ሰላም በኪሎ ሜትር ወይም በሜትር አይለካም፤ ውድ እና ተፈላጊ ነው ተብሎም እንደ ወርቅ በግራም ወይም በወቄት አይመዘንም፤ አይሰፈርም። ምክንያቱም ሰላም ከሰዎች ህልውና ከመውጣት ከመግባት ጋር የተሳሰረ ወሳኝ ጉዳይ ነውና የሰላም ዋጋ ከምንም ከማንም በላይ ውድ ነው።ዋጋ አይወጣለትም፣ አይለካም ፤ አይሰፈርም። ስለሆነም ሁሉም ሰው ሰላምን ሊጠብቅ፣ ስለሰላም ሊያስብና ሊያስተምር ያስፈልጋል።
የሰላም ማጣት ኑሮን ያቃውሳል። ዕቅድን ያፈርሳል። አላማን ያስታል፤ የመኖር ተስፋን ያስቆርጣል። ሰዎች ተረጋግተው እንዳይኖሩ፣ እንዳይተማመኑና ሁሉንም ነገር በጥርጣሬ እንዲመለከቱ ጭምር በማድረግ ያልተረጋጋ ኑሮን እንዲገፉ ያስገድዳል።
ይሄ ደግሞ ስርዓት አልበኝነት እንዲፈጠር ህግ፣ እንዳይከበርና የታሰበው የብልጽግና ጎዳና እንዲጨናገፍ ምክንያት ይሆናል።ስለዚህ ለሰላም የሚሰጠው ዋጋ ከሁሉ ነገር በፊት የቀደመ ፤ ደረጃውም ከፍ ያለ መሆን አለበት። ስለዚህ ሁላችንም ሰላማችንን ለመጠበቅ ለሰላም ዘብ መቆም ይገባናል።
የሰላም መደፍረስ ሀገርን ሲያፈራረስ፣ ዜጎችን ለስደት፣ ለሞትና እንግልት ሲዳርግ አይተናል።ሰላም ማጣት ምን አይነት አስከፊ እንደሆነ በየሀገሮቻቸው በጦርነት በሚናጡ ፣ የጥይት ናዳ ከሚርከፈከፍባቸው ሀገሮች ከነሶሪያ፣ ሊቢያ… ተመልክተናል። ዜጎች ወጥተው ወርደው ያፈሩት ሀብት በአጭር ጊዜ ዶግ አመድ ሲሆን ህንፃዎች ወደ ፍርስራሽነት ሲለወጡ አይተን አዝነናል። ዛሬም ስደተኛ ሶሪያውያን ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያንን ሲማጸኑና ለዕለት ጉርሳቸው እጃቸውን ሲዘረጉ እያየን ጭምር ነው። ይሄ ትናንት ያልነበረ ዛሬ በተፈጠረው የሰላም መደፍረስ የተከሰተ ነው። እኛም “ብልጥ ከሰው ሞኝ ደግሞ ከራሱ ስህተት ይማራል” እንደሚባለው ሁሉ እኛም እንደብልጦቹ ከሌሎች ተምረን የሀገራችንን ሰላምና አንድነት የህዝቦችን ደህንነት መጠበቅ አለብን።
አሁን በአገራችን አንዳንድ አካባቢዎች የሚታዩ የሰላም መደፍረሶች ህዝቡ ተረጋግቶ እንዳይኖር፣ ተማሪውም በሰላም ወጥቶ ገብቶ እንዳይማር፣ ነጋዴው ነግዶ፣ አርሶ አደሩም አርሶ ፣ሌላውም ሰርቶ እንዳይገባ እያደረገው ይገኛል። ትልቅም ስጋት ፈጥሯል። ሰሞኑን በሀገራችን አንዳንድ አካባቢዎች ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድና ለአጠቃላይ ሀገራዊ ለውጡ ያላቸውን ድጋፍ ለመግለጽ በተለያዩ ከተሞች የድጋፍ ሰልፎችን አድርገዋል። አሁንም እያደረጉ ይገኛሉ።
ይሄ ሀሳብን በሰላማዊ መንገድ መግለጽ አንዱ ለውጡ ያስገኘው የዜጎች መብት ነውና ይሄ ዲሞክራሲያዊ ሂደት ሊበረታታ ይገባል። በዲሞክራሲያዊ መንገድ ሀሳብን በአደባባይ መግለጽ ልዩነትን አቻችሎ አንድነትን አስጠብቆ መንቀሳቀስ የስልጡን አንዱ አካሄድ ነው። ሆኖም ግን አንዳንድ ቦታዎች ላይ የሚሰሙትና የሚታዩት ሀሳቡን በዲሞክራሲያዊ መንገድ ለመግለጽ ከወጣ ዜጋ ጋር መጋጨት በየትኛውም መስፈርት ድጋፍ አያገኝም። ተገቢም ትክክልም አይደለም።
ኢትዮጵያውያን ላንፋታ ሆነን በዘር፣ በሀይማኖት፣ በቋንቋ፣ በቀለም የተጋመድን፣ላንለያይ ተዋህደን የተሰራን ነን። ይሄ ህብራችን ሊያፋቅረን እንጂ ሊያጋጨን አይገባም። አስተሳሰብ፣ የፖለቲካ ልዩነት የሚፈታውም በጦርነት በሴራ ፖለቲካ ሳይሆን በመነጋገር በመወያየት በጠረጴዛ ዙሪያ ውይይት ነውና ይሄንን መንገድ መከተል ያስፈልጋል።
አሁን በአንዳንድ ቦታዎች በሚታዩት ሁከትና ብጥብጥ ሀገርን ማሳደግና ዲሞክራሲን ማጎልበት አይቻልም። በመሆኑም የሚኖሩ ልዩነቶች እንደተጠበቁ ሆነው ሁሉም ዲሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ ሀሳቡን ሊያራምድ ይገባል። ስልጡን ፖለቲከኛው፣ ደጋፊውና ምሁሩ ሀሳቡን አደባባይ አውጥቶ በሀሳብ የበላይነት አሸንፎ ተመራጭ መሆን አለበት። በየትኛውም መንገድ ለማንኛውም ዜጋ የሚበጀው በሀሳብ የበላይነት በልጦ መገኘት ነው። ይሄ ሁሉ የሚሆነው ደግሞ ሰላም ሲኖር ነውና ከሁሉም በፊት ሰላም ይቅደም።
አዲስ ዘመን የካቲት 16/2012