የጥበብ አላማ፣ ግብና ተግባር በሁለት ዋና ዋና ዘርፎች ላይ ይንጠለጠላል። “ጥበብ ለጥበብነቱ”፤ ወይም “ጥበብ ለማህበራዊ ለውጥ” አለምን ከሁለት ጎራ ከፍለው ያወያያሉ። ምንም እንኳን ምርጫው የግል ቢሆንም ሁለቱም የየራሳቸው አድናቂ፤ ተግባሪ አላቸው። ያም ሆኖ ምርጫው እንደየ አካባቢው ሁኔታ፤ እንደየ አገራቱ ሁለንተናዊ እድገትና ስልጣኔ፣ ጥበብን የማጣጣም አቅምና ፍላጎት ይወሰናል።
ወደ አፍሪካ ስንመጣ ግን ሚዛኑ ወደ “ጥበብ ለማህበራዊ ለውጥ” አድልቶ እናገኘዋለን፤ ። ይህ ለምን ሆነ የሚል ጥያቄ መነሳቱ አይቀርም። እንደሚታወቀው አለም (ሼክስፒር እንዳለው) ቲያትር ነች። ዥንጉርጉርነቷም የሚጀመረው ከዚሁ ነው። የአለም ዥንጉርጉርነት ከሚገለፅባቸው አንዱ ሀብት ሲሆን ይህም ባለፀጋነትንና ደሀነትን አጣምሮ (ላይ/ታች) የያዘ ሲሆን፤ ከ19ኛው ክፍለ ዘመን መባቻ ጀምሮ ብሶበት፤ ቀለምና ዘርን ተንተርሶ ወደ አድራጊ ፈጣሪነት ነግሷል። በዚህን ጊዜ ነው ልዩነቱ እየሰፋና እየከፋ የሚሄደው። በዚህን ጊዜ ነው የጥበብ አላማ፣ ግብና ተግባር የሚለያየው፤ በዚህ ጊዜ ነው የህዝቦች ለጥበብ ያለ አተያይ ግራና ቀኝ ላይና ታች የሚቆመው። ማርክስ “መደብ” እንዳለው ሁሉም የየራሱን መደብ ይሰራና ቁጭ ይላል። ከዛ ትግል …
ነገሩ አይደንቅም። ገዥና ተገዥ፣ ሀብታንምና ደሀ፣ ጭቁንና ጨቋኝ (እንደ ቅኝ ገዥዎችና አፓርታይድ ስርአት አራሞጆች ደግሞ “ነጭ” እና “ጥቁር”) … ስለ አንድ ነገር ተመሳሳይ እይታን ሊይዙ አይጠበቅም። ይሁን ቢባል እራሱ አተያዩ የ”እውነት” እና የ”ውሸት” ተብሎ በሁለት ከመከፈል አያመልጥም። ለምን? እራሱ የተፈጥሮን ተፈጥሮ ይቃረናልና ነው። ይህ አንድ የሚያስታውሰን ቁም ነገር አለ። የአፍሪካ ህፃናት የሚመገቡት አጥተው በከፋ ረሀብ ላይ መገኘታቸው የተነገራቸው ፈረንሳዊት (ንግስት?) “ለምን ኬክ አይበሉም?” አሉ ተብሎ አንድ ሰሞን መነጋገሪያ ሆኖ ነበር፤ ልክ ናቸው። ታዲያ ስለማያውቁት ረሀብ ምን ይበሉ? ያወቁት ነገር ቢኖር ህፃናቱ የሚበሉት ማጣታቸውንና እሳቸው ጋር ደግሞ ኬክ እንደልብ መኖሩን ነው። አለቀ። ለእነዚህ ሁለት ሰዎች የማይክል ጃክሰን “ትሪለር” ምንና ምናቸው ነው? ጥያቄው። በአፍሪካ የነፃነት ዋዜማ ሲስተዋል የነበረው ይሄው ነበር። ማግስቱም ቢሆን ገና አልፀዳም። በመሆኑም ነው አፍሪካዊያን ስለ ጥበብ ያላቸው አቋምና እይታ “ጥበብ ለማህበራዊ ለውጥ” ላይ ያተኮረው።
