
የድሬዳዋ ስፖርት አካዳሚ ግንባታ ሙሉ በሙሉ ተጠናቆ በቀጣይ ዓመት ወደ ሥራ እንደሚገባ ተገለፀ። በድሬዳዋ ወጣቶችና ስፖርት ኮሚሽን የስፖርት ማስፋፋትና ማልማት ዳይሬክተር አቶ ኢብሳ ዱሪ ለአዲስ ዘመን እንደገለፁት፣ የአካዳሚው ግንባታ ዘጠና ስምንት በመቶ ተጠናቋል።
እንደ አቶ ኢብሳ ገለፃ፣ በ2011 ዓ.ም ግንባታው የተጀመረው የድሬዳዋ ስፖርት አካዳሚ በተለያዩ ደረጃዎች በከተማ አስተዳደሩ በጀት እንዲገነባ ነው የተደረገ ሲሆን፣ ከባለድርሻ አካላት የተውጣጣ ልዑክ ወደ ስፔን ባርሴሎና ተጉዞ የልምድ ልውውጥ ካደረገ በኋላ የተወሰነ የዲዛይን ማሻሻያ ተደርጎበታል። በዚህም የተሻለ አካዳሚ ሆኖ አገልግሎት እንዲሰጥ ተገንብቷል።
“የቤት ውስጥ ስፖርቶችን ቁሳቁስ አስገብቶ የማስተካከል ሥራ ነው የሚቀረው” ያሉት አቶ ኢብሳ፣ የአካዳሚው ግንባታ እስካሁን 348 ሚሊዮን ብር ወጪ እንደተደረገበት ጠቁመዋል። ዳይሬክተሩ አክለውም፣ አካዳሚው ሙሉ ለሙሉ ሊጠናቀቅ የሚቀሩት የተወሰኑ የማስተካከያ ሥራዎች ብቻ እንደሚቀርና በቀጣይ ዓመት ወደ ሥራ ይገባል ተብሎ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል። በዚህም 2018 ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ 120 ስፖርተኞችን ተቀብሎ ወደ ሥራ ይገባል ብለዋል። በሁሉም የኦሊምፒክ የስፖርት አይነቶች ሥልጠናዎችን እንደሚሰጥ የሚጠበቀው ይህ አካዳሚ፣ በድሬዳዋ ብቻ ሳይሆን የምስራቅ ኢትዮጵያ ኢሊት ስፖርተኞችን በማሰልጠን ብቁና ውጤታማ እንዲሆኑ ለማስቻል ከኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ ጋር በመነጋገር ሰልጣኞችን ለመቀበል እየተዘጋጀን እንደሚገኝ አቶ ኢብሳ ተናግረዋል።
አካዳሚው በውስጡ አንፊ ቲያትር፣ አርቴፊሻል ሳር የተነጠፈበትን የእግር ኳስ ሜዳ ጨምሮ ለተለያዩ የስፖርት አይነቶች የመለማመጃ ሁለገብ ሜዳዎች፣ የሜዳ ቴኒስ፣ የመዋኛ ገንዳዎች፣ ጅምናዚየም፣ መዝናኛና ቢሮዎች፣ የሰልጣኞች ማደሪያ ክፍሎችና ሌሎችም አንድ አካዳሚ ሊኖረው የሚገባ መሠረተ ልማቶችን አካቷል። የአትሌቲክስ መለማመጃ ትራክ/መም እንደሚሠራለትና፣ ለውድድር ግን የድሬዳዋ ስቴድየምን መም እንደሚጠቀሙ አቶ ኢብሳ አስረድተዋል። በተጨማሪም አካዳሚው እስከ 2500 ሰው የሚይዝ ዘመናዊ የስብሰባ አዳራሽ ያለው ሲሆን፣ እንደ ከተማም እንደ ምስራቅ ሀረርጌም ትልልቅ ስብሰባዎችን እያስተናገደ እንደሚገኝ አቶ ኢብሳ ገልፀዋል።
አካዳሚው ካካተታቸው የስፖርት መሠረተ ልማቶች ብዙ የተባለለትና ትኩረት የተሰጠው ለውሃ ዋና ስፖርት የተገነባው የቤት ውስጥ መዋኛ ገንዳ ቀዳሚ ነው። አካዳሚው ሁለት የመዋኛ ገንዳ ያስገነባ ሲሆን፣ አንዱና ትልቁ በኦሊምፒክ መስፈርት ለውድድር ተብሎ የተገነባው ነው። ይህ የመዋኛ ገንዳ 25 በ 50 ሜትር ርዝመት ያለው ሲሆን፣ ጥልቀቱም በትልቁ በኩል አራት ሜትር በትንሹ በኩል ደግሞ 1.70 ሴንቲ ሜትር ነው። የራሱ የመብራት ሲስተም፣ የውሃ ማጣሪያና በዓለም አቀፍ ደረጃ አስፈላጊውን ሁሉ መስፈርት አሟልቶ ነው የተገነባው። ትንሹና የመለማመጃ ገንዳው ደግሞ 15 በ25 ሜትር ርዝመት አለው።
