«መጽሐፈ ቡዳ» ዋና ትኩረቱ ማህበራዊ ሂስና ተግባራዊ ፍልስፍና ላይ ነው፡፡ ፍልስፍናው ወደ መሬት ወርዶ በቀድሞው ዘመን ከነበረው ሃይማኖታዊ፣ ማህበረ- ፖለቲካዊ፣ ባህላዊ እንዲሁም ኢኮኖሚያዊ ቀውስ፣ ግራ መጋባት፤ አድሏዊና ኢ-ፍትሀዊ አሠራር ማህበረሰቡ እንዲላቀቅ በአፅንኦት ይመክራል። ይህን የደራሲውን እይታ በርእሳችን ከጠቀስናቸው አንፃር እንመለከተዋለን።
መጽሐፉ ማህበረሰቡ በእደ ጥበብ ባለሙያዎች (ባለ’ጆች) ላይ ያለውን የተዛባ አመለካከት በእጅጉ የሚያወግዝ ነው፡፡ እነዚህ ወገኖች በማህበረሰቡ ዘንድ በእጅጉ የተገፉ፣ ከማናቸውም ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊ ተሳትፎና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት የተገለሉ መሆኑ ተገቢ አለመሆኑን ይነቅፋል፡፡ የአገሪቱ የሥልጣኔ እምብርት ሆነውና ኅብረተሰቡ በእነሱ ልዩ ልዩ የጥበብ ውጤቶች እየተገለገለና ሕይወትን እየመራ ሳለ በጥላቻና ንቀት የሚታዩ፤ የሚያበረክቱት ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ አገልግሎት መተኪያ የሌለው ሆኖ ሳለ ይህ ቀረሽ የማይባል በደል የሚደርስባቸው መሆናቸውን ያነሳል፡፡ በእነዚህና ሌሎች መሰረተ-ቢስ ምክንያቶችም ማንኛውም ጥቅማጥቅም የተነፈጉ፣ እርስትም ሆነ ጉልት የሌላቸው፣ የማህበራዊ አገልግሎቶች ተቋዳሽ መሆን ያልቻሉ፣ ጋብቻ የተከለከሉ ሆነው የእድሜ ዘመናቸውን ማሳለፋቸውና ለዚህም ኅብረተሰቡ፤ በተለይም የሀሰት ወሬ እየፈበረኩ የሚያጋጩ ወገኖች ከጥፋታቸው ሊታቀቡ፤ ከስህተታቸው ሊማሩና በሰው ልጅ እኩልነት ላይ በማመን የወደፊቱን የጋራ አገር መገንባት እንዳለባቸው «መጽሐፈ ቡዳ» ያስገነዝባል።
ይህ ብቻም አይደለም፤ ከሁሉም የከፋ የነበረው የመደብ ልዩነት መፈጠሩና አንዱን እላይ አንዱን እታች ማስቀመጡ ነው። በ«መጽሐፈ ቡዳ» (ገፅ 1፣ 3፣ 4፣ 11፣ 21፣ 44 እና ሌሎችም) ላይ እንደሰፈረው ከሆነ ከሁሉም የከፋው ስድቡ ነው። ደራሲው ይህንን ማብራራት የሚጀምረው ገና ከጠዋቱ በመጀመሪያው ገፅ ላይ «ለብዙ ዘመናት ሲሰደብ የነበረ ሥራ» በሚል ርእስ ስር ባሰፈረው ሀቲት ነው። በዚሁ ርእስ ስር ደራሲው ፍሥሐ ይሁን ከስድብ ቃላቱ ዝርዝርና ብያኔ ጀምሮ ባለጅ ቡዳ ተብሎ እንደሚሰደብ፤ ይህም በተለያዩ የአገራችን አካባቢዎች ምን ዓይነት ገፅታ እንዳለው በዝርዝር ያስቀመጠ ነው፡፡ ይህንን አፀያፊና ማህበራዊ ጉድፍ ለመንቀስ ሳይታክቱ የለፉ የአገር መሪዎችን (በተለይም አጼ ቴዎድሮስ፣ አጼ ምኒልክ እና አጼ ኃይለሥላሴ)፣ ተመራማሪዎችን፤ በተለይም አለቃ ታዬን የመሳሰሉ ልሂቃንን ያደንቃል፤ ተገቢውን ምስጋናም ያቀርባል። ፍሥሐ ይሁን እሱ እራሱ የችግሩ ሰለባና የነበሩት የተዛቡ አስተሳሰቦች ተጠቂ በመሆኑ የድርሰት ሥራውን ከእውነተኛ የተጠቂነት፣ ተበዳይነት፣ ፍትህ እና ለውጥ ፈላጊነት ስሜትና አኳያ የደረሰው መሆኑን ገልጾልናል። ይህን ያደረገበት ምክንያትም (ለምሳሌ ገፅ 44ን ይመለከቷል) ማህበረሰቡ ከስህተቱ እንዲማር፣ የሰዎች/ዜጎች መብቶች ያለምንም ገደብና አድሏዊነት እንዲከበሩ ካለው ፅኑ ሰብአዊና ዜግነታዊ ፍላጎት፤ ደሀና ሀብታም ሳይባል ሁሉም ሰው እኩል (ገፅ 44 እና 64) መሆኑ ታውቆ ሰብአዊ መብቱ እንዲከበርና ማህበራዊ አገልግሎት የማግኘት መብቱ እንዲጠበቅለት ካለው ጥልቅ ፍላጎት አንፃር መሆኑን ይናገራል።
እነዚህ በእደ ጥበብ የተራቀቁ፣ አገር ያቀኑና የሰው ልጅ የሥልጣኔ ምንጭ የሆኑ ወገኖቻችን ቀጥቃጭ፣ ቡዳ፣ ጠይብ፣ ደብተራ፣ ሞረቴ ወዘተ እየተባሉ መሰደባቸው፤ አንዱን ከሰው በታች ሌላውን ጨዋና አጥንቱ የጠራ አድርጎ የማቅረብ ነገር ፈፅሞ ሊቀር ይገባል የሚለው «መጽሐፈ ቡዳ» ይህ እስካልተወገደ፣ ከመንግሥት አመራር እስከ ሃይማኖት አባቶች፣ ከተራው ዜጋ እስከ ምሁሩ ድረስ በዚህ ችግር ውስጥ የተዘፈቁ ስለሆነ በአስቸኳይ ከዚህ አገርንና ሕዝብን ከሚያደኸይ፤ እደ-ጥበብን ከሚገድል፣ የሰዎችን ክብርና መብት ከሚነካና ሰብአዊ መብትን ከሚጥስ ድርጊት ሊቆጠቡና ከናካቴውም ከአረንቋው ሊወጡ ይገባል። አለበለዚያ ሥልጣኔ ብሎ ነገር፣ እድገት ብሎ ሀሳብ የሚታሰብ አይደለም ባይ ነው። ፍልስፍናውም የሚያርፈው እዚሁ ላይ ነው።
በእንደዚህ ዓይነት አግላይ አስተሳሰብና ጨቋኝ ተግባር ውስጥ የገባውን የኅብረተሰብ ክፍል እገሌ ነው ብሎ አንዱን ከአንዱ ለይቶ ማስቀመጥ አይቻልም። ፍሥሐ ይሁን እንደዘረዘራቸው ከሆነ ሁሉም የሀገራችን ክፍለአገራትና አውራጃዎች ያሉ ነዋሪዎች የዚህ የተዛባና አግላይ አስተሳሰብ የፀዱ አይደሉም። ምናልባት የእደ- ጥበብ ባለሙያውን «ቡዳ ነው/አይደለም» የሚል ክርክር ውስጥ ያልገባውና በቀጥታ አስተሳሰቡን ከመሰረቱ በማጣጣል በጉዳዩ ላይ የተሳለቀው የጎጃም ሕዝብ ነው። ይህንንም በሚከተለው ቃል-ግጥም ያስተነትናል፤
ጎጃሜ ቡዳ ነው ብለሽ ያወራሽው፤
ሰው ሰውን ሲበላ የታ’ባሽ አየሽው።
ምክንያቱንም «የጎጃምን ሰው ቡዳ እያለ ሲሰድቧቸው ከማንም ሰው ጋር አይጣሉም። ስቀው ዝም ነው የሚሉት[።] ቡድነት ውሸት እንደሆነ በመረዳታቸው ነው፡፡እንዲሁም በራስ መተማመን ስላላቸውና ዝቅተኝነት ስለማይሰማቸው ነው።” (21) በማለት ይነግረናል። ይህ መግቢያውን ሳይጨምር በ22 ክፍሎች የተዋቀረውና በደራሲው «ታሪካዊ ልቦለድ» የተሰኘው «መጽሐፈ ቡዳ» ቡዳ ማለት ጥበበኛ እንጂ ሌላ እንዳልሆነ፤ ጥበበኞች ደግሞ ከግለሰብ ቁስ ጀምሮ እስከ ቤተክህነትና ቤተ መንግሥት ድረስ ከፍተኛ ሥራዎችን (መዋቢያ፣ መመገቢያ፣ ማጌጫ፣ ማምረቻ …) የሰሩ፤ ሐውልቶችን የቀረፁ፣ ቤተክርስቲያኖችን ያነፁ፣ ውብ ውብ አልባሳትን ያበረከቱ፤ ዘመናዊ ሥልጣኔን ያመጡና አገር ወደ አንድ ከፍተኛ ደረጃ እንድትሸጋገር ያደረጉ እንጂ እንደሚባለው ሰው የሚበሉና ሰው ሊጠየፋቸው