የሠላም ሚኒስቴር የጦር መሳሪያ ዝውውርና አያያዝ ላይ የሚመክር ስብሰባ ሰሞኑን በአዲስ አበባ አካሂዷል። ስብሰባው የጦር መሳሪያ ለዜጎች ደህንነት ከፍተኛ ስጋት እያሳደረ ከመምጣቱ ጋር ተያይዞ በአያያዝና ዝውውሩ የጥብቅ ቁጥጥር አስፈላጊነት ላይ ትኩረት ሰጥቶ መክሯል።
የሠላም ሚኒስቴር ዴኤታው አቶ አለማየሁ እጅጉ አዋጁ የህግ የበላይነት የማረጋገጥ ከፍ ሲልም የህዝብ ደህንነትን የመጠበቅ ዓላማ ያለው ስለመሆኑ ጠቁመዋል።
የጦር መሳሪያ ዝውውርና አያያዝን ከወዲሁ መቆጣጠር ካልተቻለ ሠላምና መረጋጋትን ለማደፍረስ የላቀ አስተዋጽኦ አለው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው ህብረተሰቡ በዝውውሩና አጠቃቀሙ ላይ ግልፅ ግንዛቤ ሊኖረው ይገባልም ብለዋል።
በሠላም ሚኒስቴር የተዘጋጀው የምክክር መድረክም ይህንን ግንዛቤ ለማሻሻል ያለመ መሆኑ ተነግሯል። በመድረኩም በጦር መሳሪያ አያያዝና ዝውውር ዙሪያ የመነሻ ጥናታዊ ፅሁፎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።
ሕገ-ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር እንደሥጋት፣
ከአንድ ዓመት በፊት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ የምክር ቤት አባላቱ ላቀረቡላቸው ጥያቄዎች በሰጡት መልስ ላይ እንደተናገሩት የህገወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር ከመበራከቱ የተነሳ ኢትዮጵያ ካላት የህዝብ ቁጥር የሚበልጥ የጦር መሳሪያ ያላት ሃገር ሆናለች” ብለው ነበር።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደተናገሩት “አርሶአደሩ የጦር መሳሪያ ካልያዝኩ ራሴን መከላከል አልችልም ብሎ ስለሚያምን፤ መሬት ሸጦ መሳሪያ ይገዛል።”
በተለይ አሁን ላይ የጦር መሳሪያን ሸጦ ገንዘብ ማትረፍን እንደስራ የወሰደው ሃይል አለ፤ ለዚህም ሲባል መሬት ተሸጦና ከባንክ ብድር ተወስዶ የሚሰራ ንግድ እንደሆነ ለፓርላማ አባላት ተናግረዋል።
“በኮንትሮባንድ የሚካሄድ የመሳሪያ ዝውውር ህጋዊ እስኪመስል ድረስ እየተሰራ ነው” ያሉት ዶ/ር አብይ፤ “ይሄን ካሁኑ ካላስቆምነው ኢኮኖሚያችንም ሆነ ሰላማችንን ያደፈርሳል” ሲሉ ለጉዳዩ አጽንኦት ሰጥተውታል።
መሳሪያና የተለያዩ ሸቀጦች ወደሃገር ውስጥ በኮንትሮባንድ ገብተው፤ የቀንድ ከብት እንደሚወጣም ተናግረዋል።
“የህገወጥም ሆነ ህጋዊ መሳሪያ ዝውውር አደገኛ ነው። ስለመሳሪያ ጉዳት ከአሜሪካ መማር አለብን፤ በዚያ ጥቂት የታጠቁ ግለሰቦች ተማሪዎችን ሲገድሉ አይተናል” ብለዋል።
ህገወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውርን ለመግታትም “የጉምሩክ ቁጥጥርና ስርዓትን ማጠናከርና፤ ከጎረቤት ሃገራት ጋርም በትብብር መሰራት አለበት” ማለታቸው ይታወሳል።
በሌላ በኩል ህገ ወጥ የጦር መሳሪያ በሚያዘዋውሩ አካላት ላይ 19 የክስ መዝገቦች ተከፍተው በመሰራት ላይ መሆኑን የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ህግ ይገልፃል። የህግ ምሁራን ደግሞ የተያዙ ተጠርጣሪዎች አፋጣኝ እርምጃ ተወስዶባቸው ለሌሎች መቀጣጫ ሲሆኑ አለመታየታቸውን ይጠቅሳሉ።
የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ህግ የህዝብ ግንኙነትና የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ዝናቡ ቱኑ እንዳሉት፤ባለፈው ዓመት በህግ ያልተፈቀደውን ንብረት ወደ አገር የማስገባት ሂደት በኮንትሮባንድ ወንጀልም የሚያስጠይቅ ስለሆነ በዚህ በኮንትሮባንድ ወይም በጉምሩክ ህጉ በአዋጅ 859/2000 አንቀፅ 168 መሰረት 19 መዝገቦች ላይ ክሰ መመስረት ተችሏል። ክስ መመስረት ብቻ ሳይሆን መሳሪያዎቹም ገቢ እንዲሆኑ ተደርጓል።
ባለፈው ዓመት፤ በአምስት ወራት ውስጥ ወደ 60ሺ 94 የተለያዩ ሽጉጦች፣ወደ 136ሺ 95 የተለያዩ የሽጉጥ ጥይቶች፣ እንዲሁም ወደ 9 ከባድ መትረየስ፣ 5 ክላሾች፣ 2 ዝናር የጦር መሳሪያ እንዲሁም የተለያዩ የጦር መሳያዎች በዓቃቤ ህግ መዝገብ ክስ የተከፈተባቸው ናቸው። በምርመራ ላይ ያሉ እንዲሁም በቅርቡም የተያዙ አሉ። የክስ መዝገብ ከመክፈት ባሻገር የጦር መሳያዎችን ሲያዘዋውሩ የነበሩት ተሽከርካሪዎች ጭምር ውሳኔ አግኝተው ውርስ እንዲሆኑ መደረጉንም አቶ ዝናቡ ያስረዳሉ።
እንደ አቶ ዝናቡ ገለጻ፣ የክስ መዝገብ ከተከፈተባቸው 19 ተከሳሾች መካከል አራቱ የዋስትና መብታቸው ተከብሮላቸው ጉዳዩን በውጭ ሆነው እንዲከታተሉ ተደርጓል። ቀሪዎቹ ደግሞ የዋስትና መብታቸው ተከልክሎ በማረሚያ ቤት ቆይተው ጉዳያቸውን በመከታተል ላይ ናቸው።
የጦር መሳሪያ አስተዳደርና ቁጥጥር አዋጅ
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጦር መሳሪያ አስተዳደርና ቁጥጥር አዋጅን ታህሳስ 30 ቀን 2012 ማጽደቁ የሚታወስ ነው።
ምክር ቤቱ በመደበኛ ስብሰባው ከውጪ ጉዳይና ሠላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ እንዲሁም በተባባሪነት ከህግ ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መርምሮ ያቀረበለትን የጦር መሳሪያ አስተዳደርና ቁጥጥር ረቂቅ አዋጅን በተመለከተ ያቀረቡትን ሪፖርትና የውሳኔ ሃሳብ ተመልክቷል።
