የቅኝ አገዛዝን በመቃወም አገራዊ ሉዓላዊነትን ለማስከበር በኢትዮጵያ ታሪክ ከባዕዳን ወራሪዎች ጋር ታላቅ ተጋድሎ የተደረገባት የካቲት ወር ታላቅ የታሪክ መዘክር ናት። የካቲት 12 ቀን 1929 ዓ.ም. በሮዶልፍ ግራዚያን ትዕዛዝ በአዲስ አበባ በተከታታይ ቀናት የተፈጸመው ጭፍጨፋ ከ30 ሺሕ በላይ ኢትዮጵያውያን አልቀዋል። ይህ አሰቃቂ እልቂት የተፈጸመው የዛሬ 83 ዓመት በያዝነው ሳምንት ነው።
ወቅቱ ሴት ወንዱ ለውጊያ የተዘጋጀበት፤ አርበኛ ሆኖ መሞት የተናፈቀበት ጊዜ ነበር። የስድስት ኪሎ የያኔው ቤተመንግስት የአሁኑ ዩኒቨርስቲ ከአዲስ አበባ በግድም በውድም በተሰበሰቡ ባብዛኛው ሴቶችና ሕፃናት ተሞላ። እብሪት የተሞላበት የሩዶልፍ ግራዝያኒ ንግግር ተጀመረ። በንቀት ያየው ሕዝብ ላይ ስለ ”ታላቂቱ ጣልያን” መደስኮር ጀመረ። ግን ብዙ አልቆየም አብርሃ ደቦጭና ሞገስ አስገዶም ሕዝቡን ጥሰው ከፊቱ ደረሱ፤ ሰባት ቦንቦችን አከታትለው ወረወሩበት፣ግራዝያኒ ቆሰለ፣ የአየር ኃይሉ ኃላፊም ተገደለ። አብርሃ እና ሞገስ በቅዱስ ማርቆስ ቤተክርስቲያን በኩል ባለው የቤተመንግስቱ የጋራ አጥር ዘለው ወጡና ታክሲ ይዞ ወደሚጠብቃቸው ስምዖን ገሰገሱ፣ ስምዖን በታክሲ ወጣቶቹን ይዞ ነጎደ።
የካቲት 12 ቀን 1929 ዓ.ም አብርሃ ደቦጭ እና ሞገስ አስገዶም ግራዚያኒ ላይ ቦምብ ወርውረው ካቆሰሉት በኋላ ፋሽስቶች 30 ሺ ያህል የአዲስ አበባን ሕዝብ ጨፍጭፈዋል።
የየካቲት 12 የሰማዕታት ቀንን ከሚተርኩ መጻሕፍት ውስጥ በእማኝነት በአቶ ተመስገን ገብሬ የተጻፈው ‹‹ሊቀ ጠበብት እውነቱና የካቲት 12›› የተባለው መጽሐፍ ይጠቀሳል።አቶ ተመስገን ስለየካቲት 12 ግፍና ሰቆቃ በጻፉት ጽሑፍ ጣሊያን ኢትዮጵያ ላይ ያደረገችው ግፍና ጭካኔ እያንዳንዱን ድርጊትና ሁኔታ መሳጭ በሆነ መልኩ እንዲህ ጽፈውታል።
“ከሦስት ቀን የከተማ ጥፋት በኋላ ከሆለታ የመጡ የፋሽስት አውሬዎች በሚመለሱበት ካሚዮን በኋላው በኩል አቶ አርአያን እግራቸውን ጠርቅመው አሰሯቸው። ካሚዮኑ ሳይጐትታቸው “እኔ ወደ ሰማይ እንድገባ ሰማይ ተከፍቶ ይጠብቀኛል። እየሱስንም በዚያ አየዋለሁ። ደስ ይለኛል። ደስ ይለኛል። ደስ ይለኛል!” የሚለውን የሚሲዮን መዝሙር ዘመሩ። ፋሽስቶቹም የተሻለውን መዝሙር ብትሰማ ይሻልሃል አሏቸውና ዱኪ ዱኪ የሚለውን መዝሙራቸውን ዘመሩ።
