በፈረንጆች የካቲት 14 በእኛ የካቲት 6 ቀን ‹‹ቫላንታይን ዴይ›› የሚባለው የፍቅረኞች ቀን ነበር። በዚህ ዕለት በአንድ የሬዲዮ ጣቢያ የሰማሁት ነገር ‹‹እንኳንም የሬዲዮ ጣቢያዎች ብዙም አድማጭ የላቸውም›› ነው ያሰኘኝ። በእርግጥ አድማጭ ያጡት በእንዲህ አይነት እንቶ ፈንቶ ፕሮግራሞቻቸው ነው። ሲያወሩ የነበረው ማህበራዊ ገፆች ላይ ለቀልድ ተብሎ በፎቶ ሾፕ ሲሰራ የነበረ የቀልድ ወሬ ነው። የማህበራዊ ገጽ ተጠቃሚ ሁሉ ያ ነገር ቀልድ መሆኑን ያውቃል። ያንን እንደ ወረደ ታዳጊዎችና አዛውንቶች በሚሰሙት ዋና መገናኛ ብዙኃን ላይ መናገር ነውር ነው። ቀልዱ ‹‹አልጋ አልቋል›› የሚል ነበር።
የማህበራዊ ገጽ (በተለይም ፌስቡክ) ተጠቃሚ በአብዛኛው ወጣቱ ክፍል ነው። አዋቂዎችም ቢጠቀሙም ማገናዘብ የሚችሉና የተማሩ የሚባሉ ናቸው። ይሄን ቀልድ አይቶ ማንም እውነት ሊመስለው አይችልም። በቃ ካዝናናው ይስቃል፤ ካላዝናናውም አልፎት ይሄዳል። ሬዲዮ ላይ ግን ይህ መሆን የለበትም። የሬዲዮ አድማጭ ከሕጻናት እስከ የዕድሜ ባለጸጎች ነው። ከሃይማኖት አባቶች እስከ የቀን ሰራተኞች ነው። ለእነዚህ ሰዎች ይሄን መናገር ምን ማለት ይሆን?
እርግጥ ነው አዘጋጆቹ የተናገሩት እውነት ነው ብለው ላይሆን ይችላል፤ ቢያንስ ቢያንስ ግን ቀልድ መሆኑን እንኳን አስረግጠው መናገር ነበረባቸው። ሲቀጥል ይሄ ለሬዲዮ ጣቢያ ቀልድ መሆንም አይችልም። ስለፍቅረኞች ቀንና ስለፍቅር ብቻ ማውራት በቂ ነው። ዛሬ ፍቅረኞች ሁሉ ይገናኛሉና አልጋ ያልቃል የሚል መልዕክት ማስተላለፍ ነውር ነው። ሲጀመር ትክክለኛ ፍቅረኛሞች በየአልጋ ቤቱ የሚዞሩ አይደሉም። የፍቅረኞች ቀን ‹‹የትክክለኛ ፍቅረኛሞች ሳይሆን ለዝሙት የሚገናኙት ናቸው የሚያከብሩት›› የሚል ሀሜት ይነሳበታል። እንግዲህ በዚህ ውስጥ ‹‹አልጋ አልቋል›› የሚል ቀልድ መቀለድ ዝሙትነቱን ማሳየት ነው።
የሬዲዮ ጣቢያዎች ፕሮግራም ከማህበራዊ ገፆች በታች ሆኗል። የማህበራዊ ገጾች ‹‹ቫላንታይን ዴይ›› የሚባለውን የፈረንጅ ባህል ንቀውት ከምንም አልቆጠሩትም። ለሬዲዮ ጣቢያዎች ግን ትልቅ ፕሮግራም ነበር። ከሳምንት በፊት ሲያስተዋውቁት ነበር። ማስታወቂያዎች ሁሉ በቫላንታይን ዴይ የታጀቡ ነበሩ። ከሳምንት በፊት ነው ፕሮግራም እየቀረጹ የሰሩት። እንግዲህ የእነርሱ ‹‹ሚዲያ ካላንደር›› ይሄ ነው ማለት ነው። ማህበራዊ ገፆች በፖለቲካ፣ ኢኮኖሚና ማህበራዊ ጉዳዮች ሲጠመዱ የሬዲዮ ጣቢያዎች ግን የሚያሳስባቸው የፈረንጅ ቀን ነው። ለዚያውም እኮ የንባብ ቀንና ሌሎች ጠቃሚ ነገሮችን ቢሆን ደግ ነበር። ዳሩ ግን የእብድ ቀን (Cryzy day) ፣ የጅል ቀን (April the Fool) የሚባሉትን ነው የሚያወሩት። ማህበራዊ ገፆች ግን እነዚህን ንቀዋቸው ጉዳያቸው አይደሉም። ምናልባት ስለ እነዚህ ቀኖች ከተወራም በቀልድ መልክ ለማሳቅ ብቻ ነው። አንዳንዶቹም ‹‹የእኛ አይደለም›› በማለት ሲያሾፉበት (በአራድኛው ሙድ ሲይዙበት) ነው የሚታይ። ይሄ ማለት ዋና ጉዳያቸው አይደለም ማለት ነው።
