ከጥንት አንስቶ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ለሠርግ፣ ለኀዘን፣ ለልደትና ለሌሎችም መሰል አጋጣሚዎች ጥይት የመተኮስ ልማድ አለ። አሁን ደግሞ ተኩስና ፉከራ የሚበዛባቸው የሙዚቃ ቪዲዮዎች ሕዝቡን እንደ አዲስ በጦር መሣሪያ ፍቅር እንዲነደፍ ያደረጉት ይመስለኛል። የጦር መሣሪያ ወልዋዩ ቤትን ለማጽዳት መስታወት ከሚወለውለው ኅብረተሰብ ልቋል። ምንም የማያውቁ ሕፃናትን የጦር መሣሪያ በማስታጠቅ ፖለቲካዊ መልዕክቶችን ለማስተላለፍ ጥረት ሲደረግም ተመልክተናል።
እርጅና የተጫናቸው እናቶች መቋሚያቸውን ጥለው ክላሽንኮቭን ምርኩዝ ሲያደርጉ እጁን በአፉ ያልጫነ ማን አለ? እንደ ጊዜያዊ መፍትሔ ከመሣሪያ ጋር በፍቅር የወደቁትን እየመለመሉ ሚሊሻ፣ ፖሊስ፣ ልዩ ኃይልና መከላከያ እናድርግ ከተባለ ከሃይማኖት አባቶች ውጪ ያለው ሕዝብ ሁሉ የጸጥታ ኃይል ሊሆን ነው። ምን ይሻለናል ጃል?
በሂደት እንደ ምዕራባውያን ሕዝብ በሚሰበሰብባቸው ቦታዎች ተኩስ የሚከፍቱ ዜጎችን እንዳናፈራ ያሰጋኛል። ብዙ ነገሮች በተሟሉባት አገር የመንፈስ ጭንቀት ውስጥ የሚገቡ ሰዎች ሌሎች ላይ ከተኮሱ፣ መሠረታዊ ፍላጎቱን ለማሟላት ላይ ታች የሚል፤ የምግብ ዋስትናውን ያላረጋገጠ፤ የኤሌክትሪክና ንጹህ ውሃ አገልግሎት የማያገኝ በ10 ሚሊየኖች የሚቆጠር ሕዝብ ያላት አገር ውስጥ ምን ሊፈጠር እንደሚችል መገመት ቀላል ነው። ጡት አስጥል እንደሚባለው ሁሉ መሣሪያ አስጥል እጽ ቢኖር ምን ነበረበት።
ሰዎች ለጦር መሣሪያ ያላቸው ፍቅር ጣሪያ የነካበትን ይህን ዘመን በትክክል የሚገልጸው የመልካሙ ተበጀ ሙዚቃ ነው። እስቲ ትንሽ ላንጎራጉረው፡-
ጨምሯል ፍቅር ጨምሯል፤
ጨምሯል መውደድ ጨምሯል፤
ቤልጂግ ንሯል ፍቅር ጭም ሯል፤
ሽጉጥ ንሯል ፍቅር ጨም ሯል …
ለጦር መሣሪያ ፍቅር እጁን የሰጠ አንድ ወጣት በሠርጉ ቀን እንዲያጅቡት ለመጠየቅ ለወዳጆቹ ያደረሳት የአጃቢነት የጥሪ ካርድ ሰሞኑን ማህበራዊ ድረ ገጽ ላይ ስትዘዋወር አፈፍ አደረኳት። እንዲህ ትነበባለች፡-
አጃቢ
«እኔ ጀግናው ፍቅሩ ጠናብኝ (ስሙ ተቀይሯል) ዘንካታዋን እከሊትን ላገባት ነው!! የጋብቻ ሥነ-ሥርዓቴ የሚፈጠመው የካቲት ስምንት ስለሆነ ጠብ እርግፍ ብዬ ካሰናዳሁት ሠርጌ ላይ ከአራት ሰዓት ጀምሮ በኞቫ ሆቴል ከነ አውቶማቲክ ክላሽ ጠመንጃህ፤ ካልሆነም ከነዲሞትፈርህ፤ እሱም ባይሆን ከነምንሽርህ፤ ቢጠፋ ቢጠፋ ሽጉጥ ይዘህ ድግሴ ላይ ተገኝተህ እንድታጅበኝ በአክብሮት ጠርቼሃለሁ።»
