አንድ ዓይነት ችግርም እኮ የወግ ነው፤ ቢያንስ በዚያ በኩል እንኳን መፍትሔ ይፈለጋል። ሰውም ያግዛል። ችግር ድርብርብ ሲሆን ግን ሕይወትን ያከብዳል። አንዳንዱ ችግር ደግሞ በባህሪው ለውጭ ሰው አይታይም። ውስጣዊ ችግር አለ፤ ተመልካች እንኳን ሊያግዘው የማይችለው ማለት ነው (ሀሳብን ማካፈል እንኳን ተስፋ ነው ይላሉ እናቶችና አባቶች)።
አንዳንዱ ችግር ደግሞ ለተመልካች ቢታይ እንኳን ለማገዝም የማይመች ይኖራል። በእርግጥ የሚታይ ችግር ከሆነ ማገዣ መንገድ አይጠፋም፤ ለችግረኛው ፈተና የሚሆነው የማይታዩት ችግሮች ናቸው።
የዛሬ «እንዲህም ይኖራል» ዓምድ እንግዳችንን በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል የከፋ ዞን ዋና ከተማ በሆነችው ቦንጋ ላይ ነው ያገኘናቸው። መዲና አባሰመድ ይባላሉ። ከቦንጋ ከተማ በቅርብ ርቀት ከምትገኝ ገጠር አካባቢ መጥተው ነው መኖር የጀመሩት። ቦንጋ ከተማ ውስጥ ብዙ ዓመታትን ቆይተዋል። ዕድሜያቸው አዛውንት የሚባለው ደረጃ ላይ ነው። ምንም እንኳን በወጣትነታቸው ዘመን የነበረውን ችግር እንደ ችግር ባይቆጥሩትም አሁን ግን በኑሮ ምሬት ላይ ናቸው። ያኔ ወጣትነት ነበርና ያገኙትን ተጣድፈው ይሰራሉ፤ አሁን ግን እንደዚያ አይችሉም። ጉልበት የሚፈልጉ ሥራዎችንም አይሰሩም። ከሰው ቤት ሰርተዋል፣ የቀን ሥራ ሰርተዋል፣ ልጅ ያዢ ሆነዋል፤ የአሁኑን የጉልበት ሥራ እስከሰሩበት ጊዜ ድረስ ደግሞ ልብስ አጣቢ ነበሩ። ልብስ ማጠብ ከአቅማቸው በላይ ሆነና አሁን ለጊዜው የጉልት ሥራ ላይ ናቸው።
ከከተማዋ አንድ ዳርቻ ላይ ቁጭ ብለዋል። «ከመለመን ይሻላል» ነው የሚሉት እርሳቸው። እኔና የሥራ ባልደረቦቼ ከተማዋን ዘወር ዘወር እያልን የአካባቢው ምርት የሆኑትን የአትክልትና ፍራፍሬ ዋጋዎች እንጠይቃለን። አንዳንድ የማናውቃቸውን የአትክልትና ፍራፍሬ ዓይነቶች ደግሞ ባንገዛም «ምንድነው» እያልን እየጠየቅን ቆየን። በእነዚህ የጉልት ገበያዎች ውስጥ ስንሄድ ቆይተን ዳር ላይ ስንወጣ እኝህ ሴትዮ ለብቻቸው ቁጭ ብለዋል። ከፊት ለፊታቸው የተነጠፈው ማዳበሪያ ላይ የጠቋቆሩና የተጎሳቆሉ ሙዞች ይታያሉ። አንድ ሁለት ሸንኮራ አገዳና ሽንኩርትም ማዳበሪያው ላይ አሉ። እንደሌሎች ባለጉልቶች የገዥ ወከባ የለባቸውም። አፋቸውን በእጃቸው ከልለው አርቀው ያስባሉ።
ከደንበኞች ጋር ጭቅጭቅ
ከአጠገባቸው ሄጄ ሙዞችን እያነሳሁ ዋጋቸውን ጠየቅኳቸው። የተሰላቸ ምላሽ ሰጡኝ። «እንዴ! ሴትዮዋ ሊሸጡት አይደል እንዴ ያመጡት? ገዥ አለመሆኔ በምን ያስታውቃል?» እያልኩ በውስጤ ተገረምኩ። ምክንያታቸው የተገለጠልኝ በኋላ ነው። የእርሳቸውን ሙዝና ሸንኮራ አገዳ ብዙም አይገዟቸውም፤ ምክንያቱም ጥራቱ ሌሎች ጋ እንዳለው ዓይነት አይደለም። የሚገዟቸውም የተሻለውን የመግዛት አቅም የሌላቸው ናቸው። እዚያው ሆኜ እንዳስተዋልኩት ጎዳና ላይ የሚኖሩና በሱስ የተጎዱ ናቸው። እነዚህ ሰዎች ደግሞ በውድ ዋጋ የሚገዙ ነገሮችን የመግዛት አቅም የላቸውም። መጨቃጨቅና ኃይለ ቃል መጠቀም ያበዛሉ። ሴትዮዋ በዚህ ተሰላችተዋል።
