የሀገሬን ወቅታዊ የፖለቲካ ቡረቃና ትርምስ በሰከነ መንፈስ ስገመግም የልጅነታችንን ጊዜ ፍንትው አድርጎ ያስታውሰኛል። የልጅነት ዕድሜ መገለጫው ብዙ ነው። በአብዛኛው አብሮ አደግ ሆኑም አልሆኑ የቅጽል ስም እያወጡ መበሻሸቅ፣ መናቆር፣ ወዲያው ተጣልቶ ወዲያው መታረቅ፣ በትንሽ በትልቁ መተማማትና ቡድን እየፈጠሩ አንዱን ማቀፍ አንዱን መንቀፍ፣ ስለ ራስ ቤተሰብ ዝናና ክብር እየተረኩ አብሮ አደግን ማስቀናት፣ ተሻምቶ መብላትና ስለ ነገ ያለማሰብ ወዘተ… ቀለሙ ዥንጉርጉር ነው። እርግጥ ነው በእነዚህን መሰል መገለጫዎች ውስጥ ተሰባስቦ ማውካካት፣ በተረብ መጠዛጠዝና ራስን ከፍ አድርጎ ለማሳየት መሞከሩም የተለመደ የልጅነት ወግ ነው።
የልጅነት ተፈጥሯዊ ባህርያት እንደተጠበቁ ሆነው ሀገራዊ አባባሎቻችን፣ ተረቶቻችን በአጠቃላይ ሥነ ቃሎቻችን በአብዛኛው ሲያስተምሩን የኖሩት ከልጅነት ዕድሜ ጋር የተያያዙ አሉታዊ ምስሎችን እንጂ ውበቱን አጉልተው እንደማይገልጡልን ከአንባቢያን ይሰወራል ብዬ አልገምትም። ጥቂቶቹን ብቻ ላስታውስ፤
- ልጅ ለሳቀለት፤ ውሻ ለሮጠለት
- ልጅ ቢያስብ ምሳውን፤ አዝማሪ ቢያስብ ጠላውን
- ልጅ ከዋለበት ሽማግሌ አይውልም
- ልጅ ያለ ልጅ አከለ
- ልጅ ያቦካው ለራት አይበቃ።
እነዚህ አባባሎች ልጅነትን አጥብቀው ቢያንኳስሱም በአንጻሩ ግን “ያ ልጅነት በጊዜያቱ ደስ ማለቱ” እየተባለም ተዘፍኖለታል። “ልጅነት ተመልሶ አይመጣም” እየተባለም በጉልምስናና በእርጅና ዘመን በቁጭትና በፀፀት ይታወሳል። የልጅነት ጅልነት ፈለጉ ውስብስብ፣ ትዝታውም የትዬለሌ ነው። እንዲህም ሲባል ግን የልጅነት መገለጫው ምሉዕ በኩለሄ በሆነ ድንጋጌ ንፍገትና በትንሽ በትልቁ መጋጨት፣ ጅልነትና ከጥበብ መጉደል ብቻም እንዳልሆነ አስረግጠን ባንናገር ያለፍንበት ዕድሜና ተረኛው ባለ ዕድሜ ትውልድ መታዘቡ አይቀርም።
ብዙውን ጊዜ የሃይማኖቱ መምህራን በትም ህርታቸው ውስጥ ትኩረት የማይሰጡት ኤሊሁ የሚባል አንድ ታዳጊ ወጣት በቅዱስ መጽሐፍ ውስጥ ተጠቅሶ እናነባለን። ይህ ልጅ መከራ ያጎሳቆለውን ኢዮብን ለማጽናናት ከሩቅ ሀገር ተጉዘው ከሄዱ ሦስት አረጋውያን አባቶች ጋር አብሮ የተጎዳኘ ነበር (መጽሐፈ ኢዮብ ምዕራፍ 32)። ዕድሜው ከአባቶቹ ጋር የማይገጥመው ትንሹ ብላቴና ራሱን ከሸበቶ ታላላቆቹ ጋር በማስተያየት በምክር መሳታቸውን ሲያስተውል የገሰጻቸው እንዲህ በማለት ነበር።
እኔ በዕድሜ ታናሽ ነኝ፣ እናንተ ግን ሽማግሌዎች ናችሁ፤
ስለዚህም ሰጋሁ፤ እውቀቴን እገልጥላችሁ ዘንድ ፈራሁ።
በእድሜ ያረጁ ጠቢባን አይደሉም፤