እንግዲህ የተባለውን መሣሪያ ታጥቆ የመጣው አጃቢ በየመሃሉ መሣሪያውን መፈተሹ ግድ ነው። በተለይ በልቶ ከጠጣ በኋላ ምን ሊፈጠር እንደሚችል አስቡት። እንኳን በሞቅታ ምንም ሳይቀመስም በተለያዩ ክብረ በዓሎች ላይ በሚተኮሱ ጥይቶች የንጹሃን ሕይወት ይቀጠፋል። በተደጋጋሚ ለኀዘንና ለደስታ በተተኮሱ ጥይቶች የሰዎች ሕይወት ማለፉን የሚገልጹ ዜናዎች ሰምተናል።
ባሳለፍነው ሳምንት በባህር ዳር ከተማ በለቅሶ ላይ የተተኮሰ ጥይት የሌላ ሰው ሕይወት አጥፍቷል። ለቅሶ የነበረውም በተመሳሳይ በጥይት ሕይወቱ ላለፈው ሰው ነበር። የካቲት 17 ቀን 2011 ዓ.ም በማዕከላዊ ጎንደር ዞን አዘዞ ጠዳ ክፍለ ከተማ ሠርግ ለማድመቅ ከቤተ ዘመድ የተተኮሰ ጥይት የሙሽሪትን ሕይወት ቀጥፎ ደስታው ወደ ኀዘን ተቀይሯል። የዛሬ ዓመት በየካቲት ወር በቢሾፍቱ አቅራቢያ በሊበን ዝቋላ ወረዳ በምትገኘው ትንሿ የገጠር ከተማ አሹፌ የአንድ ሆቴል ምርቃት ላይ የተገኙ ታዳሚዎች በደስታ ወደላይ ሲተኩሱ በመሃል መድረክ ላይ ሙዚቃ ሲጫወት የነበረ ታዋቂው ኦሮምኛ ዘፋኝ ልቡን ተመቶ ሕይወቱ አልፏል።
ስለድምጻዊው አሟሟት መረጃ የሰጡ አንድ ኢንስፔክተር በሃይማኖት አባቶችና በገዳዎች ምክር ጭምር ጥይት መተኮስ ቀርቶ እንደነበር ተናገሩ። ቀጠሉና ለውጡን ተከትሎ በተለያዩ በዓላትና አከባበሮች ላይ ደስታንም ሆነ ኀዘንን ለመግለፅ መተኮስ እንደተጀመረ ገለጹ። የፈረደበት ለውጥ አዋዜ ሆኗል።
ይልቅ የኢንስፔክተሩ ንግግር ከለውጡ አምስት ዓመታት ቀደም ብሎ የሆነን ነገር አስታወሰኝ። ነሐሴ 14 ቀን 2004 የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር መሞታቸው ከተሰማ በኋላ በአርባ ምንጭ ከተማ በመንግሥት ባለሥልጣናት ትዕዛዝ በተዘጋጀው የኀዘን ዝግጅት ላይ የአካባቢው ታጣቂዎች በሙሉ ለኀዘን መግለጫ የሚሆን ጥይት እንዲተኩሱ ታዘዙ። በኀዘን መግለጫው ዝግጅት ወቅት የከተማው ታጣቂዎች በሙሉ እንዲተኩስ፣ ያልተኮሱ የመሣሪያ አፈሙዝ እየተሸተተ መሣሪያውን እንዲያወርድ ማስጠንቀቂያ ተሰጠ።
በወቅቱ በተተኮሱ ጥይቶች አንድ አዋቂ ወዲያውኑ ሲሞት አንድ ወጣት ደግሞ ቆስሎ ሆስፒታል ገባ። የመንግሥት ባለሥልጣናትም በመገናኛ ብዙኃን ቀርበው፤ ሕዝቡ በመሪው ሞት በከፍተኛ ሁኔታ በማዘኑ በተተኮሰው ጥይት ሰው እንደሞተና የሰው መሞትም ይሁን መቁሰል ከሕዝቡ ኀዘን ብዛት የተከሰተ እንደሆነ ሲገልጹ ተሰምተዋል። መንግሥትም እንዲህ ያለ ትዕይንት አካል ሆኖ ያውቃል ለማለት ያህል ነው።