ከእማማ መዲና ጋር እያወራሁ አንድ በወጣትነት ዕድሜ ላይ የሚገኝ ሰው መጣ። አለባበሱም፣ አካላዊ ሰውነቱም፣ ንግግሩም ጤናማ አይደለም። መቅረጸ ድምጼን ሳላስቆም (እየቀረጸ) ከእማማ መዲና አፍ ላይ አወረድኩት። ይህን ያደረኩት እሱም በነፃነት እንዲያወራ እርሳቸውም በነፃነት ተከራክረው እንዲሸጡ ነው። እኔ ልተወው እንጂ እርሳቸው ግን በሚገባ እየነገሩት አይደለም። ልጁም የሚናገረው ጤናማ ንግግር አይደለም። ወይ አይገዛ ወይ አይሄድ! እያነሳ እየጣለ እሱ በሚፈልገው ዋጋ ብቻ እንዲሸጡለት ይጨቃጨቃል። እርሳቸው የነገሩትን ዋጋ ሰጠሁለትና ገዝቶ ሄደ።
ልጁ ከሄደ በኋላ ስጠይቃቸው እርሳቸው ጋ የሚመጡ ገዥዎች እንዲህ ናቸው። በቀላል ዋጋ የሚገዙ ነገሮችን ስለያዙ መደበኛ ገዥዎች አይመጡም። እርሳቸውም የሚገዟቸው በቀላል ዋጋ ነው። አንዳንዴ ደግሞ ብዙ የሚገዙ ነጋዴዎች መራርጠው የተረፋቸውን ይሰጧቸዋል። በቀን አገኙ ቢባል ከፍተኛው አሥር ብር ነው። ጭራሹንም ምንም ሳያገኙ የሚገቡበት ቀንም አለ።
ወደዚህ ሥራ ከገቡ ገና አንድ ዓመትም አልሆናቸውም። ከዚያ በፊት ልብስ በማጠብ ነበር የዕለት ጉርሳቸውን የሚሸፍኑት፤ በዚያ ላይ የሚያስተምሯት ልጅ አለቻቸው። ጉልበታቸው ባይደክም ኖሮ ልብስ ማጠቡ ከዚህኛው ሥራ የተሻለ ነበር። በዚች በቀን አምስት ቢበዛ አሥር ብር በሚገኝባት ሥራ በወር ሁለት መቶ ብር የቤት ኪራይ ይከፍላሉ። አንዳንድ ጊዜ ምንም ሳይኖራቸው የቤት ኪራይ የሚከፈልበት ቀን ይደርሳል፤ ያኔ ይጨነቃሉ። እንደምንም ባለቤቶችን ለምነው ቀኑ ካለፈ በኋላ ይከፍላሉ። ሌላ የተሻለ ንግድ ለመጀመር ደግሞ መነሻ ገንዘብ ያስፈልጋልና አልቻሉም።
በዚህ ሁሉ ውስጥ ግን ጠንካራ ናቸው። አንድም ቀን የሰው እጅ አይተው አያውቁም። አገር ምድሩ ጤነኛና ወጣት ለማኝ በበዛበት እማማ መዲና በልመና ብዙ ብር ከማግኘት ሰርቶ ትንሽ ብር ማግኘትን መርጠዋል። በልመና ጠግቦ ከማደር ሰርተው ያገኙትን በልቶ ማደርን መርጠዋል። ይህ ሁሉ ችግር ሲያጋጥማቸው አንድም ቀን ለልመና እጃቸውን ዘርግተው አያውቁም።
ከባዱ ፈተና የልጃቸው ነገር ሆኗል
አሁን የእማማ መዲና ችግር ኑሮ አይደለም፤ ገንዘብ አለማግኘታቸው አይደለም። የጠዋት ማታ ጭንቀታቸው የልጃቸው ነገር ነው። አንዲት ልጅ ናት ያለቻቸው። ይቺ እንደ ዓይናቸው ብሌን የሚያዩዋት ልጃቸው ከአጠገባቸው ጠፍታባቸዋለች። የት እንዳለች አያውቁም። በሕይወት ትኑር አትኑር አያውቁም። ራሷን ለመለወጥ ሥራ ገብታ ይሆናል ሲሉ ራሳቸውን ያጽናናሉ። ድንገት ደግሞ «ሞታ ቢሆንስ!» የሚል መጥፎ ስሜት ውስጣቸውን ያላውሰዋል። በማስታወቂያ የማስነገር አቅሙም እውቀቱም የላቸውም። አንዴ ይገድሏታል፤ አንዴ ሥራ ያስይዟታል፤ ይህ የእናት ሆድ ነው። የእማማ መዲናን ስሜት ለማወቅ በጣም ቀላል ነው። የእናትና ልጅ ግንኙነት መረዳት ብቻ በቂ ነው። እናት ማለት ልጇ ትምህርት ቤት ሄዳ (የት እንዳለች እየታወቀ ማለት ነው) የምትጨነቅ ናት። እናት ማለት ውሃ ለመቅዳት የሄደች ልጇን የማታምን ናት፤ እናት ማለት ከሞቀ ቤቷ የተቀመጠች ልጇን የምትናፍቅ ናት። ታዲያ እማማ መዲና የት እንዳለችና በሕይወት ትኑር አትኑር ላላወቋት ልጃቸው እንዴት ይሆኑ ይሆን? ለዚህም ነው ያቺን ጉልት ይዘው ጎዳና ላይ ቁጭ ሲሉ አርቀው የሚያስቡት።
ልጅቷ ለምን ጠፋች?
