር የለም። በተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ ላይ የጋብቻ የምስክር ወረቀት አይነተኛ ማስረጃ ሆኖ ቀርቧል። በመሆኑም በየትኛውም ሁኔታ የሚደረግ ጋብቻ የምስክር ወረቀት ያለው ከሆነ ጋብቻውን ተከትሎ ለሚፈጠሩ የፍርድ ቤት ጉዳዮች እንግልትን የሚቀንስ ይሆናል።
በነባሩ የቤተሰብ ሕግ የጋብቻ ውልና የጋብቻ ጽሁፍ ጽንሰ ሐሳቦች እየተምታቱ አንዳንድ ጊዜም አንድ አይነት ተደርገው እየተወሰዱ ውሳኔ ይሰጥ ነበር። በተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ የጋብቻ ጽሁፍ በሚል የተቀመጠውን ከሕጉ ውስጥ በማውጣት በጋብቻ ምስክር ወረቀት እንዲተካ በማድረግ የጋብቻ ውል በነበረበት ሁኔታ እንዲቀመጥ ተደርጓል። ይኸውም የጋብቻ ምስክር ወረቀት የጋብቻ ሥርዓቱ ከተፈፀመ በኋላ ወይም ሲመዘገብ ጋብቻ ስለመፈፀሙ ለማረጋገጥ በክብር መዝገብ ሹም የሚሰጥ ሲሆን የጋብቻ ውል ተጋቢዎቹ የንብረት ግንኙነታቸውን አልፎ አልፎም ግላዊ ግንኙነታቸውን አስመልክተው የሚፈራረሙት ሰነድ ነው።
ከትዳር መስራች ጥንዶች መካከል አንዱ ስለትዳር አጋሩ በቂ መረጃ ሳይኖረው ወይንም ማወቅ የነበረበትን ሳያውቅ ወደ ትዳር የገባ እንደሆነ ነገሩን ባወቀ ጊዜ ትዳሩን ለማፍረስ የሚችልባቸው ሁኔታዎች አሉ። እነዚህ ሁኔታዎች በነባሩ የቤተሰብ ሕግ ጋብቻ በዋና መሳሳት (መፈፀም ያልነበረበት) ተደርጓል ተብሎ ሊወሰድ የሚችለው። በሚያገባው ሰው ሃይማኖት መሳሳትና የሥጋ ደዌ የያዘውን ወይም የሩካቤ ሥጋ ግንኙነት ለመፈፀም ከማይችል ሰው ጋር ጋብቻ ከተፈፀመ ነበር። በተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ ላይ ግን መሠረታዊ ስህተት የሚባለው ከቀዳሚው ሰፋ ያለ ሐሳብ በመያዝ ሊድን የማይችል (ለተወላጅ ሊተላለፍ የሚችል በሽታ) ያለበት መሆኑ የታወቀ እንደሆነ፤ የሩካቤ ሥጋ መፈፀም የማይችል የሆነ እንደሆነ፤ ከተመሳሳይ ፆታ ጋር የግብረ ሥጋ ግንኙነት የመፈፀም ልምድ ያለው እንደሆነ ሲረጋገጥ መሆኑን ደንግጓል።
ከላይ በተጠቀሱትም ሆነ ሌሎች ምክንያቶች በድሮው የቤተሰብ ሕግ ጋብቻን ለመቃወም የሚችሉት የቤተዘመድ እንደራሴ፤ አካለመጠን ያላደረሰው ልጅ፤ ወይም ዓቃቤ ሕግ ብቻ ነበሩ። በተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ ላይ ግን ጋብቻን ለመቃወም የሚችሉትን በተመለከተ የዓቃቤ ሕግ ሚና እንደተጠበቀ ሆኖ ማንኛውም ያገባኛል የሚል ወገን ተቃውሞ ሊያቀርብ እንደሚችል ተደንግጓል። በነበሩ ሕግ ጋብቻ እንዳይፈፀም የሚቀርብ ተቃውሞ የጋብቻው በዓል እስከሚከበር ባለው ጊዜ ውስጥ በማንኛውም መንገድ ሊቀርብ እንደሚችል ተደንግጓል። በተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ ላይ የጋብቻው ተቃውሞ በጽሁፍ ሆኖ ጋብቻው ከመፈፀሙ ከአስራ አምስት ቀን በፊት መቅረብ እንዳለበት ተደንግጓል። በነባሩ የቤተሰብ ሕግ ጋብቻ እንዳይፈፀም በተሰጠ ውሳኔ ላይ ይግባኝ ማቅረብ እንደሚቻል አልተደነገገም። በተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ ላይ ጋብቻ እንዳይፈፀም በተሰጠ ውሳኔ ላይ ይግባኝ ማቅረብ እንደሚቻል ተደንግጓል። ከዚሁ ጋር በተያያዘ በነባሩ ሕግ ጋብቻ እንዳይፈፀም የሚቀርብ ተቃውሞ የጋብቻው በዓል እስከሚከበር ባለው ጊዜ ውስጥ በማንኛውም መንገድ ሊቀርብ እንደሚችል ተደንግጓል። በተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ ላይ ከቀድሞ ወይም ከፈታችው ባሏ ጋር የምትጋባ ከሆነ ወይም ነፍሰጡር አለመሆኗ ከተረጋገጠ በብቸኝነት ለመኖር የተወሰነውን ጊዜ ሳትጠብቅ ጋብቻ ለመፈፀም እንደምትችል ተደንግጓል።
