
አንድ አምራች ኢንተርፕራይዝ ወደ ሥራ ለመግባትና ወደ ምርት ምዕራፍ ለመሸጋገር እንዲሁም ተወዳዳሪ ሆኖ ለመውጣት ከሚያስፈልጉት መሠረታዊ ነገሮች አንዱና ዋነኛው ፋይናንስ ነው። ይሁን እንጂ በሀገሪቱ ባለው ነባራዊ የፋይናንስና የባንክ ሥርዓት ባንኮች የብድር አገልግሎት የሚሰጡት ዋስትና ለሚያቀርቡ ከፍተኛ ኢንተርፕራይዞችና ኢንዱስትሪዎች ነው። በሌላ በኩል ደግሞ አነስተኛ የብድር አቅራቢ ወይም ማይክሮ ፋይናንስ (Micro Finance) ተቋማት ደግሞ የአቅም ውስንነትና የፋይናንስ አቅርቦት ችግር ስላለባቸው፤ የብድር አገልግሎት የሚሰጡት ለጥቃቅን ኢንተርፕራይዞች ነው።
በዚህ ማዕከል ሀገሪቱ ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ በምታደርገው ሽግግር እና ለሀገሪቱ ነፍስ ወከፍ ምርት እድገት እንዲሁም ለዜጎች ሰፊ የሥራ እድል በመፍጠር ከፍተኛ ሚና እየተወጡ ያሉ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ግን ብድር ለማግኘት የሚያስይዙት ዋስትና ስለማይኖራቸው፣ ባንኮች ብድር ለመስጠት የሚያስቀምጡት መስፈርት ከባድ በመሆኑ መስፈርቱን ስለማያሟሉ እና ማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት ለነዚህ ተቋማት ለማበደር የአቅም ውስንነት ስላለባቸው፤ ባንኮችም ሆነ ማይክሮ ፋይናንስ እንደማያበድሯቸውና እንደማይደግፏቸው የዓለም ባንክ ጥናት ያመላክታል፡፡
እነዚህን በመሀል የተዘነጉ “missing middle” አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞችን በፋይናንስ አቅርቦት፣ በንግድ ሥራ ልማት፣ በፕሮጀክት አዘገጃጀት እና በፋይናንስ አስተዳደር፣ በተግባር በተደገፈ ሥልጠና ጭምር … ወዘተ በመደገፍ ምርትና ምርታማነታቸውን የማሳደግ ዓላማ ያነገበ በኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት ሥር የአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዝ ፋይናንስ ፕሮጀክት እ.ኤ.አ በ2017 ወይም በ2009 ዓ.ም መቋቋሙ ይታወሳል።
ፕሮጀክቱ በሁለት ምዕራፍ እየተከናወነ ያለ ሲሆን፤ ከተቋቋመ ጊዜ ጀምሮ እስካሁን ድረስ በሁለቱ የፕሮጀክቱ ምዕራፍ ከዓለም ባንክ እና ከአውሮፓ ኢንቨስትመንት ባንክ የተገኘ 476 ሚሊዮን ዶላር ካፒታል ተይዞ ወደ ሥራ ተገብቷል። በዚህም ባለፉት ሰባት ዓመት ተኩል በኢትዮጵያ ልማት ባንክ፣ በማይክሮ ፋይናንስ ተቋማትና በንግድ ባንኮች በኩል ከ469 ሚሊዮን ዶላር በላይ 7,525 ለሚሆኑ አነስተኛና መካከለኛ አምራች ኢንተርፕራይዞች የካፒታል ዕቃ ፋይናንስና የሥራ ማስኬጃ ብድር ተሰራጭቷል። በሌላ በኩል በጨርቃ ጨርቅ፣ በቆዳ፣ በአግሮ ፕሮሰሲንግ እንዲሁም ተያያዥ ዘርፍ ለተሰማሩ 2,654 ለሚሆኑ አምራች ኢንተርፕራይዞች የንግድ ልማት አገልግሎት ስልጠና ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል፡፡