ካሚዮኑ ሞተሩን አስነስቶ ሲነዳ ታስረው ቁመው ነበርና ያን ጊዜ ዘግናኝ አወዳደቅ አቶ አርአያ ወደቁ። ካሚዮኑም እየፈጠነ ጐተታቸው። ከአዲስ አበባ እስከ ሆለታ አርባ ኪሎ ሜትር ይሆናል። ካሚዮኑ ከዚያ ሲደርስ ያ ከካሚዮኑ ጋር የታሰረው እግራቸው ብቻ እንደተንጠለጠለ ነበርና የካሚዮኑ ነጂ ከካሚዮኑ ፈታና ለውሾች ወረወረው።
እኔንም ያለሁበትን ቤት ሰብረው ከዚያ ቤት ያለነውን አውጥተው ከየመንደሩም ሕዝቡን ያጠራቀሙበት መሐል ጨመሩን። ስምንት መትረየስ በዙሪያችን ጠምደዋል። በዚያም ቦታ ቁጥራቸው በብዙ የሆኑ ሐበሾችን አስቀድመው ገለዋቸዋል። ሬሣቸውም ተቆላልፎ በፊታችን ነበረ። እኛንም በዚያ ሊገድሉን ተዘጋጁ። ለመትረየስም ተኩስ እንድንመች ያንዳችንን እጅ ካንዱ ጋር አያይዘው አሰሩን።
አሥረውን ወደ መተኰሱ ሳይመለሱ አንድ ታላቅ ሹም መጣ። የርሱም ፖለቲካ ልዩ ነበረ። ፋሽስቶች የሚያደርጉትን የሰላማዊ ሕዝብ መግደል፤ ሕፃናቶችን ከአባትና እናታቸው ጋራ በቤት ዘግቶ ማቃጠል መልካም ብሎ ቢወድ እንኳን እኒያ ቦምብ በቤተ-መንግስቱ ስብሰባ የወረወሩት ሐበሾች ሳይታወቁ እንዲቀሩ አይወድም ነበርና ስለዚህ ካሚዮኖች ይዞ እየዞረ ፋሽስቶች የሚገድሉትን እያስጣለ ወደ እስር ቤት ለምርመራ ይወስድ ነበር። እኛንም እንዲተኮስብን ታሰረን ከቆምንበት ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጠበል አጠገብ ካለው ሸለቆ እስራታችንን አስፈትቶ በአምስት ረድፍ ወደላይኛው መንገድ ለመድረስ ስንሄድ በአካፋ ራሳቸውን የተፈለጡ እጅግ ብዙ ሰዎች አየን።
ለጊዜው እስር ቤት ያደረጉት ማዘጋጃ ቤትን ነበር። በአምስት ካሚዮን ያጠራቀመንን ሰዎች በዋናው መንገድ እንድንቆም አዘዘን። ዙሪያችንንም ከበው በሳንጃ እየወጉን ጭፍቅ ብለን በመንገዱ ቆምን። ከወደኋላችን ትልቁን የጣሊያን ካሚዮን በላያችን ላይ ነዱብን። አስራ ስምንት ቆስለው አልተጨረሱም፤በሳንጃ ጆሮአቸውን ወጓቸው። በአንድ ጊዜ ማለት አርባ ስምንት ሰዎች ጨፈለቀ። ተካሚዮኑ ወደኋላ ያፈገፈጉትን እሥረኞች ዙሪያውን ሳንጃ መዘው የቆሙት ወጓቸው። እኔም በካምዮኑ ጉልበቴን መታኝ።
በሌሊት ወስደው ከገደሉት በእስር ቤት የቀረው ያንሳል። ነገር ግን በዚህ ለመግደል ሲያወጡ የሚበልጥ በዚያ በር ያገቡ ነበር። በበነጋው ከተደበደበው ሕዝብ ከኪሱ የተገኘውን እየቆጠሩ ለሹሙ አስረከቡ፤ እኔም ከጽሕፈት ቤቱ ፊት ለፊት ነበርሁ። የደበደቧቸውን የሐበሾችን የጋብቻ ቀለበታቸውን በሲባጐ እንደ መቁጠሪያ ሰክተው ደርድረው በአንገታቸው አግብተው አቀረቡት። አንዱ ቆጥሮ መዝኖም እስኪያስረክብ ሌላው ገና ባንገታቸው ነበር።
