የሥራ ጠባዬ ወደመስክ የሚያስወጣ ነው። የመንግሥት ሠራተኛ ባልሆንም የውሎ አበል ተመኑን በቅርብ አውቀዋለሁ።በመንግሥት አካላት በተለይ ለመገናኛ ብዙኃን (ለመንግሥትም፣ ለግልም) በሚዘጋጁ ስብሰባዎችና ዓውደጥናቶች ላይ ተካፋይ የመሆን ዕድሉ ነበረኝ።እሱም ብቻም ሳይሆን የምታሳቅቀዋን የመንግሥት የውሎ አበል ክፍያ ቀምሼም አውቃለሁ።
በተደጋጋሚ ለስብሰባና ለወርክሾፕ የምሄድበት አዳማ ከተማን ለአብነት ያህል ላንሳ።ንጹህና ደረጃውን የጠበቀ መኝታ (አልጋ) ከ500 ብር በታች ማግኘት እምብዛም አይታሰብም።ልብ በል!.. ንጹህና ደረጃውን የጠበቀ መኝታ ነው ያልኩት።በንጹህ መኝታ ላይ መስተናገድ ደግሞ የመንግሥትና የግል ድርጅት ሠራተኛ ወይንም አለቃና ምንዝር ተብሎ ደረጃ የሚወጣለት ሊሆን አይችልም፤ አይገባምም።
በተጨባጭ የመንግሥት ሠራተኞች የውሎ አበል ክፍያ አነስተኛ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ለአልጋ ግፋ ቢል ከ150.00 ብር በላይ ለመክፈል የሚያስችል አይደለም።ይኸም የሚሆነው ብዙውን ጊዜ ስብሰባ አዘጋጆች የሻይ እና የምሳ መስተንግዶ ስለሚኖራቸው ለማብቃቃት ሲባል አንዳንድ ጊዜ እራትን መመገብ በመዝለል ጭምር መሆኑ አውቃለሁ።እናም ለመንግሥት ሠራተኛው ለመስክ ሥራ መውጣት ሰቀቀን ሆኖ ኖሯል።
ችግሩ አንዳንድ የመንግሥት ተቋማትን ሳይፈልጉ በግድ ሕጋዊ መሰል ስርቆት ውስጥ ከቷቸዋል።ሕጋዊ ስርቆት ምንድነው ሊባል ይችላል።አንድ ሰው ለሦስት ቀናት የመስክ ሥራ ወጣ እንበል።በሦስት ቀን ተባዝቶ የሚሰጠው የውሎ አበል ወጪውን ስለማይሸፍንለት ብዙውን ጊዜ ሠራተኛው ወደመስክ ለመሄድ ያንገራግራል።ምናልባት ከሄደም ወጪውን ከኪሱ መደጎም የግድ ይሆናል።በዚህ ምክንያት ተቋማት ለሠራተኞቻቸው የሚከፍሉት አበል ቢያንስ የቀን ወጪያቸውን እንዲሸፍንላቸው በማሰብ ሠራተኛው የሚቆይበትን ቀናት በእጥፍ ወይንም ከዚያ በላይ አስልተው የሚከፈሉበት አሠራር የተለመደ ሆኗል።
ሕጋዊ ስርቆት ያልኩት ይህን አሠራር እስከተ ቋሙ ከፍተኛ አመራር ድረስ ታውቆ ግልጽ በሆነ መንገድ የሚከናወን በመሆኑ ነው።በእውነቱ በተንቀሳቀስኩባቸው የመስክ ሥራዎች መሰል አሠራር ተደጋግሞ ማየቴ ለካስ ስርቆትም ሲለመድ ሕጋዊ ይሆናል የሚል ስሜትን አጭሮብኛል፡፡
አንዳንድ መንግሥታዊ ተቋማት ደግሞ ብዙ ጊዜ ከፍተኛ ወጪ ያለው የመኝታ ወጪ በራሳቸው በመሸፈን ለምግብና ለትራንስፖርት ብቻ አበል የሚከፍሉበት አሠራርም አለ።ተቋማቱ ይህን ለማድረግ የተገደዱት በአመዛኙ አነስተኛውን የአበል ክፍያ ሥርዓት ለማካካስ በማሰብ ነው፡፡