በነባሩ የቤተሰብ ሕግ ጋብቻ ፈጽመው ስድስት ወር ያልሞላቸው ተጋቢዎች በስምምነት ለመፋታት እንደማይችሉ አልተደነገገም ነበር። በተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ ላይ ተጋቢዎቹ የባህሪ ትውውቅ ለማድርግም ሆነ ችግሮቻቸውን በስምምነት ለማስወገድ የተወሰነ ጊዜ ያስፈልጋቸዋል ተብሎ ስለሚገመት በስድስት ወራት ጊዜ ውስጥ በስምምነት ፍች እንዲፈጽሙ አልተፈቀደም።
ዳኛ ጎሽዬ ጨምረው እንደተናገሩት፤ ቤተሰብን መጠበቅ የሕግ ብቻ ሳይሆን የማህበረሰቡም ጭምር ነወ፡፡ ቤተሰብ የአንድ ማኅበረሰብ በጣም ጠቃሚ እና መሠረት የሆነ አካል ነው። ቤተሰብ አንድ ግለሰብን ከአጠቃላይ ማኅበረሰብ ጋር የሚያገናኝ ታላቅ ድልድይ ነው። እንዲሁም ተፈጥሮዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበረሰባዊ ጥቅም አለው። በእርግጥ ቤተሰብ በአባላቱ ቁጥር ትንሽ ሊሆን ይችላል ነገረግን የአንድ ቤተሰብ መፍረስ አጠቃላይ ማኅበረሰቡን ይጎዳል። አንድ ህብረተሰብ እንደ ህብረተሰብ ቀጣይነት እንዲኖረው ያስፈልጋል። ባህሉ፣ ቋንቋው፣ ሥርዓቱ፣ ወጉ ወዘተ ተጠብቆለት እንዲቀጥል የሁሉም የህብረተሰብ ምኞትና ፍላጎት ነው። ይህ ህብረተሰብ ደግሞ ቀጣይነት እንዲኖረው ቤተሰብ መኖር አለበት። ምክንያቱም ቤተሰብ የህብረተሰብ ምሰሶ ነውና። በመሆኑም ለህብረተሰቡ ምሰሶ የሆነው ቤተሰብ በህብረተሰቡ ዘንድ ጥበቃ ሊደረግለትም ይገባል። ጥበቃ የሚደረግለትም ቤተሰብ ከመመስረቱና ጋብቻ ከመፈፀሙ በፊት መሟላት ያለበት ቅድመ ሁኔታዎችን ወደ ጋብቻም ከተገባ በኋላም በተጋቢዎቹ መካከል የሚኖረውን ግላዊም ሆነ፣ ንብረት ነክ ግንኙነታቸውን፣ በህብረተሰቡ የሚጠበቅባቸውን ግዴታ የመሳሰሉትን ነገሮች በሕግ እና በሥርዓት እንዲመሩ ማድረግ አስፈላጊ ነው።
በተሻሻለው የቤተሰብ ሕግም ላይ እነዚህ ነገሮች በግልፅ እና በዝርዝር ተቀምጠዋል። ይህ ሕግ ጋብቻ ለመፈፀም የሚያስፈልጉ ቅድመ ሁኔታዎችን እና ክልከላዎችን፣ እነዚህ ክልከላዎች ወይም ቅድመ ሁኔታዎች ሳይሟሉ ጋብቻው ቢፈፀም የሚያስከትለውን ሕጋዊ ውጤት፣ ጋብቻ ሕጉን ተከትሎ ከተፈፀመ በኋላ በተጋቢዎቹ ስምምነት ግላዊ ግንኙነታውን እና ንብረት ነክ ግንኙነታቸውን አስገዳጅ የሆኑ የሕግ ድንጋጌዎችን ሳይቃረኑ በጋብቻ ውላቸው መወሰን እንደሚችሉ ደንግጓል። ሕጉ ይህን ሁሉ ያደረገው ተጋቢዎች በፍቅርና በሰላም እንዲኖሩና ወልደው ከብደው የህብረተሰቡን ቀጣይነት ለማረጋገጥ እንዲችሉ መሆኑንም አቶ ጎሽዬ ተናግረዋል። የተሻሻለው የቤተሰበ ሕግ ቀድመው የነበሩ በርካታ ክፍተቶችን አስተካክሏል ያሉት አቶ ጎሽዬ ይህም ሆኖ ሕጉ ከተሻሻለ ሃያ ዓመት የሞላው በመሆኑ ዛሬም ተገቢውን ጥናት በማድረግና ከነባራዊ ሁኔታ ጋር በማጣጣም መስተካከል ያለባቸው ነገሮች ካሉ መፈተሽ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
አዲስ ዘመን አርብ የካቲት 20/2012
ራስወርቅ ሙሉጌታ