ስለሺ ባዬ ይባላል። የአይቲ ባለሙያና በጥበቡ ዓለም በፎቶ ግራፍ ሙያ ላይ ተሰማርቷል። በቅርቡ ‹‹ጣና ውሃ አይደለም›› በሚል ርዕስ ካዛንችስ አካባቢ በሚገኘው ፈንድቃ የባህል ማዕከል ውስጥ የፎቶ አውደ ርእይ አዘጋጅቶ ለእይታ ማቅረብ ችሏል። ሥራዎቹም በታዳሚያን ዘንድ አድናቆት ከማግኘታቸው በዘለለ ለወደፊት ተስፋ ከተጣለበት የፎቶ ግራፍ ባለሙያዎች ውስጥ ቀዳሚ እንደሚሆን እስከ መመስከር ደርሰዋል።
‹‹ጣና ውሃ አይደለም›› የሚለው የፎቶ አውደ ርእይን ሲያቀርብ በዋናነት በአማራ ክልል ውስጥ በተለይም በጣና ዙሪያ ያሉትን ህይወት ያላቸው እና ህይወት አልባ ተፈጥሮዎችን በምስል በማስቀረት፤ ሥነ ምህዳሩንና የአኗኗር ዘይቤውን በመግለፅ ግንዛቤ ለመፍጠር እንደሆነ ያስረዳል።
ስለሺ ጣናና ጣና ዙሪያ ባህላዊ፣ ታሪካዊ፣ ሃይማኖታዊ ጉዳዮች መኖራቸውን ይናገራል። እነዚህ በርካታ እሴቶችንም በካሜራው ታግዞ በምስል ያስቀራል። በተለይ የጣናና ማህበረሰቡን መስተጋብር፣ የዕደ ጥበብ ውጤት ሃይማኖታዊ ሥርዓት እና ሌሎች ጉዳዮችንም በድንቅ የጥበብ እይታ በታሪክ መልክ ያስቀራል። ለዚህም ነው ጣና ውሃ ብቻ ሳይሆን ከዚያም ያለፈ ማንነት አለው ብሎ የሚያምነው።
‹‹እያንዳንዱ ቦታዎች በሰዎች ዘንድ ሲጠሩ የሚሰጡት ትርጉም አለ›› የሚለው ፎቶግራፈር ስለሺ ከዚያ ባለፈ ስፍራዎቹ በተለያዩ ምክንያቶች ማለትም ሚስጢራዊም በሆነ መንገድ ከዋናው ስማቸው እና ግብራቸው በዘለለ የተለየ ትርጓሜ ሊኖራቸው ይችላል በማለት እይታውን ያጋራናል። በዚህ መነሻ እንደርሱ እምነት አጽንኦት ሊሰጣቸው የሚገቡ ስፍራዎችን በተለያየ መንገድ መግለፅ ተገቢ እንደሆነ ይነግረናል። በዚህ መነሻ ደግሞ የምስል አውደ ርእዩ ላይ ባቀረባቸው ሥራዎቹ ጣና ከውሃነቱና ግዘፍ ከነሳው ስፋቱ በላይ ተጨማሪ ማንነት እንዳለው፤ ውሃ ብቻ እንዳልሆነ ለማሳየት እንደፈለገ ያነሳልናል።
ስለሺ በጣና ዙሪያ ለዓመታት ኖሯል። ትውልዱ ባህርዳር ሲሆን በጣና ውሃ ተከቦና ልጅነቱን በውብ ተፈጥሮ አጅቦ ነው ያደገው። ይህ ዕድል ደግሞ አብሮ ተዛምዶ ከመኖር ባሻገር ማንነቱን በውብ ተፈጥሯዊ እሳቤ እንዲቀርፅ አድርጎታል። ጥበባዊ እይታው ሲገለጥም ከዚህ መነሻ ነው። የፎቶ ካሜራውን ሲያነሳ በቅድሚያ በዚህ ስፍራና ዙሪያ ያሉ ውብ እውነቶች ናቸው በፊቱ ላይ ድቅን የሚሉት። አካባቢው ላይ የሚሆኑትን እያንዳንዱን ድርጊት እንደ ዕለት ተዕለት ሁነት ብቻ አያያቸውም። ከዚያ ባለፈ ውበታቸውን በምስል ሲያስቀረው ታሪክ፣ ጥበብ እና ማንነትን ተላብሰው ያገኛቸዋል። ለዚህም ነው ለራሱ ጥማት ማርኪያ ብቻ ሆኖ እንዳይቀር ለዕይታ ለታዳሚያን ይፋ ሊያደርጋቸው የወደደው።