ከገቢዎች ሚኒስቴር የተገኘ መረጃ እንደሚጠቅሰው የውሎ አበል ማለት አንድ ሠራተኛ የተቀጠረበትን ሥራ ለማከናወን መደበኛ የሥራ ቦታው ከሚገኝበት ከተማ ውጪ ከ25 ኪሎ ሜትር በላይ ርቆ በሚሄድበት ጊዜ ለመኝታ፣ ለምግብ፣ ለመጠጥና ለተዛማጅ ወጪዎች የሚከፈል አበል ነው በማለት ፍቺ ይሰጠዋል፡፡
ከሐምሌ 1 ቀን 2004 ዓ.ም ጀምሮ የወጣውና እስከአሁን በሥራ ላይ የሚገኘው የመንግሥት ሠራተኞች የቀን ውሎ አበል መመሪያ እንደሚያመለክተው የመንግሥት ሠራተኛው በየትኛውም ክልል ሄዶ ቢሰራ ከፍተኛ ደመወዝ አለው የሚባለው 225 ብር የሚታሰብለት ሲሆን፤ አነስተኛ ደመወዝ ተከፋይ ነው የሚባለው ደግሞ በቀን 111 ብር ክፍያን እንደሚያገኝ የአዲስ ዘመን ታኅሣሥ 22 ቀን 2012 ትችት አዘል ርዕስ አንቀጽ ይጠቁማል፡፡
እዚህ ላይ ሁለት አበይት ማነቆዎችን ማንሳት ይቻላል።አንዱና ዋናው ነገር የሚከፈለው አበል የወቅቱን ገበያ ያገናዘበ አለመሆኑ ነው።ለመኝታ፣ ለምግብ፣ ለመጠጥ ተብሎ የተሰጠ አበል አንዱን እንኳን (የመኝታውን) ወጪ በአግባቡ መሸፈን የማይችልባቸው ከተሞች መኖራቸው ይታወቃል።ለምሳሌ በአዲስአበባ በ225 ብር ንጹህና ደረጃውን የጠበቀ መኝታ ማግኘት ይቸግራል።በባህርዳር፣ በመቀሌ፣ በድሬዳዋ፣ በሐረሪ፣ በሐዋሳ… እንዲሁ ተመሳሳይ ነው፡፡
ሁለተኛውና ሌላው አብይ ጉዳይ አበሉ የሚከፈለው ለምግብ፣ ለመኝታ…ሆኖ ሳለ በደመወዝ መጠን ሠራተኞችን አበላልጦ የተለያዩ ክፍያዎችን የማሰቡ ተገቢነት ጉዳይ ነው።አንድ የመንግሥት ተቋም ሾፌር እና ሥራ አስኪያጅ ለመስክ ሥራ ሲወጡ ንጹህ ምግብ፣ ንጹህ መኝታ በማግኘት ረገድ በደመወዝ መጠን የሚሰላና አድልኦ የሚያስከትል የክፍያ ሥርዓት የሚተገበርበት አሠራር ትንሽ ለሰሚው ግራ ነው።እናም ለምግብና ለመኝታ ወጪ በደመወዝ ስኬል ከፍና ዝቅ ማለቱ በግሌ ትክክል ነው ብዬ አላምንም።አለቃና ምንዝሩም ጭምር ለመስክ ሥራ ሲወጣ ለሚበላበትና ለሚተኛበት አድልኦ አዘል የክፍያ ሥርዓት ማስቀመጥ የእኔ ሆድ፣ ከአንተ ሆድ ይበልጣል የሚል ትርጉም ከመስጠት የዘለለ ፋይዳ ያለው አመክንዮ ማቅረብ አያስችልም።እናም ለመስክ ሥራ የሚሰጥ የአበል ክፍያ ለሁሉም ሠራተኞች እኩል እንዲሆን ማድረግ ፍትሐዊነትን በማስፈን ረገድ ያለው ድርሻ ጉልህ ይሆናል፡፡
ለመሆኑ አዲሱ ማሻሻያ ምንን ያሳያል?