እ.ኤ.አ በ1955 ኖርዲክ አፍሪካ ኢንስቲትዩት (Nordic Africa Institute) የተባለ ተቋም በአፍሪካ የጥበብን ድርሻ በተመለከተ በአይነቱ ልዩ የሆነና “African Images in and of Africa” በሚል የተሰየመ ትልቅ ኮንፈረንስ አዘጋጅቶ በርካታ አለም አቀፍ ምሁራን የተገኙና የተለያዩ ጥናቶችን ያቀረቡ ሲሆን የተደረሰበትም ማጠቃለያ የአፍሪካ ጥበብ በተለይም “ሙዚቃ የአፍሪካዊያንን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግሮች መጋፈጥ፣ ማጋለጥ፣ መፍትሄ መጠቆምና ህብረተሰቡን ከእነዚህ ችግሮች ነፃ ማውጣት ይገባዋል” የሚል ነበር። ይህ የዛሬም የአፍሪካ አቋም ነው።
የአፍሪካ ጥበብ (African Art) ከሌሎቹ፤ በተለይም ካደጉት አገራት የሚለየው በዚሁና በዚሁ መሰረታዊ ጉዳይ ነው። በመሆኑም ነው በአፍሪካ ከ”ጥበብ ለጥበብነቱ” ከሚለው “ጥበብ ለማህበራዊ ለውጥ” የሚለው ሚዛኑን የሰቀለው።
የ”ጥበብ ለማህበራዊ ለውጥ” አራማጅ አፍሪካዊያን ምሁራን፣ ንድፍ ሀሳብ ቀማሪዎችና አንቂዎች የቹና አቼቤን “Things Fall Apart” ልቦለድ (ቁንጮ ስራው ነው)፣ የቦብ ማርሌይን በርካታ ዜማዎች፣ የደቡብ አፍሪካዊቷ ማሪያ ኬሪንና ሌሎችንም ዋቢ በማድረግ ፊት ለፊት ይቆማሉ።
እነዚህ ግንባር ቀደም ተፋላሚዎች ይህንን እንዲሉ ያደረጋቸው “አፍሪካን መቀራመት” የወለደው የኢምፔሪያሊስቶች መስፋፋት፣ የቅኝ ገዥዎች ወረራና ፀረ-አፍሪካ ተግባራት፣ የከፋ ጭቆና፣ ስር የሰደደ ድህነት፣ የተበላሸ የፖለቲካ ስርአት፤ ነባሩ ቱባ ባህላቸው በቅኝና እጅ አዙር ቅኝ ገዥዎች መሰበሩ ወዘተ ምክንያት መሆኑን በማስረጃ አስደግፈው ይናገራሉ። አፓርታይድ፣ የባህል ወረራ፣ የማንነት ስብራት፣ የሀብትና ንብረት ዘረፋ፣ የቋንቋ ደፈቃ፣ የስርአተ ትምህርቱ ከአፍሪካዊነት መነቀል (በኬኒያ፣ ናይጄሪያ … እስካሁን መልሶ መትከል እንኳን አልተቻለም) እና የባህል ወረራ ሁሉ ለ”ጥበብ ለማህበራዊ ለውጥ” አፍሪካዊ ተቀባይነት ተገቢውን አስተዋፅኦ አድርገዋል። የጉዳዩ ማስኬጃ፣ መታገያና ማታገያው የአድዋው ድል የወለደው የ”ኢትዮጵያዊነት ንቅናቄ” መሆኑ ደግሞ ለእይታው ስር መስደድ ያደረገው አስተዋፅኦ ከበቂ በላይ ተሰንዷል።
ከቀዳሚ ተጠቃሹ ንጉስ ሀይለሥላሴ፣ ጁሊየስ ኔሬሬ፣ ጆሞ ኬኒያታ፣ አህመድ ሴኩ ቱሬ፣ ኳዋሜ ኑክሩሁማ፣ ቶማስ ሳንካራ፣ ሙአመር ጋዳፊ፣ ማርኮስ ጋርቬይ፣ ማልኮም ኤክስ፣ ደብሊው.ኢ.ቢ.ዱ ቦይስ፤ ማንዴላ፣ ንጉጊ፣ሁፍ ማስክላ እንዲሁም ሌሎች በርካታ አፍሪካ- አሜሪካዊያን እኩል (ምንልባትም በላይ) ስማቸው የሚነሳ የፈጠራው አለም ሰዎች በርካቶች ሲሆኑ፤ ህይወቷን ሙሉ ለዜጎች ሰብአዊ መብት መከበር አሳልፋ የሰጠችው ደቡብ አፍሪካዊቷ ሚሪያም ማኬባ (Mama Africa)፣ ቦብ ማርሌይ፤ ቱስ ምኔይሌ፣ ሳሙኤል ጄምስ፣ ኡስማን ሰምቤል እጅግ በጣም ብዙ አፍሪካዊና