ህዝቡ የጦር መሣሪያ ፍቅር ብቻ ቢኖረው ችግር አልነበረውም። ችግሩ ጦር መሣሪያም አለው። በሕገ ወጥ መንገድ ወደ አገሪቱ የሚገባው የጦር መሣሪያ ብዛት የትየለሌ ነው። በተለያየ መንገድ ሲዘዋወር ተያዘ ከሚባለው የሚልቅ የጦር መሣሪያ ተሽሎክሉኮ አፍቃሪዎቹ ዘንድ እንደሚደርስ ጥርጥር የለውም። የቁጥጥሩ ነገር አልሆነልንም። ከወራት በፊት በቦቴ መኪና የጦር መሣሪያዎች ተደብቀው ሲገቡ መያዙን ተከትሎ ሸገር ሬዲዮ ተመሳሳይ ችግር እንዳይፈጠር እንዴት ነው የምትከላከሉት ብሎ ለፌዴራል ፖሊስ የሕዝብ ግንኙነት ጥያቄ ሲያቀርብ፣ ባለሥልጣኑ ቆፍጠን ብለው «አሁንም የያዝነው ኅብረተሰቡ ጠቁሞን ነው እንጂ እኛ የምንቆጣጠርበት መንገድ የለንም» ብለው እርፍ ብለዋል።
እነዚህ የጦር መሣሪያዎች ጽንፈኛ የፖለቲካ ኃይሎች እጅ መግባታቸው አይቀሬ ነው። እንዲያውም ትጥቅ ፈትተው ገቡ የተባሉት አካላት የጦር መሣሪያ እየናፈቃቸው (ስጋት እየተሰማቸው) መሣሪያዎቻቸውም ትጥቅ እየፈቱ (ያለ ጥይት) ወደ አገር ቤት እንዲገቡ እያደረጉ ነው ይባላል። ይህ ማለት ደግሞ ሰላም ሚኒስቴር ሰላምን ማስፈን አይችልም ማለት ነው።
ካሳለፍነው ሳምንት እስከ ትናንትናዋ ዕለት ድረስ ብቻ እንኳን የተለያዩ የጦር መሣሪያ ጥቃቶች ተፈጽመዋል። በቡራዩ ከተማ አስተዳደር አቅራቢያ በሚገኝ አንድ ሆቴል ምሳቸውን እየተመገቡ የነበሩት የከተማው ፖሊስ አዛዥ፣ የፊንፊኔ ዙሪያ ልዩ ዞን የኦሮሚያ ልዩ ኃይል አዛዥ እንዲሁም ሌላ የፖሊስ አባልና ድምጻዊ ላይ ተኩስ ተከፍቶባቸው ኮሚሽነሩ ሲገደሉ ሌሎቹ ቆስለዋል። በአምቦ ከተማ ለብልጽግና ፓርቲ ድጋፋቸውን ለመግለጽ የወጡ ሰልፈኞች ላይ በተወረወረ ቦምብ 29 ሰዎች ቆስለዋል። በጊንጪ አንድ ፖሊስ ጣቢያ ላይ ቦምብ ተወርውሮ እምብዛም ጉዳት ሳያደርስ ቀርቷል።
የጦር መሣሪያ አስተዳደርና ቁጥጥር አዋጅ መሰናዳቱ ጥሩ ነገር ነው። ወሳኙ ጉዳይ አዋጁን በትክክል ሥራ ላይ ማዋልና የተጠናከረ ቁጥጥር ማድረግ ነው። ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴርም የአገሪቱ ሉዋላዊ ድንበር ተከብሮ እያለ ነጋ ጠባ የጦር መሣሪያ እየያዙ የሚያንጎራጉሩ ድምጻውያንን አንድ ይበልልን። እንዲህ ያለው የኪነት አቅም ያለአግባብ ባክኖ ተለምዶ ሲያበቃ ይሰለችና ቀን ግድ ያለ ዕለት 24 ሰዓት በየቴሌቪዥን ጣቢያው ሲለቀቅ ተፈላጊውን ውጤት እንደማያመጣ ተረድቶ መፍትሄ ቢያመጣ ይበጃል።
አዲስ ዘመን የካቲት 18 / 2012
የትናየት ፈሩ