ለማይቀረው ክሪፕቶከረንሲ እንሰናዳ፤

በሀገራችን የክሪፕቶከረንሲ ንግድ ሕጋዊ እውቅና ባይሰጠውም፤ ቁጥራቸው ቀላል ያልሆነ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በስፋት እየተሳተፉበት ይገኛል። የሀገራችን የኤሌክትሪክ ኃይል ታሪፍ ከሌሎች ሀገራት ጋር ሲነጻጸር ርካሽ መሆኑ ከፍተኛ ኃይል የሚጠቀሙ የክሪፕቶከረንሲ አቀላጣፊዎች ወይም ክሪፕቱማይኒጎች በብዛት ወደ አዲስ አበባ እየተመሙ ይገኛል። የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎትም ለክሪፕቶ ማይኒንግ ኩባንያዎች ኃይል በመሸጥ ዳጎስ ያሉ ሚሊዮን ዶላሮችን እያገኘ ነው። ምን አደከማችሁ ክሪፕቶከረንሲ አንድ እግሩን ሀገራችን አስገብቷል። ሰሞኑን ስለክሪፕቶከረንሲ መወሳቱ አበጀህ የሚያስብለው ለዚህ ነው።

ለዚህ ነው ሰሞነኛው “የክሪፕቶ ግብይቶችን መቆጣጠር የሚያስችል ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑ፤” የሚገልጸው ዜና ለዛሬ መጣጥፌ መነሻ የሆነኝ። አዎ! በኢትዮጵያ በምናባዊ መገበያያ ገንዘቦች ግብይት ማድረግ ቢከለከልም ባልተፈቀደ መንገድ ግብይት ቢኖር ቁጥጥር ማድረግ የሚያስችል ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የፋይናንስ ደኅንነት አገልግሎት ማስታወቁን የሪፖርተር ዘገባ ያወሳል።

የተቋሙ ዳይሬክተር አቶ ሙሉቀን አማረ ይህን ያሉት ትናንት ግንቦት 26 ቀን 2017 ዓ.ም. የምሥራቅና ደቡባዊ አፍሪካ አገሮች የፀረ ሕገ ወጥ የገንዘብ ዝውውር ቡድን (Anti Money Laundry Group) በአዲስ አበባ ባካሄደው ጉባዔ ላይ በተገኙበት ወቅት ነው። ቡድኑ ኢትዮጵያን ጨምሮ 21 አገሮችን በአባልነት በመያዝ ዋና መቀመጫውን ታንዛኒያ ዳሬሰላም ያደረገ አኅጉራዊ ተቋም ነው። ተቋሙ ከኢትዮጵያ ፋይናንስ ደኅንነት አገልግሎት፣ ከተመድና ሩሲያ ጋር በመቀናጀት ለአባል አገሮች የፋይናንስ ደኅንነት ባለሙያዎች በአዲስ አበባ ሥልጠና በመስጠት ላይ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ፋይናንስ ደኅንነት አገልግሎት ዳይሬክተር አቶ ሙሉቀን አማረ ለሪፖርተር እንዳሉት ‹‹በኢትዮጵያ ከብር ውጪ የምናባዊ መገበያያ ገንዘቦች ግብይት አልተፈቀደም፣ ነገር ግን ባልተፈቀደ መንገድ ግብይት ቢኖር በሚል ጉዳዩን እንዴት መቆጣጠር እንደሚቻል ሥልጠናዎች እየተሰጠ ነው፤›› ብለዋል። ብሔራዊ ባንክ በቀጣይ የክሪፕቶ ወይም የምናባዊ መገበያያ ገንዘቦችን ቢፈቅድ አልያም ክልከላውን ተላልፈው የተገኙ ተገበያዮችን ለመለየት በሚል የቴክኖሎጂ፣ የሰው ኃይልና መሰል ቅድመ ዝግጅቶች እየተደረገ እንደሆነም አቶ ሙሉቀን ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ የክሪፕቶ ግብይቶች በይፋ ቢከለከሉም እየተፈጸሙ አይደለም ማለት ይቻላል? በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ ‹‹ግብይቱ በኢትዮጵያ በሕግ የተፈቀደ አይደለም። እስካሁን የተደረጉ ግብይቶች መጠንን ለማወቅ ጥናት ያስፈልጋል። የክሪፕቶ ቴክኖሎጂ አዲስ በመሆኑ እንደ ሀገር በቀጣይ የሚወሰነው እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ግን የሚደረጉ ግብይቶች አሉ፣ ሁሉም ግብይቶች ሕገወጥ ናቸው ላይባል ይችላል። ግን ደግሞ የኢትዮጵያ መገበያያ ገንዘብ ብር ነው፣ ከብር ውጪ ያሉ ቨርቹዋል ግብይቶች አልተፈቀዱም። ምንም እንኳን ግብይት ቢፈጸምም ግብይቱ ግን ወንጀል ስለሆነ ለሽብርተኝነትና ለሕገ ወጥ ተግባር ከዋለ ይህንን መሠረት ያደረገ ምርመራ ማድረግ ይቻላል።

