በቅዠት መንገድ ላይ

ከሦስት አስርት ዓመታት በላይ ኤርትራውያን የተሻለ ኢኮኖሚና ነፃነት እንደናፈቃቸው ይኖራሉ። ዛሬም በከፍተኛ ስቃይ፣ በዝቅተኛ ኢኮኖሚ (ድህነት) በተመሰቃቀለ እና ከፍተኛ የፖለቲካ ጭቆና ባለበት ሁኔታ ውስጥ ይገኛሉ።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ የሚመራው በአስመራ ያለው መንግሥት በነዚህ አሳሳቢ የሀገር ውስጥ ቀውሶች ላይ ማተኮርና መፍትሄ ማመንጨት ሳይሆን በጎረቤት ሀገር በተለይም ልማቷ እያስቀናው እድገቷ እያስደነበረው በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ በመግባት ቀጣናዊ አለመረጋጋትን በማባባስ ላይ ተጠምዷል።

የዜጎችን ተስፋ እና ፍላጎት ወደ ጎን በመተው በቀጣናው ትርምስን ለመፍጠር እየሠራ ነው። ይህን የተዛባ የትኩረት አቅጣጫ በመቀየር በአስቸኳይ ሰላምን፣ የተሻለ ልማትና የኢኮኖሚ እድል እንዲያገኝ የሚጠይቀው የኤርትራ ሕዝብ አስከፊ ዋጋ እየከፈለ ነው።

ለሕዝቡ በኤርትራ ውስጥ ያለው ሕይወት በአስቸጋሪ ሁኔታ የሚገለፅ ነው። ኢኮኖሚው በከፍተኛ ውድቀት ላይ ነው። የቅርብ ጊዜ መረጃዎች ይህንን ያሳያሉ። የዓለም ባንክ እጅግ የከፋ የድህነት መጠን በአስደንጋጭ ሁኔታ በኤርትራ ውስጥ ከፍተኛ ሆኖ እንደሚቀጥል ግምቱን አስቀምጧል።

እንደ ምግብ፣ ነዳጅ እና መድኃኒት ያሉ መሰረታዊ ፍላጎቶች ለተራ ኤርትራውያን ብዙ ጊዜ ብርቅ ናቸው። የዋጋ ግሽበቱ የመግዛት አቅምን እያሽቆለቆለ ሲሄድ፣ ሥር የሰደደ ሥራ አጥነት በተለይም በወጣቶች ዘንድ ተስፋ መቁረጥንና የጅምላ ስደትን እያባባሰ ነው። አሁንም ግን የኤርትራ መንግሥት ትኩረት በሀገሩና በዜጎቹ የውስጥ ጉዳይ ላይ ሳይሆን በኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያውያን ላይ ነው።

የኤርትራ መንግሥት በከፍተኛ ሁኔታ ወታደራዊ ወጪ በማድረግ፤ ወጣቱን ለውትድርና በመመልመልና በማሰልጠን ተጠምዷል። ይህ ዜጎቸን ለተስፋ መቁረጥ እየዳረገ ነው። በተለይ የማኅበረሰቡን ንቃተ ሕሊና እና የፖለቲካ ከባቢ አየር ማፈን እንደ ፋሽን ከያዘው ሰነባብቷል። ኤርትራ በዓለም አቀፍ የነጻነት አመልካች ጥናቶች በአፈና የከፋ ደረጃ ላይ ትገኛለች።

በ2024 ይፋ የተደረገው «የፍሪደም ሃውስ » ሪፖርት ኤርትራን ‹‹ነጻ አይደለችም›› ሲል ፈርጇታል፣ ይህም በዓለም ላይ የፖለቲካዊ መብቶች ባለማክበር እና ለዜጎች ነፃነት በመንፈግ ከመጨረሻዎቹ ተርታ አስመድቧታል። እንደ ሂዩማን ራይትስ ዎች እና አምነስቲ ኢንተርናሽናል ባሉ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች የግዳጅ ሥራ ተብሎ የተገለፀው ያልተወሰነ ብሔራዊ አገልግሎት ለቁጥር የሚታክቱ ኤርትራውያንን በብዝበዛ አዙሪት ውስጥ በማጥመድ ሕይወታቸውን እና የሀገሪቱን የምርታማነት አቅም እያሽመደመደው መሆኑ ተደጋግሞ ይገለፃል።

