ህዝባችን ፀብ የለሽ በዳቦ የሆነ አምባጓሮ ሲገጥመው፣ ሀብት ንብረቱ በቀማኛ ሲደፈር፣ ቃል አባይ በሆነ ሰው ሲከዳ፣ በመንግስት አካላትም ሆነ በግለሰብ መብትና ጥቅሙ ያለ አግባብ ሲገፈፍ ፍትህ በእጄ ብሎ መብቱን በሃይል ከማስከበር ይልቅ በህግ አምላክ ብሎ እማኝ ቆጥሮ ጉዳዩን ወደ ባህላዊ ፍርድ ሰጪ ወይም ህግ አስከባሪ አካል ወይም መደበኛ ፍርድ ቤት ይዞ በመሄድ መብቱን የማስከበር አኩሪ ባህል አለው።
ይህ ባህል የሁሉም የኢትዮጵያ ህዝቦች መገለጫ ነው። ከመደበኛው የፍትህ አስተዳደር በተጨማሪ የሲዳማው አቦ ወንሾ፣ የጉራጌው ጆካ፣ የየሙ ባህላዊ የዳኝነት ሥርዓት የትግራዩ፣ የአማራው፣ የጉራጌው፣ ኦሮሞው እጅግ አስደናቂ የፍትህ ሂደቶች ወ.ዘ.ተ በአገራችን ከሚገኙ ርዕትእንና ህገ ልቦናን መሰረት ያደረጉ ባህላዊ የፍትህ ሥርዓቶች ናቸው።
ዘመናዊ የህግ ስርዓት በአገራችን ሳይመሰረትም ህዝባችን እነዚህኑ ባህላዊ የፍትህ መንገዶች በመጠቀም በህግና በሰርዓት ሲተዳደር ኖሯል። የህግ የበላይነትና ልዕልና ካልተጠበቀ በሀገሪቱ የሚረቀቁ ማናቸውም ህጎች በሚፈለገው መጠን ገቢራዊ ሊሆኑ አይችሉም። ህጎች በሚፈለገው መጠን ገቢራዊ ካልሆኑና በቸልታ የሚታለፉ ከሆነ ደግሞ የዜጎች መብቶች ከመሸራረፋቸውም በላይ ሰላም ወጥቶ ሰላም መግባት የህልም እንጀራ ይሆናል።
የህግ የበላይነት በሌለበት ሀገር ውስጥ ማንኛውም ሰው በሰላም ወጥቶ ሊገባ አይችልም። መብት ሰጪዎችና ነሺዎች ጉልበተኞች ይሆኑና ስርዓት አልበኝነት ይነግሳል። ጉልበተኞቹም ሌሎች ዜጎችን እንዳሻቸው በማድረግ የባሪያና ሎሌ ስርዓት ይፈጥራሉ። ስርዓት አልበኝነት ሲገነግንም ህግን አክብሮ የሚንቀሳቀስ ዜጋ አይኖርም። ሁሉም በየፊናው እየሮጠ የራሱን የበላይነት ለማረጋገጥ ይጥራል። ይህ ሁኔታም አንድን ሀገር የነበረበትን ሰላማዊ ምህዳር በማወክ በሁከት እንዲታመስ ያደርገዋል።
የህግ የበላይነት ካልተረጋገጠ በሰላም ውስጥ ኖሮ ሀገርን ማበልፀግና ወደተሻለ ህይወት መረማመድ ያበቃለታል። እናም ይህን ሁኔታ ለመከላከልና ሰላምና መረጋጋትን ለማስፈን የህግ የበላይነት መኖር የግድ ይላል። ህገ መንግስቱ የህጎች ሁሉ የበላይ እንደመሆኑ መጠን፤ እርሱን ተከትለው የሚወጡ አዋጆችን ተፈፃሚ አለማድረግ ህገ መንግስቱን መቃወም ይሆናል።
የህግ የበላይነትን ማረጋገጥ ከክልልና ከብሄር ድንበር የሚዘል ተግባር በመሆኑ ሁሉም ክልሎችና የዞን እና የወረዳ መዋቅሮች በወንጀል የሚፈለጉ ግለሰቦችን ለህግ አሳልፎ በመስጠት ለህግ ልዕልና መቆማቸውን ማረጋገጥ ይገባቸዋል። ኅብረተሰቡም በእያንዳንዱ መንደር ለሚፈጸም ወንጀል የፌዴራልና የክልል መንግስት ኃላፊነት ነው ብሎ እጅን ከመሰብሰብ ይልቅ የራስን ድርሻ መወጣቱ የውዴታ ሳይሆን የግዴታ ጉዳይ ሊሆን ይገባዋል!
አዲስ ዘመን ቅዳሜ የካቲት 14/2012