ንፁህ የሆነውንም ልብስ በካሚዮን አምጥተውት ነበርና እየቆጠሩ አስረከቡ። ከጥቂቶች በቀር ሙሉው ልብስ በደም አልተበላሸም። በመሬትም ጣል ጣል እያደረጉ እየቆጠሩ እስኪረከቡ የጥቂቶች ልብሶች ገና እስከ ትኩስ ደም ኑረው ከመሬት መልሰው ሲያነሱዋቸው አፈር እና ግብስባሱን እየያዙት ሲነሱ አየሁ።
ይህን ባየ ጊዜ አንዱ ብድግ ብሎ ‹እርሷን አሁን ከመሬት አፈር ይዛ የተነሳችውን ደም እግዚአብሔር አየ፤ ሊፈርድ ነው። ይህ ክፉ ስራችሁ በጭካኔ ሕዝቡን የሰው ሕይወት በማጥፋት ትጫወታላችሁ። የገደላችኋቸው ወገኖቻችን ቀለበት በሲባጐ ሰክታችሁ መዝናችሁ ወሰዳችሁ። ደማችንን መሬቱ መጠጠው፤ ሬሳውም እንደ ገለባ ተከመረ። ስትገድሉ እግዚአብሔር ሊፈርድባችሁ ነው። ይኸው አሁን የእግዚአብሔር ሚዛን ሞላ። እንግዲህ ኢትዮጵያን ከቶ አትገዙም። እኔንም አሁን ልትገድሉኝ ነው› አላቸው።
ነገሩን ሳይጨርስ አምስት ቦምብ ተወረወረ። በአጠገቡ ያሉ ሁሉ ተቆላልፈው ሰማንያ ሰዎች ወደቁ። ሬሳውን ለመውሰድ ካሚዮንም አመጡ። ሬሳውን በአንድ ካሚዮን ከወሰዱ በኋላ ሌሎች ካሚዮኖችም ቁስለኞችን ለመውሰድ አመጡ። በብርቱም የቆሰሉትን እያነሱ ወስደው ከእስር ቤት በር በመትረየስ ተኰሱባዋቸው። በጥቂት የቆሰሉት ሰዎች ግን ቁስላቸውን እየሸሸጉ እንደ ደህና እየመሰሉ በእስረኛው መሐል ተሸሸጉ። ኢጣሊያኖችም እየበረበሩ ጥቂትም ቆስሎ ቢሆን ልትታከሙ ነው እያሉ እየመረጡ ከበር ገደሏቸው።
በሦስተኛው ቀን ጊዜውም ስድስት ሰዓት ሲሆን አስራ ሰባት ሰዎች በውሃ ጥማቱ ሞቱ። ከዚያ ረሐብና ውሃ ጥማት እንዲገድሉን መርጠን ነበር። ይህንንም ከልክለውን ሁለት ካሚዮን አምጥተው ከዚህ ወደሚሰፋ እስር ቦታ ሊወስዱን እየቆጠሩ ስሙን እየፃፉ 30ውን አሳፈሩት።
በመንገድም የካሚዮኑ መብራት በሚወድቅበት ስንመለከት መንገዱ ሁሉ በሬሳ ተሞልቶ ነበር። ዝም ብለው በላዩ ይነዱበት ነበር። ከመንገዱም ዳር የወደቁትን ድመቶች ጉንጫቸውን ነክሰው ጺማቸውን እያራገፉ ሲበሏቸው አየሁ። ካሚዮኑ ፊት በር በሚባለው ስፍራ በደረሰ ጊዜ ከካሚዮኑ እንድንወርድ አደረጉን። በኋላ በኩል ከነበሩት መጀመሪያ የወረዱትን ቦምብ ወርውረው ገደሏቸው። የቀረነው አንወርድም ብለን ራሳችንን በውስጥ በሸሸግን ጊዜ በኋላ በኩል ነጂው በሚቀመጥበት በኩል መትረየስ አምጥተው አስገብተው ተኩሰውብን ሞላዎችን ገደሏቸው። ይህም ቦታ ጠፍ ሁኖ የኖረ ነበረና ሳማና ልት የሚባለው ምንስ ወራቱ መጋቢት ቢሆን ቅጠሉ ለምልሞ ነበር። በታላቅ ረሃብና ውሃ ጥማት የተጨነቀው እስረኛ ያንን መራራ ቅጠል በላ። ከፊላችንም መራራ እንደሚጣፍጥ ይህን እያላመጥን እስከ አራት ሰዓት ቆየን።