ከመዋኛ ገንዳ ጋር በተያያዘ በተለያዩ አካባቢዎች የተገነቡ በርካታ የመዋኛ ገንዳዎች ቢኖሩም፣ የኦሊምፒክና በዓለም አቀፍ ደረጃ መስፈርት ለማሟላት ቴክኒካዊ በሆኑ ነገሮች ሲቸገሩ በተደጋጋሚ ታይቷል። የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ የመዋኛ ገንዳ ለዚህ አንዱ ማሳያ ነው። የድሬዳዋ ስፖርት አካዳሚ በዚህ ረገድ ችግሮች እንዳይገጥሙት ጥንቃቄ መደረጉን አቶ ኢብሳ ይናገራሉ። “እኛ ከውጭ ልምድ ልውውጥ ካደረግን በኋላ ዲዛይኑ ተከልሶ አስፈላጊውን ሁሉ በማሟላት ነው የተሠራው” በማለት ያብራሩት አቶ ኢብሳ፣ ብዙ የሥራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎችም ተመልክተው የተደሰቱበት “እንደ ድሬዳዋ አለን የምንለው ገንዳ ነው” ይላሉ። ገንዳው ቤት ውስጥ የተገነባውም ከድሬዳዋ የአየር ፀባይ አኳያ ታስቦበት ሲሆን፣ ኦሊምፒክን ጨምሮ ዓለም አቀፍ መስፈርት ያላቸው ገንዳዎች የሚገነቡት በአብዛኛው በቤት ውስጥ መሆኑንም ገልፀዋል።
“የቤት ውስጥ የመዋኛ ገንዳው መወዳደሪያና መለማመጃ ያለው ሲሆን፣ የኦሊምፒክ መስፈርት ያሟላ ነው፣ ድሬዳዋ ሀይቅም ሆነ ወንዝ የላትም፣ በተለያዩ ሀገር አቀፍ ውድድሮች ግን ከሆቴሎች ጋር በመተባበር ድሬዳዋ በርካታ ሜዳሊያ የምታገኘው በውሃ ዋና ስፖርት ነው፣ ከዚህ አንፃር ለሕዝብም ክፍት የሆነ ከሆቴሎች በግማሽ ክፍያ እንዲጠቀም ያስችላል።” ሲሉም አቶ ኢብሳ ስለመዋኛ ገንዳው አብራርተዋል።
አካዳሚው ያካተተው ሌላው ትልቅ መሠረተ ልማት ስምንት የስፖርት አይነቶችን ማስተናገድ የሚችል ሰፊና ዘመናዊ ጅምናዚየም ነው። አቶ ኢብሳ ስለዚህ ጅምናዚየም ገለፃ ሲያደርጉ “የእኛ ስፖርተኞች ኤሺያ አካባቢ ውድድር ሲኖራቸው እዚህ መጥተው ለመዘጋጀት ከአየር ፀባዩ ጋር ትልቅ እድል የሚሰጥ ነው፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) እንዲሁም ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴን ጨምሮ ብዙ ትልልቅ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ተመልክተው ተደስተውበታል።” ብለዋል።
አካዳሚው ድሬዳዋ ቀድሞ በስፖርት የነበራትን ትልቅ ስም ለመመለስ፣ እንደሀገርም በስፖርቱ ዘርፍ የራሷን ዐሻራ ለማሳረፍ ትልቅ አቅም እንደሚሆንም አቶ ኢብሳ ያላቸውን እምነት ገልፀዋል።
በቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሰኔ 3 ቀን 2017 ዓ.ም