ሽማግሌዎችም ፍርድን አያስተውሉም።
ስለዚህ ስሙኝ። እኔ ደግሞ ዕውቀቱን እገልጣለሁ።
እኔም እንደተጎለጎለ ልቃቂት ውሉን መጨበጥ የተሳነንን የሀገራችንን ፖለቲካ የምገመግመው በጨዋታው ምህዳር ውስጥ ማልያ ለብሼ፣ የመለያ ቁጥር ተሰጥቶኝና ኳሷን ከሚጠልዙት ጋር “አብዶ ለመሥራት” የተሰለፍኩ ተፋላሚ ስለሆንኩ አይደለም። በፍጹም።
በብዙ እውቀት ከእኔ የተሻሉና ከወተት ጥርሳቸው ጀምሮ ክራንቻቸው እስከተሳለበት ዕድሜ ድረስ ፖለቲካ ሲያኝኩ የኖሩ ብዙዎች እንዳሉ ይገባኛል። በእንክርዳድ ተጠምቆ የተሰጣቸውን የርዕዮተ ዓለም የጉሽ ጠላ ገፈቱን ሳያጠሉ እየተጎነጩና እያስጎነጩ ዕድሜያቸውን በሙሉ የፖለቲካ ዋንጫ ጨብጠው “ቺርስ!” በመባባል ራሳቸውንም ሆነ ዘመናቸውን ያሸበቱ ብዙ አረጋዊያን የፖለቲካ “ልሂቃን!” መትረፍረፋቸውም አልጠፋኝም።
የእድሜያቸውንና የዕውቀታቸውን ብስለት ያህል አስተውለው ከመፍረድ ይልቅ፤ ተደናብረው ሲያደናብሩን ሳስተውል ግን አገላለጹን ከታናሹ ኤሊሁ ተውሼ፤ “እውነትም በዕድሜ ያረጁ ሁሉ ለካንስ ጠቢባን አይደሉም፤ የሺህ ውበት (ሽበት) ባለጠጋ መሆን ብቻ ለፍርድና ለፍትሕ ለመወገን አቅም አይሆንም” ብዬ በድፍረት ብናገር እንደ አላዋቂ ሊያስቆጥረኝ አይገባም።
«በፖለቲካው ሠፈር ልጅነት ተመልሶ መጥቷል!»
በዕድሜ የምናከብራቸው፣ በዕውቀታቸው የማናማቸው፣ በፈተና አይበገሬነታቸው የማንጠረጥ ራቸው ጎምቱ ፖለቲከኞቻችን ወደ ልጅነት አስተሳሰብ ዝቅ ብለው ስናስተውል ለእነርሱ እያፈርን፤ ለራሳችን የወደፊት ሕይወት ብንሰጋ አይፈረድብንም። ከምክንያታዊ ፖለቲከኛነት ይልቅ በስሜት ወጀብ እየተላጉ ሕዝቡንም በግራ መጋባት ዐውሎ ነፋስ ውስጥ ሲጥሉት ስናስተውል ሰብዓዊ ክብራቸውን ሳንዳፈር አስተሳሰባቸውን ግን እንድንንቅ እንገደዳለን። ‹‹በሃሳብ ልዕልና የመቶ አሥር ሚሊዮን ሕዝብን ውክልና እንይዛለን›› በማለት እየፎከሩ በአንጻሩ ግን በብሽሽቅ አፍቃሬነት ተዘፍቀው “በእንካ ሰላንትያ!” ፍሬ አልባ ክርክር ሲቋሰሉ እያስተዋልን ከመገረም አልፈን ቆሽታችን ይደብናል።
በዕድሜ እንደበሰለ አስተዋይ መሪ በጥንቃቄ ከመራመድ ይልቅ በአቋማቸው ሲወለካከፉ ስናስተ ውል ‹‹አረጁ ወይንስ ጃጁ?›› እያልንም እናማቸዋለን። በአስተሳሰባቸውም ሽቅብ ከማደግ ይልቅ እንደ ካሮት ቁልቁል ሲሰምጡ እያስተዋልን ግራ እንጋባለን። ሽበታቸውን ብናከብርም ወደ ሕጻንነት ደረጃ መዝቀጣቸው እያሳሰበን ከልጅነታችን ዕድሜ አንዳንድ ትዝታዎች ጋር እናቆራኛቸዋለን። ምን ማለት አንደፈለግሁ ከራሴ ከጸሐፊው የልጅነት ትዝታዎች መካከል አንድ ሁለቱን በማስታወስ ሃሳቤን እያዋዛሁ ላጠናክር።
