. የከፍተኛ አመራሮችን ሹመትም አጽድቋል፡
አዳማ፡- ጨፌ ኦሮሚያ አቶ ሽመልስ አብዲሳን የክልሉ ወደ ሙሉ ፕሬዚዳንትነት አምጥቷል። የከፍተኛ አመራሮችን ሹመትም አጽድቋል።
ጨፌው ለሁለት ቀናት ባካሄደው አምስተኛ ዓመት የሥራ ዘመን 11ኛ መደበኛ ጉባኤ በአባላት በተሰጠው ድምጽ የብልጽግና ፓርቲ እሳቤ ዳር ለማድረስ ቀደም ሲል በምክትል ርዕሰ መስተዳድርነት ማዕረግ ሲሰሩ የነበሩትን አቶ ሽመልስ አብዲሳ በሙሉ ፕሬዚዳንትነት ሾሟል። ፓርቲው በክልሉ መልካም አስተዳደርና ዴሞክራሲን በማስፈን እንዲሁም የክልሉን ህዝብ ጥቅም በማስጠበቅ ረገድ ከፍተኛ አበርክቶ እንዳደረገም ተመልክቷል።
ጨፌው በክልሉ ፕሬዚዳንት አቶ ሽመልስ የቀረቡ የተለያዩ ከፍተኛ አመራሮች የሹመት ማዕረግ ሰጥቷል። በዚሁ መሰረት ወይዘሮ ጫልቱ ሳኒ ፣ምክትል ፕሬዚዳንት፣ አቶ ፍቃዱ ተሰማ የክልሉ መንግሥት ተጠሪ፣ አቶ አዲሱ አረጋ በምክትል ፕሬዚዳንት ማዕረግ የማህበራዊ ዘርፍ ክላስተር አስተባባሪ፣ አቶ ጀማል ከዲር የከተማና ቤቶች ልማት ቢሮ ኃላፊ ፣ አቶ ጌታቸው ባልቻ የክልሉ ኮሚኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ ፣ አቶ ጂብሪል መሃመድ የሰላምና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ፣ አቶ ቦጋለ ፈለቀ የኢንተርፕራይዝና ኢንዱስትሪ ቢሮ ኃላፊ ፣አቶ ካሳሁን ጎፌ የገቢዎች ቢሮ ኃላፊ ፣ አቶ ዳንኤል አሰፋ የክልሉ ጠቅላይ አቃቤ ህግ ፣ አቶ ከበደ ዴሲሳ የባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ፣ አቶ ተሾመ ግርማ የሥነ ምግባርና ጸረ-ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር ሆነው ተሹመዋል።
በሌላ በኩል ጨፌ ኦሮሚያ በተለያየ ደረጃ ለሚገኙ 49 ዳኞች ሹመት ሰጥቷል። ከእነዚህ ውስጥ 44 ወንዶችና 5 ሴቶች ይገኛሉ።
ለከፍተኛ ፍርድ ቤት 5 ዳኞች የተሾሙ ሲሆን ከእነዚህም ውስጥ 4 ወንዶች 1 ሴት ዳኞች ተሹመዋል።
ጨፌው አራት አዳዲስ ረቂቅ አዋጆችንና አንድ የማሻሻያ አዋጅን አጽድቋል። ከጸደቁት አዳዲስ አዋጆች የማዕድን ሃብት ልማትን በአግባቡ ለመጠቀም የሚያስችልና አይነቶቹን በመለየት ለተለያዩ ተግባራት መጠቀምን የሚመለከት ነው። የኦሮሚያ መንገዶች ፈንድን በተመለከተም የቀረበው ረቂቅ አዋጅ መንገድ ክልሉ ካለው ሀብትና የኢኮኖሚ ፍሰት አንጻር ወሳኝ ጉዳይ እንደሆነ ጠቅሶ ከመንግሥት ድጋፍ በተጨማሪ ሌሎች አካላት በመንገድ ሥራ ተሳትፎና ድጋፍ እንዲኖራቸው የሚያበረታታ ነው።
የኦሮሚያ የህግ ዝግጅት ረቂቅ የሚያተኩርባቸው ጉዳዮች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን የበለጠ ለማስጠበቅ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ፖሊሲዎችን ለመተግበር የክልሉን ልማትና ሰላም ለማረጋገጥ ያለመ ነው።
የገዳ ልዩ የኢኮኖሚ ዞንን አስመልክቶ የተዘጋጀው ረቂቅ አዋጅ ክልሉንና የክልሉን ነዋሪዎች ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያስችል እሳቤ ያለው ሲሆን በተለይም የውጭ ባለሃብቶችን በመሳብ በኩል ክልሉን በማስተዋወቅ ኢኮኖሚያ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ታስቦ የጸደቀ አዋጅ ነው ።
በሌላ በኩል የኦሮሚያ የህግ ዝግጅት አዋጅ ማሻሻያ የተደረገበት ሲሆን ይህም የመንግሥት ተሿሚዎች ፣ የህዝብ ተመራጮችና ከኃላፊነት የተነሱ የህግ ባለሙያዎች የሚገባቸውን ጥቅማ ጥቅም ለማስከበር የተሻሻለ ነው። ይህም ወደ ስልጣን የሚመጡ ሰዎች ያለምንም ስጋት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ የሚያስችልና ስልጣን ከለቀቁ በኋላም ያለምንም ስጋት እንዲኖሩ ዋስትና የሚሰጥ መሆኑ ተጠቁሟል።
አዲስ ዘመን የካቲት 12/2012
ኢያሱ መሰለ