የተወሰኑ ልምምዶች አሉ ቅድሚያ ግንዛቤው ያስፈልጋል። በቀጣይ በግልጽ ቢፈቀድ በአግባቡ ግብይቱን ሞኒተርና ሬጉሌት ለማድረግ ከተከለከለ ደግሞ ይህንን በሕግ የተከለከለን ፈጽሞ የሚገኝ አካልን ለማስቀጣት ዝግጅቱ ያስፈልጋል፤›› ሲሉም ዳይሬክተሩ ምላሽ ሰጥተዋል።

ሽብርተኞች ሀብት ለማሰባሰብ የምናባዊ መገበያያ ገንዘቦችን የመጠቀም ዓለም አቀፍ ልምድ ያለ ቢሆንም፣ እስካሁን ድረስ በኢትዮጵያ የምናባዊ መገበያያ ገንዘቦችን በመጠቀም ከኢትዮጵያ ወደ ሌሎች ሀገሮችም ሆነ ከውጭ ሀገሮችም ወደ ኢትዮጵያ የደረሰ ጉዳት እንደሌለም ተገልጿል። በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀረ ሽብርተኝነት ፕሮግራም መሪ የሆኑት ከማል አንዋር በበኩላቸው ምናባዊ ገንዘቦች ከሽብርተኝነት ባለፈ ለግብር ስወራ፣ የሕገወጥ የገንዘብ ዝውውር ወንጀሎችን እንዲስፋፉ እያደረጉ ነው ብለዋል። ሀገሮች እነዚህ ማጭበርበሮች እንዳይፈጸሙ በየጊዜው ሕጎቻቸውን ማሻሻል፣ የሠራተኞቻቸውን አቅም ማዳበርና የቴክኖሎጂ አጠቃቀሞችን እያዘመኑ መሄድ እንደሚኖርባቸውም ከማል አንዋር ተናግረዋል።

በምሥራቅና ደቡባዊ አፍሪካ የፀረ ሕገ ወጥ ገንዘብ ዝውውር ቡድን ከፍተኛ የሕግ አማካሪ የሆኑት ሙሉቀን ይርጋ በበኩላቸው፣ ምናባዊ ግብይቶችን የሚጠቀሙ የሽብርተኛ ድርጅቶች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን ተናግረዋል። አልቃይዳ፣ ዳኢሽ፣ አልሻባብ፣ አይኤስና ሌሎችም የሽብር ቡድኖች ይህንን የምናባዊ መገበያያ ገንዘቦችን እየተጠቀሙ ካሉ ተቋማት መካከል ዋነኞቹ እንደሆኑም ተገልጿል። ከፍተኛ አማካሪው አክለውም የምናባዊ ግብይት መሠረተ ልማቶችንና አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማትን መቆጣጠር እንደሚገባም አሳስበዋል።

ሀገሮች ምናባዊ የገንዘብ ግብይቶችን ተጠቅመው ሽብርተኝነትና መሰል ወንጀሎችን እንዳይፈጽሙ ትብብሮችን እንዲያዳብሩም አማካሪው ጥሪ አቅርበዋል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ከወራት በፊት ባሻሻለው አዋጅ መሠረት የምናባዊ ግብይትን በይፋ የከለከለ ሲሆን፣ በቀጣይ ግን እንደአስፈላጊነቱ ዘርፉ ሕጋዊ ሊሆን እንደሚችልና መመሪያ ሊያወጣ እንደሚችል በወቅቱ መግለጹ ይታወሳል። ለመሆኑ ክሪፕቶከረንሲ ምንድነው…?