‹‹ባህላዊና ታሪካዊ የዕደ ጥበብ ውጤቶችንና እና ተፈጥሯዊ ሁነቶችን በምስል አሰባስባለሁ›› የሚለው ስለሺ አዘጋጅቶት በነበረው የምስል አውደ ርዕይ ላይም ከሦስት ዓመታት ወዲህ ሲሰበስባቸው የቆያቸውን ሥራዎችና በእጅ ስልክ (ቴክኖ ሞባይል) የተነሱትን በፈንድቃ ባህል ማዕከል ማቅረብ ችሏል። በጊዜውም በርካታ ተመልካች እና አድናቆት አግኝቷል።
ፎቶግራፈሩ በጣና ውስጥና በእርሱ ዙሪያ በርካታ ነገሮች እንዳሉ ይናገራል። አብዛኛው ማህበረሰብም ሆነ ግለሰብ ጣና ሲባል አብዛኛውን ጊዜ ውሃ ብቻ እንደሆነ እንደሚያስብ መታዘቡን ይገልፃል። እርሱ ግን በዚህ ብቻ መታሰቡ ተገቢ አለመሆኑን ይናገራል። ለዚህም ነው መረዳቱን ሌሎች ላይ ለማጋባት ጥበብን እንደ መሣሪያ የተጠቀመው። ለጥበኞች ከታደለው ውስጥ ደግሞ ስለሺ የደረሰው በንስር ዓይን ምልከታ በአስገራሚ መንገድ ምስሎችን በካሜራ ማስቀረት ነው። በዚህ ችሎታው ደግሞ ጣና ውሃ ብቻ እንዳይደል ይነግረናል።
ታዲያ ጣና ውሃ ብቻ ካልሆነ ሌላ ምንድን ነው? ስለሺ ጣናን እንደ ውሃ ብቻ ሳይሆን እንደ ከተማም ልናየው ይገባል ይለናል። ለዚህ ገላጭ የሚሆን ምስልም በአውደ ርእይው ላይ አቅርቧል። ይህን ሲል በምክንያት ነው። በተለይ በዙሪያው የሚኖሩት ነዋሪዎችን በዋናነት ያነሳቸዋል። እርሱ እነዚህ የጣና ጎረቤቶች የራሳቸው ማንነት፣ ባህሪ እንዲሁም የአኗኗር ዘይቤ አላቸው ይላል። ይሄ ስሪታቸው ደግሞ ከጣና ጋር በእጅጉ የተቆራኘ ነው። እንደ እርሱ ምልከታ ጣናና ዙሪያው ብሎም ነዋሪዎቹ በአብዛኛው ሊታይ በማይችልና እጅግ በበለፀገ ስፍራ በከተማ መንፈስ ተዛምደው የሚኖሩ ናቸው። ይሄን አስተውሎቱን ደግሞ በቀላሉ በሚያስቀራቸው ምስሎች ላይ በማሳየት መነሻ ምክንያቱን ያጠናክርልናል።
‹‹ጣና ለኔ ልዩ የሚያደርገው ሐይቅም ወንዝም መሆኑ ነው›› ይለናል፤ ሌላኛውን የጣናን ጎን ሲነግረን። ይህን አስገራሚውን ተፈጥሮ በሌላ ቦታ እንዳላየውም ይገልፃል። ጣና ሲቆም ብቻ ሃይቅ፣ ሲጓዝ ደግሞ አባይ በመሆን በሁለት ግብር ይገለጣል ። ይህን አስደናቂ የተፈጥሮ ኡደት መነሻ በማድረግም ሃይቅ ብቻ ሳይሆን ወንዝም፣ ወንዝም ብቻ ሳይሆን ማንነትም፤ አልፎ ተርፎም የማህበረሰቡን የኑሮ ዘዬ የሚበይን እንደሆነ በምስሎች ውስጥ እንመለከታለን።
