አኮቴተ ዘ ቢል ጌትስ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ባለፈው በብሔራዊ ቤተ መንግሥት በተካሄደ ሥነሥርዓት የኢትዮጵያን ታላቁን የክብር ኒሻን ለቢል ጌትስ ሸልመዋል።

ይኽ የከበረ ሽልማት የጌትስ ፋውንዴሽን ባለፉት 25 ዓመታት በኢትዮጵያ ላበረከታቸው አሻጋሪ ሥራዎች እና ታላላቅ ዘመን አይሽሬ በጎ ተፅዕኖዎችን ያከበረ ነው ሲል የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት ገልጿል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው ለቢል ጌትስ ፋውንዴሽን የ25 ዓመታት አሸጋጋሪ ሥራዎች፤ ቢል ጌትስ ከቴክኖሎጂ ፈር ቀዳጅነት ወደ በጎ አድራጊነት ያደረጉትን ጉዞ በማውሳትም ዝቅ ብሎ በማገልገል፣ በአክብሮት እና በእኩልነት እምነት ላይ የተመሠረተውን አገልግሎታቸውን አድንቀዋል። ፋውንዴሽኑ በጤና፣ ግብርና፣ ዲጂታል መታወቂያ የሚያደርገው ጥረት ብሎም ጠንካራው በመከባበር ላይ የተመሠረተ ትብብር በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ተወስቷል። አኮቴተ ዘ ቢል ጌትስ፤ በሚል ምስጋና አቅርቤያለሁ።

ቢል ጌትስ እ.ኤ.አ በወርሐ ጥቅምት መጨረሻ በ1955 በሲያትል፣ ዋሽንግተን ተወለደ። የ2ኛ ደረጃ ትምህርቱን በሌክሳድ ትምህርት ቤት ተከታትሏል። ከኮምፒውተር ፕሮግራሚንግ ጋር የተዋወቀው በዚሁ ት/ቤት ነው። በዓለማችን ቁጥር አንድ በሆነው ዩኒቨርሲቲ ሀርቫርድ ከፍተኛ ትምህርቱን የጀመረ ቢሆንም በ1975 ዓ.ም ራዕዩን ለመኖር አቋርጦታል። በዚሁ ዓመት ከፖል አለን ጋር ማይክሮሶፍትን አቋቋመ። ኤም.ኤስ-ዶስን እና በኋላም ዊንዶውስን በመፍጠር የፒሲ ኢንዱስትሪውን አብዮት አቀጣጠለ። በማይክሮሶፍት ስኬት ምክንያት ከዓለማችን ቀዳሚ ባለፀጋዎች አንዱ ሆነ። በግል ኮምፒውቲንግ እና በሶፍትዌር ፍቃድ ሞዴሎች የገለጠው ራዕይ ዘርፉን ፍጹም ቀየረው። እሱን በዓለማችን ከፊት ከተቀመጡ ቢሊየነሮች አንዱ አድርጎታል። ከዚህ በኋላ ነጮች እንደሚሉት የተቀረው ታሪክ። The rest is history .

አሜሪካዊ ባለሀብት ቢል ጌትስ ሀብቱን በሙሉ በሚቀጥሉት ሁለት አስርተ ዓመታት ውስጥ ለድሃ ሀገራት ለመለገስ መወሰኑን ይፋ አድርጓል። በዓለም ቅድሚያ ትኩረት ተሰጥቷቸው ሊፈቱ የሚገባቸው ብዙ ችግሮች መኖራቸውን የተናገረው ባለሀብቱ፤ እ.አ.አ በ2045 ሀብቱን በሙሉ ለቢል እና ሜሊንዳ ጌትስ ፋውንዴሽን በማስተላለፍ ለድኃ ሀገራት የሰብዓዊ ዕርዳታ ለመለገስ መወሰኑን፤ ባለሀብቱ በፈረንጆቹ 2000 ከባለቤቱ ጋር በመሆን ባቋቋመው ቢል እና ሜሊንዳ ጌትስ ፋውንዴሽን አማካኝነት፤ ባለፉት 25 ዓመታት 100 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ለግሷል። ድርጅቱ ባደረገው ድጋፍ በበርካታ ሀገራት የክትባት አቅርቦትን ለማሳደግ፣ የኤች አይ ቪ ኤድስ ስርጭትን ለመከላከል፣ የቲቢ እና የወባ በሽታ ወረርሽኝን ለመቀነስ፣ ገንቢ ሚና ተጫውቷል።