በጊዜ ሂደት እና በቴክኖሎጂ እድገትም የአኗኗር ዘያችን በፍጥነት እየተቀየረ መጥቷል። ለዚህም ማሳያ የሚሆነን ደግሞ ‘ዲጂታል ገንዘቦችን’ ለምርት እና አገልግሎት መገበያያነት ማዋል መቻላቸው ሊጠቀስ ይችላል። 21ኛው ክፍለ ዘመን ካስተዋወቀን የቴክኖሎጂ ምጡቅ ቃላት መካከል ብዙ እየተባለለት ያለው ‘ክሪይፕቶከረንሲ’ አንዱ ነው። ኦክስፎርድ መዝገበ ቃላት ‘ክሪይፕቶከረንሲን’ እንዲህ ሲል ይገልጸዋል፤ የገንዘብ ልውውጦችን ደኅንነት የሚያረጋግጥ፣ የተጨማሪ አሃዶችን መፈጠርን የሚቆጣጠር እና ገንዘብ መተላለፉን የሚያረጋግጥ ጠንካራ ክራፕቶግራፊ የሚጠቀም መገበያያ እንዲሆን ተደርጎ የተቀረጸ ዲጂታል ገንዘብ።

ከላይ የተጠቀሰውን መስፈርት የሚያሟሉ በርካታ ዓይነት ክሪፕቶካረንሲዎች አሉ። በስፋት ከሚታወቁት መካከል ቢትኮይን፣ ኤቴሪያም፣ ሪፕል እና ቢትኮይን ካሽ የሚባሉት ከበርካታ ክሪፕቶካረንሲዎች መካከል ሊጠቀሱ ይችላሉ። በቅድሚያ የ’ዲጂታል ከረንሲውን’ ተቀላቅሏል የሚባልለት እና በስፋት በሚታወቀው ቢትኮይን ላይ ትኩረታችንን እናድርግ።

ቢትኮይን ምንድነው? ቢትኮይን ማለት በቀላል ቋንቋ፤ ዲጂታል+ገንዘብ+መገበያያ በማለት ማጠቃለል ይቻላል። ይህ መገበያያ በኪሳችን ተሸክመን እንደምንዞረው የብር ኖት ወይም ሳንቲም ሳይሆን ‘ኦንላይን’ የሚቀመጥ ዲጂታል ገንዘብ ነው። ሌላው የቢትኮይንና የተቀሩት የክሪይፕቶከረንሲዎች ልዩ ባሕሪ በመንግሥታት እና በባንኮች አለመታተማቸው እንዲሁም ቁጥጥር አለመደረጉ ነው። ቢትኮይን የሚፈጠረው ‘ማይኒንግ’ በሚባል ሂደት ነው። በመላው ዓለም በኔትወርክ በተሳሰሩ ኮምፒውተሮች ቁጥጥር ይደረግበታል። ቢትኮይንን የፈጠረው ግለሰብ/ቡድን በዓለም ላይ 21 ሚሊዮን ቢትኮይኖች ብቻ እንዲፈጠሩ ገደብ እንዳስቀመጠ/ጡ ይታመናል። የብሎክ ቼይን መረጃዎች እንደሚያሳዩት እስካሁን 17 ሚሊዮን ያህል ቢትኮይኖች ማይን ተደርገዋል።

ከሰባት ዓመት በፊት እአአ የካቲት 15 ቀን 2018 የአንድ ቢትኮይን ዋጋ 10,031 የአሜሪካ ዶላር ነበር። ከአንድ ዓመት በኋላ ማለትም የካቲት 15 ቀን 2019 የአንድ ቢትኮይን ዋጋ ወደ 3,561 የአሜሪካ ዶላር ዝቅ ብሏል። ቢትኮይን ከተፈጠረ 10 ዓመታት ተቆጥረዋል። ባለፉት አስር ዓመታትም የቢትኮይን ዋጋ እጅጉን እየጨመረ መጥቷል። የካቲት 2010 ዓ.ም የአንድ ቢትኮይን ዋጋ ከ10ሺህ ዶላር በላይ ደርሶ ነበር።

