በሸገር ከተማ ለዘንድሮው አረንጓዴ አሻራ 17 ሚሊዮን ችግኞች ለተከላ ዝግጁ ሆነዋል

ሸገር፡- በሸገር ከተማ ለአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር 17 ሚሊዮን የተለያዩ የችግኝ ዓይነቶች ለተከላ መዘጋጅታቸው የሸገር ከተማ ግብርና ቢሮ ገለጸ፡፡ በሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር በአንድ ሺህ 51 ሄክታር መሬት የአፕል እና የአቮካዶ ችግኝ እንደሚተከል ተጠቁሟል፡፡

የሸገር ከተማ የግብርና ቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ ደጀኔ በቀለ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፤ በከተማው በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር 20 ነጥብ 9 ሚሊዮን የተለያዩ የችግኝ ዓይነቶች ለመትከል ታቅዷል፡፡

በ2017 ዓ.ም በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ለመትከል ከታቀዱ ችግኞች 50 በመቶ የተለያዩ ፍራፍሬዎችን እና 30 በመቶውን ደግሞ ሀገር በቀል ዛፎችን ለመትከል መታቀዱን በመግለጽ፤ አጠቃላይ ለመትከል ከታቀደው ችግኝ 17 ሚሊዮን የተለያዩ የችግኝ ዓይነቶች መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል፡፡

የችግኝ ተከላው የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎችን፣ ተቋማትን እና የመንግሥት ሠራተኛውን በማሳተፍ እንደሚከናወን ጠቁመው፤ ከሰኔ ወር አንስቶ የችግኝ ተከላው በመጀመሩ እስከ ሐምሌ አምስት ቀን 2017 ዓ.ም ለማጠናቀቅ መታቀዱን ጠቁመዋል፡፡

ከአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በተጨማሪ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እንደ ቢሮ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሠራ መሆኑን የተናገሩት አቶ ደጀኔ፤ በአረንጓዴ አሻራ በተጀመረው የፍራፍሬ ችግኝ ተከላ በክላስተር አንድ ሺህ 51 ሄክታር መሬት ላይ የአፕል እና የአቮካዶ ችግኝ እንደሚተከል ተናግረዋል፡፡

ምክትል ኃላፊው እንደተናገሩት፤ እስከ ሰኔ 20 ቀን 2017 ዓ.ም በሚቆየው የአረንጓዴ አሻራ የፍራፍሬ ችግኝ ተከላ መርሃ ግብር 821 ሄክታር መሬት ላይ የአፕል ችግኝ በስፋት ይተከላል፡፡ እንዲሁም ደግሞ በ221 ሄክታር መሬት ላይ የአቮካዶ ችግኝ በመትከል፤ እንደ አጠቃላይ አንድ ሺህ 51 ሄክታር መሬት በአቮካዶና በአፕል ችግኝ ለመሸፍን ታቅዷል።

በሸገር ከተማ ከሚገኙ 12 ክፍለ ከተማዎች ሰባቱ ደጋማ የአየር ፀባይ እንዳላቸው በመጥቀስ፤ በእነዚህ ሰባት ክፍለ ከተማዎች 921 ሺህ የአፕል ችግኝ እና ወይናደጋ አየር ጸባይ ባለባቸው አምስት ክፍለ ከተማዎች 70 ሺህ የአቮካዶ ችግኝ እንደሚተከል አመላክተዋል።

ኢትዮጵያ እስካሁን የአፕል ምርት ከውጭ ሀገር እንደምታስገባ ያነሱት ምክል ኃላፊው፤ የፍራፍሬ ተከላው የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እና ምርትና ምርታማነትን ከማሳደግ ባለፈ እንደ ሀገር የአፕል ምርት ኤክስፖርት ለማድረግ እንደሚያስችል ጠቁመዋል።

ማኅበረሰቡ የደን ችግኞችን ከመትከል በተጨማሪ፤ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በጓሮ ሆነ በሌሎች አካባቢዎች የፍራፍሬ ችግኞችን እንዲተክል እና እንዲንከባከብ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

በከተማው ሰኔ 5 ቀን 2017 ዓ.ም በተደረገው የአፕል ችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ላይ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት አባላት፣ ጋቻና ሲርናዎች( ደንብ አስከባሪዎች) እና የአካባቢው ነዋሪዎች ተሳትፈውበታል።

ዓመለወርቅ ከበደ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሰኔ 7 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You