በዘፈቀደ ማሰር፣ በግዳጅ መሰወር፣ ሙሉ በሙሉ የገለልተኛ ሚዲያ ወይም የፍትህ አካላት አለመኖር፣ ምንም አይነት የዴሞክራሲ ሂደት አለመኖሩ በዚህችው ሀገር የሚታይ የመልካም አስተዳደር ውድቀት መገለጫዎች ናቸው። ስለዚህ የኤርትራ ሕዝብ ብሶቱን የሚገልጽበት መድረክ አጥቶ፣ መሰረታዊ ነጻነቶች ወይም መንገዶች በሌለበት ሥርአት ስር ይኖራሉ። ይህ ሁሉ የውስጥ ችግር እያለ ግን መንግሥታቸው ትኩረቱን አሁንም ያደረገው በኢትዮጵያ ላይ ነው።

የኤርትራ መንግሥት እነዚህን ነባራዊ የውስጥ ተግዳሮቶች ፊት ለፊት ከመጋፈጥ ይልቅ የኢትዮጵያ የውስጥ ፖለቲካ ላይ ያተኮረ ይመስላል። ይህ ከፍተኛ ጣልቃ ገብነት አዲስ ሳይሆን ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በተለይም የትግራይን ግጭት ተከትሎ ተባብሷል። በአንዳንድ መገናኛ ብዙሀን እንደምንሰማው፣ የስለላ መረጃዎችን ጨምሮ ታማኝ ምንጮች እንደሚያስረዱት የኤርትራ መንግሥት በኢትዮጵያ ውስጥ ለሚንቀሳቀሱ የተለያዩ የኢትዮጵያ ታጣቂ ኃይሎች ቀጥተኛ ድጋፍ ይሰጣል። ይህም የሥልጠና፣ የጦር መሣሪያዎችን ድጋፍ እና መሸሸጊያ ቦታን ያካትታል።

ከዚህም በላይ የኤርትራ መንግሥት ኢትዮጵያን ለማተራመስ አበክሮ እየሠራ መሆኑን በኢትዮጵያ የሚገኙ ባለሥልጣናት እና ገለልተኛ ታዛቢዎች በተደጋጋሚ ሲከስሱ ተመልክተናል። ይህ ተግባር ክልላዊ ትብብርን ከማጎልበት ይልቅ የኢትዮጵያን የውስጥ ጉዳይ በመጠቀም የራስ አቅምን ማጠናከር ላይ ያተኮረ ይመስላል። ይህ ስትራቴጂ ፀረ-መንግሥት አንጃዎችን መደገፍ ብቻ ሳይሆን የሀሰት መረጃ ዘመቻዎችን እና ዲፕሎማሲያዊ እንቅስቃሴዎችን ኢትዮጵያን ከክልላዊ ተፅእኖ ፈጣሪነት መነጠልን ያካትታል።

የኤርትራ መንግሥት ቅድሚያ የሚሰጣቸው ጉዳዮች ከሕዝቡ መሰረታዊ ፍላጎቶች በተቃራኒ የሆኑ እና አስደንጋጭ ናቸው። ከምንም በላይ ኤርትራውያን የተረጋጋ ኢኮኖሚ፣ ልማትና ያንን ለማስቀጠል ሰላም ይሻሉ። ዜጎች ቤተሰቦቻቸውን ለመመገብ፣ ለልጆቻቸው መሰረታዊ የጤና እንክብካቤ እና ትምህርት እንዲያገኙ በሀገራቸው ውስጥ ቀጣይነት ያለው ሥራ ይፈልጋሉ።

ኤርትራውያን ወጣትነታቸውን የሚገዘግዘውን እና አቅማቸውን እና ጉልበታቸውን የሚበላውን በግዳጅ የሚዋጉበት አረመኔያዊ ሥርዓት እንዲያበቃ እነደሚፈልጉ የሚታዩ ምክንያቶች አሉ። በተመሳሳይም ነፃነትን ይናፍቃሉ፡፡ በዘፈቀደ ከመታሰር፣ ያለ ፍርሃት ሃሳባቸውን በነጻነት ለመናገር፣ የመሰብሰብ ነፃነት፣ የአምልኮ ነፃነት እና የሀገራቸውን ዕጣ ፈንታ በመቅረጽ የመሳተፍ ነፃነትን ይናፍቃሉ፤ ከምንም ነገር በላይ ሰላምን ይፈልጋሉ። ሰላም ማለት ጦርነት አለመኖሩን ብቻ ሳይሆን በፍትህ፣ በእርቅ እና በሕግ የበላይነት ላይ የተገነባ አዎንታዊ ሰላም ከማንኛውም የዓለም ሕዝብ በላይ ያስፈልጋቸዋል።

ይሁን እንጂ አሁን ያለው አገዛዝ እነዚህን አንገብጋቢ ጉዳዮች ችላ ያላቸው ይመስላል። ይልቁንም የተባባሰ ጭቆናን፣ ኢኮኖሚያዊ ቸልተኝነትን እና ቀጣናዊ ውጥረትን የሚያባብስ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ኤርትራን ወደ ሌላ ግጭት ሊያስገባት ዳር ዳር እያለ ነው። የኤርትራ መንግሥት ርምጃዎች የሕዝቡን ደህንነት እና መብት ለመጠበቅ ቸልተኝነት ያሳየ ነው።