የሪፖርተር ዘገባ እንዲህ ይላል።የመንግሥት ሠራተኞች የቀን የውሎ አበል የደመወዝ ደረጃን መሠረት አድርጎ ለመስክ ሥራ መዳረሻ አካባቢዎች በተተመነ የክፍያ ሰንጠረዥ እንዲከፈል የሚያስገድድ መመሪያ ስለመውጣቱ ያወሳል፡፡
የሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን በዚህ ሳምንት ያወጣው መመሪያ የመንግሥት ሠራተኞች ከመደበኛ ሥራ ቦታ ክልል ውጪ ለሥራ ሲንቀሳቀሱ የሚከፈላቸው የቀን ውሎ አበል፣ መመሪያው ለመስክ ሥራ መዳረሻ አካባቢዎች ባስቀመጠው የተመን ሰንጠረዥና የሠራተኞች የደመወዝ ደረጃ መሠረት እንዲከፈል ይደነግጋል።
ለአብነት ለመቀሌ ከተማ የተተመነው ዝቅተኛው የቀን አበል 348 ብር ሲሆን፣ ከፍተኛው ደግሞ 468 ብር ነው። ይህም ማለት የሠራተኛው ወርኃዊ ደመወዝ ከ1,100 ብር እስከ 3,933 ብር ከሆነ ለመቀሌ ከተማ የተተመነውን ዝቅተኛ የቀን አበል የሚያዝ ሲሆን፣ ወርኃዊ ደመወዙ ከ9,056 ብር በላይ የሆነ ሠራተኛ ደግሞ ከፍተኛውን የቀን አበል ማለትም 468 ብር እንደሚያገኝ በመመሪያው ተደንግጓል።
ለአዲስ አበባ ከተማ የተተመነው የቀን አበል ከሁሉም አካባቢዎች ከፍተኛ ሲሆን፣ ወደ አዲስ አበባ ለመስክ ሥራ የተመደበ የመንግሥት ሠራተኛ ከላይ በተገለጸው ወርኃዊ የደመወዝ መጠን መሠረት የሚያገኘው ዝቅተኛ የቀን አበል 468 ብር ሲሆን፣ መካከለኛው 549 ብር ነው።ወርኃዊ ደመወዛቸው ከ9,056 ብር በላይ የሆኑት ደግሞ 724 ብር በቀን እንዲያገኙ ወስኗል። ከክልል ከተሞች ዝቅተኛ የቀን አበል የተተመነው ለጅግጅጋ ከተማ ሲሆን፣ ከላይ በተገለጸው ወርኃዊ የደመወዝ ደረጃ መሠረት ለጅግጅጋ የተተመነው መነሻ የቀን አበል 314 ብር፣ ከፍተኛው ደግሞ 404 ብር ነው።
በየክልሉ ሥር ለሚገኙ የዞን ዋና ከተሞች የቀን ውሎ አበል መጠንም በመመሪያው ተተምኖ የቀረበ ሲሆን፣ ከላይ በተገለጸው የደመወዝ ምጣኔ መሠረት በትግራይ ክልል ለሚገኙ የዞን ከተሞች የሚከፈለው ዝቅተኛ ወይም መነሻና ከፍተኛ የቀን አበል እንደ ቅደም ተከተላቸው 279 ብርና 417 ብር እንደሚሆን ተተምኗል። በተመሳሳይ በአማራ ክልል ለሚገኙ የዞን ከተሞች የተተመነው መነሻና ከፍተኛ የቀን አበል እንደ ቅደም ተከተላቸው 277 ብርና 409 ብር እንደሆነ በተመን ሰንጠረዡ ተገልጿል።
በመንግሥት ሠራተኞች የቀን ውሎ አበል ተመንና አከፋፈል ሥርዓት ላይ የሚኒስትሮች ምክር ቤት የካቲት 7 ቀን 2012 ዓ.ም ተወያይቶ ባሳለፈው ውሳኔና ለሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን በተሰጠው ሥልጣን መሠረት የወጣው መመሪያ፣ ከመንግሥት ተሿሚዎች በስተቀር ከፌዴራል እስከ ቀበሌ አስተዳደር እርከን ድረስ በአገር አቀፍ ደረጃ ተፈጻሚ እንደሚሆን ደንግጓል።
የውሎ አበል ተመኑ ምን አዲስ ነገር ይዟል?