አፍሪካ-አሜሪካዊ ድምፃዊያን የለውጡ አንቀሳቃሽ ሞተሮች እንደነበሩ ታሪክ ይናገራል። ሰአሊ ዋልተር ባተስትና ሌሎችም እዚሁ ምድብ ስር ናቸው። (እዚህ ጋ ኢትዮጵያን ከሌላው አፍሪካዊ ለመለያየት በማሰብ እቴጌ ጣይቱ ብጡልን “እናንተ ጥቁር አይደላችሁም። ለምን አፍሪካ አፍሪካ ትላላችሁ?” ሲል ለጠየቃቸው ሰላቶ “ታዲያ ምንድን ነን?” ሲሉ የመለሱትንም መዘንጋት ታሪካዊ ክህደት ይሆናል።)
ከደራሲያንም በኩል ተመሳሳይ ሲሆን ዎሌ ሶይንካ፣ ፒተር አብረሀም (በደም ኢትዮጵያዊ)፣ አሌክስ ላጉማ፣ ቹና አቼቤ፣ ፀጋዬ ገብረመድህን፣ ሴዳር ሲንጎር፣ ክንፈ አብረሀ (ባመሻሽ እድሜያቸው ብእራቸው ወደ ፖለቲካው በማመዘኑ የማይታለፍ አስተዋፅኦዋቸውን አደበዘዘው እንጂ) እና ሌሎች በርካቶችም ቀዳሚ የቅኝ አገዛዝና አፓርታይድ ትግል ፊት መሪዎች በመሆን ከቅኝ አገዛዝና አፓርታይድ ስርአት በፊት (ዋዜማ፣ ጊዜ/መባቻ እና በኋላ/ማግስት ባለው ሂደት ውስጥ ከፍተኛውን የነጭ የበላይነት በማጋለጥ፣ ህዝቡን በማንቃትና በማታገል፤ አገዛዙን ከነሰንኮፉ (አሁንም አልጠፋም የሚሉ ቢኖሩም) ነቅሎ በመጣል ስራ ተሰርቷል።፤ ነባሩን መልሶ በመትከል፤ የህብረተሰቡን ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊ፤ ከሁሉም በላይ ሰብአዊ መብቱን ከማስከበርና አፍሪካዊ ማንነቱን ከማስመለስ አኳያ ከፍተኛ ሀላፊነትን የተወጡ ናቸው። ፍልስፍናቸው ኢትዮጵያንኒዝም “Ethiopianism”፣ “Harlem Renaissance”ና ከእሱ የተገኘው “Négritude ”ም ሳይሰመርባቸው ቢታለፉ ሀሳቡን ጎደሎ ያደርጉታል።
በተለያዩ ወቅቶች በተካሄዱ የአፍሪካ ምሁራን ውይይቶች በከፍተኛ ደረጃ ሲያከራክር የቆየው “የአፍሪካ ጥበብ ምን ምን ላይ ማተኮር አለበት?” የሚለው ነው። ይህም ለበርካታ ዓመታት ውይይት፤ ንድፈ ሀሳባዊ ክርክር ከተደረገበት በኋሏ “የአፍሪካ አተያይም ሆነ ጥበብ ሊያተኩርባቸው የሚገቡ አበይት መስኮች “ሥነጽሑፍ” እና “ፍልስፍና” መሆናቸው ተለይቷል። ይህም ከአፍሪካ ባህል፣ እምነትና ማንነት አንፃርና “የአፍሪካን ችግር በአፍሪካዊ መፍትሄ መፍታት”፤ “አፍሪካ ለአፍሪካዊያን” (ዛሬ በአፍሪካ ህብረት ደረጃ እየተቀነቀኑ ያሉ) ላይ እንዲያተኩር ስምምነት ላይ በመደረሱ ይሄው የአፍሪካ እሴቶች ተገቢውን ቦታና አለም አቀፍ ደረጃቸውን ለማግኘት ችለዋል። (ለምሳሌ “የአፍሪካ ሥነጽሑፍ/African Literature” ራሱን ችሎ በአለም አንጋፋ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መሰጠት ከጀመረ ቆየ)።
አዲስ ዘመን አርብ የካቲት 13/2012
ግርማ መንግሥቴ