የኢፌዴሪ ስፖርት ኮሚሽን ከትናንት በስቲያ ምሽት አገራቸውንና ህዝባቸውን በዓለም አቀፍ ውድድሮች ላኮሩ ውጤታማ አትሌቶች እና ባለሙያዎችን ሸልሟል። በካፒታል ሆቴል በተደረገው የሽልማት ስነስርዓት በ2011ዓ.ም መጨረሻና በ2012 ዓ.ም መጀመሪያ ወራት በተካሄዱ በአህጉርና ዓለም አቀፍ ውድድሮች ተሳትፈው ውጤት ያስመዘገቡ አትሌቶችና ባለሙያዎች ከ20 ሺ እስከ 80 ሺ ብር ሸልሟል። ለዚህም አምስት ሚሊዮን ብር ወጪ ማድረጉ ታውቋል።
በሞሮኮ ተካሂዶ በነበረው የመላ አፍሪካ ጨዋታ የወርቅ ሜዳሊያ ላስመዘገቡ አትሌቶች 40 ሺ ፣የብር ሜዳሊያ ላመጡ 30 ሺ እንዲሁም የነሐስ ሜዳሊያ ስመዘገቡ 20 ሺ ብር ሽልማት ተበርክቶላቸዋል። በዶሀ የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና ወርቅ ላመጡ አትሌቶች እና አሰልጣኞች 80 ሺ ፣የብር ሜዳሊያ ላስመዘገቡ 50 ሺና የነሐስ ሜዳያ ላመጡ 30 ሺ ብር ሽልማት ተበርክቷል። ከመላ አፍሪካ ጨዋታዎች እና ከዓለም ቻምፒዮና ውድድሮች በተጨማሪ በአፍሪካ መስማት የተሳናቸው የአትሌትክስ ቻምፒዮና፣ በ6ኛው የአፍሪካ ኢንተርናሽናል ቴኳንዶ ቻምፒዮና እና በምሥራቅ አፍሪካ ጤረጴዛ ቴኒስ ቻምፒዮና ተሳትፈው ውጤት ያስመዘገቡ ስፖርተኞች እና አብረው የተጓዙ የልዑካን ቡድኖች ተሸላሚ ሆነዋል።
በዓለምና በአህጉር አቀፍ የስፖርት መድረኮች አገራቸውንና ህዝባቸውን ላኮሩ አትሌቶችና ባለሙያዎች በመንግሥት ደረጃ እውቅናና ሽልማት መሰጠት ከነበረበት ጊዜ መዘግየቱ ቅሬታ ፈጥሮ የሰነበተ ሲሆን፤ ስፖርተኞችን በዚህ ደረጃ ማበረታታትና መሸለም ለሌላ ትላልቅ የውድድር መድረኮች መነሳሳት እንዲችሉ ያግዛልም ተብሏል።
የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት ዶክተር አሸብር ወልደጊዮርጊስ ፤መንግሥት በዓለም ቻምፒዮናና በመላ አፍሪካ መድረኮች ውጤት በማስመዝገብ አገራቸውንና ህዝባቸውን ላኮሩ አትሌቶች እና ባለሙያዎችን ከምስጋና ጋር ሽልማት ማበርከቱ የሚያስመሰግነው መሆኑን ገልጸዋል። ኢትዮጵያን በመወከል ውጤት የሚያመጡ አትሌቶችን ማበረታትና መሸለሙ በቀጣይ ተጠናክሮ እያደገ የሚሄድ መሆኑን የጠቆሙት ፕሬዚዳንቱ «በቶኪዮ ኦሊፒክም ሜዳሊያ ለሚያመጡ አትሌቶች በጋራ ትላልቅ ሕንፃ የሚገነቡበት ቦታ እንጂ ትንሽ ነገር አይበረከትላቸውም » ሲሉ ተናግረዋል። በቶኪዮ ኦሊምፒክ ኢትዮጵያን ወክለው የሚሳተፍ አትሌቶች ከወዲሁ ለድል እንዲነሳሱ የሚያስችሉ እንቅስቃሴዎች እየተደረጉ መሆኑንም ጠቁመዋል። ለዚህም ጠቅላይ ሚኒስተር ዶክተር አብይ አህመድን ለኦሊምፒክ አንድ ቢሊየን ብር ተጠይቀው ‹‹ለስፖርት የምን አንድ ቢሊየን ብር እስከ ሦስት ቢሊየን እንሰበስባለን፣ በቅርቡ የ1ቢሊዮን ብር እራት 1ሺ ሰው እጋብዛለሁ ብለው ቃል መግባታቸውን›› ዶክተር አሸብር ተናግረዋል።
የኢፌዴሪ ስፖርት ኮሚሸን ኮሚሽነር ኤልያስ ሽኩር በበኩላቸው፤ የጀግናው አበበ ቢቂላን ድል በቀጣዮቹ ትውልዶች የድል ችቦ ቅብብሎሽ ተከብሮ እና ይበልጥ ጎምርተቶ ለመቀጠሉ ምስጢሩ አትሌቶችን ለማምጣት ሁሉም ባለድርሻ አካላት ክለቦች ፣ፌዴሬሽኖችና መንግሥት በቅንጅት ታዳጊዎችን ማዕከል ያደረገ ሥራ መሥራት እንደሚጠይቅ አብራርተዋል።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ የካቲት 7/2012
ዳንኤል ዘነበ