በኢትዮጵያ የፖለቲካ ሥርዓቶች ታሪክ ውስጥ ከሚገኙ ቁልፍ ጽንሰሀሳቦች መካከል አንድነትና ልዩነት (ብዝሃነት) ዋነኞች ናቸው። ፖለቲካው ራሱ የሚዘወረው በሁለቱ መካከል ባለው ተቃርኖና ልዩነት ነው። በመካከላቸው የነበረው ጤናማ ያልሆነ ግንኙነት ውስብስብ ሀገራዊ ችግር ሲፈጥር ኖሯል። ሁለቱም ያለ እርስ በእርስ የማይኖሩ ነገር ግን ደግሞ እንዳይስማሙ ተደርገው ቆይተዋል። እንዳይስማሙ የምናደርገው ግን እኛው በተለይም የሀገራችን ፖለቲከኞችና ሊህቃን ናቸው። አንዳንዶቻቸው የአንድነት አቀንቃኞች ናቸው። ሌሎች የብዝሃነት ታጋዮች ናቸው። ሁለቱም ተቃራኒ ቢመስሉም የሚያስተሳስራቸው የጋራ ጠባይ አላቸው። ሁለቱም እንከን አለባቸው – አንዱን በሌላ ውስጥ ማየት አይፈልጉም። በሁለቱ መካከል በሐሳብ በተሰራ የልዩነት ግድግዳ አንድነትን ከወዲህ፤ ብዝሃነትን ደግሞ ከወዲያ ማዶ ያስቀምጣሉ። በእነርሱ እምነት አንዱ በሚገኝበት ቦታ ሌላኛው መኖር ወይም መገኘት አይችልም። ፍላጎታቸው አንዱን በመወገን ሌላውን አዳክሞ መጣል ነው።
የተወሰኑ ዜጎች አንድነትን ያቆለጳጵሳሉ፤ ብዝሃነትን ግን ያንኳስሳሉ። አንዳንዶች ደግሞ ስለ ልዩነት እንጂ ስለ አንድነት ማሰብ አይመቻቸውም። ለምን ይሆን ብዙ ኢትዮጵያውያን ከሁለቱ ስለአንዱ እንጂ ስለሁለቱም አፋቸውን ሞልተው መናገር የሚፈሩት? ለምንድነው አንዱን በመፍቀድና በማቀፍ ሌላውን መንቀፍና አለመፍቀድ የተፈጠረው? በግልጽ የሚታየውን ልዩነት መደበቅ ወይም የሌለ ማስመሰል ምንድነው ፋይዳው? አንድነትን በጭፍን መግፋትስ ምንና ማንን ይጠቅማል? ሰዎች በአንድነት ውስጥ ልዩነቶች መኖራቸውን፤ በልዩነቶች ውስጥ አንድነት መኖሩን መረዳት ለምን ይሳናቸዋል? አንድነትን ከፍ አድርጎ ልዩነትን ዝቅ ማድረግ የተፈጠረው ባለማወቅ ሳይሆን በማወቅ ነው።
ከጥንት ጀምሮ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ የነበረው ትርክት በውስጣችን ለኢትዮጵያ የማይመች ማንነት ቀርጿል። አንድነትን ብቻ የሚያውቅ ኢትዮጵያዊ ማንነት ባንድ በኩል፤ ብዝሃነትን ብቻ የሚረዳ ማንነት በሌላ በኩል አለ። በእውን በመሬት ላይ ያለውን ማንነት በመተው በሐሳብ የሚንሳፈፍ ማንነት ፈጥሯል። በእኛ በኢትዮጵያውያን ሕይወት ውስጥ አንድ ግልጽ የማይሆን ነገር አለ። አንዳንድ የሰራናቸውንና የምንሰራቸውን ስለምናውቅ እንፈራለን። የፈራናቸውን ነገሮች ለመሸፋፈን ስንል ከመጠን በላይ የምናወድሳቸው ሌሎች ነገሮችን እንፈጥራለን በሐሳብ። ጊዜ ለመግዛት ውሸትን በውሸት እንሰፋለን። በዚህ ምክንያት ሁሌ ሚዛናዊ ያልሆነ አቋም እንይዛለን፤ ወደ ጫፍ የወጣ አስተሳሰብ ወይም እምነት እናራምዳለን። በቀኝ ጫፍና በግራ ጫፍ ላይ ቆመን ማብቂያ በሌለው ንትርክ እንመራረዛለን።
አንዳንድ ኢትዮጵያውያን አንድነትን አንዳች ዓይነት ረቂቅ ኃይል አድርገው በማግዘፍ ብዝሃነትን የማይፈለግና እርባና ቢስ አስመስለው ያቀርባሉ። ይህ የሆነውና የሚሆነው ያለ ምክንያት አይደለም። ሲጀመር እንዲህ ዓይነት እምነት የሚፈጠረው ሀገርን ከሚመሩት ገዢዎች ፍላጎትና ጥቅም ልክ የተቀረጸ አገዛዝ፤ ይኸንኑን ለማስፈጸም በሚዘረጋው ሥርዓትና በሚቋቋሙት ተቋማት ባሕርይ፤ ሥርዓቱ ሕዝቡን ከጎኑ ለማሰለፍ ሲል በሚያራምደው ርዕዮተ ዓለምና በሚያሰርፀው አስተሳሰብ ነው። ሀገሪቱን ሲመሩ የነበሩ አገዛዞች የተለያዩ ማንነቶችን ወደ አንድ ማንነት ጨፍልቀው መግዛት ፍላጎታቸውና ጥረታቸው ነበር። የተለያዩ የብሔርና የብሔረሰብ ባሕሎችን በማጥፋት አንድ ባሕል (monoculture) ብቻ በሀገሪቱ ውስጥ እንዲፈጠር የገዢዎች ጠንካራ ፍላጎት ነበር። ይህን እውን ለማድረግ የኢትዮጵያን የብዝሃነት (diversity) አጥፍቶ የአንድ ባሕል (monocultural) ማሕበረሰብ ለመፍጠር እንደ እስትራቴጂ የተወሰደው አንድነትን በማጋነን ብዝሃነትን ማሳነስና በሂደት ውስጥ እንዲጠፋ ማድረግ ነው።
የነበረው multicultural setting ያልተፈለገውና ያልነበረው monocultural setting የተፈለገው ለምንድነው? የተመረጠውስ ለማን ነው? ለሀገሪቱ እድገትና ደህንነት ታስቦ ነው ወይስ የመሪዎች ፍላጎትና ጥቅም፤ ምኞትና ሕልም በመሆኑ ብቻ ነው ? አንድነትም ሆነ ብዝሃነት የተፈጥሮ ችግር የላቸውም። በአግባቡ ካልተያዙ ወይም በሰዎች አስተሳሰብ፤ ፍላጎትና ትርጉም ግን በቀላሉ ወደ ችግር መቀየር የሚችል ባሕርይ አላቸው። በእርግጥ የኢትዮጵያ ሕዝብ በዚህ ጉዳይ እምብዛም ሲቸጋገር አልታየም። ችግሮች የተፈጠሩት ሁለቱም በጨቋኝ ገዢዎች አዕምሮ ሲቃኙና በቋንቋቸው ሲገለጹ ነው። በፍላጎታቸው ልክ አንዱን ከሌላው በመነጠል ሕዝብን ቢቻል የሚያሳምኑበት አሊያም የሚያደናግሩበት መሳሪያ አደረጉአቸው። ኢትዮጵያ የብዝሃነት መናኸሪያ መሆንዋ ይታወቃል። ይህ በሀገራችን የተፈጥሮ ሥርዓት፤ በሕዝባችን ሕይወትና ግንኙነት ውስጥ ይታያል። ባለመታደል ይህ የሀብትና የቅርስ፤ የውበትና የድምቀት፤ የኃይልና የዕውቀት ምንጭ የሆነው ብዝሃነት ለኢትዮጵያ ጨቋኝ ገዢዎችና ሥርዓቶቻቸው ፀጋ ሳይሆን መርገምት ሆኖ ታያቸው። መጥፋት እንደሚኖርበት ችግር እንጂ መጎልበት እንደሚገባው ፀጋ አልታሰባቸውም። በነበራቸው መንግስታዊ፤ ሕጋዊ፤ ፖለቲካዊና ርዕዮተ ዓለማዊ አቅም ለማፈን መሞከርን መደበኛ ተግባራቸው አደረጉ።
የሚያፍን ኃይልና ሥርዓት ባለበት ሀገር ውስጥ ላለመታፈን (በነፃነት፤ በሥልጣን፤ በመብትና በጥቅም ጥያቄ ዙሪያ) የሚንቀሳቀስ ኃይል ይፈጠራል። ብዝሃነት በባሕርይው ለተቀናቃኝ መፈጠር ምቹ ነው። በተለይ ጨቋኝ ሥርዓት በሚገዛው ብዝሃዊ ሕብረተሰብ ውስጥ ተቀናቃኝነት ብሎም ጠላትነት፤ አመፅ ብሎም ጦርነት ይከሰታል። ገዢዎች የተቀናቃኝን አቅም የሚያዳክም ወይም የሚያጠፋ አካላዊና ርዕዮተ ዓለማዊ ጥቃት ይፈፅማሉ። የራሳቸውን ተቀባይነት ለማጠናከርና ተቀናቃኝን ድጋፍ ለማሳጣት የሚያስችሉ አስተሳሰቦችን ሕዝብ ውስጥ ያሰርፃሉ። የጭቆና ሰለባ የሆኑ ወገኖች በበኩላቸው የገዢዎችን አስተሳሰብ፤ እምነትና የመጨቆኛ ኃይል ለመስበር መታገል የግድ ይሆንባቸዋል። በኢትዮጵያ አንድነትን ማወደስና ብዝሃነትን ማንኳሰስ፤ አንድነት በማራቅ ብዝሃነትን ማጥበቅ የተፈጠረው በእነዚህ ምክንያቶች ነው።
ከተመሪው ሕዝብ መካከል በማወቅ ወይም ባለማወቅ እንዲህ ዓይነቱን ርዕዮተ ዓለም የሚደግፉና የራሳቸው እምነት እስከመሆን ድረስ የሚያደርሱ አሉ። በብሔር-ብሔረሰባዊ ማንነታቸው ምክንያት በገዢዎች ርዕዮተ-ዓለም ተጠምቀው የአገዛዞቻቸው ጠባቂና ተንከባካቢ ወገኖች ይፈጠራሉ። ገዢዎች የወደዱትን መውደድ፤ የጠሉትን መጥላት የግድ ይሆንባቸዋል። በሐሳብ ደረጃ ራሳቸውን የገዢው መደብ አካል ያደርጋሉ። ገዢዎች ተራውን ሕዝብ ሳይጠቀሙ የተጠቀሙ፤ ሳያገኙ ያገኙ፤ ሳይከበሩ የተከበሩ፤ ሳይለዩ የተለዩ በማስመሰል ከተቀረው ሕዝብ ነጥለው ከጎናቸው ያሰልፏቸዋል። በተጨባጭ ሕይወታቸው ከተቀረው ተጨቋኝ ሕዝብ የተለዩ ባይሆኑም በአስተሳሰባቸው ከገዢዎች ጋር ሊቧደኑ ይችላሉ። በውል ቢያውቁት ፈቅደው የማይሆኑትን ነገር ይሆናሉ። ባልተረዱት መንገድ ራሳቸውን የጉዳዩ ባለቤት አድርገው በማያገባቸው ገብተው የሞቱት፤ የታሰሩ፤ የተሰደዱና የተሰቃዩ ወገኖች ብዙ ናቸው።