በዚህም የጦር መሳሪያ አስተዳደርና ቁጥጥር ረቂቅ አዋጅ የጦር መሳሪያ ቁጥጥር የሀገርንና የህዝብን ሰላምና ፀጥታ ለማስጠበቅ እንዲሁም የዜጎችን እና የህዝቦችን መብትና ደህንነት ለማስከበር አስፈላጊ መሆኑን በመገንዘብ መዘጋጀቱ ተነግሯል።
እንዲሁም ግለሰቦች የታጠቋቸውን የጦር መሳሪያዎች የህብረተሰቡን ሰላምና ፀጥታ ለማስጠበቅ ተግባር ሊውሉ የሚችሉበትን እድል መፍጠር አስፈላጊ በመሆኑ ነው የተዘጋጀው ተብሏል።
በስራ ላይ ባሉ ህጎችና አሰራሮች ያልተፈተሹ ጉዳዮችን በዝርዝር ህግ መደንገግ እና ወጥነት ያለው ስርዓት መፍጠር በማስፈለጉና ሀገሪቱ ያፀደቀቻቸውን ህገ ወጥ የጦር መሳሪያ ቁጥጥርን የሚመለከቱ ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን ለማስፈፀምና ዓለም አቀፍ ትብብር ለማድረግ የሚያስችል ስነ ስርዓት መዘርጋት አስፈላጊ በመሆኑ መዘጋጀቱን ታውቋል።
በረቂቅ አዋጁ የተቀመጠው ድንጋጌ ማንኛውም አይነት የጦር መሳሪያ ፣ብዛት ያላቸው ጉዳት አድራሽ ስለቶችና ተያያዥነት ያላቸውን የመሳሪያው መገልገያዎችን ይመለከታል።
በዚህም ከፍቃድ ውጪ የጦር መሳሪያ፣ የጉዳት ማድረሻ እቃ፣ የጦር ሜዳ መነጽር፣ በጦር መሳሪያ ላይ ሊገጠም የሚችል ማንኛውም አይነት መነጽር ወደ ሀገር ማስገባት፣ ከሀገር ማውጣት፣መያዝ፣ ማስቀመጥ፣ ማከማቸት፣ መገልገል፣ ማሳየት፣ መደለል፣ መሸጥ፣መግዛት፣ ማስተላለፍ፣ማዘዋወር፣ ማጓጓዝ፣ ማምረት፣ ማሰልጠንና ማስወገድ ክልክል ይሆናል።
በዚህ ረቂቅ አዋጅ እንደ ሳንጃ፣ ገጀራ፣ ሴንጢ፣ አስለቃሽ ጭስና ኬሚካሎች ለህብረተሰቡ አደገኛ በሆነ ሁኔታ መገልገልና በብዛት ይዞ መገኘት ነው ክልከላ የተቀመጠበት።
ፍቃድ በሚሰጣቸው የጦር መሳሪያዎች መለያ ምልክት ያለው ወይም ሊኖረው ይገባል የሚለውም በረቂቅ አዋጁ የተደነገገ ሲሆን፤ ይህም የመሳሪያ አምራች ከሌለው ደግሞ በተቆጣጣሪ ተቋሙ መለያ እንዲኖረው ይደረጋል።
የጦር መሳሪያ ፍቃድ ያላቸው አካላት ሰላማዊ ሰልፍ ወይም አድማ በሚደረግባቸው አካባቢ፣ በምርጫ ቦርድ በተከለከሉ ስፍራዎች፣ በህዝብ መዝናኛና በስፖርት ማዝወተሪያ፣ በትምህርትና ሀይማኖት ተቋማት እና መሰል የህዝብ አገልግሎት መስጫ ስፍራዎች ይዞ መገኘትን ይከለክላል።
ፍቃድ ማግኘት ክልከላ የተደረገባቸው ተቋማትም የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሀይማኖትና የእምነት ተቋማት፣የበጎ አድራጎት ድርጅትና ማህበራት እንዲሁም የትምህርት ተቋማት ናቸው። የጦር መሳሪያ ፍቃዱ በአዋጁ የተቀመጠ ሲሆን፤ የጥይት ብዛት በመመሪያ የሚቀመጥ ይሆናል የሚለውም በአዋጁ ተደንግጓል።
ቀደም ብለው የታጠቁት የህብረተሰብ ክፍሎች የታጠቁት የጦር መሳሪያ ያልተከለከለ እስከሆነ ድረስ በአንድ ዓመት የሽግግር ጊዜ ተቆጣጣሪው ተቋም በአካባቢያቸው ተገኝቶ በሚያወጣው የጊዜ ሰሌዳ ቀርበው ህጋዊ ማድረግ ይኖርባቸዋል።
