ጥንታዊ ሥልጣኔዎች በሙሉ የተፀነሱትና የፋፉት በወንዞች ዳርቻ ስለመሆኑ የታሪክ ማስረጃዎች አጠንክረው ያረጋግጡልናል። ቅድመ ታሪክን ጥቂት ፈቅ ብለን ስንመረምርም የፍጥረተ ሰብ እስትንፋስና ህልውና “ሀ” ብሎ የጀመረው ገነትን ለማጠጣት ከዔደን ይፈልቁ ከነበሩ አራት ግዙፍ ወንዞች (ፊሶን፣ ግዮን፣ ጤግሮስና ኤፍራጠስ) እንደነበር ቅዱስ መጽሐፍ በዝርዝር ይተርክልናል። ግዮን በሚባለው ጥንታዊ ስሙ የተጠራው የእኛው የዓባይ ወንዝ ግን በተለየ ሁኔታ የብዙ ሥልጣኔዎች መሠረት ብቻ ሳይሆን የጥበብና የዕውቀት እስትንፋስ ጭምር እንደነበር ቀደምት የአርኪዮሎጂና የታሪክ ሰነዶች ይመሰክራሉ።
የግብፅ ፈርዖኖች ሥልጣኔ በዓባይ ወንዝ ዳርቻዎች ላይ መስፋፋቱ ብቻ ሳይሆን ተፀንሶ የተወለደውም ከራሱ ከግዮን ውሃ ማህፀን ውስጥ መሆኑን ቀደም ባሉት ጽሑፎቼ ዝርዝሩን ማስነበቤ ለጋዜጣው አንባቢዎች እንግዳ አይሆንም። ይህንን የዓባይ ወንዝና የፈርዖኖች ቁርኝት በተመለከተ በግብፆች አፈ ታሪክ ለዘመናት ሲታመን የኖረው ወንዙ የውሃ ምንጭ ብቻ ሳይሆን “የመለኮትና የአማልክቶቻቸው ማደሪያና መሠልጠኛ” መሆኑን ጨምር ለመተንተን መሞከሬን ልብ ይሏል። ሃፒ የታላቁ ዓባይ “አምላክና ታላቅ ስም” መሆኑንም ጥንታዊ የአርኪዮሎጂ ማመሳከሪያዎችን ዋቢ አድርጌ ዝርዝሩን ማስነበቤን አስታውሳለሁ።
ለማስታወስ ያህል፤ ዓባይ ወንዝ ከጥንት እስከ ዛሬ በፈርዖን ልጆች ዘንድ ሲታመን የኖረውና ዛሬም ድረስ የአምልኮተ ዓባይ ጉዳይ ሊደበዝዝ ያልቻለው በግብፃውያን ሥነ ልቦና ውስጥ አጥብቆ የተዘራው ዘር በዘመናት ውስጥ ሥር ሰዶ ስለኖረ ነው። እንዲሁ በጥቅሉ ለማስታወስ ያህል ዓባይ ወንዝ ለግብፆች፤ “የአማልክቶች ዋና አምላክ፣ የሕይወትና የመኖር እስትንፋስ፣ የፈውስና የመድኃኒቶች ምንጭ፣ የሀብትና የክብር ካዝና፣ የተትረፈረፈ የእህል አዝመራና የማከማቻ ጎተራ፣ ከመከራና ከድርቅ ታዳጊና ተራዳዒ” እንደሆነ ተደርጎ ነበር፤ ነውም። ይህ ትርክት በተረት ተረትና በአድባሬ ወግ ዘይቤ የሚያቀነቅኑት ብቻ ሳይሆን “ሕይወትን እስከ መስጠት” ጭምር ታምኖበት የተወራረዱበት የመኖር ያለመኖር ጉዳይ እንደሆነ ብዙ ማስረጃዎችን በማጣቀስ መተንተን ይቻላል።