ስለእውነት አንድነት ያለ ልዩነት ኖሮ አያውቅም። ልዩነትም ያለ አንድነት ልዩነት አይሆንም። አንዱ ያለ ሌላው ትርጉም የለውም፤ ሕልውናም አይኖረውም። ያለ ልዩነት እንዴት ስለአንድነት ማውራት ይቻላል? ያለ አንድነት እንዴት ስለ ልዩነት ማሰብ ይቻላል? ባጭሩ አንዱ ያለ ሌላው አይታሰብም። ብዝሃነት የተፈጥሮም ሆነ የሰው ስራ ውጤት ነው። ሳረትሬ የተባለው የፈረንሳይ ፈላስፋ እንዳለው እያንዳንዱ ሰው የት፤ መቼና ከማን እንደሚወለድ መወሰን ወይም መምረጥ አይችልም። ጥቁር ወይም ነጭ፤ ኦሮሞ ወይም ሽናሻ ሆኖ መወለድ የራሱ ምርጫ ሳይሆን የተፈጥሮ ውሳኔ ነው። ሰው ሰራሽ የሚሆነው ደግሞ ሰው የሚፈልገውን የትምህርት ዓይነት፤ ሙያ፤ የመኖሪያ ሥፍራ፤ እምነት፤ ርዕዮተ ዓለምንና የመሳሰሉትን መርጦ መሆን ወይም መከተል ይችላል።
የሰው ልጅ ብዝሃነት ዘርንና ቋንቋን፤ እምነትን (ሃይማኖት) እና ባሕልን፤ አመለካከትንና እሴትን፤ ርዕዮተ ዓለምንና ሥነ-ልቡናን መሠረት አድርጎ በመፈጠሩ ከማንነት ጋር የተያያዘ ነው። በፖለቲካና በርዕዮተዓለም ትግል አኳያ በተለይ በብዝሃ ሕብረተሰብ ውስጥ የማንነት ጉዳይ እጅግ በጣም ቁልፍ ነው። ቀስቃሽና አነሳሽ ከመሆኑ አንጻር ሌሎች ሰዎችን በቀላሉ ለማቀፍም ሆነ ለመግፋት፤ ለመሰብሰብም ሆነ ለመበተን የሚያገለግል ነው። ለገዢዎች ወይም ለተቀናቃኞቻቸው አቅም በመፍጠር ወይም በማሳጣት አገልግሏል። የኢትዮጵያ ጨቋኝ ገዢዎች በአንድነት መሳሪያነት ብዝሃነትን ለማዳከም የሞከሩት ከዚህ አንጻር ነው።
በእርግጥ በኢትዮጵያ ብዝሃነትን መጨፍለቅ የተፈለገው የማይበገር አንድነትን ለመፍጠር ይመስላል – ለአንዱ የሚወግን አንድነት። ለመሆኑ ይህ አንድነትን ምን ያህል ጠቀመው? በንጹህ ሕሊና ካየን ከጠቀመው በላይ ጎድቶታል። የእርሱ ኦሮሞ መሆንንና ያንተ አማራ ወይም ወላይታ መሆንን፤ የእርሱ ጋሞ መሆንንና የሌላው ካምባታ ወይም ሐዲያ መሆንን ከመጥላት ይልቅ ማድነቁ የሚመረጥ ነበር። ገዢዎች ለራሳቸው ጉዳይ ሲሉ በፈጠሩትና በሚፈጥሩት ችግር ምክንያት ሁሌ ልዩነትን እንደ መርገምት እያሰብን እንድንኖር ተደርገናል። ሌሎች ወገኖች ደግሞ የአንድነትን አስፈላጊነት ለማሳነስ ተንቀሳቅሰዋል። በእርግጥ ብዙዎቹ የማይፈልጉት አንድነትን ሳይሆን በአንድነት ስምና ሽፋን የሚፈጸመውን ግፍና በደል ነው። የእነዚህ ወገኖች ኃጢአት ደግሞ መጥላትና መታገል የነበረባቸው የሚፈፀመውን ግፍና በደል እንጂ አንድነትን አይደለም።