ከሁለት ዓመት ከነበረው ዋጋ ጋር ሲነጻጸርም ከ27 እጥፍ በላይ ጨምሯል። አሁን ላይ ደግሞ ከአንድ ዓመት በፊት ከነበረው ዋጋ ጋር ሲነጻጸር ወደ 3 እጥፍ በሚጠጋ ዋጋ ቀንሷል። ከሁለት ዓመታት በፊት ዋጋ በፍጥነት ሲጨምር ለዋጋው መጨመር ምክንያቱ በትክክል ይህ ነው ማለት አልተቻለም። አንዳንድ የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ግን ኢንቨስተሮች ‘’ዕድሉ እንዳያልፋቸው’’ ከሚገባው በላይ ፈሰስ እያደረጉበት ነው የሚል ምክንያት ያቀርባሉ። ሌሎች ደግሞ የቢትኮይን ተቀባይነት እየጨመረ በመምጣቱ ዋጋው እንደጨመረ ያስቀምጣሉ።

በቢትኮይን ግብይት መፈጸም ይቻላል?

አዎ። ለሚያቀርቡት ምርት እና አገልግሎት ቢትኮይንን በክፍያ መልክ የሚቀበሉ በርካቶች ድርጅቶች አሉ። ማይክሮሶፍት፣ የፈጣን ምግብ አቅራቢዎቹ ኬኤፍሲ እና ሰብዌይ፣ የጉዞ ወኪሉ ኤክስፔዲያን ከመሳሰሉ ባለብዙ ሚሊዮን ገንዘብ ኩባንያዎችን አንስቶ እስከ ሆቴሎች እና ካፊቴሪያዎች ቢትኮይንን በክፍያ መልክ ይቀበላሉ። በቢትኮይን አማካኝነት ክፍያ ሲፈጸም የገዢውን ማንነት ይፋ አለማድረግ ያስችላል። ይህም በርካቶች በኢንተርኔት አማካኝነት ማንነታቸውን ሳይገልጡ አገልግሎቶችን እንዲያገኙ ስለሚያስችላቸው በቢትኮይን አማካኝነት የሚደረጉ የንግድ ልውውጦች ቁጥር እጅጉን ጨምሯል።

ቢትኮይን እንደስጋት? አሸረትስ በተባለ የፋይናንስ ተቆጣጣሪ ኩባንያ ውስጥ ባለሙያ የሆኑት ብራደሊይ ራይስ በቢትኮይን ላይ ምንም አይነት ቁጥጥር እንደማይደረግበት ያስታውሳሉ። ቢትኮይንን በመጠቀም የገዢው ማንነት ይፋ ሳይደረግ በየትኛውም ሰዓት እና በየትኛውም ስፍራ የቢትኮይን ዝውውር ማድረግ ይቻላል። የገዢው ማንነት ይፋ ሳይደረግ ግብይት መፈጸም ይቻላል። በዚህም ሕገ-ወጥ ቡድኖች የጦር መሣሪያዎች እና እፆችን ሊገዙ እና ሊሸጡ ይችላሉ፣ ሕገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውር እና አሸባሪዎችን ለመደገፍ ያስችላል በማለት ቢትኮይንን ጨምሮ ሌሎች ክሪይፕቶከረንሲዎች ላይ ያላቸውን ስጋት የሚያነሱ በርካቶች ናቸው።

በሌላ በኩል በርካታ የፋይናንስ ባለሙያዎች ቢትኮይን ላይ ምንም ዓይነት ቁጥጥር አለመደረጉ ተፈላጊነቱን እንደጨመረው ያወሳሉ። እአአ 2009 ላይ ከበርካቶች ጋር የተዋወቀው ቢትኮይን፤ ሕጋዊ ነው? ወይስ አይደለም? በሚሉ ጥያቄዎች ታጅቦ ቆይቷል። ‘ሕጋዊ ነው? ወይስ አይደለም?’ ለሚለው ጥያቄ ምላሽ የምናገኘው ግን የት የሚለው ሲካተትበት ብቻ ነው። አሜሪካ፣ ካናዳ፣ የአውሮፓ ኅብረት እና አውስትራሊያን የመሳሰሉ የዓለማችን ግዙፍ ኢኮኖሚዎች ለቢትኮይን አዎንታዊ ምልከታ አላቸው።