ይህን ስል ግን ሁሉም የሬዲዮ ጣቢያዎች ናቸው ማለት አይደለም። እንኳን ሁሉም የሬዲዮ ጣቢያዎች ከአንድ የሬዲዮ ጣቢያ እንኳን ሁሉም ፕሮግራሞች ማለት አይደለም። ተወዳጅ የሆኑ የሬዲዮ ጣቢያዎችና ተወዳጅ የሆኑ ፕሮግራሞች አሉ። እያወራሁ ያለሁት ከፌስቡክ ወሬዎች በታች ስለሆኑት ስለሆነ እንጂ።
ሁላችንም እንደምናስተውለው ግን ከሬዲዮ ጣቢያዎች ማግኘት ያለብንን ነገር እያገኘን አይደለም። እስኪ በሬዲዮ ሰበር ዜና ሰምቶ የሚያውቅ አለ? በባህሪው ግን ለሰበር ዜና ምቹ ሬዲዮ ነበር። እየሰማን ያለነው ግን ከቴሌቭዥን ጣቢያዎች ነው። ቴሌቭዥን ብዙ ውጣ ውረድ አለበት። ብዙ መሳሪያዎች ያስፈልጋል፤ ካሜራና የቀጥታ ሥርጭት ዕቃዎች እስከሚሟሉ ጊዜ ይወስዳል። ሬዲዮ ግን ቀጥታ ስቲዲዮ ገብቶ ማውራት ነው፤ ወይም ከቦታው በስልክ ብቻ ማስተላለፍም ይቻላል። ዳሩ ግን በሬዲዮ ትኩስ ዜናዎችን መስማት የተለመደ አይደለም። በተቃራኒው በቴሌቭዥን ጣቢያዎች ነው፤ ይባስ ብሎም በህትመት መገናኛ ብዙኃን ነው አዳዲስ ዜና የሚታየው።
በአገሪቱ ውስጥ አንድ ሁነት ሲፈጠር ሬዲዮ ከፍቶ ከመከታተል ይልቅ ቴሌቭዥን ወይም ማህበራዊ ገጾችን መከታተል አትራፊ እየሆነ ነው። ሬዲዮ ሳደምጥ አምሽቼ ከተኛሁ ጠዋት የምሰማው ሁሉ አዳዲስ ነገር ነው። በቴሌቭዥንና በማህበራዊ ገጾች ሲቀባበሉት ያደረ ነው። ሬዲዮ ጣቢያዎች አላዩም አልሰሙም ማለት ነው? ወይስ ለመናገር ምን እያገዳቸው ይሆን?
በተለይም ቅዳሜና እሁድ የመዝናኛ ፕሮግራሞች ይበዛሉ። እነዚህ የመዝናኛ ፕሮግራሞች ደግሞ በተባባሪ አዘጋጆች የተያዙ ናቸው። ፕሮግራሙ ከሳምንት በፊት ነው የሚቀረጸው። ምናልባት ሁነቱ በካላንደር ቀድሞ የማይታወቅ ወቅታዊ የተከሰተ ክስተት ከሆነ በዚያ ፕሮግራም አይካተትም። የጣቢያው ሪፖርተሮች ደግሞ በእነዚያ ፕሮግራሞች ስለማይኖሩ የተፈጠረው ወቅታዊ ጉዳይ ሽፋን አያገኝም ማለት ነው። አንዳንድ የሬዲዮ ጣቢያዎች ግን የጣቢያውን ሪፖርተሮች ጣልቃ አስገብተው ሁነቱን ሲያስዘግቡ (ሽፋን ሲሰጡ) ሰምቻለሁ።
ሬዲዮ ቀላል የሚባለው የመገናኛ ብዙኃን አይነት ነው። በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኘው የህብረተሰብ ክፍል የሚጠቀምበት ነው። የቴሌቭዥን፣ የኢንተርኔትና የህትመት መገናኛ ብዙኃን ተደራሽ ያልሆነው የህብረተሰብ ክፍል የሚጠቀምበት ነው። አርሶ አደሩና ተማሪው በቀላሉ ይዞት የሚንቀሳቀስ ነው። ከምንም በላይ ደግሞ ሬዲዮ በሳይንሳዊ ባህሪው ‹‹Blind Medium›› ተብሎ ይጠራል። ለዓይነ ሥውራን ተደራሽ ነው። ምስል ከሳች ነው። ሁነትን በዓይነ ህሊና የሚያሳይ ነው።
