ሀገራዊ ችግር የሆነውን የድህነትና ሥራ አጥነት ችግር ለመፍታት ኢንቨስትመንትን ማስፋፋት ወሳኝ ነው። ኢንቨስትመንት ሲስፋፋ የሥራ ዕድል ይፈጠራል። የመንግሥት ገቢ ያድጋል። ሀገር ትለማለች፤ ሕዝቡም ተጠቃሚ ይሆናል። ስለሆነም የሀገር ውስጥም ሆነ የውጭ ኢንቨስትመንትን በመሳብ በኩል ሁሉም ኃላፊነቱን መወጣት አለበት።
አዳዲስ ኢንቨስትመንቶችን ለመሳብ አሠራርን ማዘመን፤ አገልግሎት አሰጣጥን ፈጣንና ቀልጣፋ ማድረግ፣ የመሠረተ ልማት አቅርቦት ማቀላጠፍ፤ ሰላምና ደህንነት ማረጋገጥ ተገቢ ነው። ለዚህ ደግሞ በየደረጃው ያሉ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ተግባራቸውን በሚገባ ሊወጡ ይገባል።
የኢንቨስትመንት ማደግና መስፋፋት የወጣቱን ሥራ አጥነት ችግር በስፋት ይቀርፋል። ለሥራ የተጋ፣ ከብሶት የራቀ አምራች ኃይል በመፍጠርም በርካታ ማሕበራዊ ችግሮችንም ለመፍታት ያስችላል።
በኦሮሚያና በአማራ ክልል ደብረብርሃን ከተማ በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ስድስት ወራት በድምሩ 89 ቢሊዮን ብር ካፒታል ያስመዘገቡ ባለሀብቶች ኢንቨስት አድርገዋል። ለ105ሺ ዜጎችም የሥራ ዕድል ይፈጥራሉ። ይህ የሚያሳየው ኢንቨስትመንትን በመሳብ ረገድ ጥሩ ሥራ መሰራቱን ነው። በኢንቨስትመንት ረገድ ሰፊ ለውጦች እየታዩ መሆኑንም አመላካች ነው። ስለሆነም ሊደነቁም ይገባል።
በኦሮሚያ ክልል በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያዎቹ ስድስት ወራት 26 ነጥብ ዘጠኝ ቢሊዮን ብር ካፒታል ያስመዘገቡ 154 ፕሮጀክቶች ወደ ሥራ ገብተዋል። ውጤታማ መሆን ያልቻሉ የአስራ አንድ ፕሮጀክቶች ውል ተቋርጧል። ወደ ሥራ ከገቡት መካከል 143ቱ የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች፤ አራት የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት፣ አምስቱ የዳያስፖራ ባለሀብቶች ሁለቱ ከውጭ ባለሀብቶች ጋር በሽርክና የሚሰሩ ናቸው።
ከሀገር ውስጥ ባለሀብቶች 53ቱ በግብርናው ዘርፍ ግንባር ቀደም ሚና የነበራቸው አርሶ አደሮች መሆናቸው ሲታይ ደግሞ ሊበረታታ የሚገባው ተግባር ነው።
የኢንቨስትመንት ዘርፎች ማኑፋክቸሪንግ፣ ግብርና፣ አግሮ ኢንዱስትሪ፣ አገልግሎትና ሶላር ኢነርጂ ሲሆኑ፤ በክልሉ ባሉ 20 ዞኖች ተሰራጭተው ይገኛሉ። አጠቃላይ ፕሮጀክቶቹ ወደ ሥራ ሲገቡ 31 ሺ 211 ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል የመፍጠር አቅም አላቸው።
በክልሉ ኢንቨስትመንት እየተስፋፋ ብዛቱ፣ ስብጥርና የባለሀብቱ ተነሳሽነት በየጊዜው እየጨመረ መምጣቱ በኦሮሚያ ክልል ኢንቨስትመንት ኮሚሽን የተሰራውን ብርቱ ሥራ ያሳያል። ስለዚህ ይህን አጠናክሮ መቀጠል ይገባል። ዜጎችን የሥራ ባለቤት ለማድረግ መንግሥት ለጀመረው ሥራ አጋዥ በመሆኑ ማጠናከር ተገቢ ነው።
በአማራ ክልል ደብረብርሃንም ከኢንቨስትመንት አንጻር ሳቢ ከተማ ሆናለች። እሰየው ነው። በዞኑ በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ስድስት ወራት 60 ቢሊዮን ብር ያስመዘገቡ 369 ባለሀብቶች ወደ ሥራ ገብተዋል። በዚህም ለ74ሺ ዜጎች የሥራ ዕድል የሚፈጠርላቸው በመሆኑ ሲታይ ሊበረታታ የሚገባው ነው።
በከተማዋ በ2011 በጀት ዓመት መዋዕለ ንዋያቸውን አፍስሰው የነበሩ የባለሀብቶች ቁጥር 301 ነበር። ዘንድሮ በግማሽ ዓመት 369 ደርሷል። ከእነዚህ መካከል 269 የሚደርሱት በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ የሚሰማሩ ሲሆን፤ የውጭ ምንዛሬም ያስገኛሉ። በከተማዋና በአካባቢው ለሚገኙ ወጣቶች ሰፊ የሥራ ዕድል ይፈጥራሉ። ይሄ ትልቅ ድል ነው። ስለሆነም ተጠናክሮ መቀጠል አለበት።
ይሁንና ልንደርስበት ከምንፈልገው የዕድገት ደረጃ አንጻር የሀገር ውስጥ ሆነ የውጭ ኢንቨስትመንት ፍሰት ከዚህ በበለጠ መጠን እንዲጨምር መስራት ያስፈልጋል። ለኢንቨስተሮች እንቅፋት የሚሆኑ አሠራሮች በማዘመን፣ መንግሥት ማድረግ የሚገባውን ድጋፍ በወቅቱና በሚገባው መጠን በማድረግ ከዚህ የበለጠ ኢንቨስትመንት መሳብ ይቻላል። ይገባልም።
ስለዚህ በኦሮሚያና በአማራ ክልል ደብረብርሃን ከተማ የታየው የበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ስድስት ወራት የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ አጠናክሮ ማስቀጠል ያስፈልጋል። ሌሎችም ክልሎችና ከተሞች ትምህርት ወስደው እንደ ሀገር ከፍተኛ ኢንቨስትመንት በመሳብ የሥራ ዕድልን በመፍጠር የሥራ አጥ ቁጥር መቀነስ እንዲሁም የውጭ ምንዛሪ ግኝት ማሳደግ ይቻላል!
አዲስ ዘመን የካቲት 19/2012