የአሰላ ከተማ ኢኮኖሚያዊ እድገትን የማስተናገድ አቅም እንዲኖረው ተደርጎ እየዘመነ ነው

አሰላ፡- የአሰላ ከተማ የሀገሪቱን ኢኮኖሚያዊ እድገት የማስተናገድ አቅም እንዲኖረው ተደርጎ እየዘመነ መሆኑን የከተማዋ ምክትል ከንቲባ አቶ አብዱላሂ ሃሙ አስታወቁ። በከተማዋ በሚከናወነው የኮሪዶር ልማት አፍሮስ 3ሺህ 500 ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ እድል መፍጠሩን አመለከቱ።

አቶ አብዱላሂ በስፍራው ለተገኙት የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ጋዜጠኞች እንደገለጹት፤ መንግሥት ለከተሞች እድገት ትልቅ ትኩረት መስጠቱን ተከትሎ፤ የአሰላ ከተማ የሀገሪቱን ኢኮኖሚያዊ እድገት የማስተናገድ አቅም እንዲኖረው ተደርጎ እየተሠራ ነው።

በከተማዋ በፌዴራል መንግሥት፣ በክልሉ መግሥትና በከተማ አስተዳደሩ አቅም የሚገነቡ የተለያዩ ፕሮጀክቶች እንዳሉ ያመለከቱት ምክትል ከንቲባ አቶ አብዱላሂ፤ በበጀት ዓመቱ 32 አነስተኛ እና ትልልቅ ፕሮጀክቶች በሥራ ላይ እንዳሉ ጠቁመዋል።

ከነዚህም 12 ፕሮጀክቶች ካለፈው ዓመት የተሸጋገሩ እንደሆኑ፤ 20 የሚሆኑት አዳዲሶች መሆናቸውን አስታውቀው፤ ሁሉም በተያዘላቸው መርሃ-ግብር መሠረት በዚሁ ዓመት የሚጠናቀቁ መሆናቸውን አመልክተዋል።

ፕሮጀክቶቹ በ500 ሚሊዮን ብር በጀት እየተከናወኑ መሆኑንም ጠቅሰው፤ አንድ ጤና ጣቢያን ወደ ሆስፒታል ለማሳደግ G+3 ህንጻ እየተሠራ እንደሆነ፤ ደረጃውን የጠበቀ የመሰብሰቢያ አዳራሽም በአንድ ዓመት ውስጥ ተገንብቶ ሥራ ላይ እንደዋለ ገልጸዋል።

የኮሪዶር ልማትን በተመለከተም በተያዘው በጀት ዓመት 25 ኪሎ ሜትር ለማልማት ታቅዶ እስከ ባለፈው ሳምንት ድረስ ወደ 20 ኪሎሜትር የለማ መሆኑን ገልጸዋል። ልማቱ ባለሀብቱና ህብረተሰቡም የተሳተፈበት እንደሆነ አስታውቀዋል።

በኮሪዶር ልማቱ የባለሀብቶች ተሳትፎ 250 ሚሊዮን የሚገመት መሆኑን አመልክተው፤ በመንግሥት አቅም የሚለማው፣ መብራትና ሌሎች ወጪዎችን ጨምሮ 300 ሚሊዮን ብር እንደሚደርስ አቶ አብዲላሂ አመልክተዋል።

የከተማዋ ነዋሪዎችና ባለሀብቶች በማፍረሱም ይሁን መልሶ በማልማቱ ላይ ደስተኛ እና ግንባር ቀደም ተሳታፊ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ አቅም ያላቸው ራሳቸው እያፈረሱ በተቀመጠው ዲዛይን መሠረት እንደገነቡ፤ አቅም ለሌላቸው በጀት ተመድቦ እንደተሠራላቸው አስታውቀዋል።

በቀጣይ በጀት ዓመትም በኮሪዶር ልማት 20 ኪሎ ሜትር ለማልማት የሚያስችል ዲዛይን መጠናቀቁን ገልጸው፤ የኮሪዶር ልማቱ ከሌሎች ትልልቅ ከተሞች ዘግይቶ መጀመሩ ልምድና ተሞክሮን ቀምሮ ለመሥራት እድል የሰጠ ነው ብለዋል።

አሰላ ከተማ በተዳፋት ቦታ ላይ መቀመጧ በፔዳል ለሚሠሩ ብስክሌቶች አመቺ እንዳላደረጋት ጠቅሰው፤ በኤሌክትሪክ ለሚሠሩ ብስክሌቶች የሚያመች መንገድ ለመሥራት ጥናት እየተደረገ መሆኑን አብራርተዋል።

እስከ አሁን በኮሪዶር ልማቱ 100 የሚደርሱ ነዋሪዎች መፈናቀላቸውን ገልጸው፤ ከነዚህም 75 ለሚሆኑ ምትክ ቤት እንደተሠራላቸው፤ ለሌላ ዓላማ የተሠሩ ቤቶችም እንደተሰጧቸው አስረድተዋል። ቤት እያላቸው በቀበሌ ቤት ይኖሩ የነበሩ ሰዎችም ወደ ራሳቸው ቤት እንዲገቡ መደረጉን አስታውቀዋል።

የኮሪዶር ልማቱ አፍርሶ የመገንባት ሥራ የሚከናወንበት በመሆኑ 3ሺህ 500 ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ እድል የፈጠረ ነው ያሉት አቶ አብዱላሂ፤ ሥራው ቀንና ሌሊት ሲሠራ የነበረ መሆኑም ለከተማው ነዋሪዎች አዲስ የሥራ ባህልን ያለማመደ ነው ብለዋል።

በኮሪዶር ልማቱ የመብራት መሠረተ ልማቶችን ከመንገዶች ላይ ለማስነሳት 6 ሚሊዮን ብር መጠየቁ እና የተመደበው በጀት ዝቅተኛ መሆን በሥራው ላይ ካጋጠሙ ተግዳሮቶች ተጠቃሽ መሆኑን አስታውቀዋል። ፕሮጀክቱ እነዚህን መሰናክሎች አልፎ ውጤታማ እንደሆነም ገልጸዋል።

ከወንዝ ዳር እና ከአረንጓዴ ልማት ጋር ተያይዞ ከ2013 ዓ.ም ጀምሮ በርካታ ሥራዎች መሠራታቸውን ጠቁመው፤ በዋናነትም ኮምቦልቻ ወንዝን ተከትሎ በሶስት ኪሎ ሜትር ርዝመት 10 ሄክታር የሚሸፍን የአረንጓዴ ልማት፤ በሶስት የሥራ ምዕራፎች ተከፍሎ እንደተሠራ አስታውቀዋል።

የአሰላ ከተማ ባለሀብቶች እና ነዋሪዎች በተለያዩ የልማት ሥራዎችና በኮሪዶር ልማቱ ለነበራቸው ተሳትፎና ላበረከቱት አስተዋጽኦ ምክትል ከንቲባው አቶ አብዱላሂ ምስጋና አቅርበዋል።

ኢያሱ መሰለ

አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሰኔ 3 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You