አሳሳቢውን ጉዳይ በጥበብ
አሁን ላይ ጣና ታሟል። ውብ መልክ ላይ ማዲያት እንደሚወጣው ሁሉ ጣና ላይ ደግሞ እንቦጭ በቅሎ መልከ ጥፉ ሊያደርገው እየታገለ ነው። ይሄ የማይደበቅ ሐቅ ደግሞ ስለሺን ያሳስበዋል። በአሉታዊ ጎን ጣና ምን እንደሚመስል አሁንም በምስሎቹ በማስቀረት ሌላኛውን የጣናን ጎን በጥበባዊ እይታ ያስቃኘናል። ምስሎቹ የመረረ እውነትን የሚያሳዩ ናቸው። ልባችን እንዲደነግጥ፤ ለመፍትሄው እንድንበረታ ደወል ናቸው።
‹‹ጣና በእንቦጭ ምክንያት የመድረቅ ችግር እየገጠመው ነው›› የሚለው ፎቶግራር ስለሺ በጣም በቁጭት ውስጥ ሆኖ ቀጣይ ትውልድ ስለጣና የሚኖረው እሳቤና ምልከታ እንደሚያሳስበው ይናገራል። በተለይ ጣና ሲባል ትውልዱ ደረቅ መሬት የሚል ትርጉም ብቻ እንዲያስቡ እንዳያደርጋቸው ሥጋት አለው። ከዚህ መነሻም ጭምር ነው ምስሎቹን በየጊዜው ለማስቀረት የሚሞክረው። ጣና ውሃ አይደለም ሲል ወደፊት ይህን ችግር መቋቋም ካልተቻለ ትውልዱ ደረቅ መሬት ማግኘቱ አይቀርም እንጠንቀቅ በማለት ለማሳሰብ ጭምርም ነው።
ማስተዋልና ዕይታ
የጣና ውሃ አይደለም የምስል ስብስቦች ዋና ሐሳብ ከማስተዋል እና ከእይታ ጋር የተያያዘ እንደሆነ ስለሺ ይነግረናል። ምክንያቱን ሲያስቀምጥም እንዲህ ይላል። ይህ ትውልድ ብዙ የቤት ሥራ አለበት። ከዚህ ቀደም ኢትዮጵያን ያስረከቡ አባቶች በታሪክ በባህል እንዲሁም በማንነት ጭምር ራሳቸውን ጠብቀው ያለፉ እንደሆኑ ያምናል። በተለይ ማህበራዊ ግንኙነታቸውና ርዕስ በርዕስ የመከባበር ባህላቸው የዳበረም አስደናቂም እንደሆነ ይገልፃል።
በሌላኛው ጎን አሁን ላይ ያለው ትውልድ በተለይ ደግሞ በአፍላ እድሜ ውስጥ የሚገኙት በውጭው ዓለም ጩኸት ውስጥ የሰመጡና ማንነታቸውን ለማጣት እሚንገታገቱ መሆናቸውን ይናገራል። በተለይ ስለሺ ስለ ትውልዱ ጠንከር ባለ አገላለፅ ሲናገር ‹‹የሚኖሩበትን ትተው የማይኖሩበትን የሚመኙ ››ናቸው ይለናል። ከዚህ መነሻ መሐል ሰፋሪ የሆነው ጉልማሳውና በወጣትነት መሐል የሚገኘው ትውልድ ሃላፊነት የመውሰድ ግዴታ እንዳለበት ይናገራል። ይህ መሐል ላይ የሚገኝ ትውልድ የአባቶቹን፣ የአያቶቹን መከባበር፣ አብሮ መኖርና ባህላዊ እሴቶችን የማስቀጠል ሃላፊነት እንዳለበት በፅኑ ይገነዘባል።
