ጥምቀት የአደባባይ በዓል በመሆኑ ከውጭ ሀገር የሚመጡ እንግዶችን ሳይቀር ሁሉንም ያሳትፋል፡፡ ከጥር 10 የከተራ ቀን ጀምሮ የበዓሉ አክባሪዎች በየአጥቢያቸው ታቦታትን አጅቦ ወደማደሪያቸው በመሸኘትና ጥር 11ቀንም ታቦታቱን ወደየደብራቸው በመመለስ በደማቅ ስነስርአት ያከብሩታል፡፡
ከአካባቢ ጽዳት ጀምሮ የበዓሉን ታዳሚ በማስተናበርና የፀጥታ ችግር እንዳይኖር ከፀጥታ አካላት ጋር በትብብር ማህበራዊ አገልግሎት በመስጠት የጎላ ሚና በመወጣት ደግሞ ወጣቶች ከፍተኛ ድርሻ አላቸው፡፡
ላለፉት 14 አመታት በጥምቀት በዓል ማህበራዊ አገልግሎት ሲሰጥ የቆየው ወጣት እዮብ ገዛኸኝ በሚኖርበት አራት ኪሎ በሚገኘው ቅድስት ስላሴ ቤተክርስቲያን ውስጥ ከሌሎች ወጣቶች ጋር በመሰባሰብ በየአመቱ ከሚያከናውነው መንፈሳዊ ተሳትፎው በተጨማሪ ማህበራዊ አገልግሎቱ እንደሚያስደስተው ይናገራል፡፡ከአባቶችና እናቶች ምርቃትና ምስጋና ለማግኘትም ይናፍቃል፡፡
ወጣት እዮብ እንዳስረዳው በአራት ኪሎ አካባቢ ቁጥራቸው ወደ ስምንት የሚደርስ ታቦታትን ወጣቱ በቅብብሎሽ በቀይ ምንጣፍ በመሸኘትና በመመለስ ያስተናግዳል፡፡ታዳሚውም ንጹህ ነገሮችን እንዲያይ ጎዳና ያፀዳል፣ያስተባብራል፡፡
በዓሉ ሰላማዊ ሆኖ እንዲያልፍም ከፀጥታ አካላት ጋር በቅንጅት ስለሚሰራ ስጋቶች ቀድመው ነው የሚወገዱት፡፡ወጣቱ እዮብ ይህን ስራ ለማከናወን ከሁለት ወር ጀምሮ ነው ዝግጅት ያደረገው፡፡ልምዱም ስላለ በየአመቱ ውጤታማ ስራ እያከናወነ ይገኛል፡፡ተግባሩ መንፈሳዊ ጭምር በመሆኑ ከስሜታዊ ነገር ተቆጥቦ በመግባባት ነው ተልእኮውን የሚወጣው፡፡
ወጣቱ በጥምቀት በዓል ብቻ ሳይሆን በሌሎች አመታዊ ክብረበዓላትም በተመሳሳይ እንደሚፈጽሙ የገለጸው ወጣት እዮብ፤ ይህን ተግባሩን በእለት ተእለት ኑሮውም እንዲተገብር በመካከላቸው መግባባት ቢኖርም ለበዓሉ በሚፈጸመው መጠን እንዳልሆነ ግን ይናገራል፡፡መለመድ እንዳለበትና ተግባሩ በቤተክርስቲያናት አካባቢ ብቻ መወሰን እንደሌለበት ያምናል፡፡
ወጣት እዮብ፣ በተለይ በጽዳት በኩል እንዳለው በሺዎች የሚቆጠር ህዝብ በሚታደሙበት የጥምቀት በዓል ከፍተኛ ቆሻሻ ይመነጫል፡፡ወጣቱ ይህን ቆሻሻ በማስወገድ የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው ይላል፡፡
እንዲህ ያለውን የወጣቱን ተሳትፎ በአዲስ አበባ ከተማ በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ነዋሪ የሆኑት ወይዘሮ ፀጋ አራጌ በአድናቆት ይገልጻሉ፡፡ወጣቱ ከማህበራዊ አገልግሎቱ በተጨማሪ በጨዋታ በማድመቅ፣የጋብቻ መሰረትም በመጣል ሁለተናዊ ተሳትፎ የሚያደርግበት በዓል እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡እርሳቸውም በወጣቱ ተሳትፎ የሚደሰቱበት እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ይህን ተሳትፎውን በሀገር ሰላምና አንድነት ላይ አጠናክሮ እንዲቀጥል ይመክራሉ፡፡
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ዋና ኃላፊ መምህር ዕንቁባህሪ ተከስተ፣ ቤተክርስቲያን ወጣቱን ይዛ እንደምትንቀሳቀስና በተለይም በጥምቀት በዓል የወጣቶች ተሳትፎ ከፍተኛ እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡መምሪያው ከወጣቶችና ከፀጥታ አካላት ጋር ከበዓሉ መዳረሻ ከቀናት በፊት በመገናኘት ምክክር በማድረግ ዝግጅቱን ያጠናክራል፡፡ ቤተክርስቲያን ወጣቶችን በማሳተፍ የምታከናውነው ስራ የትውልድ ቅብብሎሽን እንደሚያጠናክር ይገልጻሉ፡፡
በሃይማኖቱ፣ በስነምግባሩ የተገነባና በማንነቱ የማይደራደር እንዲሁም ፈተና ቢያጋጥመውም በቀላሉ ሊሸረሸር የማይችል እንዲሆን፣ ሀገራዊ ሰላም አስተማማኝ ሆኖ እንዲቀጥል ትውልድ በመቅረጽ የበኩሏን አስተዋጽኦ በማበርከት ላይ መሆኗንም አስረድተዋል፡፡
‹‹ላልይበላን ያነፀ ትውልድ ጥበብና ፍልስፍና እንደሌለው ተደርጎ መወሰድ››የለበትም ያሉት መምህር ዕንቁባህሪ፤ ወጣቱ ቀንአዊነቱ ለሃይማኖቱ ብቻ ሳይሆን ለሀገሩም ጭምር መሆን እንዳለበት ይመክራሉ፡፡በበዓሉ ወቅት ከጽዳት ጀምሮ የሚያደርገውን እንቅስቃሴ ቤተክርስቲያን ሁሌም እያመሰገነችና በማስተባበርም አብራ እየሰራች መሆኑን ገልጸዋል፡፡
መምህሩ እንዳሉት የጥምቀት በዓል በሀገር አቀፍ ተመሳሳይ የሆነ መርሃግብር ስላለው የወጣቱም ተሳትፎ በሀገር አቀፍ ተመሳሳይ ነው፡፡በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ 223 አብያተ ክርስቲያናትና 76 ባህረጥምቀት ይገኛሉ፡፡በከተማዋ ከሶስት ሺህ ያላነሱ ወጣቶች ማህበራዊ አገልግሎት በመስጠት ይሳተፋሉ፡፡
ወጣቱ በጥምቀት በዓል የሚያደርገው ማህበራዊ ተሳትፎ በአዘቦቱም ቀጣይነት እንዲኖረው በማስተባበር ሌሎች ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡና ማህበረሰቡም የወጣቱን ተግባር እንዲያበረታታ መምህር ዕንቁባህሪ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 3/2011
ለምለም መንግስቱ