እአአ የ1964ቱ የቶኪዮ ኦሊምፒክ ኢትዮጵያ በታሪኳ ተሳታፊ የሆነችበት ሶስተኛው ኦሊምፒክ ነው። ታላቁ አትሌት አበበ ቢቂላ በኦሊምፒክ ማራቶን ለራሱ እና ለአገሩ ሁለተኛውን፣ በውድድሩ ደግሞ ብቸኛውን ሜዳሊያ ያገኘበትም ነበር። አሁን ደግሞ ጃፓን ከሃምሳ ስድስት ዓመታት በኋላ ኦሊምፒክን በምድሯ ለማስተናገድ ወራት ብቻ የቀሩበት ጊዜ ላይ እንገኛለን። በዚህ ታላቅ የስፖርት መድረክም የተሻለ ታሪክ ለማስመዝገብ ኢትዮጵያ በተለየ ትኩረት በመንቀሳቀስ ላይ ትገኛለች። በታላቁ የኦሊምፒክ መድረክ ከውጤታማነት ባሻገር ተሳትፎም ክብርን ያስገኛል። በውጤታማነት ድርብ ክብርን ለመጎናጸፍ ደግሞ ትኩረት፣ ጥረትና ጽናት አስፈላጊ መሆናቸው ይታመናል።
በኦሊምፒክ መድረክ የአገሪቷን ስም በተደጋጋሚ ያስጠራው እንዲሁም ከፍተኛውን የውጤታማነት ስፍራ የሚይዘው የአትሌቲክስ ስፖርት ነው። ኢትዮጵያ ደግሞ በዚህ ስፖርት በተመዘገቡ ሜዳሊያዎች አማካኝነት ከውጤታማዎቹ አገራት መካከል 36ኛ ስፍራ ላይ ትገኛለች። ነገር ግን በዚህ መድረክ ውጤታማ ያደረጓት አትሌቶች የኋላ ታሪክ ቢጠና በግላቸው የሚያደርጉት ጥረትና ጽናት ሰፊውን ድርሻ ይይዛል። በመሆኑም መንግስት የተሻለ ትኩረት በመስጠት ውጤታማነቱን ለማሳደግና ለማገዝ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ አስታውቋል።
ለዚህም የመጀመሪያው ርምጃ አትሌቶች የዝግጅት ጊዜያቸውን በትኩረት እንዲያሳልፉ በተሻለ ስፍራ እንዲያርፉ ማድረግ ነው። በመሆኑም የዝግጅት ኮሚቴው ከኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ጋር ባደረጉት ውይይት ለውድድሩ የተመረጡ አትሌቶች ካምፓቸውን ከፍተኛ ደረጃ ካላቸው ሆቴሎች መካከል በአንዱ እንዲያደርጉ አቅጣጫ ተሰጥቷል። በዚህም መሰረት በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ጥሪ የተደረገላቸው አትሌቶች ተሰባስበው ወደ ልምምድ እንደሚገቡ ተገልጿል።
ከዚህ ቀደም በብሄራዊ ቡድን የታቀፉ አትሌቶች የላብ መተኪያ ወጪ እጅግ አናሳ መሆኑ በቅሬታ መልክ የሚነሳ ነበር። ይህንንም ለመቅረፍ በመንግስት በኩል በተቀመጠው አቅጣጫ መሰረት ለታዋቂ አትሌቶች 50ሺ ብር ደሞዝ እንዲያገኙ እንዲሁም ለሌሎች ጀማሪ አትሌቶች 10ሺ ብር በየወሩ የሚከፈላቸው ይሆናል። በልምምድ ግብዓት እንዲሁም ትጥቅ በኩልም ችግር እንዳይገጥማቸው እየተሰራ መሆኑም የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ከአትሌቲክስ ፌዴሬሽን ጋር በመሆን ከትናንት በስቲያ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ተገልጧል።