አዲሱ የውሎ አበል ተመን አሁንም ከገበያው ጋር ሲነጻጸር በቂ ነው የሚባል አይደለም።ይኸም ሆኖ አሁን በሥራ ላይ ከነበረው አንጻር ሲነጻጸር ግን ከፍተኛ ለውጥ መሻሻል ማሳየቱ በጥሩነቱ መውሰድ ይቻላል።ለአብነት ያህል ለአዲስአበባ ከተማ የተያዘው የቀን ውሎ አበል ከፍተኛው 724 ብር ላይ ላዩን ሲታይ ብዙ ሊመስል ይችላል።
የዚህ አበል ተከፋይ ሊሆኑ የሚችሉት ግን በአመዛኙ በከፍተኛ አመራር ደረጃ ያሉ ባለሙያዎች ናቸው።እነዚህ ግለሰቦች ደግሞ ቢያንስ ንጹህ እና ደረጃው የጠበቀ እንዲሁም ለደህንነታቸው አስተማማኝ የሆነ መኝታ ለማግኘት በትንሹ ከብር 500 በላይ ክፍያ ሊጠብቃቸው እንደሚችል ሲታሰብ አበሉ አሁንም ያን ያህል ሊጨበጨብለት የሚችል አለመሆኑን ማስተዋል ይቻላል።
እዚህ ላይ መንግሥት የመክፈል አቅም የለውም፣ በሚል ተደጋግመው የሚነሱ ምክንያቶች አሉ።እነዚህ ምክንያቶች ግን ከአበል ክፍያ ጋር መገናኘታቸው ተገቢ ነው ብዬ አላስብም። አንድን የመንግሥት ሠራተኛ ከቤትህ ርቀህ ሥራዬን ሰርተህልኝ ና ብለህ ከላከው በኋላ ለሚጠጣበትና ለሚበላበት በቂ ገንዘብ መንፈግ ሥጋ ሰጥቶ ቢላዋ እንደመከልከል ይቆጠራል።ሰፋ ተደርጎ ሲታይም ኢ-ሰብዓዊነት ይሆናል።በሌላ በኩልም አሁንም አበል በተጨመረ ማግስት የከዚህ በፊቱ ዓይነት ሕጋዊ መሰል ስርቆቶች የሚቀጥሉ ከሆነ መንግሥት ከኪሳራ በስተቀር የሚያተርፈው አይኖርምና ቢታሰብበት ለማለት ነው፡፡
በዚህ አጋጣሚ ታክስ የሚጣልበትና የማይጣ ልባቸው የውሎ አበል ዓይነቶችን በተመለከተ ከገቢ ዎች ሚኒስቴር ያገኘሁትን መረጃ አጋርቼ ልሰናበት፡፡
የውሎ አበል ከግብር ነፃ የሚደረግበት ሁኔታ
1.በሀገር ውስጥ ለሚደረጉ ጉዞዎች የሚከፈል ውሎ አበል፤
ሀ. አንድ ተቀጣሪ የሚከፈለው የቀን ውሎ አበል ከገቢ ግብር ነፃ የሚደረገው ከብር 500 ወይም ከደመወዙ 4 በመቶ ከሁለቱ ከፍተኛ ከሆነው መጠን ባልበለጠ ብቻ ነው፡፡
ለ. ለፊደል ተራ ሀ አፈፃፀም አንድ ተቀጣሪ የአልጋ አበል ያለገደብ ወይም በተወሰነ ገደብ በደረሰኝ የሚወራረድለት ከሆነ በደረሰኝ መሠረት ለአልጋ የተከፈለው ገንዘብ ከግብር ነፃ የሚደረግ ሲሆን ለቁርስ፣ ምሳ፣ እራት የመሳሰሉ ወጪዎች የሚሰጠው የውሎ አበል ከግብር ነፃ ሊደረግ የሚችለው ከብር 300 ወይም ከደመወዙ 2 ነጥብ 5 በመቶ ከሁለቱ ከፍተኛ ከሆነው መጠን ባልበለጠ ብቻ ነው፡፡