ቢል እና ሜሊንዳ ጌትስ ፋውንዴሽን መሥራች ቢል ጌትስ የፋውንዴሽኑን 25ኛ ዓመት ምሥረታ አስመልክቶ በዚያ ሰሞን ባወጣው መግለጫ “እኔ ከሞትኩ በኋላ ሰዎች ስለ እኔ ብዙ ነገር ሊናገሩ ይቻላሉ፤ ነገር ግን የዓለማችን ቱጃር ቢል ጌትስ አረፈ የሚለው ንግግር ግን አይኖረም፤ ምክንያቱም በሕይወት እያለሁ ሀብቴን በሙሉ ለድሆች ዕርዳታ ለመስጠት ወስኛለሁና” ብሏል። ቢል ጌትስ በዓለም አቀፍ ደረጃ በፖሊዮ፣ በወባ፣ በኩፍኝ አማካኝነት የሚከሰቱ የእናቶችንና የጨቅላ ሕፃነትን ሞት ለማስቀረት ፍላጎት እንዳለው፤ የ69 ዓመቱ የማይክሮ ሶፍት ኩባንያ መሥራች እና ባለቤት ቢል ጌትስ አሁን ያለው አጠቃላይ ሀብት መጠን 108 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ሲሆን ከ20 ዓመታት በኋላ 200 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር እንደሚደርስ ይጠበቃል።

ለሰብዓዊና ለበጎ ተግባራት ድጋፍ በማድረግ የሚታወቀው ቢል ጌትስ እ.ኤ.አ በ2026 በዓለም ለጤና ዘርፍ የሚሰጠው ድጋፍ እስከ 9 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ይደርሳል። ባለሃብቱ ካፈራው ሀብት ውስጥ 1 በመቶውን ብቻ በማስቀረት በ20 ዓመታት ውስጥ 99 በመቶውን ለድሃ ሀገራት ለመለገስ መወሰኑን ገልፆ፤ ውሳኔው ሃብታም ሀገራት ለድሃ ሀገራት ይሰጡት የነበረውን ድጋፍ ማቆም በመጀመራቸው ነው ብሏል። እንደቢዝነስ ዴይሊ ዘገባ ቢል ጌትስ የሜሊንዳ እና ጌትስ ፋውንዴሽን በ2045 ሥራውን እንደሚያቆም ጠቅሶ፤ በዚህ ጊዜ ውስጥ የድጋፍ ሥራውን በፍጥነት ለማከናወን እንደሚጥር ተናግሯል። የዓለምን ገበያ መቆጣጠር ችሏል።

ጌትስ ቀስ በቀስ በድርጅቱ ውስጥ ካለው ተሳትፎ እየቀነሰ የመጣ ሲሆን በ2000 ከአመራርነቱ በ2014 ደግሞ ከሊቀመንበርነቱ ለቋል። ቱጃሩ ቢልጌትስ ገንዘቡን ለሌሎች ለማከፋፈል የተነሳሳው ከባለሃብቱ ዋረን ቡፌት እና ሌሎች በጎ አድራጊዎች በመመልከት መሆኑን ተናግሯል። ይኹን እንጂ ተቺዎቹ ቢል ጌትስ ፋውንዴሽኑን ግብርን ላለመክፈል እንደ መሸሸጊያ ይጠቀምበታል ሲሉ ይተቹታል። ጌትስ በብሎጉ ላይ በጻፈው ረዥም ጽሑፍ ፋውንዴሽኑ ሦስት ዓላማዎችን ዘርዝሯል።