ትዝታ አንድ፤
ከልጅነት ባህላዊ ጨዋታዎች መካከል ቡሄ መጨፈር በቀዳሚነት ይጠቀሳል። እርግጥ ስያሜውና የጨዋታው ዓይነት ከባህል ባህል ሊለያይ እንደሚችል አይጠፋኝም። ያደግሁት ቡሄ ሳልጨፍር ነው ለሚለው ተከራካሪም መብቱን መጠበቅ ግድ ይሏል። ለምን ሳይጨፍር አደገ ብሎ መሟገት ጉንጭ አልፋነት ነው። ይህ ጸሐፊ ከልጅነት ዘመኑ በአንደኛው ዓመት ከብጤዎቹ ውሪዎች ጋር ተቧድኖ ቡሄ ለመጨፈር መሰባሰቡ ትዝ ይለዋል። ትዝታው ብዙ አስፈጋጊ ገጠመኞች ስላሉት ግለ ታሪክ መጽሐፉ በቅርቡ ለንባብ ሲበቃ ሁሉም ይዘከዘካል።
የቡሄ ጨፋሪ ውሪዎች ቡድን ተመሠረተ። አለቃና ዳቦ ያዥ ተመርጦም “የቡሄ በሉ!” ስምሪቱ ተጀመረ። የሁሉም ጨፋሪዎች ጉጉትና ናፍቆት በጭፈራ የምንሸለመው ሙልሙል ዳቦ ከመቼው ተሰባስቦ በበላን የሚል ነበር። ሙልሙል መያዣውን የታናሽ እህቴን አዲስ የአንገት ልብስ የአደራ ቃል አክብዳ ያዋሰችን እናቴ ነበረች።
ጥቂት ቤቶች አንደጨፈርን በልጅነት ችኮላ የሰበሰብነውን ሙልሙል ለመቃመስ ወደ አንድ ቦታ ሰብሰብ ብለን ዳቦ ያዢያችን ሙልሙሎቻችንን እንዲያስረክበን ጠየቅነው። ብልጥም ጅልም የነበረው ያ ዳቦ ያዥ ጓደኛችን ፊቱን ጭጎጊት አስመስሎ እየተነፋረቀ ዳቦው እንደሌለ ገለጸልን። የት አደረግኸው ብለን ስናፋጥጠው ወድቆብኝ ይሆናል ወደ ኋላ ተመልሰን እንፈልግ ብሎ እቅጩን ነገርን። ልጅነት ጅልነትም አይደል፤ እውነት መስሎን ወደ ኋላ ተመልሰን የተንጠባጠበውን ዳቦ ፍለጋ ተያያዝን።
እውነትም አንዳንድ ቁርስራሽ ዳቦዎች በየመንገዱ ተንጠባጥበው ኖሯል። ለካንስ አጅሬ እኛ ሆ! እያልን “ኧረ በቃ በቃ ጉሮሯችን ነቃ” እያልን ስንጨፍር እርሱ ዳቧችንን ተከልሎ ይገምጥ ኖሯል። ለማሳመኛ እንዲሆነውም ጥቂት ቁርስራሽ በየመንገዱ አንጠባጥቧል። በዳቦው ሌብነት ብቻ ቢያቆም ምን ችግር ነበረበት በአደራ የተሰጠንን የዳቦ መያዢያ አዲስ የአንገት ልብስ መሃሉን ቦትርፎ ቀዶት ኖሯል። ዳቦው ሾልኮ ጠፋብኝ የሚለውን ሰበብ ለማጠናከር።
የወቅቱ የሀገሬ የፖለቲካ ጨዋታ ልክ ከልጅነቴ የቡሄ ጭፈራ ታሪክ ጋር ይመሳሰልብኛል። አንዳንድ “የሥልጣን ዳቦ ህልመኛ” የፖለቲካ መሪዎች ተከታዮ ቻቸውን “ዲሞክራሲ! ፍትሕ! ነፃነት! እኩልነት!” እያሉ እንዲጨፍሩ እያሟሟቁ እነርሱ ግን እጃቸው የገባውን የጥቅምና የሥልጣን ሙልሙል በግላጭና በስውር ሲገምጡ ማስተዋል የተለመደ ነው። ያውም እንደ ጀግና እየተኩራሩ። በዙሪያቸው የተሰበሰበው ሠራዊት በሃሳብ ልዕልና እንዲሟገት አርአያ ከመሆን ይልቅ ለጠብ እንዲበረታታ ያጀግኑታል።