ከላይ በተጠቀሱት ስጋቶች ምክንያት ቬትናም፣ ቦሊቪያ፣ ኮሎምቢያ እና ኢኳዶር በቢትኮይን መገበያየትን ከከለከሉ ሀገራት መካከል ይገኙበታል። ቢትኮይን ዓመታት ቢያስቆጥርም አሁንም ቢሆን በርካታ የዓለማችን ሀገራት ክሪፕቶከረንሲዎችን በተመለከተ ግልጽ ሕግ የላቸውም። ክሪይፕቶከረንሲዎችን መቆጣጠር የማይቻል በመሆኑም ለመንግሥታት ፈተና ሆኖ ቆይቷል።

እስኪ የበለጠ ግልጽ እንዲሆን ተጨማሪ ማስረጃዎችን እንመልከተው። የዩኒቨርሲቲ ጥናት እንደሚያሳየውም አጠቃላይ የቢትኮይን ግብይት ትስስር በዓመት ውስጥ በሰዓት እስከ 131.4 ቴራዋት ሊጠቀም ይችላል። ቢትኮይን ሀገር ቢሆን ኖሮ የሚወስደው ኃይል መጠን 106 ሚሊዮን ሕዝብ ያላት ግብፅ ከምትጠቀመው የኃይል መጠን ጋር ተመጣጣኝ ይሆን ነበር። በአሁኑ ወቅት ከቢትኮይን ሌላ ከ2ሺህ በላይ የክሪፕቶከረንሲ መገበያያ ሥርዓቶች አሉ። አንዳንዶቹ የግብይት ሥርዓቱን ከስጋት ነፃ ለማድረግ ከፍተኛ ኃይል የማይፈልጉ ሌሎች አማራጮችን ይጠቀማሉ።

ለምሳሌ አቴሪየም የሚባለው የክሪፕቶከረንሲ አይነት ፕሩፍ ኦፍ ስቴክ ተብሎ ወደሚጠራ ሥርዓት የተሸጋገረ ሲሆን ይህም በቂ ገንዘብ ያላቸው ተጠቃሚዎች በዘፈቀደ ተመርጠው እስሮችን ወደ ሂሳብ መዝገቡ እንዲያስገቡ የሚደረግበት መንገድ ነው። ነገርን ነገር ያነሳዋል እንዲሉ እንደ አዲስ መነጋገሪያ ስለሆነች ስለ ቡልጋሪያዊቷ የክሪፕቶ ንግስት ሩጃ ኢግናቶቫ እናነሳ።

ከስምንት ዓመታት በፊት ዋንኮይን በተሰኘ ሐሰተኛ የክሪፕቶከረንሲ ኩባንያዋ አማካኝነት ከ4.5 ቢሊዮን ዶላር በላይ አጭበርብራ እምጥ ትግባ ስምጥ የታወቀ ነገር የለም። ለመጨረሻ ጊዜ ግሪክ አቴንስ ከታየች በኋላ የውሃ ሽታ ሆናለች። አሜሪካ ያለችበትን ለጠቆመኝ ወሮታውን 5 ሚሊዮን ዶላር እከፍላለሁ ብትልም እስከዛሬ የበላት ጅብ አልጮኸም። ቢቸግረው በስሟ የተመዘገበን ንብረት በፍርድ ቤት እያሳገደ ይገኛል።

ፈልጎ አስፈልጎ ያጣት ኤፍቢአይ /FBI/ ሰሞኑን በጥብቅ ከሚፈልጋቸው 10 አደገኛ ተጠርጣሪዎች ዝርዝር አካቷታል። የታይም መጽሔት በሰው ልጆች ታሪክ ተወዳዳሪ ያልተገኘለት ማጭበርበር ይለዋል። ትውልደ ቡልጋሪያ ጀርመናዊ ናት። ዋንኮይን ከተሰኘው አጭበርባሪ ኩባንያ ጋር ተያይዞ ስሟ በዓለም ናኝቷል። ቢቢሲ የውሃ ሽታ የሆነችው የክሪፕቶ ንግስት ሲል የምርመራ ዘገባ ሠርቶባታል ።

