በውጭ ሀገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ቁጥር ከሶስት ሚሊዮን በላይ እንደሆነ በተለያየ ጊዜ ይገለጻል። ይህ ቁጥር እጅግ ከፍተኛ መሆኑ ለማንም ግልጽ ነው። የ2020 የዓለም ሀገራት የሕዝብ ብዛት መረጃ እንደሚያመለክተው ከ235 ሀገራትና ሉዓላዊ ያልሆኑ ግዛቶች መካከል ከሶስት ሚሊዮን ህዝብ በላይ ያላቸው ሀገራትና ግዛቶች 136 ብቻ ሲሆኑ ፤ ቀሪዎቹ 99 ደግሞ ከሶስት ሚሊዮን ህዝብ በታች ያላቸው ሀገራትና ግዛቶች ናቸው። ከዚህ ቁጥር አንጻር ሲታይ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ብዛት ከአርመን፣ ከጃማይካ፣ ከኳታር፣ ከአልቫንያ፣ ከናምቢያ፣ ከጋምቢያ፣ ከቦትስዋና ወዘተ ከመሳሰሉት ሀገራትና ግዛቶች ህዝብ የሚበልጥ ነው። ስለሆነም ይህን ሃይል ለሀገር ሰላምና ልማት ማዋል እንዲቻል በትኩረት መስራት ይገባል።
ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በአሜሪካ፣ በአውሮፓ፣ በአውስትራሊያ፣ በኢስያ፣ በአፍሪካና በመካከለኛ ምስራቅ ይኖራሉ። ከቤት ሰራተኝነት ጀምሮ እስከ ከፍተኛ የምርምር ባለሙያነትና ሃላፊነት፤ ከዝቅተኛ ገቢ እስከ ከፍተኛ ገቢ፤ እንዲሁም በባለሀብትነት ጭምር አቅም ያላቸው መሆናቸውም ይታወቃል።
ስለሆነም በየደረጃው ያለውን እውቀትና ሀብት መጠቀም ይገባል። ለዚህ ደግሞ ዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲን ትኩረት አድርጎ መስራት አለበት። በሀገር ሰላምና ኢኮኖሚ እንዲሳተፉ ብቻ ሳይሆን በአሉበት ሀገርም መብታቸው፣ ጥቅማቸውና ክብራቸው እንዲከበር መስራት የግድ ይላል። ስለሆነም ይህንን ታሳቢ ያደረገ ስራ መስራት ይጠበቅበታል።
የኢፌዴሪ መንግስት በተለይ ከለውጥ ወዲህ በውጭ ለሚኖሩ ዜጎች ትኩረት አድርጎ እየሰራ ነው። ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በሀገራቸው ጉዳይ ንቁ ተሳታፊ እንዲሆኑ የሚያስችሉ ስራዎች እንዲሁም በውጭ ሀገር ሲኖሩ ክብራቸውና መብታቸው ተጠብቆ እንዲስተናገዱ የሚያስችሉ ስራዎች ተሰርተዋል። ለምሳሌ ያህል በውጭ ሀገራት እስር ቤቶች የነበሩ ዜጎችን በማስፈታት ወደ ሀገር ቤት እንዲመለሱ የሚያስችሉ ስራዎች በተለይ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ተከናውነዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአሜሪካን የጀመሩት ዜጎችን የማወያየት ተግባር በአውሮፓ እና ደቡብ አፍሪካ ቀጥለው አሁን ደግሞ ‹‹በህብር ወደ ብልጽግና›› በሚል መርህ ዱባይ ላይ አካሂደዋል። ይህ የሚያመለክተው በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የሀገራቸው መንግስት ስለእነሱም የሚያስብና የሚሰራ መሆኑን የሚያመላክት ነው። ለዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲም ትኩረት መስጠቱን ማረጋገጫ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዱባይ ሸባብ አልአህሊ ስታዲየም ከመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት የተሰባሰቡና ከ15 ሺ በላይ ለኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ባስተላለፉት መልክእት፤ ‹‹የኢትዮጵያ ሰላምና ብልፅግና ተረጋግጦ ዜጎቿ በምቾትና ደስታ የሚኖሩበት ጊዜ ሩቅም ብርቅም አይደለም፤ ይልቁንስ ይህ ኑሮ የሰርክ ህይወት ይሆናል። በመሆኑም በመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት የሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ለሀገራቸው እድገት የራሳቸውን ጡብ ሊያስቀምጡ ይገባል›› ብለዋል።
ይህ የሚያመለክተው መንግስት በሀገር ውስጥ ለሚያከናውነው የሰላምና የልማት ስራ በውጭ ሀገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ሚና የማይተካ በመሆኑ ይህንን ሚናቸውን እንዲወጡ መንግስት ዜጎቹን ትኩረት አድርጎ እየሰራ ስለመሆኑ ማሳያ ነው።
በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ያላቸውን አቅም ለመጠቀም መንግስትም የራሱን የቤት ስራ መስራት አለበት። የመንግስት አገልግሎት መስጫ ተቋማት ቀልጣፋና ፈጣን እንዲሆኑ የአገልግሎት አሰጣጥ ሥርዓቱን ማሻሻል፤ እንዲሁም በውጭ ሀገር ያሉ ኤምባሲዎችና የቆንስላ ጽህፈት ቤቶች ለዜጎች አገልግሎት ለመስጠት በራቸውን ክፍት ማድረግ ያስፈልጋል።
ለዚህ ደግሞ መንግስት ተገቢውን ስራ እየሰራ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በውጭ ሀገር ከኢትዮጵያውያንና ከትውልደ ኢትዮጵያውያን ጋር ያካሄዷቸው የውይይት መድረኮች ለዚህ ማሳያ ናቸው። ተቋማቱ ዜጎችን በማሰባሰብና በማደራጀት ረገድ መልካም ስራ እየሰሩ መሆኑንም አመላካች ነው። ስለሆነም በውጭ ለሚኖሩ ዜጎች ትኩረት የሚያደርገው ዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ ተጠናክሮ ይቀጥላል።
አዲስ ዘመን የካቲት 8/2012