ሀብቱ ሁሉ የሚውለው የጸጥታ መዋቅር ለማስጠበቅ፣ የውጭ የሴራ ተልዕኮዎችን ለማስቀጠል እንጂ የተሰበረችውን ሀገርን ለመጠገን ወይም ዜጎቿን ተስፋ እንዲኖራቸው ለማድረግ አይደለም። ይህ የሚያሳየን በመንግሥታዊ ተግባር እና በሕዝብ ፍላጎት መካከል ያለው ጥልቅ አለመግባባት የዘመናዊቷ ኤርትራ አሳዛኝ ክስተት ስለመሆኑ ነው።

ኢትዮጵያ የራሷን የውስጥ ተግዳሮቶች ለመፍታት እየሠራች ትገኛለች። ብሔራዊ መግባባት እና የጋራ ትርክት ለመፍጠርም እየሠራች ነው። በተመሳሳይ ይህንን የሚያደናቅፍ የኤርትራን ጣልቃ-ገብነት ስታወግዝ ቆይታለች። ኢትዮጵያውያን ኤርትራ በኢትዮጵያ ምድር ላይ ለሚንቀሳቀሱ ታጣቂ ኃይሎች የምትሰጠው ድጋፍ የሀገራቸውን ሉዓላዊነት እንደጣሰ እና አለመረጋጋቷ ትልቅ ስጋት እንደሆነ ይቆጥሩታል።

አሁን ላይ የሚበጀውና ወቅቱ የሚጠይቀው መደጋገፍ መተባባር እና ድህንትን በጋራ መታገል መሆኑን ኢትዮጵያ አጥብቃ ታምናለች ለዚህም ስኬት አበክራ እየሠራች ነው፡፡ የታላቁ ሕዳሴ ግደብ የቀጣናው ሀገራት የልማት ትስስር ማዕከል እንዲሆን እየተሠራ ያለው ሥራም ይሄንን ያመላክታል፡፡ ኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳዮቿን ያለውጪ ኃይል ጣልቃገብነት መፍትሄ የመፍታት ሙሉ መብት አላት።

በመሆኑም ከጎረቤት ሀገራት የሚሰነዘሩ ትንኮሳዎች (ተቃዋሚዎችን ማደራጀትና ማስታጠቅ) እንቅስቃሴዎች እንዲቆሙ ዲፕሎማሲያዊ ጫና ማድረግ ይገባል። ገንቢ የሆነ የጎረቤት ግንኙነት ያስፈልጋል። ነገር ግን ይህ ግንኙነት በመከባበር ላይ የተመሰረተ እና የጥላቻ ድርጊቶችን የሚያቆም መሆን ይገባዋል።

ዓለም አቀፋዊ እይታ

ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በኤርትራ የሰብአዊ መብት አያያዝ እና በዲሞክራሲያዊ አስተዳደር እጦት ላይ ከፍተኛ ስጋት አለው። የተባበሩት መንግሥታት ልዩ ሪፖርተሮች ለዓመታት ስልታዊ የሆኑ በሕዝቡ ላይ የሚደርሱ በደሎችን መዝግበዋል። ምንም እንኳን ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር በቅርብ ግዜ ውስጥ የነበራትን መልካም ግንኙነት ተከትሎ በቅርብ ዓመታት አካባቢ በከፊል ማዕቀቦች ተነስተውላት ነበር ።

የኤርትራ መንግሥት በሶማሊያ የሚገኘውን አልሸባብን ጨምሮ በቀጣናው ለሚገኙ ታጣቂ ቡድኖች ድጋፍ እንደምታደርግ በማስረጃ የተረጋገጠ በመሆኑ ዓለም አቀፍ የማእቀብ ጫና ስር ነች። ከሱዳን የሚሰማ የጣልቃ ገብነት ክስም አለ፡፡ በሌላ መልኩ ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት የኤርትራን የኢኮኖሚ መቀዛቀዝ እና መንግሥት የሚከተለውን ፖሊሲ አስከፊ ተፅዕኖ አጉልተው እያሳዩ ነው።

የዓለም ባንክ እና አይ ኤም ኤፍ በኤርትራ ከልክ ያለፈ የውትድርና ወጪ፣ የብሄራዊ አገልግሎት ፕሮግራም እና የኢኮኖሚ ማሻሻያ ወይም የፋይናንስ ግልጽነት ጉድለት እያስከተለ ያለውን ጉዳት ያለማቋረጥ በተደጋጋሚ ይዘግባሉ። ስለዚህም ኤርትራ በፖለቲካ ስጋት፣ በመልካም አስተዳደር እጦት እና በተደጋጋሚ ማዕቀብ እየተዳከመች ነው ማለት ይቻላል።