ለዚህም ነው ስለሺ ጣናን ሲያስብ ከማስተዋል፣ ከማንነት፣ ከባህል፣ ከታሪክ፣ ከጥበብ፣ ከሃይማኖት እንዲሁም ከተፈጥሮ ጋር ሊገምደው የሚፈልገው። መልከአ ምድሩን እና ተፈጥሮውን ከማህበረሰቡ ጋር በአንድነት በምስሉ በመስፋት አዲስ እይታ አዲስ ቀለም የሚፈጥረው። ግን ያልነበረውን ሳይሆን የነበረውን በአዲስ መልክ እንዲታይ ጥረት የሚያደርገው። የያዝነው ወርቅ መሆኑን እርሱ ባየበት የካሜራ ዓይን የተወሰዱ ምስሎችን አይተን እውነት እንደሆነ እንድንረዳ የሚያግዘን። በተለይ እንደ ተሸነቆረች ታንኳ ሊሰምጥ አንድ ሐሙስ የቀረውን ትውልድ አንገት ለማቅናት የሚጥረው።
ስለሺ ባሰባሰባቸው ሥራዎች ውስጥ በርካታ ክፍሎችን የያዙ የተለያዩ ሥራዎች ይገኛሉ። በታሪክ፣ በመንፈሳዊ ጉዞ፣ በዕደ ጥበብ እና በሌሎች ክፍሎች ተሰባጥረዋል። ይሁን እንጂ ማህበረሰቡ ዕለት ከዕለት የሚገለገልባቸው እና የሚኖርባቸው እንጂ አዲስ የሆነ አንድም ነገር ማግኘት አይቻልም። ፎቶግራፈሩ በእያንዳንዱ ነዋሪ ቤት ውስጥ ያሉ ባህላዊና ከተፈጥሮ ጋር የተቆራኙ መገልገያ ቁሶችን በምስሉ ያስቃኘናል። ሆኖም ከዚህ ቀደም ባላየነው መንገድ ምን ያህል ውበት እንዳላቸው የምናየው በስለሺ እይታ በተነሱ ምስሎች ውስጥ ነው። እርሱ የተንሸዋረረውንና ያንቀላፋውን ማስተዋላችንን በተሰጠው ተሰጦ የመቀስቀሱን ሃላፊነት ወስዷል።
‹‹የእንጀራ ማውጫ ስፌት በሁሉም ቤት አለ ነገር ግን ውበቱን አንገነዘበውም›› ይላል ስለሺ ምን ያህል በየዕለቱ ማህበረሰቡ የሚገለገልበት ቁሳቁስ ጥበባዊ ፋይዳውን እንደማይመለከተውና እንደማይጠብቀው ሲናገር። በርካሽ ዋጋ ስለሚገኝና በየጊዜው በቴክኖሎጂ ስለማይሰፋ ብቻ ከእይታ እየተሰወረና የመጥፋት ሥጋት እያጋጠመው እንደሆነ ይናገራል። ለዚህም ነው በጣና ዙሪያ ያሉ የማህበረሰቡ መገልገያዎችን ጭምር በዕደ ጥበብ ክፍል በመለየት በምስል አስቀርቶ በአውደ ርዕይ ለዕይታ ያቀረበው።
ፎቶግራፈሩ ለምንገለገልበት ባህላዊ ቁስ፣ ለምንኖርበት ተፈጥሮ፣ ማንነታችንን ለሚቀርፀው ታሪክ እና መንፈሳዊነታችን ልዩ ትኩረት ልንሰጥ እንደሚገባ በምስሎቹ ይነግረናል። ይህ ብቻ ሳይሆን ልናሳድገው ልናበለፅገው እንደሚያስፈልግም ያሳስበናል። በተለይ አንድ ሰው ከድካሙ እረፍት ለማድረግም ይሁን ለማሰብ ዛፍ ሥር አሊያም ውሃ ዳር እንደሚቀመጥ በመግለፅ፤ ጣና የመሰለ ተፈጥሮ የሰፋ የህይወት አድማስ እንዲመለከት፤ ከውስጡ ጋር እንዲነጋገር ያደርገዋል ። እንደዚሁ ሁሉ የእርሱ ትውልድ አርቆ እንዲመለከት እና እንዲያስተውል ይህን መሰል እሳቤ ሊይዝ እንደሚገባ እምነቱን ይገልፅልናል። ለዚህም ነው ‹‹ጣና ውሃ አይደለም›› የሚለን።
አዲስ ዘመን የካቲት 8/2012
ዳግም ከበደ