ሆኖም በጊዜ ገደቡ ውስጥ ፍቃድ ያልወጣበት የጦር መሳሪያ በተቆጣጣሪው የሚወረስ ሲሆን፤ የጦር መሳሪያ ፍቃዱ ለግለሰብ በሁለት ዓመት ለድርጅት ደግሞ በ5 ዓመት መታደስ አለበት ይላል።
ተቆጣጣሪው ተቋም የፌደራል ፖሊስም ብሄራዊ የጦር መሳሪያ ቁጥጥር ስራ ክፍል አደራጅቶ በቴክኖሎጂ በታገዘ ምዝገባው መከናወን እንዳለበት በዚሁ አዋጅ ላይ ተቀምጧል፤ የጦር መሳሪያ ፍቃዱ አነስተኛ ወይም ቀላል መሳሪያን ለአንድ ሰው አንድ ብቻ የሚፈቅድ ነው።
ፍቃድ ለማግኘት ከሚያስፈልጉ መስፈርቶች ኢትዮጵያዊ ዜግነት ያለው ወይም በኢትዮጵያ የመኖር ፍቃድ ያገኘ፣ የአደንዛዥ እጽ ወይም የመጠጥ ሱስ የሌለበትና የአእምሮው ሁኔታ የተስተካከለ እንዲሁም ከአካባቢው የመልካም ስነ ምግባር መገለጫ ማረጋገጫ ማቅረብና መሰል መስፈርቶች ያስቀመጠ ነው።
ሕጉ በተቻለ መጠን በሕዝቡ ዘንድ የጦር መሣሪያ መያዝ ጥቅም እንደሌለው እምነት በመፍጠር ሰላምን መንግሥት ያስጠብቃል ወደሚል አስተሳሰብ እንዲገባ የማድረግ ፣ በሀገሪቱ ውስጥ የሕግ የበላይነትን በማረጋገጥ ሰላሙና ደህንነቱ የተረጋገጠ ማኅበረሰብ ለመፍጠር ያለመ ነው ተብሏል። በሕጉ ጉዳት አድራሽ ናቸው ተብለው የተለዩ ገጀራ፣ ሜንጫ፣ ጦር እና ቀስት ድምፅ አልባ መሣሪያዎች ሆነው እንዲካተቱ ተደርጓል። በዚሁ አዋጅ መሠረት የጦር መሣሪያ መሸጥ፣ መለወጥ፣ መደለል ከአዋጁ አላማ ጋር የማይሄዱ ናቸው። የጦር መሣሪያዎችን ከውጪ የማስገባት ፣ ከሀገር የማስወጣት፣ የመያዝ፣የማከማቸት፣ የማዘዋወር፣ ሥልጣንም የመንግ ሥት ተቋም ብቻ መሆኑን አዋጁ ደንግጓል።
አዋጁ የወንጀል ተጠያቂነትም ያስቀመጠ ሲሆን፣ ማንኛውም ሰው በአዋጁ የተመለከተውን ክልከላና ግዴታ በመተላለፍ የጸና ፍቃድ ሳይኖረው የጦር መሳሪያዎችን ያስቀመጠ፣ የያዘ፣ ያመረተ፣ ከሀገር ያወጣና ያስገባ መሰል ክልከላዎችን ሲተላለፍ እስከ 3 ዓመትና ጽኑ እስራትና እስከ 10 ሺህ ብር ይቀጣል።
በዚሁ አንቀጽ ላይ የተባሉትን በብዛት የጦር መሳሪያዎችን ይዞ የፈጸመ ሲሆን ደግሞ እስከ 15 ዓመት ጽኑ እስራትና እስከ 100 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ ይጣልበታል። የወንጀል ተጠያቂነቱ በየደረጃው በዝርዝር ተቀምጧል።
በአዋጁ ለፀጥታ አስከባሪ አካላት የሚፈቀድ የጦር መሳሪያ አይነትና ብዛት እንዲሁም በክልሎች የሚገኙ የህግ አስከባሪ አካላት ተልዕኮና ሌሎች ጉዳዮችን በሚመለከት የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ እንደሚያወጣ ተቀምጧል።
እንደማጠቃለያ