መከላከል የሚቻሉ እና እናቶችን እና ሕጻናትን ገዳይ የሆኑ በሽታዎችን ማጥፋት፣ ወባን እና ኩፍኝን ጨምሮ ተላላፊ የሆኑ በሽታዎችን ማጥፋት፣ እንዲሁም በመቶ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ከድህነት ማውጣት ናቸው። ጌትስ አሜሪካ፣ ዩኬ እንዲሁም ፈረንሳይ ለውጪ ርዳታ የሚያውሉትን በጀት መቀነሳቸውን ተችቷል። የዓለማችን ሀብታም ሀገራት ከድሃ ሕዝቦች ጎን ይቁሙ አይቁም ግልጽ አይደለም ይላል። ነገር ግን አንድ ነገር እርግጠኛ የምንሆነው፣ ጌትስ ፋውንዴሽን በሁሉም ሥራዎቹ ሀገራትን እና ሕዝቦች ከድህነት እንዲወጡ ድጋፍ ማድረጉን ይቀጥላል።

ከቢቢሲ ኒውስ አወር ጋር በነበረው ቆይታ ዶናልድ ትራምፕ የመንግሥት ድርጅቶችን ውጤታማ ለማድረግ በሚል የመሠረቱትን መሥሪያ ቤት እንዲመራ የሾሙትን ባለሀብቱን ኤለን መስክ የአሜሪካን ርዳታ በማቋረጥ ሕጻናትን እየገደለ ነው ሲል መተቸቱን በተመለከተ ተጠይቆ የርዳታ ማቋረጡ ሕጻናትን ብቻ አይደለም የሚገድለው፣ ሚሊዮን ሕጻናትን ነው” ብሏል። የዓለማችን ቱጃር ሰው ይህንን ያደርጋል ብለህ አትጠብቅም ሲል አክሏል።

ጌትስ ከቀኝ ዘመሙና ከወግ አጥባቂው ፋይናንሻል ታይምስ ጋር በነበረው ቆይታ ዶናልድ ትራምፕ በጋዛ ሰርጥ “ለሃማስ” ኮንዶም ለመግዛት የሚውል ነው በሚል ለሆስፒታል ይሰጥ የነበረ የርዳታ ገንዘብ ስለማቋረጣቸው በማንሳት ተናግሯል። መስክ በኋላ ላይ ዶናልድ ትራምፕ ያሉት ስህተት መሆኑን ጠቅሶ ስህተት እንሠራለን ቢልም ርዳታው ግን ሳይቀጥል ቀርቷል። ያንን ርዳታ በማቋረጡ [መስክ] በኤች አይቪ የተጠቁ ሕጻናትን ሄዶ ቢያይ እመኛለሁ። ሲል ጌትስ ለፋይናንሻል ታይምስ ተናግሯል።

በአንድ ወቅት ጌትስ እና የቴስላ ባለቤት ኤለን መስክ የዓለማችን የቱጃሮች ሚና መሆን ያለበት ሌሎችን ለማገዝ ገንዘብ መስጠት መሆኑን ተስማምተው የነበረ ቢሆንም ከዚያ በኋላ ግን በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተጋጭተዋል። ቢቢሲ መስክን በጉዳዩ ላይ ምላሽ እንዲሰጥ ጠይቆት የነበረ ቢሆንም ለጊዜው አልተሳካም። ጌትስ ፋውንዴሽን ኢትዮጵያን ጨምሮ ለበርካታ ታዳጊ ሀገራት በጤና ዘርፍ ድጋፍ ያደርጋል።