ወደ ውስጥ ዘለቅ ብለን ብንፈትሽ አንድነትም ሆነ ብዝሃነት በሐሳብ እንዲንሳፈፉ የተደረጉ እንጂ በመሬት ላይ በእውን የሚንቀሳቀሱ ነገሮች አይደሉም። ብዙ ኢትዮጵያውያን «እንሞትለታለን» የሚሉት አንድነት ምንንም የማይገልጽ ባዶ ቃል ነው። ምክንያቱም በውስጡ ልዩነትን ያልያዘ አንድነት ነው። ከምንም በላይ አንድነትን የሚያዳክመው ይህ ነው። ለልዩነት «እንዋደቃለን» ለሚሉ ወገኖችም ልዩነት ያለ አንድነት የተበተነ ነገር ነው። ልዩነትን አቅም የሚያሳጣው አንድነት ከሚያሳድርበት ጫና በላይ ሰዎች ስለ እርሱ ያላቸው የተዛባ ግንዛቤ ነው። ልዩነት የሚኖረው በአንድነት ውስጥ ነው፤ አንድነት የሚታነፀው በልዩነት ነው። ሰው አንዱን በሌላው ውስጥ ከማየት ይልቅ አንዱን በማጋነንና ሌላውን በማንኳሰስ ትርምስ ይፈጥራል። አንድነትም ሆነ ልዩነት ችግር የሚሆነው እኛ በማበላለጥ በምንሰጣቸው ዋጋ ወይም እሴት ነው።
የሰው ልጆች ማንነት መሠረታዊ በሆኑ ጉዳዮች አንጻር ከታየ ከልዩነት አንድነቱ ሰፊና መሠረታዊ ነው። ይሁን እንጂ ተጨባጭ በሆነው ሕይወት ውስጥ ሚዛን የሚደፋው ከመሠረታዊው ጉዳይ ይልቅ መሠረታዊ ያልሆነው ነገር ነው። ሰዎች ውሳኔ የሚሰጡት በዚሁ መሠረት ነው። ፍጅትን የሚያስከትል ስሕተት በዚህ መልክ ይፈፀማል። በመሠረታዊ ጉዳዮች አንድ ሆነው እያሉ በአላዋቂነት፤ በራስ ወዳድነትና አልጠግብ-ባይነት ስሜታቸውን መቋቋም አቅቷቸው መሠረታዊ ባልሆኑ ልዩነቶች ይፋጃሉ። ዓለም አንድ ናት። አንድነትዋ የታነፀው ደግሞ በልዩነቶች ነው – የእልፍ አዕላፍ ነገሮች አንድነት። እያንዳንዳችንን ብንመለከት በተለያዩ ነገሮች የተዋቀረ አካልና አእምሮ አለን። እያንዳንዱ አካል የራሱ ስራ አለው። አንዱ የሌላውን አካል ስራ ተክቶ መስራት አይችልም። ያንዱ አካል ስራ ለሌላው አካል ስራ ግን ጠቃሚ ነው። አንዱ ከሌላው የሚቀበል ወይም ለሌላው የሚሰጥ ነገር አለው። ነገሮች ሁሉ ጎን ለጎን የተደረደሩ ሳይሆን አንዱ በሌላው ውስጥ የሚኖር ወይም ከሌላው ጋር የተቀናጀ ወይም የተዋደደ ነው። እነዚህ ቢበተኑ ስለመኖር ማሰብ ራሱ አይቻልም። አንድ ምሉዕ የሆነ የሰው ቁሳዊ ቁመና የተለያዩ አካላት አንድነት ነው። እነዚህ የተለያዩ አካላት በሥነ-ፍጥረታዊ ሕግ ባይገጣጠሙ ኖሮ የሰው ሰውነት ከየት ይመጣል? እግርና እጆች፤ ዓይኖችና ጆሮዎች፤ አፍና አፍንጫ ለየብቻቸው ሙሉ ቁመናው ያለው ሰው አይሰጡንም። ባጭሩ የእኔ እጅ በእጅነት መታወቅ የሚችለው በተሟላ ሰውነቴ ውስጥ ብቻ ነው።