ጠ/ሚ ዐብይ አሕመድ በኢትዮጵያ የሚገኘው የጦር መሳሪያ ቁጥር ከህዝቡ ቁጥር ይበልጣል በሚል ያስቀመጡት ገለጻ ትክክለኛና ነባራዊውን እውነታ የሚያሳይ ነው። በአንዳንድ አካባቢዎች ለእለት ጉርስ የሌላቸው አርሶአደሮች በውድ ዋጋ የጦር መሳሪያ ሸምተው መታየት በቆየ ልማድነቱ የሚታወቅ ነው። መሳሪያ ሐብትን፣ ክብርን ማሳያ ተደርጎ የሚታይባቸው የኢትዮጵያ አካባቢዎች እጅግ ብዙ ናቸው።
በአማራ ክልል በሠርግ፣ በሐዘን እና ሌሎች ማህበራዊ ጉዳዮች ጋር ተያይዞ ጥይት መተኮስ የቆየ ልማድ ነው። በዚህ ክስተት አንዳንድ ጊዜ ንጹሀን ዜጎች በተባራሪ ጥይት የሚጎዱበት ሁኔታ ጥቂት የሚባል አይደለም። ልማዱ በተለይ በሕጻናትና ሴቶች ሥነልቦና ላይ እያሳደረ ያለው ጫና ቀላል አይደለም።
በሌላ በኩል በብዙ አካባቢዎች በዘልማድ የሚያዙ እንደጦር፣ ሳንጃ፣ ጎራዴ፣ሜንጫ፣ ቀስት እና የመሳሰሉት ባህላዊ መሳሪያዎች ንጹሀንን በዘርና በጎሳ እንዲሁም በሃይማኖት ለይተው ለሚጨፈጭፉ አክራሪ ግለሰቦችና ቡድኖች መሳሪያ በመሆን አገልግሏል። በተለይ ባለፉት ሁለት እና ሶስት ዓመታት ኢ- ሰብዓዊ ወንጀሉ እየተለመደ መምጣቱ የሚታወቅ ነው። ይህም ሁኔታ የህዝቦችን መተማመን፣ ሠላምና መረጋጋትን በመንጠቅ፤ ሰዎች በመረጡት አካባቢ እንዳይኖሩ፣ እንዳይሰሩ፣ ሐብት እንዳያፈሩ ወዘተ…እንቅፋት ከመሆን ባለፈም በእነዚህ ኃይላት ያልተገባ ተግባር ብዙ ንጹሃን ዜጎች ተጎጂ እንዲሆኑም ተፈርዶባቸዋል።
በሌላ በኩል በድንበር አካባቢዎች ከፍተኛ የጦር መሳሪያ ዝውውሮች እየተበራከቱ መምጣታቸው ብዙ ጉዳትን አስከትሏል። ከድንበር አካባቢዎች ነዳጅ ጭነው የሚመጡ የቦቴ ተሽከርካሪዎች ሳይቀር ወደጦር መሳሪያ ሕገወጥ ንግድ የገቡበት ሁኔታ ከገጠመኝነት አልፏል። በድንበር በቅብብሎሽ የገቡ የጦር መሳሪያዎች ደግሞ በመሀል አገር ሳይቀር ለሽያጭ የሚዘዋወሩበት ሁኔታም ተበራክቷል። የዚህ ጦስ ደግሞ እንደአዲስ አበባ ባሉ ከተሞች የተደራጁና የታጠቁ ወንጀለኞች እንዲበራከቱ የራሱን አስተዋጽኦ አበርክቷል።
እነዚህ ሰፊ ሰንሰለት ያላቸው የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴዎችን ለማስቆም ከሕግ በተጨማሪ የመንግሥት ቁርጠኝነት ወሳኝ የሆነበት ጊዜ ላይ እንገኛለን። ሕብረተሰቡም ይህን ወንጀል ለመዋጋት ትልቅ አቅም በመሆኑ ተሳትፎው ጉልህ ድርሻ ይኖረዋል። በተጨማሪም አሁን በቅርቡ በጸደቀው የጦር መሳሪያ አስተዳደርና ቁጥጥር አዋጅ መሠረት እንዲህ ዓይነቱን ሕገወጥነት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለማስታገስ እንደሚረዳም ይታመናል።
(ማጣቀሻዎች፡- ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ፣ አዲስ ዘመን ጋዜጣ፣ ፋና ብሮድካስቲንግ፣የጀርመን ድምጽ…)
አዲስ ዘመን ረቡዕ የካቲት 11/2012
ፍሬው አበበ