የልማት ድጋፍ ወይም የውጭ ኢንቨስትመንት ፍሰት እየጎረፉ ባለበት ሁኔታ የኤርትራ ሕዝብ ግን ከዚህ ተጠቃሚነት ገለልተኛ ሆኖ ይገኛል። ይህ መገለል የኢኮኖሚ ቀውሱን የበለጠ ያሰፋዋል፣ በዋነኛነት ተራውን ኤርትራዊ የሚጎዳ አዙሪት ነው። የኤርትራ መንግሥት ግን አነዚህ ዓለማቀፋዊ ሁኔታዎች ብዙም ያሳሰቡት አይመስልም። ይልቁኑ የኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ላይ እጆቹን ያለቅጥ ለመዘርጋት ሲጣጣር ይታያል።

የኤርትራ ዘርፈ ብዙ ችግር የሚፈታው በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ውስጥ በመግባት ሳይሆን መሰረታዊ የትኩረት አቅጣጫ በመቀየስ እንደሆነ የዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ ያምናል። የኤርትራ መንግሥት በኢትዮጵያ እና በቀጣናው የሚያደርገውን የማተራመስ እንቅስቃሴ በአስቸኳይ ማቆም አለበት። በአሁኑ ጊዜ ለውጭ ጣልቃገብነት እና ለውስጣዊ ጭቆና የሚውሉ ሀብቶች በሀገር ውስጥ ያለውን አስከፊ ሰብአዊ እና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ ለመቅረፍ መዋል ይኖርባቸዋል።

የኤርትራ የትኩረት አቅጣጫ መሆን ያለበት ላልተወሰነ ጊዜ እየተተገበረ ያለው የብሔራዊ አገልግሎት ሥርዓትን ማፍረስ፣ የፖለቲካ እስረኞችን መፍታት፣ ነፃ የሲቪል ማኅበረሰብና የመገናኛ ብዙኃን እንዲቋቋሙ መፍቀድ፣ ስለ ሀገሪቱ የወደፊት ዕጣ ፈንታ እውነተኛ፣ ሁሉን አቀፍ ብሔራዊ ውይይት መጀመር ላይ ነውም ተብሏል።

ኤርትራ በራሱ አመራር ታግቶ የሚኖርባት ሕዝብ ያለባት ሀገር ሆናለች። ሕዝቦቿ መሰረታዊ መብቶች እና እድሎች የተነፈጉ ናቸው። ኢኮኖሚዋ ፈራርሶ የሚገኘው በአጋጣሚ ሳይሆን ሆን ተብሎ በተደረገ የፖሊሲ ምርጫ ምክንያት ነው። ከልማትና ከሰብአዊ ክብር ይልቅ ለቁጥጥር ቅድሚያ ስለሚሰጥ መንግሥት ያለባት ሀገር ነች።

የኤርትራ መንግሥት በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ የመግባት አባዜ ተጠናውቶታል። በራሱ ወሰን ውስጥ የሚገኙ አንገብጋቢ ጉዳዮችን ወደ ጎን በመተው የዜጎችን እምነትና ፍላጎት በእጅጉ አሳልፎ እየሰጠ ነው። ስለሆነም ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የኤርትራን ሕዝብ ድምጽ ማጉላት፣ ለሰብአዊ መብት መሻሻል ግፊት ማድረግ እና ቀጣናዊ እንቅስቃሴዎችን የማተራመስ ተግባር እንዲቆም መጠየቅ አለበት።

ለኤርትራ ዘላቂ ሰላምና ብልፅግና ሊገነባ የሚችለው የሀገሪቱ መንግሥት ወደ ውስጡ ሲመለከት ነው። ሰላምና ዕድገቷ የሚረጋገጠው በሕዝቦቿ ላይ የሚደርሰውን አስከፊ ስቃይ ሲገታ እና የራሳቸውን እጣ ፈንታ ለመወሰን መሠረታዊ ነፃነት ሲፈቅድላቸው ነው። ምርጫው ሁለት ነው፤ ከቀጣናው እና ከዓለም አቀፍ ፖለቲካ ተነጥሎ መቆየት አሊያም ሰላምን፣ ነፃነትን እና ልማትን መቀበል፡፡ ሰላም!!

 ይህ አምድ በተለያዩ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ዜጎች ነፃ ሀሳባቸውን የሚሰጡበት ነው። በዓምዱ ላይ የሚወጡ ጽሁፎች የዝግጅት ክፍሉን አቋም አያመለክቱም።

በሰው መሆን

አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሰኔ 3 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You