እንግዲህ ሬዲዮ ይህን ሁሉ ባህሪ ይዞ የአገራችን የሬዲዮ ጣቢያዎች ግን በባህሪው ልክ እያገለገሉ አይደሉም ማለት ነው። የኢንተርኔትና የቴሌቭዥን ተደራሽ የሆኑ ሰዎች ያገኙትን መረጃ የሬዲዮ ተጠቃሚዎች አያገኙም ማለት ነው። ማንበብና መጻፍ የማይችለው (ቢችልም ጋዜጣና መጽሔት የማያገኘው) የህብረተሰብ ክፍል የአገሪቱን ወቅታዊ ጉዳይ አይሰማም ማለት ነው። የገጠሩ የህብረተሰብ ክፍል ሰበር ዜና አይደርሰውም ማለት ነው።
አሉ ደግሞ የማህበረሰብ ሬዲዮ ጣቢያዎች። የማህበረሰብ ሬዲዮ ጣቢያ ስሙ እንደሚያመለክተው የአካባቢው ማህበረሰብ ነው። ይሄ ማለት የአካባቢውን ማህበረሰብ ወግ፣ ባህልና ቋንቋ የሚያንጸባርቅ ማለት ነው። የሚተላለፉት ፕሮግራሞች ግን ከኢንተርኔት የሚገለበጡና ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር ምንም የማይገናኙ የውጭ አገር ጉዳዮች ናቸው። አውሮፓ ወይም አሜሪካ ወይም እስያ የተሰራ ጥናት። ለዚያውም በማህበረሰቡ ኑሮ (ለምሳሌ ግብርና) ላይ የተሰራ ሳይሆን ስለአለባበስ ወይም ስለአተኛኘት የሚሰራ ጥናት ነው። አሁን ይሄ ለገጠር ማህበረሰብ ምን ያደርግለት ነበር? እነዚያን የጥናቱ ተሳታፊዎችስ የት ያውቃቸዋል?
ሌላው የሬዲዮ ጣቢያዎች ችግር ምንም ምንጭ ሳይጠቅሱ የሌላ መገናኛ ብዙኃን ዜና መሥራት ነው (ሁሉንም እንዳልሆነ አስቀድሜ ተናግሬያለሁ)። እንዲያው ግን ያንን ዜና ሰዎች እዚያ ጋዜጣ ላይ የማያነቡት እየመሰላቸው ይሆን? ትኩስ ዜና ሊነገርበት የሚገባ ሬዲዮን ያህል ነገር እንዴት ከጋዜጣና መጽሔት ላይ ዜና ያነባል? ምናልባት አንዳንድ የዕቅድ ዜናዎች በባህሪያቸው በህትመት መገናኛ ብዙኃንም ቢሆን የሰበር ዜና ያህል ቀልብ ሊይዙ ይችላሉ፤ ዳሩ ግን ጋዜጣው ሲነበብ ከዋለና ካደረ በኋላ ማንበብ ትዝብት ነው፤ ለዚያውም ዜናውን የሰራውን ጋዜጣ ወይም መጽሔት ስም ሳይጠቅሱ። እንግዲህ ይሄ የሚያሳየው እንኳን አዲስ ዜና መሥራት የተሰሩትን እንኳን እንደማይከታተሉ ነው።
ሁሉም ይቅር! ቢያንስ ግን ይሄን ከማህበራዊ ገጾች የሚለቃቀም ቀልድ ቢተውት። ቀልድ ምንም ችግር የለውም፤ ሕጻንም ሆነ አዛውንት ቀልድና ሳቅ የማይወድ የለም። ዳሩ ግን ነውር የሆነውና ያልሆነው እየተለየ ቢሆን። ስለፍቅረኞች ቀን ማውራት ምንም ችግር የለውም። ሕጻንም ይሁን አዋቂ ዘንድ ፍቅር አለ። ዳሩ ግን የዝሙት ፍቅር ማስተዋወቅ ደግሞ ነውር ነው። የሬዲዮ ጣቢያዎች የሬዲዮን ሳይንሳዊ ባህሪ ያማከለ ዜና እና ፕሮግራም ሥሩልን!
አዲስ ዘመን ቅዳሜ የካቲት 14/2012
ዋለልኝ አየለ