አንዱ ሰው ጠርሙስ በእጁ ይዞ እየተጋፋ መጣ። ከአጠገባችን ቆሞ ሊናገረን ፈለገ። ገና ከንፈሩን ማላቀቅ ግን አልቻለም። በታላቅ ችግር በውሃ ጥማት የተያያዘውን ከንፈር አላቀቀው። ደካማ በሆነ ድምፅ “እባካችሁ! እባካችሁ!” ሲል ሰማነው። ነገሩን የሚለውን አጥርተን አልሰማነውም ነበርና ልንሰማው እንድንችል ወደ እኛ በጣም ቀረበ። እ…ባካችሁ ከእናንተ ጭብጦ የሌላችሁ ሽንቱን በዚህ ጠርሙስ ይስጠኝ ወንድሞቼ ሁለቱ በውሃ ጥማት ሞቱ፤ እኔም ልሞት ነኝ፤ እባክዎ ጭብጦ ባይኖርዎ ሽንትዎን እባክዎ ጌታ ይስጡኝ” ብሎ ልመናውን ወደ አቶ ገብረመድህን አወቀ አበረታው።
አቶ ገብረመድህን አወቀም “እኔም አንዳንተ ነኝ። ውሃ ከጠጣሁ ሦስተኛ ቀኔ ነው። ከዬት ሽንት አመጣለሁ?” እኛንም አልፎ እየዞረ ሲለምን አልቆየም። እስከ መጨረሻው ደክሞት ነበር። መናገርም አቃተው። አንድ ድንጋይም በአጠገባችን ተንተርሶ ጥቂት ጊዜ ተጋድሞ በሕይወቱ ቆየ። በመጨረሻም ግን እንደ እንቅልፍ በሞት ያችን ድንጋይ እንደተንተራሰ አሸለበ።
በዚህ ቀን በውሃ ጥም የሞቱትን ካሚዮኖች መጥተው ወሰዱዋቸው። በዚህ ጊዜ የእስር ቤቱ ሹም ቲሊንቲ ሎዊጂ ኮርቦ የሚባለው በዚያ እስር ውስጥ ገብቶ የተጠሙትን ነፍሳቸው አልላቀቅ ያላቸውን አይቷቸው ኑሯል። በኰዳው ውሀ ይዞ መጣ። ቲሊንቲም የኮዳውን ውሃ ለእስረኛው መሸጡን ሰማን። ገንዘብም ይዤ ሄድሁ። የሚሸጠው እሱ ብቻ ስለሆነ ካጠገቡ መድረስ አይቻልም። የተጠማው ብዙ ሕዝብ ውሃ ለማግኘት ዙሪያውን ከቦት ይጋፋ ነበር። ገዥውም ፋታ አያገኝም ነበር። በቀኝ እጁ ሽጉጡን አውጥቶ፤ በግራ እጁ በተጠማው ሰው በአፉ ውስጥ ትንሽ ጠብ ያደርግለታል። የኢጣሊያ አንድ ኰዳ ሁለት ጠርሙስ ተኩል ይይዛል። ቲሊንቲ አንዱን ኰዳ ውሃ ለሃያ አምስት ሰው አስጠጥቶ ሃያ አምስት ብር ለአንድ ኮዳ ተከፈለው።
የአቶ ስለሺ አሽከርም በጣም ተጠምቶ ነበር። አንድ ብር በቲሊንቲ ግራ እጅ አኖረ። እሱም ከኰዳው አጠጣው። ቲሊንቲም ውሃውን አቀረበና በአፉ አፈሰሰበት። ጠጪውም ስላልረካ ኮዳውን ቲሊንቲን ቀልጥፎ ሲያቃናው በሁለት እጁ ከአፉ አስጠግቶ ያዘው። ቲሊንቱም ሽጉጡን በዓይኑ መሐል ተኮሰበት። ሳይውጠው ገና በጉንጩ የነበረው ሲወድቅ በአፉ ፈሰሰ። ቲሊንቲም ደጋግሞ ተኩሶ ጨረሰው። እርሱ በተኰሰው ያንዱን ሰው ክንዱን አቁስሎት ስለነበር የቆሰለው ብር እንኳ ቢሰጠው እንዲሁ ያለ ዋጋ አጠጣው። ይህንም በውሃ ጥማት የሆነውን ታላቅ እልቂት እንዲቀር ውሃ በሸራ ቧንቧ ኢጣሊያኖች ከታሰርንበት ድረስ አስገብተው በ120 በርሜል ሞሉልን።