የፕሮጀክቱ ፋይናንስ አጠቃቀም ለታለመለት ዓላማ በትክክል መዋሉ በዓለም ባንክ በኩል ተገምግሟል። በዚህም ብድሩ ያለ ምንም አይነት ልዩነትና አድሎ መስፈርቱን ላሟሉ እንዲሁም በባንኩ መርህ መሠረት በሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ለሚገኙ ኢንተርፕራይዞች መሰራጨቱንና ገንዘቡ በአግባቡ ሥራ ላይ መዋሉን በማረጋገጡ ባንኩ “የዓለም ባንክ ቫይስ ገቨርነር/ WB Vice Governor Award” የሚባል የሽልማት ሰርተፍኬት ማበርከቱ ይታወሳል። እንዲሁም ገንዘቡ ለታለመለት ዓላማ ከመዋሉ ባለፈ በተለይም ሴቶችና ወጣቶችን ተጠቃሚ ከማድረግ አንፃር ፕሮጀክቱ ውጤታማ መሆኑን ገለልተኛ ወገን በሆነው በኢፌዴሪ ፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት የተደረገው ሀገር በቀል ጥናት ያሳያል።
ይሁን እንጂ በዚህ መልኩ የአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞችን ከፍተኛ የፋይናንስ ጥያቄ በፍትሃዊነት እየመለሰና እያስታገሰ ያለው ይህ ፕሮጀክት ሊጠናቀቅ ከሦስት ወራት ያልዘለለ እድሜ ብቻ ቀርቶታል። ታዲያ ፕሮጀክቱ ለአምራች ኢንተርፕራይዞች ሁለንተናዊ ድጋፍ በማቅረብ ለሀገሪቱ ከሚያበረክተው የላቀ አስተዋፅኦ አንፃር፤ ፕሮጀክቱን ለማስቀጠል ከፌዴራል ባለድርሻ አካላት ጋር የውይይት መድረክ ተካሂዷል፡፡
የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል በመድረኩ ተገኝተው ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር የሀገራት መነሻና ሰፊ የኢኮኖሚ ዕድገት መሠረት አነስተኛና መካከለኛ አምራች ኢንተርፕራይዞች እንደሆኑ አመላክተው፤ አምራች ኢንተርፕራይዞች በአንድ ሀገር ለዜጎች ሰፊ የሥራ እድል የሚፈጥሩ ከመሆናቸው ባለፈ ሀብት ለመያዝና ጠንካራ ኢኮኖሚ ለመገንባት ወሳኝ ሚና ይጫወታሉ። ይህንን ከግምት ውስጥ በማስገባት ባለፉት ስድስት ዓመታት ዘርፉን ለመደገፍ የፖሊሲና የአሠራር ማሻሻያዎች ተደርገዋል። በተለይ በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በተፈጠረ ቅንጅት ሰፊ ሥራዎች መሠራታቸውንና ለአምራቾች ምቹ ሁኔታዎች መፈጠራቸውን አንስተዋል።
የኢትዮጵያ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ዕድገት ሲታሰብ በዋናነት አነስተኛና መካከለኛ አምራች ኢንተርፕራይዞች ዋንኛ መሠረቶች ናቸው ያሉት ሚኒስትሩ፤ የኢንተርፕራይዞችን ዘላቂነትና ተወዳዳሪነት ከማሳደግ አኳያ የፋይናንስ አቅርቦት ጉዳይ የሚኖረው ድርሻ እጅግ የላቀ ነው። በመሆኑም የአምራች ኢንተርፕራይዞችን የፋይናንስ አቅርቦት ችግር ለመቅረፍ ከዓለም ባንክ ጋር በተደረገ ስምምነት፤ “በአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዝ ፋይናንስ ፕሮጀክት” በኩል ለአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች የፋይናስ አቅርቦት ተደራሽ ማድረግና ውጤት ማስመዝገብ መቻሉን ሚኒስትሩ አቶ መላኩ ገልፀዋል፡፡