ምሥጋና ለውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መ/ቤታችን ይሁንና የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ ከኢትዮጵያ ፐብሊክ ዲፕሎማሲ ቡድን ጋር በመሆን ከዘመነ ፈርዖን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ግብፆች በሚሰግዱለትና እንደ አምላክ በሚያዩት በዓባይ ወንዝ የጋራ ተጠቃሚነት ጉዳይ ለግብፅ ሕዝብና መንግሥት መልዕክት ለማድረስ በሄድንበት ወቅት እውነታው ፍንትው ብሎ ታይቶናል። ዓባይ በምድረ ግብፅ እንደምን ተከብሮና ተወድሶ፣ ተመልኮና ተደንቆ እንደሚንፈላሰስም የዓይን ምስክር ሆነን ታዝበናል። “የዓባይ ውሃ ከሚጠፋ፤ ደማችን ይደፋ” በሚል ድምጸት የተጻፉ በርካታ ሊትሬቸሮችንም ለማንበብና ለመስብሰብ ተችሏል።
በሱዳን ዋና ከተማ ካርቱም ላይ የእኛው ጥቁር ዓባይ ከነጩ ወንድሙ ጋር በስስት ሲሳሳሙና ረጂሙን ጉዟቸውን በፍቅር ተቃቅፈው እየዘመሩና የሱዳንን ምድረ በዳ እያለመለሙ ሲጓዙም በደንገል መካከል ቆሜ አስተውያለሁ። የጥቁርና የነጭ ዓባዮችን መገናኛና የመሳሳም ትርዒት የሀገራችን ሰዓሊያን በተሰጣቸው የጥበብ ፀጋ እስከ ዛሬ በሸራቸው ላይ ሊያሰፍሩ ለምን እንዳልቻሉ ብንጠይቀቸው ለኩነኔ ሳይሆን አእምሯቸውን ለማንቃት ይረዳ ይመስለኛል። ከካርቱም ራቅ ብሎ የሚገኘውን የኤሌክትሪክ ማመንጫ ግድባቸውንና የአካባቢውን ጥንታዊና ዝነኛ የሜሮዌ መንግሥት ማስታወሻ የሆኑ የአብያተ ነገሥታት ፍርስራሾችንም እያየሁ በሃሳብና በትዝታ ሺህ ዘመናት ወደኋላ አፈግፍጌ ተክዣለሁ።
በዩጋንዳው የቪክቶሪያ ሐይቅ ላይ ከፐብሊክ ዲፕሎማሲው አባላት ጋር በጀልባ እየተንሸረሸርን ከነጭ ዓባይ መነሻ ዜሮ ነጥብ በእጆቻችን ውሃ ዘግነን ፊታችንን አብሰናል። ጀልባችን በምትረጨው የውሃው “ጠበልም” ረስርሰናል፤ ተጠምቀናልም። ነጭ ዓባይ 14% የስንቅ ድርሻውን ይዞ 86% በረከት ከታቀፈው ከጥቁር ዓባይ ወንድሙ ጋር ለመገናኘት ደንገለሳ እየረገጠ ወደ ሱዳን ሲጣደፍም ቆመን በአንክሮ እየተመለከትን “በሆት ግባ!” ብለን መርቀነዋል። ለዩጋንዳውያን የሚለግሰውን የልማት ትሩፋት ስናስተውልም ውስጣችንን “መንፈሳዊ ቅንዓት” እያተራመሰው “ከሞኝ ደጅ ሞፈር ሲቆረጥ” እንዴት ሳንባንን ቀረን እያልን በራሳችን አፍረናል።
ጥንታዊው የግሪክ ፈላስፋ ሆሜር “ኢትዮጵያ ከዓለም ርቃ አሸልባ፤ ዓለምም ከእርሷ ርቆ ሺህ ዘመናት ተቆጥሯል” እያለ የተሳለቀብን እውነት ስለመሆኑ በግሌ አሜን ብያለሁ። የሀገሬን ጥቁር ዓባይ ጥቁር ፊት ባሰብኩ ቁጥርም መንፈሴ ይቆጣል። በዓባይ ጦስ ምክንያት በውጭ ወራሪዎች ሰይፍ ሀገሬ የገበረችውን የደም ግብር ሳስታውስም፤
– ዓባይ ጥቁር ነበር ከሰል የመሰለ፣
እየቀላ ሄደ ደም እየመሰለ።”
የሚለውን ሕዝባዊ ሥነቃል ያስታውሰኛል።