የሚገቡ አይደሉም የሚለው ደራሲ ፍሥሐ «አጼ ቴዎድሮስ የተግባረ እድን ሥራ እንደጀመሩት ቀጣዩ መንግሥት ቢገፋበት ኖሮ ይህ[ን] ጊዜ ባለጁ፣ ቀጥቃጩ ሁሉ በጥበብ ሰልጥኖ ብዙ ጥበብ ይሰራ ነበር።» (47) ነገር ግን ይህ ሊሆን አልተቻለውም። «የኢትዮጵያ ሕዝብ ከተማረ አባይን ልገድብ ይላል።» (32) ከሚሉትና የእኛን ቁልቁለት ከሚፈልጉት ጠላቶቻችን ባልተናነሰ እርስ በእርስ አንዱ አንዱን እየናቀ፤ እየተናናቀ እራሱንም አገሩንም የዓለም ጭራ አደረገ።
ይህ በ555 ገፆች ላይ የሰፈረ፣ በተለያዩ የእደጥበብ ሥራዎች ምስሎች የታጀበ፣ በተለያዩ የመጀመሪያና ሁለተኛ መረጃ ምንጮች የተደገፈ «ታሪካዊ ልቦለድ» መጽሐፍ ታሪኩን በተለያዩ የአቀራረብ ዘዬዎች ያቀረበ ሲሆን ዋና ዋናዎቹም ዝርውና ግጥም ናቸው። በተለይ የፈጠራውን ክፍል በግጥማዊ ምልልስ ማቅረቡ ለጉዳዩ የሰጠውን ትኩረት ሲያሳይ በምልልስ መልክ መሆኑም አንባቢ የተለያዩ ሰብእናዎችን እንዲያይ፣ እንዲመረምር፣ እንዲታዘብ፣ የደራሲውን ፍልስፍና እንዲያደንቅ/ነቅፍና የራሱ አቋም ላይ እንዲደርስ ተፅእኖ ይፈጥራል።
ቡዳ እጅግ የከበደ ስድብ መሆኑን የሚናገረው ደራሲው በተለይ «በዘር ትውልዳቸው ፈላሾች (ባለጆች) ለሆኑት ስድቡ ከባድ» (ገፅ 1) እንደሆነም ይገልፃል። ስድቡ በተረትና ምሳሌ ሳይቀር ይገለፅ እንደነበር የሚነግረን ደራሲ ፍሥሐ «ከሰው ክፉ ደብተራ፤ ካውሬ ክፉ ዳሞትራ» (37) እየተባለ አዋቂው ሁሉ ይዘለፍ እንደነበረም አልሸሸገም።
የማርክሲስት ርእዮተ ዓለም አራማጅ መሆኑን ከመጽሐፉ ማጠቃለያ ገፆች (ከሃምሳ አለቃ ገብሬ እና ከሃምሳ አለቃ አበበ ግጥማዊ ምልልሶች) የምንረዳው ደራሲ ፍሥሐ ይሁን በድርሰቱ በጠቀሳቸው የታሪክ ዘመናት ውስጥ ንቁ ተሳታፊ የሆኑ ተቋማትን፣ መሪዎችን፣ ምሁራንን፣ የችግሩ ተጠቂ ማህበረሰብ አባላትን፣ አካባቢዎችን እየጠቀሰ አብራርቷል፤ የደረሰውንም ቀውስና ቀውሱ ያስከተለውንም አገራዊ ጉዳት በዝርዝር አመልክቷል። እንደ አንድ ማህበረሰብ፤ ለዚያውም እንደ አንድ የነቃ፣ በዓለም በሥልጣኔ ምንጭነቱ፣ በሃይማኖት አጥባቂነቱ፣ ለዘመናት ተከባብሮ በመኖሩ … በሚታወቅ ሕዝብ ዘንድ ይህ ዓይነቱ አግላይነት፤ የሰብአዊ መብት ጥሰት ተግባር፣ አንዱን የበላይ አንዱን የበታች አድርጎ የማየት ሁኔታ፣ ከ«እኛነት» ይልቅ ሁል ጊዜ «የእኔ እኔ ባይነት» መንፈስ ባልተከሰተም ነበር እያለም ይቆጫል፤ ማህበረሰቡንም ያሄሳል።
የዚህ ሁሉ መነሻ «ክርስቶስ የተሰቀለበትን መስቀል የሰሩት እነሱ ናቸው።» ተብሎ በአገራችን ጠላቶች የተነገረው የውሸት ወሬ መሆኑን የሚናገረው ደራሲ ፍሥሐ ይሁን አገር እንደ አገር፤ ሕዝቡም እንደ ሕዝብ ከእንደዚህ ዓይነቱ አስከፊ ሁኔታ እንዲወጣና ሁለተኛም እንዳይደገም አጥብቆ ይመክራል። የሁሉም መብት በሁሉም እኩል እንዲከበርም አጥብቆ ያስገነዝባል።
አዲስ ዘመን አርብ የካቲት 20/2012
ግርማ መንግሥቴ