በሚቀጥለው አመት ለሚካሄደው ሀገራዊ ምርጫ መንግሥት የፖለቲካ ምህዳሩን በማስፋት፣ የምርጫና የተለያዩ የህግ የማሻሻል እርምጃዎችን በመውሰድ ላይ ይገኛል፡፡ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ሰብሰብ ብለው ጠንካራ ተፎካካሪ እንዲሆኑ እንደሚያግዛቸው ቃል ተገብቶላቸዋል፡፡ መንግሥት እየፈጠረ ያለውን ምቹ ሁኔታ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዴት እየተጠቀሙበት ነው? የመንግሥት እገዛንስ እንዴት ያዩታል?
የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ትብብር ሊቀመንበር ዶክተር አረጋዊ በርሄ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲና የሀሳብ ነጻነት እንዳልነበር በማውሳት፣ በሀገር ውስጥና በውጭ በሚኖር ህዝብ ግፊትና በጥቂት የፖለቲካ ሰዎች የተገኘውን ለውጥ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች በአግባቡ መጠቀም እንዳለባቸው ይገልጻሉ፡፡ መድረኩ ከተከፈተ ያላቸውን ፖለቲካዊ፣ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ አመለካከትም ለህዝቡ በማስተላለፍ መንቀሳቀስ እንዳለባቸው ይናገራሉ፡፡ ዕድሉ ህዝቡ የሚሻለውን ለመምረጥ ምቹ ሁኔታ ፈጥሮለታል ይላሉ፡፡
እንደ ዶክተር አረጋዊ በርሄ ማብራሪያ ምቹ ሁኔታ ቢኖርም ሁሉም እኩል እየተጠቀመበት ነው ለማለት አያስደፍርም፡፡ በአመለካከትም በአደረ ጃጀትም ዥንጉርጉር ነገር ነው የሚስተዋለው፡፡ ከፊሉ የብሄር፣ከፊሉ ደግሞ ሀገርአቀፍ ሆኖ ነው የሚንቀሳቀሰው፡፡ አንዳንዱ ለመጠቀም ጥረት ሲያደርግ ሌላው ደግሞ አክራሪና ለዘብተኛ ሆኖ ወዳልተገባ አቅጣጫ እያመራ ነው፡፡ እነዚህን የተለያዩ አመለካከቶች በተፈጠረው የሃሳብ ነፃነት ለኢትዮጵያ የሚጠቅመውን አቅጣጫ ለመከተል ውይይቶች እየተካሄዱ ነው፡፡‹‹መንግሥት ነፃነቱን ሰጥቶናል፡፡ቀሪው የእኛ የቤት ስራ ነው››ሲሉም ገልጸዋል፡፡
የተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ቁጥር እንዲቀንስ በመንግሥት እየተሰጠ ያለውን ሃሳብ እንደሚደግፉ የሚናገሩት ዶክተር አረጋዊ የፓርቲዎች ቁጥር መብዛት ህዝብን ከማወናበድ አልፎ ፓርቲዎችን እንደሚያስጨንቅና ከአምስት ፓርቲ በላይ መብለጥ እንደሌለበትም አመልክተዋል፡፡ ‹‹ፓርቲዎች የተፈጠረውን ምቹ ሁኔታ ተጠቅመው ዓላማቸውን ማሳካት እንጂ መንግሥት እርምጃ እንዲወስድ የሚገፋፋ ተግባር መፈጸም አይገባም›› በማለት ጫና ከሚፈጥር ተግባር መቆጠብ እንደሚጠበቅ ገልጸዋል፡፡
የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ሙሉጌታ አበበ በበኩላቸው እንዳሉት፤ በውጭ ሆነው ሲታገሉ የነበሩ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሀገር ውስጥ ገብተው ሰላማዊ የሆነ ትግላቸውን እንዲቀጥሉ በመንግስት የተወሰደውን እርምጃ ፓርቲያቸው በመልካም ጎኑ ይመለከተዋል፡፡ «ለሁለት አስርት አመታት ስንጮህበት የነበረውን ምላሽ እያገኘን ነው፡፡ ከኢህአዴግ አምባገነናዊ ስርአት አኳያ የተሻለ ነገር እያየን ነው፡፡ መንግሥትን እናመሰግናለን » ብለዋል ፡፡
«የተፈጠረውን ዕድል በአግባቡ ካልተጠቀ ምንበት ከእጃችን የማይወጣበት ምክንያት የለም፡፡ ወደ ኃይል ከገፋነው ኢህአዴግ ለአምባገነንነት ቅርብ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሰው ናቸው፡፡ ኢህአዴግም ናቸው፡፡ በድርጅቱ ውስጥም ያደጉ ናቸው›› በማለት ፓርቲዎች ወደኃይል ከመግፋት ይልቅ ዕድሉን እየደገፉ ለተሻለ ነገር ጥረት ማድረግ እንዳለባቸው አስረድተዋል ፡፡