ሀገሬ ሺህ ዘመናት ካንቀላፋችበት የድብርት አልጋዋ ላይ ባንና በመነሳት በዓባይ ወንዝ ላይ የህዳሴ ግድብ ገንብቼ ቢያንስ በጨለማ ተውጦ ለኖረውና እየኖረ ላለው ሕዝቤ የብርሃን ጸጋ ላድርስለት ብላ ስትነሳ የገጠማትና እየገጠማት ያለው መልከ ብዙ ተግዳሮት አንደምን የገዘፈ እንደሆነም እውነታው እያደረ በመገለጥ ላይ ነው።
የዓባይን ወንዝ በተገቢው ሀገራዊ የልማት ጥቅም ላይ ለማዋል ከቀደምት ዘመናት መሪዎች ጀምሮ ብዙ ፍላጎቶችና ጥረቶች ሲደረጉ እንደነበር መካድ አይቻልም። ለታሪክ ያለን ሀገራዊ ስስትና ንፍገት አንዱ የብሔራዊ በሽታችን መገለጫ ስለሆነ መመሰጋገን አልለመደብንም እንጂ በርካታ መሪዎቻችን ዓባይን ለማልማት የግላቸውን ጥረት ማድረጋቸው አልቀረም ነበር። የዓባይን የበረከት ስጦታነትና ኢትዮጵያዊነትን በተመለከተም ቀደምት መሪዎች በጽናት ይሟገቱ እንደነበር መዋዕለ ታሪካቸው ይመሰክራል።
የሩቅ መሪዎቻችንን እንኳ ለጊዜው በክብር አቆይተን የዛሬ 45 ዓመት ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለስላሴ ጥቅምት 23 ቀን 1957 ዓ.ም በዓለ ሲመታቸውን ባከበሩበት ዕለት የዓባይ ወንዝን ለልማት ለማዋል ሀገራችን ከፍ ያለ ፍላጎትና ጥረት እንደምታደርግ በግልጽ ተናግረው ነበር። እንዲህ በማለት፤
“ለምንወደው ለዛሬ ሕዝባችንም ሆነ፣ ከዘመን ወደ ዘመን ለሚከተለው ትውልድም ጭምር፣ የዓባይን የውሃ ሀብት ለሕይወቱ ደህንነትና ለፍላጎቱ ማርኪያ እንዲውል ማድረግ ኢትዮጵያ ከፍ ያለ ግምት የምትሰጠውና በቅድሚያ የሚያሳስባት ጉዳይ ነው። አምላካችን ያበረከተልን ይህንን ሀብቷን ለሕዝቦቻቸው ሕይወትና ደህንነት በማዋል እንዲጠቀሙበት ከጎረቤት ወዳጅ ሀገሮች ጋር በለጋስነት በጋራ ለመካፈል ዝግጁ ብትሆንም፤ ይህንን የውሃ ንብረቷን በቁጥር እየጨመረ ለሚሄደው ሕዝቧና በማደግ ላይ ላለው ኢኮኖሚዋ ጥቅም እንዲውል ማድረግ የኢትዮጵያ ተቀዳሚ የተቀደሰ ግዴታዋ ነው።”
ንጉሠ ነገስቱ በበዓለ ሲመታቸው ላይ ይህንን የመሰለ ጠንካራ ንግግር ለማድረግ የተገደዱበት ምክንያት ምናልባትም በወቅቱ የነበረው የግብፅና የሱዳን ጫና በርትቶባቸውና አሳስቧቸው ሳይሆን እንዳልቀረ መገመት ይቻላል። ቀደምት መሪዎቻችን ዓባይን ገድቦ በጥቅም ላይ ለማዋል በርካታ ፈታኝ ተግዳሮቶች እንደነበረባቸው አይካድም። የመጀመሪያው ተጠቃሽ ምንክንያት በቂ ሀብትና፣ በዘርፉ የሰለጠነ የሰው ኃይል ያለመኖር ሲሆን፤ ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ በየዘመናቱ ፋታና እረፍት የነሱን ከቅርብና ከሩቅ የዘመቱብን የውጭ ወራሪዎች ትንኮሳ፣ ሤራና እርባና ቢስ የውስጥ ሽኩቻችን ሰበብ ነበር።