ሐ. ለማንኛቸውም ድርጅት ሥራ አስኪያጅ ወይም ምክትል ሥራ አስኪያጅ የሚከፈለው የውሎ አበል ከግብር ነፃ የሚደረገው ከብር 1000 ወይም ከወርሓዊ ደመወዙ 5 በመቶ ከፍተኛ ከሆነው መጠን ባልበለጠ ብቻ ነው፡፡
መ. ለፊደል ተራ ሐ አፈፃፀም አንድ ሥራ አስኪያጅ ወይም ምክትል ሥራ አስኪያጅ የአልጋ አበል ያለገደብ ወይም በተወሰነ ገደብ በደረሰኝ የሚወራረድለት ከሆነ በደረሰኙ መሠረት ለአልጋ የተከፈለው ገንዘብ ከግብር ነፃ የሚደረግ ሲሆን ፣ ለቁርስ ምሳ፣ እራት እና ለመሳሰሉ ወጪዎች የሚሰጠው የውሎ አበል ከገቢ ግብር ነፃ የሚደረገው ከብር 600 ወይም ከወርሓዊ ደሞዙ 3 በመቶ ከፍተኛ መጠን ባልበለጠ ብቻ ነው፡፡
2. ወደ ውጭ ሀገር ለሚደረጉ ጉዞዎች የሚከፈል የውሎ አበል፣
ሀ. አንድ ተቀጣሪ የተቀጠረበትን ሥራ ለማከናወን ወደ ውጭ ሀገር ለሚያደርገው ጉዞ የሚከፈለው የውሎ አበል ከገቢ ግብር ነፃ የሚደረገው መንግሥት ከተሿሚዎች ወጪ ለሌሎች ተቀጣሪዎች ከወሰነው የውሎ አበል ልክ ባልበለጠ ብቻ ነው፡፡
ለ.የማናቸውም ድርጅት ሥራ አስኪያጅ ወይም ምክትል ሥራ አስኪያጅ ከድርጅቱ ሥራ ጋር በተገናኘ ወደ ውጭ ሀገር ለሚያደርገው ጉዞ የሚከፈለው የውሎ አበል ከገቢ ግብር ነፃ የሚያደርገው መንግሥት ከተሿሚዎች ውጪ ለሌሎች ተቀጣሪዎች በወሰነው የውሎ አበል ልክ ላይ 20 በመቶ ተጨምሮበት ይሆናል፡፡
3. ለተራ ቁጥር 2 ድንጋጌ ቢኖርም በሀገር ውስጥ ለሚደረግ የሥራ እንቅስቃሴ የኮንስትክሽን ማሽነሪ ኦፕሬተሮች የሚከፈል የውሎ አበል ከ25 ኪ.ሜ ባነሰ ወይም በበለጠ ርቀት ቢሆንም የተከፈለው የውሎ አበል ከግብር ነፃ ይሆናል፡፡
4. በተራ ቁጥር 2 እና 3 የተገለፀው ቢኖርም የመንግሥት መስሪያ ቤት ለተሿሚዎች እና ለተቀጣሪዎቻቸው ከመደበኛ የሥራ ቦታቸው ውጪ ከ25 ኪሎ ሜትር በላይ ርቀው በመሄድ ለሚያከናውኑት ሥራ የሚከፍሉት የቀን ውሎ አበል ሙሉ በሙሉ ከግብር ነፃ ተደርጓል፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 18 / 2012
ፍሬው አበበ