ፅንፈኝነት የሚለው ቃል ከአመጣጡ ጀምሮ አመፅን የሚያመለክት ሲሆን፤ የእኔ እና የእኔ ብቻ በሚል ልክፍት ውስጥ የተዋጠ ሌሎችን የማግለል በሽታ ነው። ይህ በሽታ በብዙ አገሮች የሚስተዋል ሲሆን፤ ሃይማኖት፣ ብሔርና የቆዳ ቀለምን ማዕከል በማድረግ ላይ ይመሰረታል። ያደጉት አገራት ከስልጣኔያቸው ጋር ተያይዞ የሚስተዋለው እጅግ በጣም ውስን በሆኑ ሰዎች ዘንድ በመሆኑ ፅንፈኝነት ሚዛን ደፍቶ ሌሎችን የመጉዳት እድሉ የመነመነ ነው።
በአፍሪካ የሚስተዋለው የሃይማኖትም ሆነ የብሔር ፅንፈኝነት ግን ከኋላቀርነት ጋር ተጣብቆ የብዙዎችን ህይወት ቀጥፏል። በምሳሌነት ከምትጠቀሰዋ መካከል ሩዋንዳ ዋነኛዋ ናት። ሩዋንዳዎች ምንም እንኳን ዛሬ ላይ ይቅር ተባብለው አንተ የምን ብሔር ተወላጅ ነህ ብሎ መጠየቅ እንደነውር የሚቆጠርበት ዘመን ላይ ቢደርሱም ወደ አንድ ሚሊየን የሚጠጉ ዜጎቻቸው ህይወት በፅንፈኝነት ተቀጥፏል። ብዙዎች ተሰድደዋል። ሌሎች ደግሞ በወቅቱ ባዩት እልቂት አዕምሯቸው ተቃውሷል። አገሪቷ በብዙ መልኩ ለጉዳት ተጋልጣለች።
ይህ የፅንፈኝነት ችግር “እኔ የረገጥኩትን መርገጥ አይቻልም” ብሎ ለራስ የተለየ ግምት ሰጥቶ የራስን ብሔርና ሃይማኖት ከሁሉም እንደሚሻል የማሰብ አባዜ የሚመጣው በአብዛኛው ሌሎች በአንዳንዶች ላይ በሚረጩት መርዝ ነው። በጣም የሚያሳዝነው መርዛቸውን የሚረጩት ሰዎች ማዕከል የሚያደርጉት የራሳቸውን ጥቅም ብቻ ነው። “ሃይማኖታችን ወይም ብሔራችን ተጎዳ“ አሊያም “እኛ ልዩ ዘሮች ነን” ብለው ይነሳሉ። ገንዘብና ስልጣን ይገኝበታል ብለው የሚገምቱት መንገድ ብሔር ከሆነ ብሔርን፤ ሃይማኖት ካዋጣቸው ደግሞ ሃይማኖትን እንደአማራጭ ይዘው የፈለጉትን ካርታ እየመዘዙ ይጫወታሉ። ምስኪኖች ደግሞ እነርሱ በሚረጩት መርዝ መጠቀሚያ ሆነው ህይወታቸውን ያበላሻል።
አንዳንድ ፖለቲከኞች ለራሳቸው ትርፍ ሲሉ “ብሔሬ ተጠቃ” ማለታቸው ያንን ብሔር ወይም የዚያን ብሔር ተወላጅ ለመጥቀም አስበው ላለመሆኑ ብዙ ማስረጃዎች መጥቀስ ይቻላል። የብሔር ወይም የሃይማኖት ተቆርቋሪ መሳዩ ሰው እቆረቆርለታለሁ የሚለውን ብሔር ወይንም ሃይማኖት ሰዎችን ለጦርነት ከመማገድ ውጪ እርሱ ቆሞ ግንባሩን ለጥይት አይሰጥም። ይልቁኑ ከጀርባ ሆኖ በሉ ብሎ ከማጋጋል እልፍ አይልም። ምናልባትም የባሰ ነገር ከመጣ ከጀርባ የነበረው ሰው ከብሔሩ ወይም ከሃይማኖቱ በተፃራሪ ቆሞ ደግሞ ሌላ ቁማር ሊጀምር እንደሚችል አያጠራጥርም።
የብሔርም ሆነ የሃይማኖት ፅንፈኝነትን ለማንም አያዋጣም። የማንም ብሔር ወርቅ የማንም ብሔር ጨርቅ አይደለም። የማንም ሃይማኖት ደግሞ ስህተት አይደለም። ማንም ራሱን በአንድ ቦታ ላይ አቁሞ ሌላውን መንቀፍም ሆነ ማንቋሸሽ አያስፈልግም። የሌሎችን ብሔርም ሆነ ሃይማኖት ማሳነስ ራስን ከማሳነስ የተለየ አይደለም። ሁሉም ወደ መሃል መምጣት ይኖርበታል። የሁሉም ብሔርም ሆነ ሃይማኖት መከበር አለበት። ሁሉም እኩል ተጠቃሚ ሊሆን ይገባል።
የአንዱ ተለይቶ መጠቀም አትራፊ አያደርግም። ተለይቶ ያልተጠቀመው የተጠቀመውን ያጠፋዋል። የአንዱ ተለይቶ መጎዳትም መዘዙ ተመዝዞ አያልቅም። ስለዚህ ሁሉም እኩል ይጠቀም ማንም ተለይቶ አይጎዳ፤ ተለይቶ አይጎዳ ብቻ አይደለም ተለይቶ አይጠቀም ማለት ነው። ይህ ማለት ሙሉ ለመሉ እንከን የሌለው ሥራ ይሰራል ማለትም አይደለም።
አንዳንዴና አልፎ አልፎ ችግር ሊያጋጥም ይችላል። ይህንን ችግር መቅረፍ የሚቻለው ሁሉም የሁሉንም መብት ሲያከብርና ሁሉም ወደ መሃል ሲመጣ ነው። የክርስቲያኑ መብት ሲጣስም ሆነ ጥቃት ሲፈፀምበት ሙስሊሙ መታገል አለበት። ክርስቲያኑም ለሙስሊሙ መቆም ይኖርበታል።
በሌላ በኩል ሁሉም የአገራችን ብሔሮች፤ ብሔረሰቦችና ህዝቦች አንዳቸው ለሌላው ሊቆሙ፤ ሊከራከሩና ሊታገሉ ይገባል። የሁሉም መብት እንዲከበር መሃል ሆኖ መስራት፤ ሁሉም ለሁሉም መቆርቆርና መቆም ይጠበቅባቸዋል። ያ ካልሆነ ግን ማንም አያተርፍም። ፅንፈኝነት የአንድ ብሔርና የአንድ ሃይማኖት ማጥፊያ የሌላው ብሔርና ሃይማኖት ማትረፊያ ሳይሆን ለሁሉም የማይበጅ የሁሉም መጥፊያ መሆኑን ልብ ማለት ይገባል።
አዲስ ዘመን የካቲት 15/2012