በትግሉ የተገኘውን ድል ቀድመው እየገመጡና የራሳቸውን ነፍስ በክላሽ እያስጠበቁ ሌሎችን ለሞት ያደፋፍራሉ። የችግር ደመና ሲያንዣብብ ወደ ሞቀበት ጎራ ብለው ክፉ ቀንን ካሳለፉ በኋላ ነገሩ ሲረጋጋ ቀድመው የፊት ለፊት ሰልፉን ካልመራን እያሉ “ራሳቸውን በሙሴ በትር ይመስላሉ”። የሙሴ በትር የቀይ ባህርን ለሁለት የከፈለ ተዓምራዊ በትር መሆኑ በተለምዶም ይታወቃል።
ትዝታ ሁለት፤
በ1960ዎቹ አጋማሽ በአዲስ አበባ ከተማ ሠፈሮች ውስጥ አንድ ክፉ እንቅስቃሴ ተስፋፍቶ ነበር። ዛሬም ድረስ ሰበቡ ሊገባኝ ባልቻለ ሁኔታ እንቅስቃሴው የተጀመረው የአንዱ ሠፈር ጎረምሶች የሌላኛውን ሠፈር የዕድሜ አቻዎቻቸውን በመስደብና በመበሻሸቅ ጠላትነት መፍጠር ነበር። መነሻውን እንደማስታውሰው ላየንስ ክለብ በሚባል ተቋም አማካይነት በአዲስ አበባ ዋና ዋና አደባባዮች ላይ “ሙዚቃ ለኑሮ ትምህርት ለአእምሮ!” በሚል መሪ ቃል ዝናን የተጎናጸፉ የወቅቱ የሙዚቃ ባንዶች ሕዝቡን እያዝናኑ እጅግ ጠቃሚ የሆኑ መልዕክቶች በየመሃሉ ለወጣቱ ይተላለፉ ነበር። የፖሊስ፣ የክብር ዘበኛና የጦር ሠራዊት የሙዚቃ ባንዶች ዋናዎቹ ታዳሚዎች ነበሩ። ከአብዛኛዎቹ ዝነኛ ድምጻዊያን ጋር በአካል የተዋወቅነው በዚሁ አጋጣሚ ነበር።
ትርዒቱ ሲጠናቀቅ ከሌላ ሠፈር የመጡ ጎረምሶች የትርዒቱን አስተናጋጅ ሠፈር ወጣቶች በነገር እየጎነታተሉ ግጭት በመቆስቆስ ጠብ ያለሽ በዳቦ ማለትን ያዘወትራሉ። እያደርም ብሽሽቁና ስድድቡ ከፍ ወዳለ ደረጃ ተሸጋግሮ ድንጋይ መወራወርና መፈነካከት ይጀመራል። ውሎ ሲያድርም “የቻይና ግሩፕ፣ የአሜሪካ ግሩፕ፣ የቅምብቢት ሠፈር ግሩፕ፣ የኮልፌ ልጆች ግሩፕ ወዘተ.” እየተባለ በጠራራ ፀሐይና በምሽት በሰንሰለት መጋረፍ፣ በብረት ቦክስ መፋለም፣ በሴንጢ (ሲኪኒ ሌላው ስሙ ነበር) መዘነጣጠል የተለመደ ክስተት ሆኖ አረፈው።
የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ በዚሁ ክፉ ወቅት ቤተሰብ የላከውን መልእክት አድርሶ በምሽት ወደ ቤቱ ሲገሰግስ ለጥፋት ባደፈጠ አንደኛው ቡድን ቀለበት ውስጥ በመውደቁ የደረሰበትን ኢሰብዓዊ ድርጊት ዛሬም ድረስ አልረሳውም። ለንባብ እያዘጋጀ ባለው ግለ ታሪኩ ውስጥ የትራጄዲው ትዕይንት በሚገባ ይገለጻል።
