በሎስ አንጀለስ ስደተኞች ያነሱት ተቃውሞ ጉዳት አስከተለ

የፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር በስደተኞች ላይ እየወሰደ ያለው ርምጃ ተከትሎ በአሜሪካ ሎስ አንጀለስ ከተማ ሰልፍ በወጡ ተቃዋሚዎች ላይ የጸጥታ ኃይሎች አስለቃሽ ጭስ እና የፕላስቲክ ጥይት ተኮሱ። በሎስ አንጀለስ በተነሳው ተቃውሞ የጸጥታ ኃይሎች አስለቃሽ ጭስ ሲተኩሱ፤ ተሽከርካሪዎች መቃጠላቸው ተጠቁሟል፡፡

ተቃውሞ ከጀመሩ ሶስተኛ ቀናቸውን ያስቆጠሩት ሰልፈኞች ከከተማዋ ፖሊስ እና ትራምፕ ካሰማሯቸው ወታደሮች ጋር ተፋጥጠዋል። ወታደሮች ከዓርብ ዕለት ጀምሮ ተቃውሞ የወጡትን ሰልፈኞች ወደ ኋላ ገፍተዋል። የሀገር ውስጥ ደህንነት መለያ ያላቸው የጸጥታ ኃይሎች ደግሞ አስለቃሽ ጭስ፣ የሚያቃጥል ፈሳሽ (ፔፐር ስፕሬይ) እና ሌላ ገዳይ ያልሆነ መሳሪያ በሰልፈኞች ላይ ተጠቅመዋል። ሰልፈኞች የከተማዋን ማዕከላዊ ክፍል የሚያቋርጠውን ዋነኛ መንገድ የዘጉ ሲሆን ይህም የተሽከርካሪዎችን ፍሰት ዘግቷል። በርካታ ሰዎችም በመንገዱ መሻገሪያዎች እንዲሁም በመንገዱ መግቢያ እና መውጫዎች ላይ ተሰብስበው ታይተዋል።

የከተማዋ ፖሊስ በኤክስ ገጹ ባወጣው መረጃ፤ የካሊፎርኒያ የፍጥነት መንገድ ተቆጣጣሪ መኮንኖች ሰልፈኞቹን ከመንገዱ ላይ ለመበተን መንቀሳቀሳቸውን አስታውቋል። በተቃዋሚዎች በተዘጋው መንገድ ላይ የነበረው ዘጋቢ ከቢቢሲ ጋር ቆይታ ባደረገበት ሰዓት ከኋላው የጸጥታ ኃይሎች ሰልፈኞችን ለመበተን የሚጠቀሟቸው ገዳይ ያልሆኑ ፈንጂዎች እና የሄሊኮፕተር ድምጽ ይሰማ ነበር።

ከሰዓታት በኋላ ፖሊስ ሰልፈኞች በመበተን መንገዱ እንደገና እንዲከፈት ማድረጉን አስታውቋል። መንገዱ ለመክፈት በተደረገው እንቅስቃሴ የታሰሩ ሰዎች መኖራቸውን የካሊፎርኒያ የፍጥነት መንገድ ተቆጣጣሪ ተቋም በኤክስ ገጹ ጽፏል። የተለያዩ የከተማዋ ጎዳናዎች ሰልፈኞች የሚያቀጣጥሏቸው ርችቶች እና የጸጥታ ኃይሎች የሚጠቀሙት መሳሪያ ድምጾች ሲስተጋቡባቸው ውለዋል።

በአንድ የከተማዋ ክፍል ንብረትነታቸው ዋይሞ የተባለ የትራንስፖርት ኩባንያ የሆኑ እና ሰው አልባ የኤሌክሪክ ተሽከርካሪዎች ተቃጥለው ታይተዋል። ተሽከርካሪዎቹ በቃጠሎው ሙሉ ለሙሉ ወድመዋል። በዚህም የተነሳ የታክሲ አገልግሎት አቅራቢው ዋይሞ በሎስ አንጀለስ ዳውንታውን የሚሰጠውን አገልግሎት አቋርጧል።

ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ትሩዝ በተሰኘው ማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሁፍ ሰልፈኞቹን “የተከፈላቸው አማጺዎች” በማለት ጠርተዋል። ነገር ግን ፕሬዚዳንቱ ለዚህ ወንጀላቸው ማስረጃ አላቀረቡም። የሎስ አንጀለስ ፖሊስ በበኩሉ ተቃዋሚዎች የዳውንታውን አካባቢን በአፋጣኝ ለቅቀው እንዲወጡ አሳስቧል። ነዋሪዎች፣ ነጋዴዎች እና ጎብኚዎች “ማንኛውንም የወንጀል እንቅስቃሴ እንዲጠነቀቁ እና ሪፖርት እንዲያደርጉ” አሳስቧል።

“የፖሊስ አባላት በተለያዩ አካባቢዎች የተሰበሰቡ ሰዎች ለመበተን እየተንቀሳቀሱ ” መሆኑን ፖሊስ አስታውቋል። የከተማዋ ፖሊስ በኤክስ ገጹ ባሰፈረው ማስጠንቀቂያ “ዳውንታውን ሎስ አንጀለስ ሕገወጥ ስብስብ ተብሎ ታውጇል። በአስቸኳይ የዳውንታውን አካባቢን ለቅቃችሁ እንድትወጡ” ብሏል።

የትራምፕ አስተዳደር በሎስ አንጀለስ የተነሳው ተቃውሞን ለመቆጣጠር እየተሞከረበት ያለው መንገድ ከዲሞክራቶች ትችት ገጥሞታል። የሎስ አንጀለስ ከተማ ከንቲባ ካረን ባስ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፤ “አሁን በሎስ አንጀለስ እያየን ያለነው ቀውስ በአስተዳደሩ የተቀሰቀሰ ነው” ብለዋል። የአስተዳደሩ ርምጃዎች ፍርሃት እና ድንጋጤን መፍጠሩንም ተናግረዋል።

የፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር በስደተኞች ላይ እየወሰደ ያለው እርምጃን ተከትሎ በሎስ አንጀለስ የተቀሰቀሰው ተቃውሞ ቀናትን አስቆጥሯል። ተቃውሞው ተቀጣጥሎም ትራምፕ የሀገሪቱ የብሔራዊ ጥበቃ አባላት የሆኑ ወታደሮችን አሰማርተዋል።

ሰልፈኞች የከተማዋን ማዕከላዊ ክፍል የሚያቋርጠውን ዋነኛ መንገድ የዘጉ ሲሆን፤ ይህም የተሽከርካሪዎችን ፍሰት ዘግቷል።

ሁዋን እና በርካታ ጓደኞቹ በሎስ አንጀለስ በሚገኝ አንድ የመለዋወጫ እቃዎች መደብር በሚገኝ የመኪና ማቆሚያ ተሰባስበዋል። በዚህ ስፍራ ነው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ስደተኞችን ከሀገር ለማባረር የያዙትን ፖሊሲ በመቃወም የተቀጣጠለው የሎስ አንጀለሱ ፍጥጫ መነሻው።

አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሰኔ 3 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You