የብዝሃነት አቀንቃኞች የአንድነትን እውነተነት ጥያቄ ውስጥ ማስገባት አይገባቸውም። በተመሳሳይ መንገድ አንድነታውያንም ልዩነትን የማይፈለግ አስመስለው በማቅረብ ለማጥፋት መነሳሳታቸው ስሕተት ነው። የሰውን ሰውነት ለአስረጂነት እንደገና እናንሳ። እግሮች፤ እጆች፤ ዓይኖች፤ ጆሮዎች፤ አፍ ወዘተ የሌሉበት የሰው ሙሉ ቁመና (አንድነትን) የማይኖር መሆኑ እየታወቀ ልዩነትን ዋጋ ማሳጣት አግባብ አይደለም። የአንድነትና ብዝሃነት ግንኙነትም በዚሁ መልክ መታየት ይችላል። ለመሆኑ ምን በቂ ምክንያት ቢኖር ነው በሕዝብ ሕይወት ውስጥ ያለው ብዝሃነት እንዳይኖር የተፈለገው? ምን በቂ ምክንያት ቢኖር ነው ያለ ብዝሃነት የአንድነት መኖር የታሰበው ? ይህን ጥያቄ በቀላሉ መመለስ ያስቸግራል። የተለያዩ ፍተሻዎች ቢደረጉ ግን በመጨረሻ የሚያደርሱት ካንድ ነገር ነው። የአንድነት መኖርም ሆነ የብዝሃነት አለመኖር የተፈለገው ከገዢዎች ጥቅም፤ ፍላጎትና አመለካከት አንጻር ነው። በኢትዮጵያ ታሪክ ከዚህ ውጭ ሌላ በቂ ምክንያት ይኖራል ብሎ ማሰብ ያስቸግራል።
ለአንድነት ሲባል የምናጠፋው ልዩነት ካለ ከፋፋይና አግላይ የሆነውን ነው። ለልዩነት ሲባል የሚኮነን አንድነት የሚኖር ከሆነ ጨቋኝ፤ ከፋፋይና አግላይ የሆነውን ነው። ሁለቱም በውስጣቸው ከያዙት አሉታዊ ነገሮች ከፀዱ አንድነት የልዩነትን ውበትና ድምቀት የሚያጎላ፤ ልዩነትም የአንድነትን ጉልበት የሚያፈረጥም ይሆናል። በደሎች ቢፈፀሙም ተስፋ የሚያስቆርጡ አይደሉም። ለአንድነት ሲባል ተጨፍልቆ የጠፋ ማንነት የለም። መልማት ባይችልም አንድነትም በልዩነት ምክንያት ተናግቶ አልጠፋም። የገዢዎች ርዕዮተ ዓለማዊ ሴራ የሕዝባችን እውነተኛ ሕይወትና ትስስር አልፈታውም። ባንዱና በሌሎች መካከል ያለውን ልዩነት በማጋነን አንድነትን ለመደፍጠጥም ሆነ፤ የአንድነትን አይነኬነት በመስበክ ልዩነትን ለማጥፋት ማሰብ ኪሳራ እንጂ ትርፍ አላስገኘም።