ምን አልባት ተገድላ ይሆናል የሚሉ አሉ። አይ በፕላስቲክ ቀዶ ጥገና ማንነቷን ቀይራ ጀርመን እየኖረች ነው የሚሉም አልታጡም። አይ ዱባይ ታይታለች፤ የለም ራሽያ ነው ያለችው እየተባለች መንፈስ ሆና አርፋዋለች። በማጭበርበር ወንጀል ተጠርጥራ በመላው ዓለም እየታደነች ነው። ከተሰወረች 5ኛ ዓመቷን ይዛለች። ከ4 እስከ 15 ቢሊዮን ዶላር በማጭበርበር የምትጠረጠረውና የክሪፕቶ ንግሥት በሚል ቅጽል የምትታወቀው ዶ/ር ሩጃ ኢግናቶቫ ዕምጥ ትግባ ስምጥ ከተሰወረች ዘጠነኛ ዓመቷን ይዛለች። ኤፍቢአይ ቢታክተው ማንነቷን ሳትቀይር አልቀረችም ማለት ጀምሯል። በፕላስቲክ ቀዶ ጥገና ወይም በሌላ መንገድ መሆኑ ነው።

ዕድሜዋ በ40ዎቹ የሚገመተው የቡልጋሪዋ ዕንስት ኤፍቢአይን ጨምሮ በኢንተርፓል የምትታደነው ዋንኮይን /Onecoin/ በተሰኘ ክሪፕቶከረንሲ በተፈጸመ እጅግ ከፍተኛ ማጭበርበር ነው። ኤፍቢአይ በ2017 ዓ.ም የእስር ማዘዣ ይዞ ለጥያቄ ማፈላለግ ሲጀምር ነው የክሪፕቶ ንግሥቷ ድንገት የውሃ ሽታ የሆነችው ይላል የቢቢሲው ሊዎ ሳንድስ። ነገሩ ወዲህ ነው በ2014 ዓ.ም ራሱን ክሪፕቶከረንሲ ብሎ የሚጠራው ዋንኮይን፤ ከረንሲውን ለሚያሻሽጡለት ኮሚሽን እንደሚከፍል ይፋ አደረገ። ሆኖም ዋንኮይን እንደሌሎች ክሪፕቶከረንሲዎች ዋስትና ወይም መተማመኛ የሚሰጥ የብሎክቼይን አሠራር አልዘረጋም።

የኤፍቢይ መርማሪዎችም ሆነ የፌዴራል ዐቃቤ ሕጎች ዋንኮይን ክሪፕቶከረንሲ ሳይሆን የማጭበርበሪያ ስልት ነበር የሚሉት ለዚህ ነው። የማንሀተኑ ዐቃቤ ሕግ ዳሚን ዊሊያምስ ንግሥቷ የማጥመጃ መረቧን የጣለችው ሕዝበ አዳም ከክሪፕቶከረንሲ ጋር እልል በቅምጤ የሚልበትን ትክክለኛ ጊዜ መርጣ ነው ይላሉ። ኤፍቢአይ በስምንት የተለያዩ ወንጀሎች ጠርጥሮ የከሰሳትን የክሪፕቶ ንግሥት ያለችበትን ለጠቆመ 100ሺህ ዶላር በወሮታ እንደሚከፍል ቃል ገብቷል ።

ኤፍቢአይ ይሄን ማስታወቂያ ማስነገሩ ዶ/ር ኢግናቶቫን ለመያዝ ያግዘዋል ይላል የዋንኮይንን ማጭበርበር በምርመራው ያጋለጠው የቢቢሲው ጄሚ ባርትሌት፤ የክሪፕቶ ንግሥቷን መያዝ አዳጋች ያደረገው እጇ ላይ ይገኛል ተብሎ የሚገመተው ረብጣ ግማሽ ቢሊዮን ዶላር ነው ይላል የምርመራ ጋዜጠኛው ባርትሌት። አበውስ ገንዘብ ካለ በሰማይ መንገድ አለ አይደል የሚሉት፤ ሐሰተኛ ማስረጃዎችን በማዘጋጀት የተካነች መሆኗና ገጽታዋን መቀያየሯ በቁጥጥር ስር ለማዋል የሚደረገውን ጥረት ፈታኝ ያደርገዋል ይላል ባርትሌት፤ “ዶ/ር ኢግናቶቫ ለመጨረሻ ጊዜ የታየችው በ2017 ዓ.ም ከትውልድ ሀገሯ ቡልጋሪያ ወደ ግሪክ ስትበር ነው ይለናል ቢቢሲ፤ በተለይ ባርትሌት እንዲያውም ሞታም ሊሆን ይችላል እስከ ማለት ደርሷል።