ዝግጅቱን በበላይነት የሚመራው የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ከስፖርት ማህበራትና ከሌሎች ባለድርሻዎች ጋር በመሆን ለቶኪዮ ኦሊምፒክ ዝግጅ በማድረግ ላይ እንደሚገኝ ይታወቃል። ለዝግጅቱም የቶኪዮ ብሄራዊ ዝግጅት ኮሚቴ እንዲሁም የቶኪዮ ኦሊምፒክ ቴክኒክ ኮሚቴ በሚልም ሁለት ኮሚቴዎችን አዋቅሯል። ብሄራዊ ኮሚቴው በቀድሞ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈጉባዔ አቶ አባዱላ ገመዳ የሚመራ ሲሆን፣ ትኩረቱን በሃብት አሰባሰብ፣ የልማት ስራዎች፣ የደጋፊ አባላት ላይ እንዲሁም በስፖርተኞች ሽኝትና አቀባበል ላይ ያደርጋል። በኢፌዴሪ ስፖርት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ ዱቤ ጂሎ የሚመራው የቴክኒክ ኮሚቴው ደግሞ ከተለያዩ ባለሙያዎች ጋር በመሆን በአትሌቶችና አሰልጣኞቻቸው ምርጫ ላይ የሚሰራ ይሆናል።
በዚህም መሰረት አትሌቲክስ ፌዴሬሽን እጩ አትሌቶችንና አሰልጣኞቻቸውን ከቀናት በፊት አሳውቋል። በማጣሪያ ውድድር ላይ ያሉት የቦክስና ወርልድ ቴኳንዶ ስፖርቶችን ጨምሮ ከውሃ ስፖርቶችና ብስክሌት ፌዴሬሽኖችም ጋር ኮሚቴው በትብብር በመስራት ላይ ይገኛል። ቀደም ብሎ ወደ ዝግጅት ምዕራፍ በመግባት ላይ የሚገኘው የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን በበኩሉ 90 አትሌቶችንና 15 አሰልጣኞችን በማጨት ወደ ልምምድ ለመግባት በመንደርደር ላይ እንደሚገኝ አስታውቋል። ብሄራዊ ቡድኑ በሶስት ምዕራፍ የተከፈለ ዝግጅት የሚያደርግ ሲሆን፤ በመጨረሻም 50 አትሌቶች ወደ ቶኪዮ የሚጓዙ ይሆናል። ለጊዜው በተሳትፎ ደረጃ የተያዘው ከ800ሜትር እስከ እርምጃ ባሉት ርቀቶች ቢሆንም ሚኒማውን ማሟላት ከተቻለ በ400ሜትርም ተሳታፊ የመሆን እድል እንደሚኖር ተጠቁሟል።
የቴክኒክ ኮሚቴው ቀድሞ ዝርዝራቸው ይፋ የተደረጉትን አሰልጣኞች የተመረጡበት መስፈርትም በርካታ አትሌቶችን በማስመረጥ እንዲሁም በዓለም አቀፍ ውድድሮች ባላቸው ልምድ መሆኑን ገልጿል። የአትሌቶች የምርጫ መስፈርት ደግሞ እአአ በ2019 ባስመዘገቡት ሰዓት መሰረት በመምረጥ በስራ አስፈጻሚ ኮሚቴው የጸደቀ መሆኑ ተብራርቷል።
ለኦሊምፒክ የሚደረገው ዝግጅት አገርን ለማስጠራት የሚደረግ እንደመሆኑ በሁሉም አካላት ዘንድ በተለይም በአትሌቲክስ ፌዴሬሽንና ኦሊምፒክ ኮሚቴ አመራሮች በኩል ያለው አለመግባባትን ከወደ ጎን በመተው ለውጤታማነት በጋራ መስራት አስፈላጊ መሆኑ በመግለጫው ተጠቁሟል።
አዲስ ዘመን አርብ የካቲት 13/2012
ብርሃን ፈይሳ