ለልጅቷ መጥፋት ገፊ ምክንያት የሆነው የኑሮው ሁኔታ ነው። ምክንያቱም ይህ የልጅነትና የወጣትነት አዕምሮ ነው። የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በአንድ ወቅት የሰራውን ዘገባ ብዙዎቻችሁ ታስታውሱ ይሆናል። ከዶሮ ማደርያ ቤት ውስጥ ትኖር የነበረችዋ ታዳጊ ሕይወት ምን ያህል አስቸጋሪ እንደነበር ብዙዎቻችንን በእንባ ያራጨ ነበር። ታዳጊዋ ተማሪ ነበረችና ትምህርት ቤት ስትሄድ ትምህርቱን ሳይሆን የምትከታተለው «ዶሮ ዶሮ ትሸቻለሽ» እንዳይሏት ነበር የምትሳቀቀው። ጓደኞቿ ስለቦርሳ፣ ስለቀሚስና ስለጌጣጌጥ ዓይነት ሲያወሩ እሷ ከራሷ ጋር የምታወራው ስለአዳሯና ስለ የዕለት ጉርሷ ነበር። ይህን ስትናገር በልጅነት ፊቷ ላይ እንባ እየወረደ ነው። ያንን ዘገባ ያየ ሁሉ እንባውን አርግፏን። አንድ ባለሀብት ግን የብዙዎቻችንን እንባ ወደ ደስታ ቀየረ። ከዶሮ ጋር ትኖር የነበረችዋን ልጅ የቤት ባለቤት አደረጋት።
የእማማ መዲና ልጅ ምን እንደሆነች እንኳን የመናገር ዕድል ባታገኝም ከቤት የጠፋችው በኑሮ መጎሳቆል ብዛት ነው። ተማሪ ነበረች። ሌሎች የትምህርት ቤት ጓደኞቿ የያዙትን ነገር እሷ የላትም። እነርሱ የሚገዛላቸውን አይገዛላትም፤ ይባስ ሲልም የግዴታ የሆኑት እስክርቢቶና ደብተርም ይቸግራታል። እናት የመግዛት አቅም ሲቸግራቸው ይጨቃጨቃሉ። የልጅነት አዕምሮ ነውና ደግሞ በችግሩ ልክ ማሰብም አይቻልም። ለእሷ የሚታያት ሌሎች ልጆች የያዙትን አለመያዟ ነው፤ ሌሎች ልጆች የተገዛላቸው ነገር ለእሷ አለመገዛቱ ነው። ልብስ በማጠብ የሚተዳደሩ እናት ደግሞ ያንን ማድረግ ይቸግራቸዋል።
እማማ መዲና ልጃቸው ከአጠገባቸው ከጠፋች ከአንድ ዓመት በላይ ሆኗል። የዘመኑን የመገናኛ ዘዴ (ስልክ፣ ኢንተርኔት) እንኳን ተጠቃሚ አይደሉም። ልጃቸው ግን ስልክ ለመጠቀም የሚያስችል የትምህርት ደረጃ አላት፣ ዳሩ ግን እናትየዋ ስልክ ከሌላቸው በምን ትደውላለች? በጎረቤትም ሆነ በሌላ አጋጣሚ እዚህ ነኝ አላለቻቸውም። ለእናትየዋ ስጋት የሆናቸው ይሄ ነው። በሕይወት ብትኖር ኖሮ እዚህ ነኝ ብላ ትናገር ነበር ይላሉ። ጎረቤት ደግሞ ሌላ ማጽናኛ ይነግሯቸዋል። «ልጅቷ እዚህ ነኝ ካልኩ ነይ ይሉኛል ብላ ነው፤ አንቺ አትጨነቂ፤ ሥራ እየሰራች ነው። ወደቤተሰብ ለመምጣት የሚያስችል የገንዘብ አቅም ሲኖራት ትመጣለች» ይሏቸዋል።
እርግጥ ነው የዚህ ዓይነት ልጆች አሉ። ለሥራ ከቤተሰብ ርቀው ይሄዱና አመርቂ ሥራ ካላገኙ «ምን ይዤ» የሚሉት ነገር አለ። በተለይም ጊዜው እየረዘመ በሄደ ቁጥር ይህን ያህል ጊዜ ቆይቼ ለቤተሰብ የሚሆን አንድ ነገር እንኳን ሳላደርግ ይላሉ፤ ምን ስትሰራ ከረመች ይሉኛል የሚል ስሜት ይፈጠርባቸዋል።
ይህ ነገር እውነት ይሁንና እማማ መዲና ከልጃቸው ለመገናኘት ያብቃቸው!
አዲስ ዘመን ቅዳሜ የካቲት 7/2012
ዋለልኝ አየለ