ሌላውና ከላይኛው ምክንያት ጋር ተያያዥነት ያለው ፈታኝ ተግዳሮት በዓባይ ጉዳይ ዋነኞቹ የውሃው ተጋሪ ሀገራት፤ ግብፅና ሱዳን፤ የተለያዩ ስምምነቶችን እየተፈራረሙ በራሷ የተፈጥሮ ሀብት ባዕድ ባለሀገር በማድረግ ስላገለሏትና ሲሞግቷት ስለኖሩ ነበር።
የሙግቶቹን ስፋትና ጥልቀት በግርድፉ ለማስታወስ ያህል ዋና ዋናዎቹንና ደጋግመን የሰማናቸውን ጥቂቶቹን ብቻ ለአብነት ላስታውስ። እ.አ.አ በ1902 ዓ.ም ዳግማዊ አፄ ምኒልክ የፈረሙት ያልተጤነበትና በቂ ምክክር ያልተደረገበት የማጭበርበሪያ ስምምነት ሲሆን፤ የስምምነቱ ዋና መቋጫ ኢትዮጵያ ከግዛቷ በሚፈልቀው የውሃ ሀብት ምንም ዓይነት መብት ሳይኖራት የግብፅን ጥቅም ሙሉ ለሙሉ የሚያረጋግጥ ነበር።
ከዚህ ስምምነት በማስከተል የተፈረሙት ሁለት ሰነዶች የመጀመሪያው ግንቦት (ሜይ) 7 ቀን 1929 ዓ.ም በታላቋ ብሪታኒያና በግብፅ መካከል የተፈረመው ስምምነት ሲሆን፤ ዋነኛ ጭብጡም ግብፅ በዓባይ ውሃ ላይ “ተፈጥሯዊና የባለንብረትነት ታሪካዊ መብትን” የሚያረጋግጥ ነበር። ይህ ስምምነት ከተፈረመ ከሰላሳ ዓመታት በኋላ ኅዳር (ኖቬምበር) 8 ቀን 1959 ዓ.ም ግብፅና ሱዳን የተፈራረሙት ሌላው ስምምነት ነበር። በስምምነቱም ግብፅና ሱዳን ከዓባይ ውሃ የሚያገኙት ዓመታዊ የውሃ መጠን ማንንም ጣልቃ ሳያስገቡ በአዲስ መልክ ሁለቱ ብቻ የተቃረጡበት ስምምነት ነበር።
እኒህን መሰል የስምምነት እንቅፋቶች ሳይታረሙና እልባት ሳይሰጣቸው ነበር ኢትዮጵያ በቁርጠኝነት ተነሳስታ በልጆቿ ሀብትና አቅም የታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ለመገንባት ዝግጅቷን ማጠናቀቋን ለዓለም ማሕበረሰብ ያበሰረችው። ይህ እርምጃዋ ድንጋጤና መረበሽ የፈጠረባቸውና ውሳኔው ያስደነበራቸው የግብፅ መሪዎች በዘመናት ውስጥ በትንኮሳና በስመ ስምምነት ሲፈጽሙ የኖሩት ሤራ ስለከሸፈባቸው የተለያዩ ስልቶችን በመጠቀም የህዳሴው ግድብ ሥራ እንዲስተጓጎል ያልሞከሩት ዘዴ አልነበረም።
ግብፅ በዓባይ ጉዳይ እንኳን እንቅልፍ ሊወስዳት ቀርቶ ለቅጽበት እንኳ ማሸለቧ ያጠራጥራል። የኢትዮጵያ አቋም ግልጽ ነው። ውሃው የፈጣሪ ስጦታና በረከት ነው። ስለዚህም በጋራ ተጠቃሚነት የማይናወጥ መርሆዋ ኢትዮጵያም የትኞቹንም የተፋሰሱን ሀገራት ሳትጎዳ እኩል የመጠቀም መብቷ ሊረጋገጥ ይገባል። የአባይ ምንጭ መፍለቂያ መሆኗ ብቻ ሳይሆን ውሃውን ለልማት ማዋል መፈለጓም አግባብም፣ ተፈጥሯዊም፣ ሕጋዊም መሠረት ያለው ነው።