አብዛኞቹ የዛሬው ፖለቲከኞች ከዚያን ጊዜው የልጅነት ገጠመኝ ጋር ይመሳሰሉብኛል። ሀገራዊው ለውጥ ብልጭ ካለበት ጊዜ ጀምሮ ዋና መለያቸው ብሽሽቅና መናናቅ ሆኖ አንዱ ሌላኛውን ያዋርድ የነበረው በግላጭ ነበረ። እያደርም ብሽሽቁና ስድድቡ ወደ ፍልሚያ ጎራ ተለውጦ የንፁሃን ሕይወት ሲጠፋና ከፍተኛ የአካል፣ የሥነ ልቦናና የንብረት ጉዳት ሲደርስ አስተውለን አንብተናል። በሰላም እንዲታገሉ ጥሪ የቀረበላቸው የደም ጥማተኞችም የቀለህ ድምጽ ካልሰማን ያጥወለውለናል በማለት ጫካ ገብተው ንጹሃንን ጭዳ ሲያደርጉ እያየንና እየሰማን ነው። “ለምን ምክንያትና ሰበብ ነበር?” ብለን ብንጠይቅ ማንም ምክንያቱ ይህ ነበር ወይም ነው ብሎ የሚመልስልን አላገኘንም። ፍልሚያው የጨዋ ፖለቲካ ባህርይ ሳይሆን “የቻይናና የአሜሪካ ግሩፖች” መሰል ጋጠወጥነትን ያስተዋልኩበት ነው ብዬ በድፍረት የማመሳስለውም ስለዚሁ ነው።
ሽበትና ዕውቀት አደብ ያላስገዛው ባህርይ እነሆ ዛሬም ድረስ ፖለቲካችን ከጦርነት ባልተናነሰ ሁኔታ ወደ ዐውደ ግንባርነት መለወጥ ግድ ሆኗል። በጸሐፊው የግል እምነት ዛሬ እያስተዋልን ያለነው በስመ ፖለቲካ መረን የለቀቀው ክስተት ነገና ተነገወዲያ በታሪክና በትውልድ ፊት መሳቂያ መሳለቂያ አድርጎ እንደሚያስወቅሰን ቅንጣት ያህል አልጠራጠርም።
ችግሩ የፖለቲካ ካባ በለበሱ፣ አንደበታቸውንም በርዕዮተ ዓለም ፍልስፍና ባሰለጠኑት ዘንድ ብቻ ቢሆን ኖሮ “በሕግ አምላክ!” እያልን ጩኸታችንን አስተባብረን በምርጫ ካርድ ወይንም ህጸጻቸውን አጉልተን እያሳየን በሰላማዊ ፍልሚያ ገትረን በመያዝ ከሚመኙት የሥልጣን ቅዠት ልንገታቸው በቻልን ነበር። ችግሩን ያወሳሰበው “የእምነት ቤተሰቦችና አስተማሪዎች ነን!” በሚሉት ዘንድ እየተራገበ ያለው ወላፈን ጭምር ነው።
ጎበዝ ቆም ብለን ላለማስተዋል አዚህም ያደረገብን ምንና ማን ይሆን? ይህ ሀገራዊ የልጅነት ፖለቲካ መልክ እንዲይዝ ብዙዎች ቀልባቸውን አደብ እስካላስገዙ ድረስ ውጤቱ ለእነርሱም ሆነ ለጀሌዎቻቸው የሚበጅ አይሆንም። ምንም ተባለ ምን ሀገርና ትውልድ መቀጠ ላቸው አይቀርም። አንዳንድ ሟርተኞች እንደሚቃዡት ሳይሆን ሀገር ስትበለጽግ እንጂ ስትፈርስ በህልማችን አናይም። እያባሉንና እያናከሱን ላሉት ክፉዎች ይብላኝላቸው እንጂ ሕዝብ ቆም ብሎ ማሰብና መወሰን ሲጀምር ፍጻሜያቸው እንደ ጉም እንደሚበተን ጥርጥር አይገባንም። በአስተሳሰባቸው “የአባቶቻቸው ልጆች የአያቶቻቸው ቅደመ አያቶች” የሆኑ ዕድሜ እንጂ ብስለት ያላደላቸው ፖለቲከኞችም “የከሰረ ዐረብ የዱሮ መዝገቡን ያገላብጣል፤ ለምን ቢሉ ዱቤ የሰጣቸውን ደንበኞቹን ሊፈልግ” እንዲሉ ኪሳራ በኪሳራ ተከናንበው ሲተክዙ በቅርቡ እናስተውላለን። ሕዝብም በአሸናፊነት ይወጣል። እንድትፈርስ የሚመኙላት ሀገርም በአዲስ የድል ዝማሬ ትገለጣለች። ሰላም ይሁን!!
አዲስ ዘመን ረቡዕ የካቲት 11/2012
በጌታቸው በለጠ/ዳግላስ ጴጥሮስ