ቢል ጌትስ እና ፖል አለን ማይክሮሶፍትን የመሠረቱት ከ50 ዓመታት በፊት ነበር። በዚህ ተመሳሳይ ወቅት ማለትም በ1975 ዓም ቢቢሲ ቢል ጌትስን ሲያናግረው 130 ድረ ገጾች ብቻ ነበሩ። ዛሬ ኅልቆ መሳፍርት የላቸውም። እአአ በ1993 የተጀመረው ማይክሮሶፍት 21ኛው ክፍለ ዘመንን ለውጧል። ዛሬ ላይ አብዛኛው እንቅስቃሴያችን በኤሌክትሮኒክስ የታገዘ ነው። ከየትኛውም ዘርፍ በላቀ የኮምፒውተር ዘርፍ እያደገ ነው። ለተጠቃሚዎች ምቹና በቀላሉ ከቦታ ቦታ የሚዘዋወር መገልገያ ነው።

ማይክሮሶፍት ትልቅ ተቋም መሆን የጀመረው ከ1980 ወዲህ ነው። አይቢኤም እየሠራ የነበረውን ኦፕሬቲንግ ሲስተም ከገዛ በኋላ ብዙ ነገር ለውጧል። ማይክሮሶፍት ይህንን ኦፕሬቲንግ ሲስተም ከገዛ በኋላ ለሌሎች ተቋማት በሽያጭ አቅርቧል። ከዛን ጊዜ አንስቶ እስካሁን ድረስም ገቢ እያገኘበት ነው። ቢል ጌትስ በማይክሮሶፍት ውስጥ ያለውን ሥራ ሲቀጥል አጋሩ ፖል አለን በ1983 የደም ካንሰር ስለያዘው ሥራውን ለቋል። 2018 ላይ በ65 ዓመቱ ከዚህ ዓለም በሞት እስከሚለይ ድረስ ከማይክሮሶፍት በገዛው ድርሻ አማካይነት የዓለም ሀብታሞች ዝርዝር ውስጥ ተካትቶ ቆይቷል። የሚወደውን የቅርጫት ኳስ ቡድን ከመግዛት አንስቶ በተለያዩ የንግድ ዘርፎችን ተሰማርቶ ሲሠራ ነበር። ጊታር በመጫወትም ታዋቂ ነበር። ፖል አለን ከማይክሮሶፍት ከወጣ በኋላ እንደ ዊንዶውስ፣ ኤክሴልና ወርድ ያሉትን መተግበሪያዎች ማይክሮሶፍት አስተዋውቋል። ኮምፒውተርን ወደ መረጃ መለዋወጫ መሣሪያ መለወጥ ቀጣዩ የማይክሮሶት ሕልም ነበር።

ቢል ጌትስ በ1993 ከቢቢሲ ጋር ቃለ ምልልስ ሲያደርግ፣ ቤት ለቤት የመረጃ መረብ መዘርጋት ቀላል እንደማይሆን ገልጿል። ከ15 ወይም 20 ዓመታት በኋላ በየቤቱ ኮምፒውተር ይገባ ይሆናል። አሁን ያለውን ዓይነት ኮምፒውተር ሳይሆን የወደፊቱ ኮምፒውተር የተለየ ይሆናል ሲል ነበር ያኔ የተናገረው። የማይክሮሶፍት ባለሙያ ናታን ማህርቮልድ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ቁጥር ውስንና ይዘታቸውም የተገደበ እንደሆነ ይሰጡ የነበሩ አስተያየቶችን በመንቀፍ እስከ 1,000 የቴሌቪዥን ጣቢያዎች የሚከፈቱበት ጊዜ ሩቅ እንደማይሆን ተንብዮ ነበር። አስፈሪ ይመስላል። ግን ድንቅ ነገር ነው። የምትወዱት መጽሐፍ ቤት አምስት መጽሐፍ ብቻ እንዲኖረው እንደማትፈልጉ አስቡ” ብሎ ነበር። አሁን ላይ የተለያዩ መሰናዶዎች የያዙ ድረ ገጾች መብዛታቸውን ያኔ ነበር የገመተው።