ከጥቂት ሳምንታት በፊት የአሜሪካ መንግሥትን በወከሉት የፋይናንስ ሚኒስትርና በዓለም ባንክ ታዛቢነት ሀገራችንን ጨምሮ ሦስቱ የዓባይ ተፋሰስ ሀገራት (ኢትዮጵያ፣ ግብፅና ሱዳን) በዋሽንግቶንና በየሀገራቸው ዋና መዲና ተደጋጋሚና አድካሚ ድርድሮችን ሲያደርጉ መሰንበታቸው ይታወቃል። የድርድሮቹ መምከን ዋነኛ ተጠያቂዋ “ለእኔ ብቻ” በሚል አቋም ግትር ሃሳብ የምታራምደው ግብፅ ስለመሆኗ የአደባባይ ምሥጢር ነው። እስካሁን ድረስም ድርድሩ በስምምነት አልተቋጨም።
ኢትዮጵያ በጋራ የመጠቀም መብቴ ይከበርልኝ እያለች ብትወተውትና ብትማጸንም ጆሮ የሰጣት አካል አልተገኘም። ሀገራችን የቆመችለት አቋም በግልፅና ጥርት ባለ ቋንቋ ለሕዝቡ ባለመድረሱም ጉዳዩ በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገራት ላሉ ዜጎቻችን መነጋገሪያ ሆኗል።
እርግጥ ነው ኢትዮጵያ በጫናና በማንም ተፅእኖ ሉዓላዊ ጥቅሟን የሚጎዳ ስምምነት እንደማትፈርም አስታውቃለች። ጥያቄው አስገዳጆቹ ተፅእኖ ፈጣሪዎች እነማን? ለምን ምክንያትስ? የሚለው መልስ በይፋ አልተገለጸም። ከአንድ ቀን በኋላ በአሜሪካ የሚኖሩ ትውልድ ኢትዮጵያውያን የዲሲ ግብረ ኃይል በሚል ስያሜ በሚታወቀው ስብስብ አስተባባሪነት በአሜሪካ ስቴት ዲፓርትመንት ፊት ለፊት ተሰልፈው በድርድሩ ላይ አሜሪካ እንደ ታዛቢ ሳይሆን እንደ አደራዳሪ አቋም ወስዳ ብሔራዊ ጉዳት ላይ የሚጥል ውሳኔ ልታስወስን ስለሆነ ከድርጊቷ ትገታ የሚል መልዕክት ይተላለፋል ተብሎ ይጠበቃል። ይህን መሰሉ የሕዝብ ድምጽ በውጭ ሀገራት ብቻ ሳይሆን በሀገር ውስጥም ተጠናክሮ ቢደመጥ ጊዜው እንደሆነ ብዙዎች ያምናሉ።
በተለያዩ የፖለቲካ አመለካከቶች ምክንያት ዜጎች የየራሳቸው አቋም ቢኖራቸውም በታላቁ ህዳሴ ግድባችንና በዓባይ ወንዝ አጠቃቀም ግን ማንም ጣልቃ ገብቶ ሊያስገድድ እንደማይችል ሀገራዊ አቋም መያዙ ያኮራል። መንግሥትም ቢሆን በየጊዜው ግልጽና ጥርት ያለ መረጃ ለሕዝቡ ቢሰጥ ይጠቅማል። ነገሮችን መሸፋፈን ባህላችን ቢሆንም በዚህ ጉዳይ ግን “መቼስ ምን ይደረግ” ተብሎ በትዝብት ብቻ የሚታለፍ እንዳልሆነ ቢታወቅ መልካም ይሆናል። እስከ መቼስ በሞኝነት ከደጃፋችን ላይ ሞፈር እየተቆረጠ እንዘልቀዋለን። አይሆንም። አይደረግም። ሰላም ይሁን!!
አዲስ ዘመን የካቲት 18 / 2012
በጌታቸው በለጠ/ዳግላስ ጴጥሮስ