አነስተኛና መካከለኛ አምራች ኢንተርፕራይዞችን መደገፍ ኢትዮጵያን የመደገፍ ሥራ መሆኑን በመገንዘብ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ለዘርፉ አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርጉ ሚኒስትሩ አሳስበው፤ ኢንተርፕራይዞችን በአግባቡ መደገፍና ተወዳዳሪ እንዲሆኑ በትኩረት መሥራት ይገባል። ተወዳዳሪነታቸውን ከሚያስቀጥሉና ከሚያረጋግጡ ጉዳዮች አንዱ ፋይናንስ ነው። ስለዚህ የኢንተርፕራይዞችን የፋይናንስ ጥያቄ እያስታገሰ ያለው ፕሮጀክት ቀጣይነት እንዲኖረው ሁሉም ሊረባረብ ይገባል ብለዋል ሚኒስትሩ።
የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት ዋና ዳይሬክተር አለባቸው ንጉሤ (ዶ/ር) በበኩላቸው የአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዝ ፋይናንስ ፕሮጀክት ለሀገራችን ብቻ ሳይሆን ለሌሎች ሀገራትም ተሞክሮ መሆን የሚችል የላቀ አፈፃፀም ያለው ፕሮጀክት እንደሆነ ገልጸው፤ ፕሮጀክቱ ወደ ሥራ ከገባ ጊዜ ጀምሮ በሊዝ ፋይናንስ በርካታ ኢንተርፕራይዞች ተጠቃሚ በመሆናቸው ዛሬ ላይ ተወዳዳሪ ለመሆን በቅተዋል። እንዲሁም የፕሮጀክቱ ፋይናንስ አጠቃቀም ገለልተኛ በሆነ ሀገር በቀል ተቋም ባጠናው ጥናት ተፈትሾ ውጤታማ መሆኑ ተረጋግጧል ብለዋል።
በቅርቡ የተጀመረው የገጠር ኢንዱስትሪያላይዜሽንና ትራንስፎርሜሽን ኢኒሽየቲቭ የአምራች ዘርፉን መሰረት ሰፊ ለማድረግና የኢንዱስትሪ ጥሬ ግብዓትና የሰው ኃይል ወደ አለበት የገጠሩ የሀገራችን ክፍል ለማስፋት እንደሚጠቅም የገለፁት ዋና ዳይሬክተሩ፤ በጥናት የተረጋገጠው እና ከፋይናንስ ፕሮጀክቱ የተገኘው ልምድ የሚያሳየው፤ ኢኒሺየቲቩን ስኬታማ ማድረግ የሚቻለው ዘመናዊ ቴክኖሎጂን፣ የፋይናንስ አቅርቦትን ከስልጠና ጋር በማቀናጀት መስጠት ሲቻል ነው። በመሆኑም የፕሮጀክቱ ቀጣይነት ለኢኒሺየቲቩ ስኬታማነት ቁልፍ ሚና እንደሚጫወት ጠቁመዋል፡፡
በመድረኩ አስተያየታቸውን የሰጡ የኢፌዲሪ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኢንዱስትሪና ማዕድን ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት በበኩላቸው እንደገለፁት፤ በፕሮጀክቱ በኩል ለአምራች ኢንተርፕራይዞች የሚቀርበውን የፋይናንስ አቅርቦት በዘላቂነት ማስቀጠል ካልተቻለ ዘርፉ ወደ ኋላ ይመለሳል። ከዚህ ባሻገር ዘርፉ ለሀገር ኢኮኖሚ ዕድገትና ብልፅግና የሚያበረክተው አስተዋፅኦ ይቀንሳል። በመሆኑም በቀጣይ አምራች ኢንተርፕራይዞች ዘላቂ የፋይናንስ አቅርቦት ማግኘት እንዲችሉ የሚረዳ የሕግ ማሕቀፍ ማዘጋጀት እንደሚያስፈልግ በአጽኖት ተናግረዋል፡፡
