በዓለም የቁንጅና ውድድር የኢትዮጵያ መልክ

በአውሮፓውያኑ የዘመን ቀመር በ1951 አሁን ያለው ዓለም አቀፍ የቁንጅና ውድድር ተጀመረ። ከዚያ በፊትም ከ19ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ ጀምሮ እንደነበር የተጻፉ ሰነዶች ያሳያሉ። ያም ሆኖ ግን መደበኛው እና እነሆ ለ72ኛ ጊዜ ሲካሄድ የቆየው የቁንጅና ውድድር የተጀመረው በ20ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ በ1951 ነው። ይህ ውድድርም ለ38 ዓመታት በተከታታይ በእንግሊዝ ሀገር ሎንደን ሲካሄድ ቆይቶ ከዚያ በኋላ በሌሎች የዓለም ሀገራት መካሄድ ጀምሯል።

የጳውሎስ ኞኞ ‹‹አጼ ቴዎድሮስ›› እና የገሪማ ታረፈ ‹‹የቋራው አንበሳ አባ ታጠቅ ካሣ›› የሚሉት መጻሕፍት እንደሚገልጹት፤ በኢትዮጵያ የቁንጅና ውድድር የተጀመረው ከ 160 ዓመታት በፊት በ1857 ዓ.ም በዳግማዊ አጼ ቴዎድሮስ በጎንደር ነበር። የመስቀል በዓልን ምክንያት በማድረግ በሁለተኛው ቀን የተደረገው ይህ የቁንጅና ውድድር ራሳቸው አጼ ቴዎድሮስ በፈረሳቸው በሚሳብ ሠረገላ የተገኙበት ሲሆን በእምቢልታና መለከት ታጅቦ በደማቅ ሥነ ሥርዓት ተካሄደ። አሸናፊዋም ጣይቱ ይልማ ትባላለች።

የዓለም የቁንጅና ውድድር በበይነ መረብ ገጹ ላይ ታሪኩን ሲናገር፤ ውድድሩ እንደተጀመረ አካላዊ ውበት ላይ የተመሠረተ ነበር። ይህ የአካላዊ ውበት ውድድር ከሴት መብት ተሟጋቾች ጠንከር ያለ ወቀሳ አጋጠመው። ብዙ ማሻሻያዎችን ሲያደርግ ቆይቶ ዛሬ የደረሰበት መስፈርት ላይ ደርሷል። የዛሬው የቁንጅና ውድድር መሪ ሃሳብ ‹‹ውበት ለዓላማ›› የሚል ሆነ። የተወዳዳሪዎች መስፈርትም አካላዊ ቁንጅና ብቻ ሳይሆን፤ በራስ መተማመን፣ የተግባቦት ክህሎት፣ እውቀት እና ማህበራዊ ኃላፊነትን መወጣት ሆነ።

እነሆ ኢትዮጵያዊቷ ሀሴት ደረጀ እነዚህን መስፈርቶች አሟልታ፣ የዓለም የቁንጅና ውድድር ዳኞችን አስደምማ፣ ሀገሯን አስተዋውቃ፣ ማህበራዊ ኃላፊነቷን ልትወጣ ከአፍሪካ አንደኛ ከዓለም ሁለተኛ ሆና ወደ ሀገሯ ገብታለች።

ሞዴል ሀሴት ደረጀ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጸችው፤ በትምህርት እና በጤና ላይ ከሚሠራው ከዓለም አቀፉ ማያ ፋውንዴሽን ጋር በመሆን ሕጻናት እና እናቶች ላይ ትሠራለች። እናቶች የራሳቸው የፋይናንስ ነፃነት እንዲኖራቸው ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ትሠራለች። በትምህርት እና በጤና ብዙ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸውን ልጆች በመለየት ድጋፍ እንዲደረግላቸው ትሠራለች።

‹‹ንግግሬን የወሬ ማሳመሪያ አድርጌ መቅረት አልፈልግም›› ያለችው ሞዴል ሀሴት፤ የባህል አምባሳደር እንደመሆኗ በሄደችበት ሀገር ሁሉ ኢትዮጵያን እንደምታስተዋውቅ ተናግራለች። ‹‹እኔን በስም የሚያውቀኝ የለም! ሀሴት ብለው ሳይሆን የሚጠሩኝ ኢትዮጵያ ብለው ነው። ለእኔ ሀገሬን ማስተዋወቅ ትልቅ ነገር ነው። አሁን በተሰጠኝ የባህል አምባሳደርነት ደግሞ አዲስ አበባን ብቻ ሳይሆን ሙሉ ኢትዮጵያን አሳያለሁ›› ብላለች።

እንደ ሞዴል ሀሴት ገለጻ፤ ኢትዮጵያ ብዙ የሚነገር ነገር አላት፤ ዓለም ሊያውቀው የሚገባ ነገር አላት። የኢትዮጵያን ድንቅ ተፈጥሮ እና ድንቅ ባህል ማሳየት ዓለም ኢትዮጵያን እንዲጎብኝና እንዲውቃት ያደርጋል። ከዚህ በኋላ ራሷን በኢትዮጵያ ታሪክ የበለጠ አዳብራ ለዓለም እንደምታስተዋውቅ ተናግራለች። የቁንጅና ውድድር በኢትዮጵያ ውስጥ ብዙም ያልተሠራበት ስለነበር በቀጣይ እንዲሠራበትና ከእሷ በኋላ የሚሄዱት የተሻለ ዕድል እንዲኖራቸው እንደምትሠራም ተናግራለች።

የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ ረዳት ፕሮፌሰር ነብዩ ባዬ በሞዴል ሀሴት የአቀባበል ሥነ ሥርዓት ላይ እንደተናገሩት፤ ኢትዮጵያ በሞዴል ሀሴት አማካኝነት በዓለም ተዋውቃለች። የሞዴል ስጦታ ከአካላዊ ቁንጅና ባሻገር ነው። የፍቅር እና የሥራ ሰው መሆኗን ከማሳየቷም ባሻገር የሀገር ፍቅርን ለዓለም አሳይታለች።

ሚሊዮን እና ቢሊዮን የዓለም ሕዝብ በሚከታ ተለው መድረክ በከፍተኛ በራስ መተማመን ሀገርን ማስተዋወቅ፣ የሀገርን ታሪክ እና ምንነት መናገር ትልቅ የዲፕሎማሲ ሥራም ነው። ዓለም የኢትዮጵያን መልካም ገጽታ አለማየቱን በድፍረት መናገሯ ጀግንነቷን ያሳያል ብለዋል።

እንደ ሚኒስትር ዴኤታው ገለጻ፤ ሞዴል ሀሴት ዓለም ሊያውቃቸው የሚገባቸውን የኢትዮጵያ መልካም ነገሮች ተናግራለች፤ ይህን ያደረገችው ገና ማሸነፏን እንኳን ሳታውቅ ነው። በጤና እና በትምህርት ሊሠሩ የሚገባቸውን ሥራዎች መናገሯ ዓለምን ያስተማረ ነው ያሉት።

የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ ነፊሳ አልመሃዲ በአቀባበል ሥነ ሥርዓቱ ላይ በሰጡት አስተያየት፤ በቁንጅና ውድድር ዘርፍ የኢትዮጵያን ገጽታ በዓለም አደባባይ ማሳወቅ የተለመደ አልነበረም፤ ዕውቅና የመስጠት እና ዘርፉ ላይ የመሥራት ውስንነትም ይታያል። ሞዴል ሀሴት በዓለም አደባባይ ኢትዮጵያን ማስተዋወቋ እና የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ዕውቅና መስጠቱ ዘርፉን እንዲነቃቃ ያደርጋል ብለዋል።

‹‹ውስጣዊ ውበት ከሌለ መናገር የምንፈልገውን ነገር እንኳን መናገር አንችልም›› ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ፤ ሞዴል ሀሴት ከውጫዊ ውበቷ ባሻገር ውስጣዊ ውበቷን እና ሥብዕናዋን ለዓለም ያሳየችበት መድረክ ነበር። ሞዴልነቷ በሁሉም ነገር መሆኑን ገልጸዋል።

እንደ ሚኒስትር ዴኤታዋ ገለጻ፤ የፋሽን ኢንዱስትሪ እንደ መዝናኛ ብቻ የሚታይ አይደለም፤ የኢኮኖሚ እና የቱሪዝም ዘርፍም ጭምር ነው። በፋሽን ዘርፍ ለሚማሩ ተማሪዎችም መነቃቃት እና መበረታታት የሚፈጥር ነው። ሞዴል ሀሴት ሀገሯን ለዓለም የገለጸችበት መንገድ በተቋማት ደረጃ እውቅና ሊያሰጣት የሚገባ ነው። የባህል አምባሳደር እንደመሆኗም በሁሉም ክልሎች እና በመላው ዓለም እንድታስተዋውቅ አሳስበዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባህል፣ ኪነ ጥበብ እና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ሂሩት ካሳው(ዶ/ር) እንደገለጹት፤ ሞዴል ሀሴት ለዚህ ሥብዕና፣ ብቃት እና አስተዋይነት የበቃችው በቤተሰቦቿ የአስተዳደግ ብቃት ስለሆነ ለወላጆቿም አርዓያ የሚሆን ነው ብለዋል።

የሞዴል ሀሴት ማሸነፍ የሀገርን ገጽታ ከማስተ ዋወቅም ባለፈ በኢትዮጵያ ትኩረት ያልተሰጠውን የፋሽን ኢንዱስትሪ እንዲነቃቃ አድርጓል። የሕዝቡንም ሆነ የመንግሥትን አመለካከት ያነቃ እና የቀየረ ነው። ከዚህ በኋላ ዘርፉ ላይ ኢንቨስት ለማድረግ እንደሚያነሳሳ ነው የገለጹት።

በዓለም አቀፍ ደረጃ በቁንጅና ውድድር የሚያሸንፉ ሴቶች ከአካላዊ ውበት ባሻገር ሀገርን ማስተዋወቅ፣ የበጎ አድራጎት ሥራዎችን መሥራት እና በሞዴልነታቸው ለመልካም ሥብዕና አርዓያ ሆነው እንደሚሠሩ የዓለም አቀፍ ሞዴሎች የታሪክ ገጾች ያሳያሉ።

ዋለልኝ አየለ

አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሰኔ 3 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You