የዕድል ጉዳይ ሆኖ ኢትዮጵያ የብዝሃነት ሀገር ናት። አለመታደል ሆኖ ደግሞ ይህ ፀጋ ሳይሆን እርግማን መስሎ የታያቸው የኢትዮጵያ ጨቋኝ ገዢዎች አንዱን ይዘው ሌሎችን ሲያሳድዱ ኖሩ። የሚበጀንን ነገር ወደ ማይበጀን ነገር አስለወጡን፤ የማይበጀንን ነገር እንደሚበጀን ነገር እንድናቅፈው አደረጉን። በዚህ ምክንያት የአንዱ ዋጋ የሌላው ዋጋ መሆኑን ዘንግተን ከሁለቱም ማግኘት የሚገባንን ዋጋ ራሳችንን ስናሳጣ ኖርን። መሆን እንችል የነበረውን እንዳንሆን ሆን። መሆን ያልነበረብን እንድንሆን ተደረግን። ይህ አሻጋሪ ያልሆነ አስተሳሰብ ትውልዶችን እየተከተለና እየበከለ፤ እያበላና እያባላ ቀጥሏል። ባንዱና በሌላው መካከል ያለውን ልዩነት በማጉላት አንድነትን ለመደፍጠጥ፤ በሐሳብ ብቻ በገዘፈ አንድነት ልዩነትን ለማቅለጥ መሞከር አልበጀንም። ከእንግዲህ ውድቀትና ውርደት ይበቃናል። መንገዳችንን እንቀይር።
የሀገራችን መፃኢ ዕድል በዛሬው ትውልድ መዳፍ ውስጥ ነው። አንድነትና ብዝሃነት የሚፋለሱ አይደሉም። በዜግነታዊ ማንነታችንና በብሔር-ብሔረሰባዊ ማንነታችን መካከል ያለው ችግር ተፈጥሮአዊ አይደለም። ኢትዮጵያዊነት ብዝሃነትን በእኩልነት ማቀፍ ከቻለ፤ ብዝሃነት ኢትዮጵያዊነትን በቅንነት ካከበረ የሚከበርና የሚታፈር፤ የሚደመጥና የሚፈቀር ኢትዮጵያዊ ማንነትን መፍጠር ይቻላል። ለሰው ልጅ የማይበጀው ነገር ጠላት ነው – መሆን የማይፈልገውን ስለሚያደርገውና መሆን የሚፈልገውን ስለሚያሳጣው። ይህ ደግሞ የሚፈጠረው ከሁለት ቦታ ነው – ከራስ ውስጥና ከራስ ውጭ። የኢትዮጵያ ችግሮች ባብዛኛው የተፈጠሩትና የሚፈጠሩት ከውጭ ሳይሆን ከውስጣችን ነው። ካወቅንበት ይህ ራሱ ለኛ መልካም አጋጣሚ ነው።
የሚከበርና የሚታፈር፤ የሚደመጥና የሚፈቀር ኢትዮጵያዊ ማንነትን ለማነጽ አንድ ነገር ብቻውን በቂ ነው ቅንነት። ቅንነት ካለ የሚጎድሉ ሌሎች ነገሮችን ማሟላት ይቻላል። ለመልካም ነገር በቅንነት መነሳሳት ካለ በውስጣችን ያሉ እኩይ ነገሮች ይከስማሉ፤ በቦታቸው መልካም ነገሮች ያብባሉ። ቅንነትን ለማግኘት ብዙ መድከም አይጠበቅብንም። ምንጩ ከኛው ነው። ባንድ በኩል መልካም ነገርን ለማሰብና ለመስራት፤ ለመፍጠርና ለማምጣት፤ በሌላ በኩል መጥፎ ነገርን ላለማሰብና ላለመስራት፤ ላለመፍጠርና ላለማኖር ፈቃደኛ ከመሆን የሚመነጭ ነው – ቅንነት። ከዚህ የሚበልጥ ምን መልካምነት አለ ?
ሰላም
አዲስ ዘመን አርብ የካቲት 13/2012
ጠና ደዎ (ፒኤችዲ)፣አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