ዕድሉ ቢኖርም ያለው ተጨባጭ ሁኔታ ለምርጫ ምቹ ሁኔታ አለ ብሎ ፓርቲያቸው አያምንም፡፡ የሀገሪቷ መረጋጋትና የዜጎች በህይወት የመኖር መብት መረጋገጥ አለበት፡፡ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች ተፈናቅለው በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ሆነው የምረጡን የምርጫ ኮሮጆ ይዞ መቅረብ ተገቢ ነው ብሎ ፓርቲያቸው እንደማያምንና ህዝቡ በአካባቢውና በቀዬው መምረጥ እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡
ሰላሙን ለማረጋጋት የፖለቲካ ፓርቲዎች ሚና ቢኖራቸውም የአንበሳውን ድርሻ መንግሥት መውሰድ አለበት፡፡ሀገርን የሚያናጋ ነገር ሲፈጠር በልበ ሰፊነት መታለፍ የለበትም፡፡ እርምጃ መወሰድ አለበት፡፡ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጀምሮ ዋጋ የተከፈለው ኢትዮጵያ የጥቂቶች መኖሪያ እንድትሆን አይደለም፡፡ በውይይትና በድርድር እየተባለ የመንግሥትና የህዝብ ህልውና መጣስ የለበትም፡፡ ኢህአዴግ አምባገነን የማይሆንበት ምክንያት የለም፡፡ መንግሥት ማህበራዊ አገልግሎቶች ላይ ትኩረት ማድረግ አለበት በማለት አክለው ገልፀዋል፡፡
ከተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ቁጥር መቀነስ ጋር ተያይዞ ለሚቀርበው ሃሳብም አቶ ሙሉጌታ‹‹ ገዥው ፓርቲ የፈጠራቸው ፓርቲዎች አሉ፡፡ ይህን መፈተሽ ነው፡፡ ምርጫ ቦርድ በአዋጅ የመቆጣጠር ስልጣን ተሰጥቶታል፡፡በዚህ መሰረት እነማን መስፈርቱን እንደሚያሟሉ መለየትና ህጋዊ መሰረት ማስያዝ ይችላል፡፡ምርጫ ቦርድ ልጆቹን የማያውቅ አባት ሆኖ ነው የቆየው››ሲሉም ሃሳብ ሰጥተዋል፡፡ ፓርቲያቸውም ከሰፈርና ከጎጥ ካልወጡ ፓርቲዎች ጋር መደራደር አይፈልግም ብለዋል፡፡ወደ አንድ መምጣትንም ፓርቲያቸው እንደሚደግፍ፤ ነገር ግን ወደአንድ ሲመጣ ፓርቲያቸው ህልውናውን ጠብቆ ግንባር ሊፈጥር ይችላል በማለት ገልጸዋል፡፡
‹‹መንግሥት ለምርጫው እየፈጠረ ያለውን ምቹ ሁኔታ ጅምሩን ገና እያየን ነው፡፡ተጀመረ እንጂ እልባት አላገኘም››በማለት ሃሳባቸውን የሰጡት የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግረስ (ኦፌኮ)ሊቀመንበር ዶክተር መረራ ጉዲና፤ ከምርጫ ቦርድ ጋር ስምምነት ተፈጥሮ ገና ወደማዋቀር አልተገባም፡፡አዋጅም ገና አልወጣም፡፡ሌሎች ህጎችም በጥናት ላይ ናቸው፡፡ውይይቶችም እየተካሄዱ ነው፡፡እነዚህ ሁሉ ባሉበት ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል ለማለት አያስደፍርም ብለዋል፡፡
ከምርጫ ጋር ተያይዞ በመንግሥት ላይ ይሰነዘር የነበረው ወቀሳ አሁን ወደ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ዞሯል ስለሚባለው ጉዳይ ዶክተር መረራ በዚህ ደረጃ ላይ እንዳልተደረሰና አሁንም ኳሱ በመንግሥት ሜዳ ላይ ነው ሲሉ ለአስተያየቱ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
ዶክተር መረራ ችግር ውስጥ የገቡ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችን የማስተካከል ኃላፊነት የመንግሥት ድርሻ እንደሆነና በሀገሪቷ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ቁጥር ከ10 እንደማይበልጡ ፣80 የሚባለው ገዥው ፓርቲ የሚያውቃቸው እንደሆኑና እራሱ መለየት እንዳለበት ተናግረዋል፡፡
አዲስ ዘመን ጥር 3/2011
ለምለም መንግሥቱ