ይህም የሚያሳየው የፕሮጀክቱ ፋይናንስ አጠቃቀም ውጤታማነት ከከፍተኛ የመንግሥት አመራሮች ባሻገር የሕዝብ እንደራሴ ምክርቤት አባላት ጭምር በአንደበታቸው እንደመሰከሩለት ነው። ገለልተኛ በሆነ ተቋም ተፈትሾ አሳታፊነቱ፣ ውጤታማነቱ መረጋገጡንም ያሳያል። እንዲሁም የፋይናንሱ ምንጭ ራሱ ዓለም ባንክ ጭምር የፕሮጀክቱን አፈጻጸም ገምግሞ የምስክር ወረቀት ማበርከቱን ያመላክታል።
ፕሮጀክቱ ውጤታማ፣ ስኬታማ፣ አሳታፊ … ወዘተ መሆኑ በተለያዩ አካላት የተመሰከረለት ከመሆኑ ባለፈ ባለፉት ስድስት ዓመታት ከ469 ሚሊዮን ዶላር በላይ የሥራ ማስኬጂያና የሊዝ ፋይናንስ ብድር በማቅረብ የአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ዋነኛ የፋይናንስ ምንጭ ነው። በዚህም ፕሮጀክቱ የአምራች ኢንተርፕራይዞች ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ለሀገራዊ የምርት እድገት ከፍተኛ ሚና እየተወጣ ይገኛል። ኢንተርፕራይዞች ጥራት ያለው ተወዳዳሪ ምርት አምርተው በሀገርና በውጭ የገበያ እድል ተጠቃሚ እንዲሆኑ አስችሏል። በዘርፉም ዜጎች ሰፊ የሥራ እድል እንዲፈጠርላቸው አድርጓል።
በመሆኑም ፕሮጀክቱ ከተቋረጠ አብዛኞቹ አምራች ኢንተርፕራይዞች የፋይናንስ አማራጭ አጥተው “ከባሕር የወጣ ዓሳ” ሊሆኑ ይችላሉ። አማራጭ የፋይናንስ ሥርዓት ካልተዘረጋ ደግሞ በሀገር ምርትና ምርታማነት ላይ ጥላ ማጥላቱ አይቀሬ ነው። ስለዚህ የፕሮጀክቱ ቀጣይነት ፋይዳው ዘርፈ ብዙ፣ በዛው ልክ ደግሞ በመቋረጡ የሚመጣው ጉዳቱ ፈርጀ ብዙ መሆኑን ተገንዝቦ፤ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ለፕሮጀክቱ ቀጣይነት መረባረብ ይገባቸዋል። በተለይ የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት መሥሪያ ቤት አምራች ኢንተርፕራይዞችን የሚደግፍ ተቋም እንደመሆኑ መጠን፤ ስለፕሮጀክቱ አስፈላጊነትና ፋይዳ ለሚመለከታቸው አካላትና ተቋማት በማስገንዘብ ፕሮጀክቱ እንዲቀጥል በትኩረት ሊሠራ ይገባል። ሆኖም ፕሮጀክቱን በተለያየ ምክንያት ማስቀጠል ካልተቻለ ግን ከወዲሁ ታስቦበት ለአምራች ኢንተርፕራይዞች መሰል አማራጭ የፋይናንስ ምንጭ የማፈላለግ ሥራ ሊሠራ ይገባል።
ይህ አምድ በተለያዩ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ዜጎች ነፃ ሀሳባቸውን የሚሰጡበት ነው።በዓምዱ ላይ የሚወጡ ጽሁፎች የዝግጅት ክፍሉን አቋም አያመለክቱም።
በሶሎሞን በየነ
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሰኔ 3 ቀን 2017 ዓ.ም