የኮምፒውተር ቴክኖሎጂ በመጠቀም ሰዎች ማየት የሚፈልጉትን ርዕሰ ጉዳይ ዝርዝር መምረጥ ይችላሉ ሲል ነበር የማይክሮሶፍት ባለሙያ የተናገረው። ዓለም በሁላችንም መዳፍ ሥር የሚሆንበት የወደፊት ዓለም ባለሙያዎቹ ቀድመው ተንብየዋል። በ1993 ዲጂታል ሚዲያ የተባለው መጽሔት አርታዒ ዴኒስ ካሩሶ ማስጠንቀቂያ ሰጥታ ነበር። በቴሌቪዥን ሁሉንም መረጃ ማግኘትና መቆጣጠር ወይም የምንፈልገውን ነገር ማዘዝ ማለት የኛን የግል መረጃ በኔትወርክ ውስጥ ማሳለፍ ማለት ነው ስትል ነበር በወቅቱ የተናገረችው። በኔትወርኩ መነሻ ላይ ያለው ሰው ምን እያየን እንደሆነ ያውቃል። የክሬዲት ካርድ ቁጥራችንን ይወስዳል። ስለኛ እንዲታወቅ የማንፈልገውን መረጃ ባጠቃላይ ያውቃል ስትልም ስጋቷን ገልጻለች።

ከዓመታት በኋላም የግል መረጃ አጠባበቅ ጉዳይ መነጋገሪያ ነው። ዛሬም ብዙዎች ስለ መረጃ ደኅንነት ጥያቄና ስጋት ያነሳሉ። መረጃ እንደ ሸቀጥ ሲሆን ሰዎች ስለ አንድ ነገር የሚያስቡበት መንገድም ይለወጣል። እንዴት እንደሚያስቡ መቅረጽ የሚቻልበትንም መንገድ ነው ስትል አርታዒዋ አስጠንቅቃ ነበር። መረጃ የማይጠበቅ ከሆነና እንደ ሸቀጥ ገበያ ላይ ከወጣ የሚኖረውን አደጋ ገልጻለች። ከኢንተርኔት ጋር በተያያዘ መረጃን ጠብቆ ለማቆየት የሚደረግ ጥረት ግን ፈታኝ ነው። መረጃ ሙሉ በሙሉ ተቆልፎበት የሚቀመጥ ነገር እንዳልሆነ ትናገራለች። መረጃ ሙሉ በሙሉ ከተዘጋ ሳይንቲስቶች በነፃነት መረጃ መለዋወጥ አይችሉም ማለት ነው። ለሁሉም አካል መረጃ ክፍት ይሁን ከተባለ ደግሞ መረጃን የገቢ ምንጫቸው የሚያደርጉ ይኖራሉ። ቴክኖሎጂ አስደናቂ ነው። ኃያልም ነው። ኃያልነቱ አወንታዊም አሉታዊም ጎን አለው ስትልም ታስረዳለች። ማይክሮሶፍት እየተስፋፋ ከመምጣቱ ጋር ኢሜል ተያይዞ ይነሳል። የተቋሙ ባለሙያ ማይክ ሙሬ ኢሜል “ዲጂታል መንደር ፈጥሯል። ጊዜና ድንበር ይሻገራል” ሲል ነው የሚገልጸው።

ሰዎች በየትኛውም የዓለም ጥግ ካሉ ሰዎች ጋር መረጃ መለዋወጥ የሚችሉበት መንገድ በመፍጠር ኢሜል ዲጂታል አብዮት አስነስቷል። በ1993 መጨረሻ የድረ ገጾች ቁጥር 623 ደርሷል። በየሦስት ወሩ የድረ ገጾች ቁጥር በእጥፍ እየጨመረም ሄዷል። በ1994 ቁጥሩ 10,022 ደርሷል። በ1995 ቢል ጌትስ “ኢንተርኔት ከአይቢኤም ኮምፒውተር መፈጠር ቀጥሎ ትልቁ ግኝት ነው” ብሎ ነበር። ማይክሮሶፍት ወርድስ 95ን የለቀቀውም ከዚህ በኋላ ነበር። ከዚያ ወዲህ ያለውን ዓለም የለወጠ ፈጠራም ሆኗል።

ሻሎም !

አሜን።

በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን) fenote1971@gmail.com

አዲስ ዘመን እሁድ ሰኔ 1 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You