«አንድ ሰው ጠዋት ተነስቶ የራሱን ጥፍር ቢያስተካክል፣ ቁርሱን ሰርቶ ቢበላ በጎ ፈቃድ ሰራ አይባልም። አንድ ሰው በጎ ነገር አደረገ የሚባለው የራሱን ጊዜ፣ የራሱን ዕውቀትና ሀብት ሰውቶ ሌላ ወንድሙን ወይም እህቱን ሲያግዝ ነው። በጎ የሚለው ቃል የሚሰራው ለሁለተኛ ወገን ነው። በጎነት ራስን በመንከባከብ፤ ለራስ መልካም ነገር በማድረግ የሚታይ ሳይሆን፤ ለሌሎች ጥሩ ሥራ በመሥራት የሚገለጽ ነው።
«…እያንዳንዱ አገራት እኔ ሞቼ አገር ይቀጥል የሚሉ ጀግኖች ባይኖራቸው ኖሮ ኢትዮጵያ አሁን ያላትን ቅርጽ ማግኘት አይቻልም ነበር። እናቶች ጊዜያቸውን አባክነው ልጆቻቸውን ለማሳደግ ባይወስኑ ትውልድ አይቀጥልም ነበር።…» በማለት ወርቃማ ዕድል የገጠማቸው የበጎ ፈቃድ አገልጋዮች በአፍሪካ ህብረት አዳራሽ ተሰብስበው የአደራ ቃል ከኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ በተሰጣቸው ወቅት የተላለፈላቸው መልዕክት ነበር።
አዎ እኒህ ወጣቶች በሚሰማሩበት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሥራ ላይ የሚያበረክቱት አስተዋጽኦ የትዬለሌ የሚሆነው በጎ ለማድረግ አእምሯቸውን ባዘጋጁት መጠን ልክ ነው። መልካም ለመስራት የተዘጋጀ ምንም የሚያግደው ባለመኖሩ ያሰበውን ያሳካል።
የተባበሩት መንግሥታት የበጎ ፈቃደኞች ፕሮግራም በጎ ፈቃድን እንዲህ ሲል ይገልጸዋል። «በጎ ፈቃድ የሁሉም ሥልጣኔና ማህበረሰብ አካልና ውጤት ነው። ጽንሰ ሀሳቡ ሲተነተን እያንዳንዱ ሰው ያለ ትርፍ ፍለጋ፣ያለ ክፍያ፣ ሙያዊ አጽንኦት ባልተጫነው ሁኔታ ግለሰቦች ለጎረቤታቸው፣ ለማህበረሰባቸውና ለሕዝብ በጠቅላላ የሚያበረክቱትን አስተዋጽኦ ያመላክታል። ይህ አስተዋጽኦ ደግሞ በተለያዩ መስኮች በተግባር ሊተረጎም የሚችል ሲሆን፤ እንደምሳሌም በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውሶች ወቅት እርዳታን በማሰባሰብ፣ በግጭቶች ወቅት መረጋጋትን በማስፈን፣ እርቅ በማውረድና ድህነትን በማስወገድ ተግባር ውስጥ በመሳተፍ ለውጥ ማምጣት ይቻላል»።
በበጎ ፈቃድ ዘርፍ ሩዋንዳውያን የሚያከናውኑት ተግባር በአብነት ይጠቀሳል። የተባበሩት መንግሥታት የልማት ፕሮግራም እ.አ.አ. በ2016 ያወጣው መረጃ እንደሚያመለክተው «በጎ ፈቃደኝነት ለሩዋንዳውያን የባህላቸው አንድ አካል ሆኗል። የአገሪቱን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ለማቃለልም በጎፈቃደኝነት ትልቁን ድርሻ ይዟል።
በየወሩ የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ፖል ካጋሜን ጨምሮ ሚኒስትሮችና ሌሎች የኅብረተሰብ ክፍሎች በተዋረድ የሚሳተፉበት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሥራ ይሠራል» ሲል ያወድሳቸዋል።
በኢትዮጵያም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የበጎ ፈቃደኛነት አገልግሎት የሚሰጡ ወጣቶች ቁጥር እየተበራከተ መጥቷል። በተለይ ትምህርት ቤቶች በሚዘጉበት በክረምት ወቅት በርካታ ወጣቶች ትርፍ ጊዜያቸውን የበጎ ፈቃደኝት አገልግሎት በመስጠት ለሀገራቸው እድገትና ልማት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እያበረከቱ ነው።
ባለፉት ዓመታት በአገር አቀፍ ደረጃ ከ10 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች በደም ልገሳ፣ በትምህርት፣ በአካባቢ ልማት፣ በትራፊክ ደንብ ማስከበር አገልግሎት፣ በምርት ስብሰባና በሌሎች የሥራ መስኮች ተሰማርተው ወገኖቻቸውን ሲደግፉ እንደነበር ከኢፌዴሪ ወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር ድረ ገጽ ያገኘነው መረጃ ያስረዳል።
ሰሞኑን ለበጎ ፈቃድ አገልግሎት ስምሪት ሥልጠና ለመከታተል የታጩት ወጣቶች ዘርፈ ብዙ ሥራ ይጠብቃቸዋል። የበጎ ፈቃድ አምባሳደሮች ተብለው ዕውቅና በተሰጣቸው መልካም አሳቢዎች የሚያገኙት ሥልጠና ቀጣይ ሥራቸውን የተቃና ለማድረግ የሚያስችላቸውን ሰብዕናና ክህሎት እንደሚላበሱ ከወዲሁ ተተንብዮአል።
በርግጥም እነዚህ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ልዑካን በሚሰማሩበት ሥፍራ ለሚያበረክቱት አስተዋጽኦ የኅብረተሰቡ ድርሻ የጎላ ሊሆን ይገባል። እነዚህ ወጣቶች በደረሱበት ሥፍራ ሁሉ መልካምን ለማድረግ ሲሰማሩ ሊደግፉት የተላኩለት ልጆቹን በመልካም አይቶና እንደራሱ ልጅ ተመልክቶ ከእነርሱ የሚደረግለትን ድጋፍ በጸጋ በመቀበል የበኩሉን ድጋፍ ማድረግ ይጠበቅበታል።
በበጎ አድራጎት ተግባር የሚሰማሩትም አገልግሎት የሚሰጡት ለራሳቸው ወገን እንደሚሆን አውቀውና ቃልኪዳናቸውን ጠብቀው መልካምን በማድረግ ተወዳጅነትንና ዝናን ማትረፍ ቀዳሚ ተግባራቸው ሊያደርጉት፤ ተናፋቂነትንም ማስረጽ ይጠበቅባቸዋል።
አዲስ ዘመን የካቲት 18/2012