ዓለም የምትመራው በሀሳብ ነው። ሊያውም የተለያዩ ሀሳቦች ቀርበው የተሻለው የቱ ነው? በሚል ብዙዎቹ ምርጥ ሀሳቦች በልዩነት ቀርበው እጅግ በጣም የተሻለ የተባለው ሀሳብ አሸንፎ አገር፣ እንዲያም ሲል ዓለም ይመራበታል።
ይሁን እንጂ ሁሉም አካል ወይም ፖለቲከኛ ደግሞ ሀሳብ አለው ማለት አይቻልም። አንዳንዱ ሀሳብ ያለቀበት በሚመስል መልኩ ራሱን እና ጊዜውን በግጭት እና በሴራ ፖለቲካ የሚያጠፋ፤ ህዝብንም ወዳልተፈለገ አውዳሚ አቅጣጫ የሚመራ አመለካከት ያለው እዚሁ አቅራቢያችን መኖራቸው ምን ነካቸው አስብሏል።
ይህ አጥፊ አመለካከት ወይም አባዜ በተለይ አገር ከሚመራ የሚጠበቅ ሳይሆን የሚወገዝ ተግባር ነው። ጥፋት ጥፋትን፤ ግጭት ግጭትን፤ ጦርነት ደግሞ ጦርነትን እንጂ ሌላ ምን ሊወልድ። የሀሳብ አለመግባባት ወይም ልዩነት ተፈጥሯዊ ነው።
ልዩነት የሚፈታበት መንገድ ግን ተፈጥሯዊ ሳይሆን የአመራር ጥበብን ይጠይቃል። ይሁን እንጂ በ‹‹እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል›› አስተሳሰብ ህፃናትን ጭምር ለጥፋት እና ለሴራ ፖለቲካ ማዘጋጀት ዛሬም ከትናንት አለመማራችንን በግልፅ የሚያሳይ ነው።
ይህን ድርጊት ተምሳሌታዊ በሆነ መንገድ በመገናኛ ብዙሀን ሳይቀር በማሰራጨት ህጻናትን ለጦርነት ማዘጋጀት ወይም መስበክ ተገቢ እንዳልሆነ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ ባወገዙበት በሰሞኑ ንግግራቸው “ልጆቻችንን እስክሪቢቶና እርሳስ፣ መጸሀፍ ቅዱስና ቁርአን እንጂ የጦር መሳሪያ አናሸክማቸውም” ሲሉ የኮነኑት።
በመሆኑም በረባ ባልረባ የኢትዮጵያን ሰላምና አብሮነት ከማደፍረስ ይልቅ አንድነቷን መጠበቅ ያስፈልጋል። ነገር ግን በአንድነትና በሰላም ስም ታዳጊዎችን የጦር መሳሪያ ማሸከምና ስለጦርነት ማስተማር ተገቢ ካለመሆኑ በላይ ዓለም ያወገዘው ተግባር መሆኑን ልብ ሊባል ይገባል።
ህፃናትን ገና በለጋ ዕድሜያቸው ስለቴክኖሎጂ፣ ፈጠራና፣ አብሮነት ማስተማር ሲቻል በሰላም አገር የጦርነት ነጋሪት መጎሰምና ስለጦርነት ማስተማር ምን ይሉት ተግባር ይሆን? የሞራል ጥያቄም የሚያስነሳ ነው። በፖለቲካ ሀይሎች መካከል የተፈጠረ ችግር ካለ በመደማመጥ ለችግሮች ዘላቂ መፍትሄ ማበጀት ብልህነት ነው፤ የአመራር ጥበብንም ይጠይቃል። ይሁን እንጂ ህጻናትን ስለጦርነት ማስተማር በስነ ልቦናቸው ላይ ጭምር ሳይፈልጉ ችግር መፍጠር በመሆኑ ሊወገዝ ይገባል። ህፃናቱ ነገ አድገው ፖለቲከኛ ቢሆኑ እንኳ ችግሮችን በውይይት ከመፍታት ይልቅ ጦርነትን ብቸኛ አማራጭ አድርገው እንዲያዩ መጥፎ ትምህርት እንዲሰንቁ ማድረግ አይገባም።
«የአገሩን ሰርዶ በአገሩ በሬ» እንደሚባለው በፖለቲካ ፓርቲዎች መካካል የተፈጠረ መቃቃር ካለ በጠረጴዛ ዙሪያ ተወያይቶ መፍታት ያስፈልጋል። ልዩነትም ካለ በሀሳብ ልዕልና አምኖ መቀበልን ይጠይቃል። ይህም ካልሆነ በባህላችን ልዩነትን በሽምግልና ለመፍታት የአገር ሽማግሌዎች ግንባር ቀደሙን ሚና እንዲጫወቱ ምቹ ሁኔታ መፍጠር ያስፈልጋል።
የፖለቲካ ፓርቲዎችም ሆኑ አገር እየመሩ ያሉ አካላት የህዝቦችን የአብሮነት ገመድ ከሚበጥስ፣ ህጻናትን ስለ ጦርነት ከሚያስተምር፣ ህዝቦችን ለግጭት ከሚዳርጉ ድርጊቶች መቆጠብ አለባቸው።
የሀሳብ ልዩነትን በውይይትና በሀሳብ የበላይነት በማመን መፍታት እየተቻለ ወደ ድህነት አረንቋ ከሚዘፍቅና ለጋ ወጣቶችን ወደ ጦርነት ከሚገፋ ኋላቀርነት መራቅ ይገባል። እክሳሪም፣አውዳሚና ትውልድን የሚያሳጣ ነው። ስለዚህ ችግሮች በሀሳብ ልዕልናና ውይይት መፍታት የአሁኑ ዘመን ብቸኛ አማራጭና ተመራጭ መሆኑን ልብ ይሏል።
አዲስ ዘመን የካቲት 13/2012