በዋንኮይን ገንዘቧን የተጭበረበረችው ጄን ማክአዳም እሷም ሆነች ጓደኞቿ እስከ 250ሺህ ፓውንድ የሚደርስ እንደተበሉ ለቢቢሲ ተናግራለች። ጓደኛዬ ሊያመልጠን የማይገባ የኢንቨስትመንት ዕድል ስትል መልዕክት ትልክልኛለች። ከዚያ ወዲያው በዌቢናር ሊንኩን ተጠቅሜ ዋንኮይንን ተቀላቀልሁ ትላለች ማክአዳም ያቺን ዕድለ ቢስ ቀን ስታስታውስ። መጭበርበሬን የተረዳሁት ከወራት በኋላ ነው።

ራሷን የክሪፕቶ ንግሥት ብላ የምትጠራው ዶ/ር ሩጃ ኢግናቶቫ ቢትኮይንን የሚፎካከር ዋንኮይን የተሰኘ ክሪፕቶከረንሲ ፈጥሬያለሁ በማለት በማይጨበጥ ተስፋ እየሞላች ቢሊዮኖችን ኢንቨት እንዲያደርጉ ታግባባ ነበር ሲል ያስታውሳል የቢቢሲው ባርትሌት፤ በ2016 ሰኔ ግም ሲል የዛን ጊዜዋ የ36 ዓመቷ የንግድ ሰው ዶ/ር ሩጃ ኢግናቶቫ ከአፍ እስከ ገደፍ በአድናቂዎቿና በተከታዮቿ በተሞላው በታዋቂው የዌምብሌ አሪና /የመሰብሰቢያ አዳራሽ/ በውድ ቀሚስ ተውባ በአልማዝ ጉትቻ አጊጣና ደማቅ ቀይ ሊፕስቲክ ተቀብታ ብቅ ስትል አዳራሹ በጩኸትና በፉጨት አስተጋባ ።

ዋንኮይን በዓለማችን ታላቁ የክሪፕቶከረንሲ ለመሆን እየገሰገሰ መሆኑን፤ በየትም ቦታ ማንኛውንም ክፍያ መፈጸም እንደሚያስችል ለአድናቂዎቿ ገለጸች ይለናል ባርትሌት፤ ቢትኮይን ዋጋው ከሽርፍራፊ ሳንቲሞች ተነስቶ በ2016 ዓም አጋማሽ ላይ ወደ መቶ ዶላሮች ማሻቀቡ የብዙ ኢንቬስተሮችንና ሌሎችን ቀልብ መሳቡና ተፈላጊነቱ ማደጉ ይነገራል። ዶ/ር ሩጃ ዋንኮይን ቢትኮይንን በቅርቡ እንደሚዘርረውና በሁለት ዓመታት ውስጥ ማንም ስለቢትኮይን እንደማያወራና ታሪክ እንደሚሆን በመፎከር በአሪናው የታደሙ የደጋፊዎቿን ልብ አሞቀች።

ወቅቱ በመላው ዓለም የሚገኙ ሰዎች ዋንኮይን ላይ ኢንቨስት በማድረግ የዚህ አዲስ ክስተት አካል ለመሆን የቋመጡበት ነበር ይላል የምርመራ ጋዜጠኛው ባርትሌት፤ ለቢቢሲ ሾልኮ የደረሰ ሰነድ በዚሁ ዓመት የመጀመሪያዎቹ 6 ወራት ብቻ እንግሊዛውያን 30 ሚሊዮን ፓውንድ ኢንቨስት ማድረጋቸውን ያስረዳል። እንግሊዛውያን በአንድ ሳምንት ብቻ ዋንኮይን ላይ 2ሚሊዮን ፓውንድ ኢንቨስት አድርገዋል።

ሻሎም !

አሜን።

  በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን) fenote1971@gmail.com

አዲስ ዘመን ሰኞ ሰኔ 2 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You