እኒያ ሁለት ሹማምንቶች ማርሻሎና ቲሊንቲ እስረኛውን እያካፈሉ ከዚያ ወዲህ ያለው ይጠጣ እያሉ ሲከላከሉ አንድ ጊዜ እስረኛው እንደ ናዳ ተንዶ ጥሷቸው ሄደና ውሃም የቻለውን ያህል ይጠጣ አለ። በርሜሉንም ገና ያላየው ነበር። እነርሱም በዚህ ግፊት እኒህ ውሃ ሲሸጡ የዋሉ ሹማምንቶች ተድጠው ሞተው ኑረዋል። የሹማምንቶቻቸውን ሞት ስላወቁ ሰው ላይ ቦምብ ይወረውሩበት ጀመር። በበርሜሎች ዙሪያ ሬሳው ተከመረ። ውሃ ለእስረኛ ሲሸጡ ውለው እግዜር ፈርዶባቸው የተዳጡትንም የሹማምንቶቻቸውን በቀል ተበቀሉን።
አንድ ሺ አምስት መቶ የሚያህል እስረኛ ሞተ። መብልና ውሃ የሰጡን ሹማምንቶች ወደ ቤታቸው በተመለሱ ጊዜ ቁጣቸውን አድሰው በዙሪያው በውድሞው ያሉ ፋሽስቶች በሰው ህይወት ሊጫወቱ ቦምብ ይወረውሩብን ጀመረ። በዙሪያው ከሚወረወር ቦምብ ለመሸሽ የማይደረስበት መሃከለኛውን ቦታ ለመያዝ እርስ በርሳችን ተጨናንቆ ተጋፍቶ ቆሞ ሳለ በዙሪያ ዳር የሚወረወሩት ቦምቦች ከመሀል ሊያደርሳቸው ስለማይችል ቦምብ ውርውራ ስለአቃታቸው መትረየሱን ለመሀል ጠምደው ተኮሱብን። ከጥይት ለመዳን የፈለገ ሲተኛ የቆመው ህዝብ ጨፈለቀው። የቆመውን መትረየስ ጠረገው። የቆሰለና ያልቆሰለ የሞተና ደህነኛ እስኪጠባ ድረስ ተቆላልፎ አደረ።
በዚያ ማታ በቦምብ የገደሏቸውን ሬሳውን ሳይወስዱ ስለቀሩ ወደ በሩ ሲል ወዳለው ማዕዘን አንድ ሴት እስከ ልጇ የታሰረች በቦምብ ተመታ ሞታ ኑሯል። ልጇ የእናቱንም ሬሳ በደረቷ ላይ ተሰቅሎ ገና በሕይወት እንዳለች ሁሉ ይጠባት ነበር። እስረኞችም ይህን ሕፃን አንስተው ትናንት በግፍ ልጇ ለተዳጠባት ሴት እባክሽ አጥቢው ብለው ሰጧት። ያችም ሴት ለልጇ ምትክ እንዳገኘች ደስ ብሏት አልተቀበለችም። እንዲያውም ወርውራ ጣለችው። ነገ ኢጣሊያኖች በቦምብ ለሚገድሉት ለማሳደግ አላጠባም። ለመትረየስና ለሳንጃም አላሳድግም ብላ ወረወረችው። በዚያ ብርቱ ፀሐይ ተንጋሎ ወድቆ ብርቱ ለቅሶ አለቀሰ። ›› ሲሉ የዛሬ 83 ዓመት ፋሺስት ኢጣሊያ የደረሰውን እልቂት በምናብ አስቃኝተውናል።
አዲስ ዘመን ረቡዕ የካቲት 11/2012
አያሌው ንጉሴ