በሀገራችን ሁለት ዓመታትን ሊያስቆጥር የአንድ ወር እድሜ የቀረው ለውጥ ያስገኘውን ድልና የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ጠቅላይ ሚኒስትርን አመራር በመደገፍ ሰሞኑን በተለያዩ ክልሎች የድጋፍ ሰልፎች ተካሂደዋል።
ከአንዱ በስተቀር ሁሉም ሰልፎች ህዝቡ ድጋፉን በማረጋገጥ በሰላም ተጠናቅቀዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩም ለዚህ የህዝብ ድጋፍ ምስጋናቸውን ገልፀዋል። ሌሎች የፖለቲካ ሃይሎች በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የጠሯቸው የድጋፍ ሰልፎችና የአዳራሽ ውስጥ ስብሰባዎችም እንዲሁ በሰላም መካሄዳቸውን የመገናኛ ብዙሃን ዘገባዎች ያመለክታሉ።
የፖለቲካ ፓርቲዎችና አክቲቪስቶች እንደ አሸን በፈሉባት እና የተለያየ አመለካከት በነፃነት በሚንሸራሸርባት ሀገር የድጋፍ ሰልፎቹና የስብሰባዎቹ በሰላም መካሄድ የፖለቲካ ባህሉ እየጎለበተ ለመምጣቱ አንድ ማሳያ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል።
ከእነዚህ ስኬታማ መድረኮችና ሰልፎች በተፃራሪው ደግሞ በአንዳንድ የኦሮሚያ ክልል ከተሞች በመንግሥት ባለሥልጣናት እና ለድጋፍ ሰልፍ በወጣ ህዝብ ላይ ጭምር ጥቃት የተፈፀመበት ሁኔታ ተስተውሏል።
በዚህም በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ዞን አምቦ ከተማ ባለፈው እሁድ ለውጡን እና የጠቅላይ ሚኒስትሩን አመራር በመደገፍ በወጡ ፈረሰኞች ላይ በተፈፀመ የቦንብ ጥቃት በ29 ሰዎች ላይ ቀላል ጉዳት ደርሷል፤ ከእነዚህም መካከል 28ቱ ህክምና አግኘተው ወደ ቤታቸው መመለሳቸውን መረጃዎች አመልክተዋል።
በተመሳሳይ በቡራዩ ከተማ ሰሞኑን በተፈፀመ ግድያ የቡራዩ ከተማ አስተዳደርና ፀጥታ ጽህፈት ቤት ሃላፊ ተገድለዋል፤ ሌሎች ሦስት ሰዎችም ቆስለዋል። ተመሳሳይ እርምጃዎች በምዕራብ ሸዋ ዞን ጀልዱ እንዲሁም በነቀምት መፈፀማቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ። በምዕራብ ወለጋ አካባቢም መሰል ድርጊቶች ሲፈፀሙ መቆየታቸው ይታወቃል።
የፖለቲካ ፓርቲዎች ከዱርና ከስደት እንዲሁም ከሀገር ውስጥ ተሰባስበው ስለዴሞክራሲ እየሠሩ ባሉበት በአሁኑ ወቅት እነዚህ ድርጊቶች መፈፀማቸው በእጅጉ ያሳዝናል። በዚህ የውይይት ዘመን መሣሪያ ይዞ መነሳት የመሸነፍ ምልክት መሆኑ ሊታወቅ ይገባል። ለዚያውም ውይይቱ ገና ውሃው ባልሞቀበት ሁኔታ የመሸነፍ ምልክት ማሳየት የመወዳደር ብቃት ማነስንም ያመለክታል።
በመወያያትና በዴሞክራሲ የዳበረች ሀገር ለመገንባት ራዕይ ተሰንቆ እየተሠራ ባለበት ወቅት መሣሪያ አንስቶ ግድያ መፈፀም፣ የጥቃቱ ፈፃሚዎች ራሳቸው የሚፈልጉትን ዓላማም አያሳካም።
በሀገራችን በ1966 ለውጥ ማግስት ከውይይት ይልቅ ባለሥልጣኖችን በመግደል ደርግን ለማንበርከክ የተደረጉ ሙኩራዎች ትውልድን በሉ እንጂ ያስገኙት ፋይዳ አልነበረም። ይህ ታሪክ መደገም አልነበረበትም። ዴሞክራሲ በጠማቸው ወገኖች የመጣው ይህ ለውጥ በዚህ አይነቱ የፈሪ ዱላ የሚደናገጥ አለመሆኑም መገንዘብ ይገባል።
ሀገሪቱ ምርጫ ለማካሄድ በዝግጅት ላይ ትገኛለች። በዚህ ዓላማን ማሳካት ይቻላል። ከዚህ በመለስ ግን በዚህ ወሳኝ የፖለቲካ ምዕራፍ ላይ ዜጎችን መግደልና ህዝብንና ሀገርን የሚያሸብር ድርጊት መፈፀም በራሱ ከባድ ወንጀል ነው።
መንግሥት ይህን ዘግናኝ ድርጊት የፈፀሙ አካላትን አድኖ በመያዝ የሕግ የበላይነትን ማረጋገጥ ይኖርበታል። በተጠርጣሪዎቹ ላይ አስፈላጊውን ምርመራ በማድረግና የሕግ የበላይነትን በማስከበር በግድያ የፖለቲካ አላማን ማሳካት እንደማይቻል ለሌች ማስገንዘብም ይገባዋል።
መንግሥት ግጭት እንዲቀሰቀስ በማድረግ እና በመሳሰሉት የሰው ህይወት እንዲጠፋ ፣ መፈናቀል እንዲደርስ ሀብትና ንብረት እንዲወድም አድርገዋል በሚል በርካታ ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ሥር በማዋል ጉዳያቸውን በፍርድ ቤት እየተመለከተ መሆኑ ይታወቃል።
አንዳንድ ተጠርጣሪዎች ጉዳያቸው ተጣርቶ ነፃ ተብለው የተለቀቁበት ሁኔታ ቢኖርም፣ እስከ አሁን ውሳኔ አግኝተው የተቀጡ ወንጀለኞች ግን የሉም። በቁጥጥር ሥር ያልዋሉ ተጠርጣሪዎችም በርካታ ናቸው። በጠቅላይ ሚኒስትሩ ላይ ጭምር ተመሳሳይ ድርጊት ፈፅመዋል የተባሉ ተጠርጣሪዎች ጉዳይ አሁንም ድረስ ውሳኔ አላገኙም።
የተጠርጣሪዎቹን ጉዳይ በማፋጠን ጥፋተኞች አንዲቀጡ ማድረግ ላይ በትኩረት መሠራት ይኖርበታል። ይህ ሲሆን ተመሳሳይ ድርጊት ሊፈፀም የሚችልበት ዕድል ይጠባል። ሰሞኑን በተፈፀሙ የግድያ እርምጃዎች የተጠረጠሩትንም በቁጥጥር ሥር በማዋል እና ለሕግ አቅርቦ ውሳኔ እንዲሰጥ በማድረግ በሃይል ፍላጎትን ማስፈፀም እንደማይቻል ማሳየትና ዓላማን ማሳካት የሚቻለው በውይይት እና በውይይት ብቻ መሆኑን ማስገንዘብም ይገባል።
አዲስ ዘመን የካቲት 17/2012